የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 14 ገጽ 128-ገጽ 130 አን. 4
  • የራስን ተፈጥሮአዊ አነጋገር መጠቀም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የራስን ተፈጥሮአዊ አነጋገር መጠቀም
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተቀላጠፈና ጥራት ያለው አነጋገር፤ በውይይት መልክ ማቅረብ
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • በጭውውት መልክ መናገር
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • በጭውውት መልክ መናገር
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • በትምህርት ቤቱ የሚሰጡህን የተማሪ ክፍሎች መዘጋጀት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 14 ገጽ 128-ገጽ 130 አን. 4

ጥናት 14

የራስን ተፈጥሮአዊ አነጋገር መጠቀም

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

እንደ ወትሮህ ማለትም ከሰው ጋር እንደምትጨዋወት ሆነህ ተናገር። የሌሎችን አነጋገር እንደኮረጅህ በሚያስመስል መንገድ አትናገር።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በምትናገርበት ጊዜ ከልክ በላይ ስለ ራስህ በማሰብ የምትረበሽ፣ የምትጨነቅና የምትደናገጥ ከሆነ አድማጮችህ ንግግርህን በትኩረት መከታተል ሊያዳግታቸው ይችላል።

የራስህን ተፈጥሮአዊ አነጋገር ተጠቅመህ ሐሳብህን የምትገልጽ ከሆነ የሚያዳምጡህ ሰዎች እምነት ይጥሉብሃል። አንድ ሰው ጭንብል አጥልቆ ቢያነጋግርህ የሚነግርህን ነገር ማመን አይከብድህም? ከራሱ ከሰውዬው መልክ ይልቅ ያጠለቀው ጭንብል የሚያምር ቢሆንስ? የሚናገረውን ነገር ታምነዋለህ? ለማመን እንደምትቸገር የታወቀ ነው። እንግዲያው ሌላ ሰው ለመምሰል ከመሞከር ይልቅ የራስህን ተፈጥሮአዊ አነጋገር ተጠቀም።

የራስን ተፈጥሮአዊ አነጋገር መጠቀም ሲባል ግን ግዴለሽ መሆን ማለት አይደለም። የሰዋስው ግድፈት፣ የተሳሳተ የቃላት አጠራርና ጥርት ብሎ የማይሰማ አነጋገር ሊታረሙ የሚገባቸው ነገሮች ናቸው። በተጨማሪም ዘመን አመጣሽ የአነጋገር ፈሊጦችን መጠቀም አይገባም። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን አነጋገራችንም ሆነ ጠባያችን የሚያስከብር እንዲሆን እንፈልጋለን። በራሱ ተፈጥሮአዊ መንገድ የሚናገር ሰው ንግግሩ ድርቅ ያለ አይሆንም፤ አድማጮቹንም ለማስደመም ብዙ አይጨነቅም።

በመስክ አገልግሎት። ከቤት ወደ ቤት በሩን ልታንኳኳ ስትል ወይም በሌላ ቦታ ላገኘኸው ሰው ለመመሥከር ስታስብ ፍርሃት ፍርሃት ይልሃል? አብዛኞቻችን እንዲህ የሚሰማን ቢሆንም ይህ ስሜት ይበልጥ የሚያስቸግራቸው አሉ። ውጥረት ድምፃችን እንዲለወጥ ወይም እንዲርገበገብ ሊያደርግ ይችላል። የስሜት መረበሽ ከገጠመን ደግሞ ያልታሰበበት እንቅስቃሴ ልናደርግ እንችላለን።

አንድ አስፋፊ እንዲህ ዓይነት ችግር እንዲገጥመው ምክንያት የሚሆኑት የተለያዩ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። አድማጮቹ ለእርሱ ስለሚኖራቸው ግምት ወይም አቀራረቡ የተዋጣለት ስለ መሆን አለመሆኑ በማሰብ ይጨነቅ ይሆናል። ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ ያለ ነገር ቢሆንም ከልክ በላይ መጨነቅ የሚያስከትለው ችግር ይኖራል። አገልግሎት ልትጀምር ስትል ፍርሃት የሚሰማህ ከሆነ ምን ብታደርግ ይሻላል? ጥሩ ዝግጅት ማድረግና ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ በጣም አስፈላጊ ነው። (ሥራ 4:​29) ሰዎች ፍጹም ጤንነት አግኝተው በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ አጋጣሚ በመስጠት ይሖዋ ስላሳየው ታላቅ ምሕረት አስብ። ስለምትረዳቸው ሰዎችና እነዚህ ሰዎች ምሥራቹን መስማታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሰላስል።

ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች የራሳቸውን ምርጫ የማድረግ መብት እንዳላቸውና መልእክቱን ሊቀበሉም ላይቀበሉም እንደሚችሉ መዘንጋት የለብህም። ኢየሱስ በጥንቷ እስራኤል ይመሰክር በነበረበት ጊዜም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አልነበረም። የአንተ ሥራ መስበክ ነው። (ማቴ. 24:​14) ሰዎቹ እንድትናገር ባይፈቅዱልህ እንኳን ልታነጋግራቸው መሄድህ ራሱ አንድ ምሥክርነት ነው። ትልቁ ነገር ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም መሣሪያ አድርጎ እንዲጠቀምብህ ፈቃደኛ ሆነህ መገኘትህ ነው። ሰሚ ጆሮ በምታገኝበት ጊዜ አነጋገርህ እንዴት ዓይነት መሆን አለበት? ዋናው ትኩረትህ ሰዎቹን መርዳት ላይ ከሆነ አነጋገርህ ተፈጥሮአዊ ለዛውን የጠበቀና ማራኪ ይሆናል።

ለሰዎች በምትመሠክርበት ጊዜ እንደወትሮህ ሆነህ ካነጋገርካቸው ዘና ብለው ያዳምጡሃል። እንዲያውም ልታካፍላቸው የፈለግኸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለመቀበል ይቀልላቸው ይሆናል። እነርሱም የሚሳተፉበት ውይይት ሊሆን ይገባል እንጂ ድርቅ ያለ ስብከት መሆን የለበትም። የወዳጅነት መንፈስ ይኑርህ። ለእነርሱም ትኩረት ስጥ እንዲሁም የሚሰጡትን አስተያየት አዳምጥ። ቋንቋው ወይም ባሕሉ ከማታውቀው ሰው ጋር ስትነጋገር የአክብሮት መግለጫዎችን መጠቀምን የሚጠይቅ ከሆነ እንደዚያ ማድረግ እንደሚኖርብህ የታወቀ ነው። ሆኖም በማንኛውም ጊዜ ሞቅ ያለ ፈገግታ ማሳየት ትችላለህ።

ከመድረክ ስትናገር። በርከት ላሉ ሰዎች ንግግር ስትሰጥ የራስህን ተፈጥሮአዊ አነጋገር በመጠቀም ከአንድ ግለሰብ ጋር እንደምታወራ ሆነህ መናገርህ የተሻለ ይሆናል። ሆኖም አድማጮችህ ብዙ ከሆኑ ድምፅህን ጎላ ማድረግ እንዳለብህ ግልጽ ነው። ንግግሩን አንድ በአንድ በቃልህ ለመሸምደድ ከሞከርህ ወይም እያንዳንዱን ዝርዝር ነጥብ ማስታወሻህ ላይ ከጻፍክ ስለ ቃላቱ አሰካክ ከልክ በላይ ተጨንቀሃል ማለት ነው። ትክክለኛ የቃላት አሰካክ አስፈላጊ ቢሆንም ስለዚህ ጉዳይ ከልክ በላይ ከተጨነቅህ ንግግሩ ድርቅ ያለና ለዛ የሌለው ይሆናል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የራስህን ተፈጥሮአዊ አነጋገር ተጠቅመሃል ማለት አይቻልም። የምትናገራቸውን ነጥቦች አስቀድመህ መዘጋጀት ይኖርብሃል። ይሁንና ከቃላቱ ይልቅ ይበልጥ ማተኮር ያለብህ ሐሳቡ ላይ ነው።

ስብሰባ ላይ ቃለ ምልልስ ሲደረግልህም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በደንብ ተዘጋጅ እንጂ መልሶችህን ጽፈህ አታንብብ ወይም ሸምድደህ አትምጣ። ሐሳብህን በራስህ ተፈጥሮአዊ አነጋገር ለዛ ባለው መንገድ መግለጽ እንድትችል እንደወትሮህ የድምፅህን መጠን፣ ፍጥነትና ቃና እየለዋወጥህ ተናገር።

አንድ ጥሩ የንግግር ባሕርይ እንኳን ከልክ በላይ ከተጋነነ ለአድማጮች አርቲፊሻል ሊሆንባቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ጥርት አድርገህ ልትናገር እንዲሁም ትክክለኛ የቃላት አጠራር ልትጠቀም ይገባል። ይሁን እንጂ ንግግርህ ለዛ እስኪያጣና የተውሶ እስኪመስል ድረስ መሆን የለበትም። አካላዊ መግለጫዎች በተገቢ ሁኔታ ከተሠራባቸው ንግግርን ሕያው ለማድረግ ሊረዱ ቢችሉም ድርቅ ያሉ ወይም የተጋነኑ ከሆኑ ግን የአድማጮችን ትኩረት ይሰርቃሉ። ድምፅህ በጥሩ ሁኔታ ሊሰማ ይገባል። ሆኖም በጣም መጮህ የለብህም። አልፎ አልፎ በጋለ ስሜት መናገር ጥሩ ቢሆንም መጮህ አለብህ ማለት አይደለም። በንግግርህ መሃል ድምፅህን መለዋወጥ፣ በግለት መናገር እና ተገቢውን ስሜት ማንጸባረቅ ቢኖርብህም የአድማጮችህን ትኩረት ወደ ራስህ መሳብ ወይም አድማጮችህን ማሸማቀቅ የለብህም።

አንዳንድ ሰዎች በዕለት ተዕለት ውይይት ሳይቀር ሐሳባቸውን እንደ ንግግር አሰካክተው የመግለጽ ችሎታ አላቸው። ሌሎች ደግሞ ሐሳባቸውን የሚገልጹት በወሬ መልክ ነው። ዋናው ነገር በማንኛውም ጊዜ ጥሩ የአነጋገር ልማድ ማዳበርህ ነው። እንዲህ ዓይነት ልማድ ካዳበርክ ዘና ብለህ በራስህ ተፈጥሮአዊ አነጋገር አድማጮችን የሚማርክ ንግግር ማቅረብ አይቸግርህም።

ለሌሎች ስታነብብ። ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ የራስህን ተፈጥሮአዊ አነጋገር መጠቀም ጥረት ማድረግ ይጠይቅብሃል። ይህን ለማድረግ የትምህርቱን ዋና ዋና ነጥቦች ለይተህ ማወቅ እንዲሁም እንዴት እንደተብራሩ ማስተዋል አለብህ። እነዚህ ዋና ዋና ነጥቦች ግልጽ ሊሆኑልህ ይገባል። አለዚያ ግን እንዲሁ ቃላቱን ማነብነብ ብቻ ይሆንብሃል። ያልተለመዱ ቃላት ካሉ ትክክለኛ አጠራራቸውን ለማወቅ ጥረት አድርግ። ትክክለኛ የድምፅ አሰባበር እንዲኖርህና ሐሳቡን በትክክል በሚያስተላልፍ መንገድ ቃሎቹን እያስተሳሰርክ ማንበብ እንድትችል ጮክ ብለህ ተለማመድ። ንባብህ የተጣራ እስኪሆን ድረስ ደግመህ ደጋግመህ ተለማመድ። ንባብህ ሞቅ ባለ ስሜት የሚደረግ ውይይት እንዲመስል በቅድሚያ ሐሳቡን በደንብ ልትረዳው ይገባል። በራስህ ተፈጥሮአዊ መንገድ ማንበብ ማለት ይሄ ነው።

በአብዛኛው ለሌሎች የምናነብበው ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ነው። በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠን የንባብ ክፍል በተጨማሪ በአገልግሎትም ሆነ ንግግር ስንሰጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እናነባለን። ወንድሞች በመጠበቂያ ግንብ ጥናትና በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ወቅት እንዲያነቡ ይመደባሉ። አንዳንድ ጥሩ ብቃት ያላቸው ወንድሞች በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በንባብ የሚቀርብ ንግግር እንዲሰጡ ይመደባሉ። መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌሎች ጽሑፎችን ስታነብ በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ የሚቀመጡትን ንግግሮች ሕያው አድርገህ አቅርብ። የተለያዩ ባለታሪኮች የተናገሩት ሐሳብ ካለ ድምፅህን እንደ ባለታሪኮቹ እየለዋወጥህ አንብብ። እዚህ ላይ አንድ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ አለ። ተፈጥሮአዊ አነጋገርህን ተጠቅመህ ንባቡን ሕያው ልታደርገው ይገባል እንጂ ድራማ የምትሠራ መምሰል የለብህም።

የራስህን ተፈጥሮአዊ አነጋገር ተጠቅመህ የምታነብበው ንባብ የጭውውት መልክ ይኖረዋል። እንደምታምንበት በሚያሳይ መንገድ የቀረበ ይሆናል እንጂ የተውሶ አይመስልም።

ይህንን ማድረግ የሚቻልበት መንገድ

  • በራስህ ተፈጥሮአዊ አነጋገር ተጠቀም። ማሰብ ያለብህ ስለ ይሖዋና ሰዎች እርሱን እንዲያውቁ ስለ መርዳት እንጂ ስለ ራስህ መሆን የለበትም።

  • ንግግር በምትዘጋጅበት ጊዜ ዋነኛ ትኩረትህ በነጥቦቹ ላይ እንጂ በቃላት አሰካኩ ላይ አይሁን።

  • ንግግር ስታቀርብም ይሁን ከሰዎች ጋር በምታደርገው የዕለት ተዕለት ጭውውት የግዴለሽነትን አነጋገር አስወግድ። እንዲሁም አንዳንድ የንግግር ባሕርያትን ለማንጸባረቅ የምታደርገው ጥረት የሰዎችን ትኩረት ወደራስህ የሚስብ ሊሆን አይገባም።

  • ለሌሎች የማንበብ አጋጣሚ ስታገኝ በደንብ ተዘጋጅ። የጽሑፉን መልእክት በደንብ ተረድተህ በስሜት አንብብ።

መልመጃ:- (1) ሚልክያስ 1:​2-14⁠ን አንብብና ተናጋሪዎቹ እነማን እንደሆኑ ልብ በል። ከዚያ በኋላ ስሜቱን ጥሩ አድርጎ በሚገልጽ መንገድ ድምፅህን እያሰማህ አንብብ። (2) በሦስት የተለያዩ ቀናት አገልግሎት ከመውጣትህ በፊት የዚህን ትምህርት የመጀመሪያ ሁለት አንቀጾችና በገጽ 128 ላይ “በመስክ አገልግሎት” በሚለው ንዑስ ርዕስ የሠፈረውን ሐሳብ እያነበብህ ምክሩን ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ