በተሰበሰበ ሕዝብ ፊት መናገር ትችላለህ!
ማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ በብዙ ሰዎች ፊት ለመናገር ያደረገችውን ሙከራ ስታስታውስ በጣም ያስቃታል። “ጥቂት ከተናገርኩ በኋላ ተዝለፍልፌ ወደቅሁ!” ስትል ተናግራለች።
ምንም እንኳ የማሪ ተሞክሮ ከበድ ያለ ቢሆንም ብዙዎች በሕዝብ ፊት ቆሞ መናገርን ምን ያህል እንደሚጠሉ ያሳያል። አንዳንዶች ከሞት የከፋ ዕጣ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል! “ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈራችሁ ነገር ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ለሰዎች በማቅረብ በተካሄደ አንድ ጥናት ላይ ይህ ሁኔታ ታይቷል። ሰዎች በጣም ከሚፈሯቸው ነገሮች መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛሉ ተብሎ አስቀድሞ የተገመተው “ከፍ ያለ ቦታ፣” “ገንዘብ ነክ ችግሮች፣” “በአውሮፕላን መብረር፣” “ሥር የሰደደ ሕመም፣” እና “ሞት” ነበር። ከሁሉ ይበልጥ ግን በአንደኛ ደረጃ የሚያስፈራቸው ነገር “በተሰበሰቡ ሰዎች ፊት ቆሞ መናገር” ሆኖ ተገኘ!
ሌላው ቀርቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ የታወቁ ሰዎች እንኳ መጀመሪያ ላይ በሕዝብ ፊት ቆሞ መናገር እንደሚያስፈራቸው ገልጸው ነበር። ኤርምያስ “ገና ልጅ ስለሆንሁ የመናገር ችሎታ የለኝም” ሲል ተናግሯል። (ኤርምያስ 1:6 የ1980 ትርጉም ) ሙሴ ለተሰጠው ሥራ የሰጠው መልስ ‘እኔ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ’ የሚል ነበር። (ዘጸአት 4:10, 13) ሆኖም ኤርምያስም ሆነ ሙሴ የተዋጣላቸው ተናጋሪዎች ሆነዋል፤ በታዋቂ መሪዎች ፊትና በጣም ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ቆመው ተናግረዋል።
የአንተም ሁኔታ እንደዚሁ ሊሆን ይችላል። በሕዝብ ፊት የመናገር ችሎታ በውስጡ ታምቆ የሚገኝ ማንኛውም ሰው ሊያዳብረው የሚችለው ነገር ነው። የሚከተሉትን ሐሳቦች በተግባር በመተርጎም በሕዝብ ፊት የመናገርን ፍርሃት ልትቋቋም ትችላለህ:-
1. እኔ እንዲህ ነኝ አትበል
“እኔ ዓይን አፋር ነኝ።” “እኔ ልጅ ነኝ።” “እኔ አርጅቻለሁ።” “እኔ በጣም ፈሪ ነኝ።” እነዚህ ራሳችን ለራሳችን የምናወጣቸውን ስያሜዎች የሚጠቁሙ ምሳሌዎች ናቸው። ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች ላይ መድረስ እንዳትችል ጋሬጣ ይሆኑብሃል።
ብዙውን ጊዜ እኔ እንዲህ ነኝ እያልን ለራሳችን የምናወጣቸው ስያሜዎች ራሳችን ተንብየን ራሳችን የምንፈጽማቸው ትንቢቶች ይሆናሉ። ለምሳሌ ያህል እኔ “ዓይን አፋር” ነኝ የሚል ሰው ምን ጊዜም ዓይን አፋርነትን ከሚፈታተኑ አጋጣሚዎች ይሸሻል። እንዲህ ማድረጉ ደግሞ ዓይን አፋር ነኝ ብሎ ሙሉ በሙሉ እምነት እንዲያድርበት ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት እኔ እንዲህ ነኝ ብሎ ራሱ የፈጠረውን ነገር ሲያደርግና ሲያጠናክረው ይኖራል። አንድ የሥነ ልቦና ጠበብት “አንድ ነገር ማድረግ አልችልም የሚል እምነት ካደረብህ . . . የምታደርገው ነገር ያን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ይሆናል” ብለዋል።
በሃርትፎርድ ዩኒቨርሲቲ (ዩ ኤስ ኤ) የሚሠሩት ዶክተር ሊን ኬሊ ዓይን አፋርነት ራሳችን የምንቀርጸው ጠባይ ሊሆን ይችላል ብለዋል። የቀረጽነውን ጠባይ እርግፍ አድርገን መተው እንችላለን። ዓይን አፋርነትን፣ መድረክ ላይ ወጥቶ ለመናገር መፍራትንና በሕዝብ ፊት ንግግር ለማቅረብ እንዳንችል እንቅፋት የሚሆኑንን ሌሎች ነገሮችም በተመለከተ ሁኔታው እንደዚሁ ሊሆን ይችላል።
2. የመረበሽ ስሜትን ተጠቀምበት
ለረጅም ጊዜ በተዋናይነት የሠራች አንዲት ሴት ለብዙ ዓመታት በዚህ ሙያ በመሥራት ልምድ ባካበተችበት በአሁኑ ጊዜ በተመልካቾች ፊት ስትቀርብ የመረበሽ ስሜት ይሰማት እንደሆነና እንዳልሆነ ተጠይቃ ነበር። “አዎን፣ አሁንም ቢሆን በተመልካቾች ፊት ተውኔት ባቀረብኩ ቁጥር ፍርሃት ፍርሃት ይለኛል። ይሁን እንጂ ለብዙ ዓመታት ይህን የመረበሽ ስሜት መቆጣጠር ችያለሁ” ብላለች።
እንግዲያው ግብህ የመረበሽ ስሜትን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ሳይሆን መቆጣጠር መሆን ይኖርበታል። ለምን? ምክንያቱም ሁሉም ዓይነት የመረበሽ ስሜት መጥፎ ነው ሊባል ስለማይቻል ነው። ሁለት ዓይነት የመረበሽ ስሜቶች አሉ። አንዱ ከዝግጅት ጉድለት የሚመጣ ነው። ሁለተኛው ግን በጎ ጎን ያለው ጭንቀት ነው። እንዲህ ዓይነቱ የመረበሽ ስሜት የምትችለውን ሁሉ ጥረት እንድታደርግ የሚያነሳሳህ በመሆኑ ይጠቅምሃል። ይሄኛው የመረበሽ ስሜት ነገሩን በቸልታ እንደማትመለከተው የሚያሳይ ነው። የመረበሽን ስሜት በተቻለ መጠን በጣም ለመቀነስ የሚከተሉትን ነገሮች ለማድረግ ሞክር:-
የምታቀርበውን ንግግር እንደ ጭውውት አድርገህ ተመልከተው። “ልክ እንደ ተራ ወሬ ነው፤ ወሬ ደግሞ ምንጊዜም የምትናገሩት ነገር ነው” በማለት በአድማጮች ፊት በመናገር የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ቻርልስ ኦስጉድ ተናግረዋል። አድማጮች በጥቅሉ የምታወያዩት ሰው ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ዘና ማለትና ፈገግ ማለት ተገቢ ሊሆን ይችላል። አቀራረብህ የጭውውት መልክ ያለው ሲሆን ይበልጥ ዘና ማለት ትችላለህ። ይሁን እንጂ የምታቀርበው ትምህርትና ሁኔታው ንግግሩን መደበኛውን ሥርዓት በጠበቀ መንገድ፣ ለሚተላለፈው ትምህርት ክብደት በሚሰጥ ሁኔታና ጠንከር ያለ መልእክት በሚያስተላልፍ አነጋገር እንድትናገር ሊያስገድድህ ይችላል።
አድማጮች ከአንተ ጎን መሆናቸውን አስታውስ! ተናጋሪው የመረበሽ ስሜት በሚታይበት ጊዜም እንኳ አብዛኞቹ አድማጮች አብረው ይጨነቃሉ። ስለዚህ አድማጮችን እንደ ጓደኞችህ አድርገህ ተመልከታቸው። የተዋጣለት ንግግር እንድታቀርብ ይመኛሉ! እነርሱ የአንተ እንግዶች እንደሆኑና አንተ ደግሞ አስተናጋጃቸው እንደሆንክ አድርገህ አስብ። አድማጮች የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማኝ ሊያደርጉ ይገባል ብለህ ከማሰብ ይልቅ እንግዳ ተቀባዩ አንተ እንደመሆንህ መጠን እነርሱ የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ እንዳለብህ ራስህን አሳምነው። ሁኔታውን በዚህ መንገድ መመልከትህ የሚሰማህ የመረበሽ ስሜት እንዲቀንስ ለማድረግ ይረዳሃል።
ስለ ራስህ ሳይሆን ስለምታስተላልፈው መልእክት አስብ። ራስህን አንድ የቴሌግራም መልእክት እንዲያደርስ የተላከ መልእክተኛ እንደሆንክ አድርገህ አስብ። መልእክተኛው ብዙም ትኩረት አይሰጠውም፤ መልእክቱን የሚቀበለው ሰው የሚፈልገው የቴሌግራሙን መልእክት ነው። ለአድማጮች መልእክት በምታቀርብበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ዋናው ትኩረት የሚደረገው በአንተ ላይ ሳይሆን በመልእክቱ ላይ ነው። በምታቀርበው መልእክት በጣም እየተመሰጥክ ስትሄድ የዚያኑ ያህል ስለ ራስህ የሚሰማህ ጭንቀት ይቀንሳል።
ንግግሩን ከማቅረብህ በፊት ብዙ አትብላ። ታዋቂ የሆኑ አንድ ተናጋሪ አንድ ጊዜ የሁለት ሰዓት ንግግር ከማቅረባቸው በፊት ከባድ ምግብ በልተው እንደነበረ ያስታውሳሉ። ንግግሩን ሲሰጡ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ ሲናገሩ “በአንጎሌ ውስጥ መኖር የነበረበት ደም ወደ ሆዴ ወርዶ ከሥጋ ጥብስና ከድንች ጋር ይታገል ነበር” ብለዋል። በአድማጮች ፊት ቀርበህ ከመናገርህ በፊት ከባድ ምግብ መመገብ ከሁሉ ይበልጥ መጥፎ እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። ስለምትጠጣውም ነገር ማሰብ አለብህ። ካፌይን እንድትረበሽ ሊያደርግህ ይችላል። አልኮል ደግሞ የስሜት ሕዋሳቶችህን ያደነዝዛቸዋል።
ሁልጊዜ በአድማጮች ፊት ቆመህ መናገር ስትጀምር ወዲያውኑ የመረበሽ ስሜት ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልምድ እያገኘህ ስትሄድ ይህ የመረበሽ ስሜት መናገር ስትጀምር ብቻ የሚሰማህ እንጂ ከዚያ በኋላ የማይዘልቅና መናገርህን ስትቀጥል ወዲያውኑ የሚጠፋ ስሜት መሆኑን ትገነዘባለህ።
3. ተዘጋጅ!
“ንግግር ዓላማ ያለው ጉዞ ነው፤ በመሆኑም ቅድመ ዝግጅት የግድ ያስፈልጋል” በማለት ዴል ካርኒጌ ተናግረዋል። “አንድ ሰው እንዲሁ ከምንም ተነስቶ አንድ ነገር ላይ ሊደርስ አይችልም።” ስለዚህ አንድ ነገር ላይ ለመድረስ በደንብ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ጥሩ የመናገር ችሎታ ያለህ መሆኑ ብቻ ለአድማጮች የሚፈይደው ነገር የለም። ታዲያ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?
ምርምር በማድረግ ፍሬ ነገሩን ለይተህ አውጣ። ምርምር ስታደርግ አትቸኩል። ለሌሎች ሐሳብን በጥሩ መንገድ ማስተላለፍ ስለሚቻልበት መንገድ ከፍተኛ ጥናት ያካሄዱት ጆን ዎልፌ “በአድማጮች ፊት በተረጋጋ መንፈስ ለመናገር የሚያስችላችሁ ብቸኛው መንገድ የምትናገሩትን ነገር ጠንቅቃችሁ ማወቃችሁ ነው” በማለት ተናግረዋል። የምታቀርበውን ርዕሰ ጉዳይ በደንብ አጥናው። ልትጠቀምበት የምትችለውን ያህል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ መረጃዎችን አሰባስብ። ከዚያም “ስንዴውን” “ከገለባው” እየለየህ ያዘጋጀኸውን ጽሑፍ በሚገባ መርምረው። “ገለባውም” ቢሆን ይተዋል ማለት አይደለም፤ በምታስተላልፈው ትምህርት ላይ ተጨማሪ ትምክህት እንዲያድርብህ ያደርጋል።
በጥልቀት አስብበት። የምታቀርበውን ርዕሰ ጉዳይ ‘አመንዥከው።’ በቀን ውስጥ በማንኛውም አጋጣሚ ሁሉ አሰላስለው። “ሰባት ቀን አሰላስለው፤ ሰባት ሌሊት አልመው” በማለት ዴል ካርኒጌ ተናግረዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ” ሲል መክሮታል። ይህን ከማለቱ በፊት ግን ጳውሎስ “በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም በተመስጦ አስብባቸው” ብሎ አሳስቦታል። አዎን፣ ጥሩ ተናጋሪ መጀመሪያ በደንብ ያሰላስላል።— 1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16 አዓት
የምታስተላልፈው መልእክት ጠቀሜታና አጣዳፊነት የሚሰማህን የመረበሽ ስሜት በጣም እስኪያዳክመው ድረስ አሰላስል። ኤርምያስ ስለሚያስተላልፈው መልእክት እንደሚከተለው ብሎ እንዲናገር ያስቻለው ይህ ነው:- “በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፣ መሸከምም አልቻልሁም።” (ኤርምያስ 20:9) ይህን የተናገረው መጀመሪያ ላይ የተሰጠውን ሥራ በተመለከተ “የመናገር ችሎታ የለኝም” ያለው ያው ሰው ነው።
አድማጮችህን ግምት ውስጥ አስገባ። ጥሩ አለባበስ ይኑርህ። በተጨማሪም ምርምር አድርገህ ያሰባሰብከው መረጃ ከአድማጮችህ ሁኔታ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። ስለዚህ አድማጮችህ ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው መርምር:- የሚያምኑባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ስለምታቀርበው ርዕሰ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር ምንድን ነው? የምታስተላልፈው ትምህርት ለዕለታዊ ኑሯቸው ምን ያህል ተስማሚ ነው? በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በመመርኮዝ ንግግርህን ስታቀርብ አድማጮች የምታስተላልፈው ትምህርት ከሚያስፈልጓቸው ነገሮች ጋር በቀጥታ የተያያዘ እንደሆነ አድርገው በመመልከት ይበልጥ በጥሞና ያዳምጡሃል።
የምትችለውን ሁሉ አድርግ
በዛሬው ጊዜ ዓለም በጣም የተራቀቀ ማንኛውም ዓይነት ፈጣን የመገናኛ ዘዴ አላት። ሆኖም “በአብዛኞቹ ሁኔታዎች ከሁሉ ይበልጥ ውጤታማ የሆነው የመገናኛ ዘዴ ሰው ከሰው ጋር የሚያደርገው የሐሳብ ግንኙነት ነው” በማለት ጌት ቱ ዘ ፖይንት የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። ከላይ የቀረቡት ሐሳቦች በእንዲህ ዓይነቱ የሐሳብ መገናኛ መሥመር የተዋጣልህ መሆን እንድትችል ሊረዱህ ይገባል። አላስፈላጊ በሆነ ፍርሃት ወደ ኋላ ከማለት ይልቅ በአድማጮች ፊት መናገር እንደምትችል ትገነዘባለህ!
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስሜትን የሚያረጋጉ እንቅስቃሴዎች
ሁኔታዎች አመቺ ሆነው ሲገኙ በአድማጮች ፊት ቀርቦ ከመናገር በፊት የሚከተሉትን እንቅስቃሴዎች ማድረጉ የመረበሽን ስሜት ሊቀንስ ይችላል።
● የእጆችህን ጣቶችና ክንድህን እጥፍ ዘረጋ አድርጋቸው። ትከሻዎችህን ወደ ላይ ከፍ አድርግ፤ ከዚያም ፈታ አድርጋቸው። ደጋግመህ እንደዚህ አድርግ።
● ራስህን ወደፊት ደፋ አድርግና ወደ ግራና ወደ ቀኝ አንቀሳቅሰው።
● አገጭህን ወደ ግራና ወደ ቀኝ አንቀሳቅሰው። አፍህን በደንብ ክፈተው።
● ለስለስ ባለ ቃና ድምፅህን ከፍና ዝቅ እያደረግህ አፍህን ዘግተህ አንጎራጉር።
● ደጋግመህ በዝግታ ወደ ውስጥ በኃይል ተንፍስ።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አቀራረብን ማሻሻል
ራስህን ከአድማጮች ብዛት ጋር አስማማ:- ብዙ አድማጮች ሲኖሩ ስሜትህን የምትገልጽባቸው መንገዶች ይበልጥ ጎላ ማለት አለባቸው። አካላዊ እንቅስቃሴዎችህ ይበልጥ ሰፋ ማለት አለባቸው፤ ድምፅህም ይበልጥ ኃይል ያለው መሆን ይኖርበታል።
ድምፅህ ጣዕም እንዲኖረው አድርግ። አንድ ሰው አንድ ቃና ብቻ ያለው የሙዚቃ መሣሪያ ሲጫወት የሚኖረውን ሁኔታ እስቲ አስብ! መሣሪያህ ድምፅህ ነው። አቀራረብህ የማይለዋወጥ “አንድ ቃና” ብቻ ያለው ከሆነ አድማጮችህን ታሰለቻቸዋለህ።
አቋምህን ተመልከት። ከልክ በላይ መዝናናት ግድ የለሽነትን ያሳያል። ድርቅ ብሎ መቆም ደግሞ ጭንቀትን ያመለክታል። ዘና በማለትና ንቁ በመሆን ሚዛናዊ ለመሆን ጣር፤ ሆኖም ግድ የለሽ መሆን ወይም ራስህን ማስጨነቅ የለብህም።
አካላዊ እንቅስቃሴ። አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያገለግለው አንድን ነጥብ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽ ብቻ አይደለም። ጡንቻዎችን ዘና ከማድረጉም በላይ የተስተካከለ አተነፋፈስ እንዲኖር ያደርጋል፤ የድምፅን ቃና ያስተካክላል፤ እንዲሁም ስሜታችንን ያረጋጋል።
አለባበስህ ልከኛ ይሁን። ለአድማጮች የምታቀርበው መልእክቱን እንጂ ልብስህን አይደለም። አድማጮች ስለ አለባበስህ ያላቸው አመለካከት አንተ ለራስህ አለባበስ ካለህ አመለካከት የበለጠ እንጂ ያነሰ ግምት አይሰጠውም።
አድማጮችህን እያየህ ተናገር። በኳስ ቅብብል ጨዋታ ኳስ ስትወረውር የወረወርከው ኳስ መያዝና አለመያዙን ትመለከታለህ። በንግግር ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሐሳብ ወደ አድማጮች “የሚወረወር” ራሱን የቻለ ነገር ነው። የተወረወረውን ሐሳብ “መያዝ አለመያዛቸው” የሚታወቀው ራሳቸውን በመነቅነቅ፣ ፈገግ በማለት ወይም በትኩረት በመመልከት በሚያሳዩት ምላሽ ነው። የወረወርካቸው ሐሳቦች “መያዝ አለመያዛቸውን” ለማረጋገጥ አድማጮችን በሚገባ ተመልከት።