ጥናት 16
መረጋጋት
አንድ ተናጋሪ በተለይ በተደጋጋሚ ንግግር የመስጠት አጋጣሚ ከሌለው መድረክ ላይ ሲወጣ የመረበሽ ስሜት ቢያድርበት እንግዳ ነገር አይደለም። አንድ አስፋፊ አገልግሎት ወጥቶ የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ሰዎች ሲያነጋግር ፍርሃት ሊሰማው ይችላል። ኤርምያስ የነቢይነት ተልዕኮ ሲሰጠው “እነሆ፣ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም” ብሎ ነበር። (ኤር. 1:5, 6) ይሖዋ ኤርምያስን ረድቶታል፤ አንተንም ይረዳሃል። ቀስ በቀስ ተረጋግቶ የመናገርን ችሎታ ታዳብራለህ።
አንድ ተናጋሪ የተረጋጋ ነው የሚባለው ሳይረበሽ ንግግሩን ማቅረብ ሲችል ነው። መረጋጋቱን ከአካላዊ ሁኔታው መረዳት ይቻላል። ከሌላው ጊዜ ባልተለየ መልኩ በሥርዓት ቆሞ ይናገራል። የእጁን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል። ድምፁ የተስተካከለና ስሜቱን የሚገልጽ ይሆናል።
በአንድ የተረጋጋ ተናጋሪ ላይ የሚንጸባረቁትን እነዚህን ሁኔታዎች እንደምታሟላ ሆኖ ባይሰማህ እንኳ ልታሻሽል ትችላለህ። እንዴት? በመጀመሪያ አንድ ተናጋሪ የሚረበሸውና መረጋጋት የሚያጣው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ምክንያቱ ከሰውነታችን የአሠራር ሂደት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል።
አንድ ከበድ ያለ ነገር ይገጥምህና ያንን በተሳካ መንገድ መወጣት ትፈልጋለህ። ይሁን እንጂ እንዳሰብከው ይሳካልህ እንደሆነና እንዳልሆነ እርግጠኛ ካልሆንክ መጨነቅህ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ሰውነትህ ተጨማሪ አድረናሊን እንዲያመነጭ አንጎል ትእዛዝ ያስተላልፋል። አድረናሊን በሰውነትህ ውስጥ ሲረጭ የልብ ምትህ እንዲጨምር፣ አተነፋፈስህ እንዲቀየር፣ እንዲያልብህ ወይም እጅህ እንዲንቀጠቀጥና ጉልበትህ እንዲብረከረክ እንዲሁም ድምፅህ እንዲርገበገብ ሊያደርግ ይችላል። ይህ የሚከሰተው ሰውነትህ የገጠመህን ሁኔታ መወጣት የሚያስችል ተጨማሪ ኃይል ለማመንጨት ሲጥር ነው። ፈታኝ የሚሆነው ግን ሰውነትህ የሚያመነጨውን ይህን ኃይል በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞ በግለት መናገር መቻሉ ነው።
ፍርሃትን መቀነስ የሚቻልበት መንገድ። በተወሰነ መጠን ፍርሃት ቢሰማህ እንግዳ ነገር እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብሃል። ይሁን እንጂ መረጋጋት እንድታገኝ ፍርሃትህን መቀነስና ሁኔታውን በሰከነ መንፈስ በጥበብ መያዝ አለብህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
በደንብ ተዘጋጅ። ንግግርህን ለመዘጋጀት በቂ ጊዜ መድብ። ትምህርቱን በደንብ ልትረዳው ይገባል። የንግግርህን ነጥቦች የምትመርጠው ራስህ ከሆንክ አድማጮችህ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያላቸውን እውቀትና ንግግሩን የምታቀርብበትን ዓላማ ግምት ውስጥ አስገባ። ይህም ይበልጥ ጠቃሚ የሆኑትን ነጥቦች ለመምረጥ ይረዳሃል። መጀመሪያ ላይ እንዲህ ማድረጉን አስቸጋሪ ሆኖ ካገኘኸው ልምድ ያለው አንድ ተናጋሪ አማክር። ነጥቦችህንና አድማጮችህን ጥሩ አድርገህ እንድትገመግም ሊረዳህ ይችላል። አድማጮችህን የሚጠቅም ትምህርት እንደተዘጋጀህና በአእምሮህ በደንብ እንደተቀረጸ እርግጠኛ ስትሆን ይህንን ንግግር ለማቅረብ የሚያድርብህ ጉጉት የሚሰማህን ፍርሃት ለማሸነፍ ይረዳሃል።
ለመግቢያህ ልዩ ትኩረት ልትሰጥ ይገባል። ምን ብለህ እንደምትጀምር እርግጠኛ ሁን። ንግግርህን ከጀመርህ በኋላ የመረበሽ ስሜቱ ቀስ በቀስ እየጠፋ ይሄዳል።
ለመስክ አገልግሎት ስትዘጋጅም ቢሆን ማድረግ ያለብህ ይህንኑ ነው። ስለምትወያይበት ርዕሰ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ስለምትመሠክርላቸው ሰዎችም ልታስብ ይገባል። መግቢያህን ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅ። ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች ልምድ ቅሰም።
ንግግር ለማቅረብ ስታስብ ሐሳቡን አንድ በአንድ ጽፈህ ብትቀርብ የተሻለ መረጋጋት እንደሚኖርህ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ይህ ንግግር በሰጠህ ቁጥር ይበልጥ እንድትፈራ ሊያደርግህ ይችላል። እርግጥ እያንዳንዱ ተናጋሪ የሚይዘው የማስታወሻ መጠን የተለያየ ነው። ይሁንና ትኩረትህ ትምህርቱ ላይ እንዲያርፍና ፍርሃትህ እንዲቀንስ የሚረዳህ ቃላቱን ወረቀት ላይ ማስፈርህ ሳይሆን አድማጮቼን የሚጠቅም ትምህርት ተዘጋጅቻለሁ የሚል ትምክህት በውስጥህ ማሳደርህ ነው።
ድምፅህን እያሰማህ ንግግሩን መስጠት ተለማመድ። እንዲህ ያለው ልምምድ የተዘጋጀኸውን ነገር በቃላት አቀናብረህ መግለጽ እንደምትችል ትምክህት እንዲያድርብህ ይረዳሃል። ልምምድ ስታደርግ አቀራረቡ በአእምሮህ ስለሚቀረጽ ንግግሩን ስትሰጥ በቀላሉ ልታስታውሰው ትችላለህ። እውነታውን እያሰብህ ተለማመድ። አድማጮችህን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ተቀምጠህ የምታቀርብ ከሆነ ተቀምጠህ፣ ቆመህ የምታቀርብ ከሆነ ደግሞ ቆመህ ተለማመድ።
ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ጸሎት ይመልሳል? “በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል።” (1 ዮሐ. 5:14) ፍላጎትህ ይሖዋ እንዲከበር ማድረግና ሰዎችን በቃሉ አማካኝነት መርዳት ከሆነ ጸሎትህን እንደሚመልስልህ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ማወቅህ ክፍልህን ጥሩ አድርገህ ማቅረብ የሚያስችል ብርታት እንድታገኝ ይረዳሃል። ከዚህም በላይ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ የውሃት እና ራስን መግዛት ያሉትን የመንፈስ ፍሬዎች ስታፈራ ክፍልህን ተረጋግተህ ለማቅረብ የሚያስችል ሁኔታ ይኖርሃል።—ገላ. 5:22, 23
ልምድ አዳብር። በአገልግሎት ብዙ በተሳተፍህ መጠን ፍርሃትህ እየቀነሰ ይመጣል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ሐሳብ የምትሰጥ ከሆነ ንግግር ማቅረብ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። በጉባኤ ብዙ ንግግር በሰጠህ መጠን ከእያንዳንዱ ንግግር በፊት የሚሰማህ ፍርሃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል። ንግግር የመስጠት ብዙ አጋጣሚ ማግኘት ትፈልጋለህ? በትምህርት ቤቱ ክፍል ተሰጥቷቸው በተለያየ ምክንያት ማቅረብ የማይችሉ ካሉ እነሱን ተክተህ ለማቅረብ ዝግጁ ሁን።
ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉ ካደረግህ በኋላ ደግሞ መረጋጋት እንደሌለህ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩት ምልክቶች ምን እንደሆኑ መመርመርህ ጠቃሚ ይሆናል። እነዚህን ምልክቶች ለይቶ ማወቅና ከዚያም እንዴት ማስቀረት እንደሚቻል መማር ተረጋግተህ ለመናገር ይረዳሃል። እነዚህ የመረበሽ ምልክቶች በምታደርገው አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም በድምፅህ ሊንጸባረቁ ይችላሉ።
በአካላዊ እንቅስቃሴ የሚገለጡ የመረበሽ ምልክቶች። መረጋጋትህን ወይም አለመረጋጋትህን ከአቋቋምህና ከእጅህ እንቅስቃሴ ማየት ይቻላል። እስቲ ከእጅህ እንቅስቃሴ እንጀምር። እጅን ወደ ኋላ ማጣመር፣ ወደ ታች ቀጥ አድርጎ መዘርጋት ወይም አትራኖሱን ሙጭጭ አድርጎ መያዝ፣ ደጋግሞ እጅን ኪስ ውስጥ መክተትና ማውጣት፣ ኮትን መቆለፍና መፍታት፤ ጉንጭን፣ አፍንጫንና መነጽርን፣ ሰዓትን፣ እርሳስን፣ ቀለበትን ወይም ማስታወሻን መነካካትና ያልታሰበበት የእጅ እንቅስቃሴ አለመረጋጋትን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው።
እግር ያረፈበትን ቦታ ማቀያየር፣ እዛው እንደቆሙ መወዛወዝ፣ ግትር ብሎ መቆም፣ ከትከሻ መጉበጥ፣ ከንፈርን ደጋግሞ በምራቅ ማራስ፣ አሁንም አሁንም ምራቅ መዋጥና የትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ ማለት የመተማመን ስሜት እንደሌለህ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።
ከልብ ጥረት ካደረግህ እነዚህ የመረበሽ ምልክቶች እንዳይታዩብህ ማድረግ ትችላለህ። በአንድ ጊዜ አንዱን ብቻ ለማሻሻል ሞክር። ችግሩ ምን እንደሆነ ለይተህ ካወቅህ በኋላ ይህን ለማስወገድ ምን ማድረግ እንደሚኖርብህ አስቀድመህ አስብ። እንደዚህ ዓይነት ጥረት ካደረግህ በአካላዊ ሁኔታህ መረጋጋት ይታይብሃል።
በድምፃችን የሚንጸባረቁ የመረበሽ ምልክቶች። የመረበሽ ስሜት ካለብህ ድምፅህ ሊቀጥን ወይም ሊርገበገብ ይችላል። ምናልባት ደጋግመህ ጉሮሮህን ትጠርግ ወይም ስትናገር ትጣደፍ ይሆናል። ድምፅህን ተቆጣጥረህ ለመናገር ከልብህ ጥረት ካደረግህ እነዚህን ችግሮችና አጉል ልማዶች ማስቀረት ይቻላል።
ፍርሃት ፍርሃት ካለህ መድረክ ላይ ከመውጣትህ በፊት ደጋግመህ አየር በደንብ ሳብ። ሰውነትህን ዘና ለማድረግ ሞክር። አለመረጋጋትህን ከማሰብ ይልቅ የተዘጋጀኸውን ትምህርት ለአድማጮችህ ለማቅረብ በተነሳህበት ዓላማ ላይ አተኩር። ንግግርህን ከመጀመርህ በፊት አድማጮችህን ቃኘት በማድረግ የሚቀልህን ሰው ተመልከትና ፈገግ በል። መግቢያህን በዝግታ ከጀመርህ በኋላ ቀስ በቀስ ግለትህን መጨመር ትችላለህ።
ልትጠብቀው የምትችለው ውጤት። የፍርሃት ስሜትህን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንደምትችል አድርገህ አታስብ። ንግግር በመስጠት የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው ብዙ ተናጋሪዎችም ገና ወደ መድረክ ለመውጣት ሲያስቡ ፍርሃት ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ይህን ፍርሃታቸውን መቆጣጠር ተምረዋል።
ከውጭ የሚታዩብህን የመረበሽ ምልክቶች ለማስቀረት ልባዊ ጥረት የምታደርግ ከሆነ አድማጮችህ ተረጋግተህ እንደምትናገር ይሰማቸዋል። ውስጥህ የመረበሽ ስሜት ይኖር ይሆናል። ይሁን እንጂ አድማጮች ይህንን የሚያውቁበት ምንም መንገድ ላይኖር ይችላል።
ሰውነትህ ውስጥ የሚረጨው አድረናሊን የመረበሽ ምልክት እንዲታይብህ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ኃይልም እንደሚጨምርልህ አትዘንጋ። ይህን ኃይል ተጠቅመህ በስሜት ተናገር።
ከላይ የጠቀስናቸውን ነገሮች ለመለማመድ ንግግር የመስጠት አጋጣሚ እስክታገኝ ድረስ መጠበቅ አያስፈልግህም። በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ተረጋግተህ ትክክለኛውን ስሜት በሚያንጸባርቅ መንገድ መናገርን ተማር። ይህን ማድረግህ ንግግር ስትሰጥም ሆነ ስታገለግል የመተማመን መንፈስ እንዲኖርህ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል።