ጥናት 13
አድማጮችን ማየት
ዓይናችን በውስጣችን የሚሰማንን ስሜትና አመለካከታችንን ያንጸባርቃል። መገረም፣ ፍርሃት፣ ርኅራኄ፣ ፍቅር፣ ጥርጣሬ ወይም ሐዘን ሊነበብበት ይችላል። አንድ አረጋዊ ሰው አብረዋቸው ብዙ መከራ ስላሳለፉ የአገራቸው ልጆች ሲናገሩ “በዓይናችን እንግባባ ነበር” ብለዋል።
ሌሎች ደግሞ ዓይናችን የሚያርፍበትን በማየት ስለ እኛም ሆነ ስለምንናገረው ነገር አንድ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። በብዙ ባሕሎች ሰዎች በወዳጃዊ ስሜት እያየ የሚያነጋግራቸውን ግለሰብ ማመን አይከብዳቸውም። በአንጻሩ ደግሞ መሬት መሬት የሚያይ ወይም ዓይኑ ሌላ ቦታ የሚያማትር ሰው ከገጠማቸው ሰውዬው ከልቡ እየተናገረ መሆኑን ወይም ችሎታውንና ብቃቱን ሊጠራጠሩ ይችላሉ። በሌሎች ባሕሎች ደግሞ አንድ ሰው ሲያወራ ትክ ብሎ ዓይን ዓይን የሚያይ ከሆነ እንደ ዓይን አውጣነት ወይም እንደ ድፍረት ይቆጠርበታል። ከተቃራኒ ፆታ ወይም ከአለቃው ወይም ከሌላ ባለ ሥልጣን ጋር ሲነጋገርም ቢሆን ትክ ብሎ የሚያይ ከሆነ ተመሳሳይ ስሜት ሊያሳድር ይችላል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ አንድ ልጅ ከአረጋዊ ሰው ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ዓይኑን የማይሰብር ከሆነ እንደናቃቸው ይቆጠራል።
ይሁን እንጂ እንደ ነውር የማይቆጠር ከሆነ አንድ በጣም አስፈላጊ ነጥብ ስንናገር የሰውዬውን ዓይን ትኩር ብለን ማየታችን ለመልእክቱ ክብደት ይሰጠዋል። ተናጋሪው ጉዳዩን ከልብ እንደሚያምንበትም ሊያሳይ ይችላል። ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ተገርመው “እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል?” ብለው በጠየቁ ጊዜ ኢየሱስ እንዴት እንደመለሰላቸው ልብ በል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- ‘ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ:- ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው።’ (ማቴ. 19:25, 26) ሐዋርያው ጳውሎስም በአድማጮቹ ፊት ላይ የሚነበበውን ስሜት በአንክሮ ይከታተል እንደነበር ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ። በአንድ ወቅት ጳውሎስ ንግግር ሲሰጥ ከልጅነቱ ጀምሮ ሽባ የነበረ አንድ ሰው በቦታው ተገኝቶ ነበር። ሥራ 14:9, 10 እንዲህ ይላል:- ‘ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኵር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፣ በታላቅ ድምፅ:- ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም አለው። ብድግ ብሎም ተነሥቶ ይመላለስ ነበር።’
ለመስክ አገልግሎት የሚረዱ ሐሳቦች። በመስክ አገልግሎት ስትካፈል ሰዎችን በወዳጅነትና በፍቅር አነጋግራቸው። ውይይቱን ለመጀመር እንደ ሁኔታው በጋራ የሚያሳስባችሁን ጉዳይ በተመለከተ አንድ ጥያቄ ልታነሳ ትችላለህ። በዚህ ጊዜ የአድማጭህን ዓይን ለማየት ወይም ቢያንስ ገጽታውን በአክብሮትና በደግነት ለመመልከት ጥረት አድርግ። ውስጣዊ ደስታው ዓይኑ ላይ የሚነበብ ሰው የሚያሳየው ሞቅ ያለ ፈገግታ በጣም ይማርካል። ይህም ምን ዓይነት ሰው እንደሆንህ እንዲገነዘብ የሚያስችለው ከመሆኑም ሌላ ዘና ብሎ እንዲያዳምጥህ ሊያደርገው ይችላል።
በሰውዬው ዓይን ላይ የሚነበበውን ስሜት ማስተዋልህ ምን ማድረግ እንዳለብህ ሊጠቁምህ ይችላል። ሰውዬው ከተቆጣ ወይም ደግሞ ምንም ፍላጎት ከሌለው ይህንን ስሜቱን መረዳት ትችል ይሆናል። የምትነግረው ነገር ግራ አጋብቶት ከሆነም ይህንን ልታስተውል ትችላለህ። ቶሎ ከአንተ መገላገል ከፈለገ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ይህንን መረዳት አይቸግርህም። በጉጉት እያዳመጠ ከሆነም ይህን ስሜቱን በግልጽ ማንበብ ይቻላል። ዓይኑ ላይ የሚነበበው ስሜት ፍጥነትህን እንደ አስፈላጊነቱ ለማስተካከል፣ እርሱን ይበልጥ በውይይቱ ለማሳተፍ፣ ውይይቱን ለማቆም ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዴት እንደሚካሄድ በአጭሩ ለማሳየት እንድትወስን ሊረዳህ ይችላል።
ስትመሰክርም ይሁን መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና የሰውዬውን ዓይን በአክብሮት እያየህ ለማነጋገር ጥረት አድርግ። ይሁን እንጂ ሊያሳፍረው ስለሚችል አታፍጥጥበት። (2 ነገ. 8:11) ሆኖም አለፍ አለፍ እያልህ ከሌላው ጊዜ ባልተለየ አስተያየት በወዳጅነት መንፈስ ተመልከተው። ይህ በብዙ አገሮች ከልብ የመነጨ አሳቢነትን የሚገልጽ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌላ ጽሑፍ ስታነብብለት ዓይንህ ጽሑፉ ላይ ማረፉ አይቀርም። ይሁን እንጂ አንድ ነጥብ ለማጥበቅ ስትፈልግ ለአፍታም ቢሆን ሰውዬውን ትክ ብለህ ትመለከተው ይሆናል። አለፍ አለፍ እያልክ ቀና ብለህ ማየትህ እየተነበበ ስላለው ነገር ምን እንደተሰማው ለማስተዋል ይረዳሃል።
ዓይን አፋር ከሆንክና መጀመሪያ አካባቢ አድማጭህን እያየህ መናገር ከተቸገርህ ተስፋ አትቁረጥ። ልምድ እያገኘህ ስትሄድ እንደ አስፈላጊነቱ አድማጭህን ማየት ቀላል ይሆንልህና ከሌሎች ጋር በምታደርገው ውይይት ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል።
ንግግር ስታቀርብ። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተራራ ስብከቱን ከመጀመሩ በፊት “ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ” በማለት ይነግረናል። (ሉቃስ 6:20) ከእርሱ ምሳሌ ተማር። ለተሰበሰቡ ሰዎች የምትናገር ከሆነ ንግግርህን ከመጀመርህ በፊት ለጥቂት ሰኮንዶች ቆም በልና በሙሉ ዓይንህ ተመልከታቸው። ይህ በብዙ ቦታዎች በአድማጮች መካከል ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ነጥሎ መመልከትን ይጨምራል። ወደ ንግግርህ ከመሄድህ በፊት ለጥቂት ጊዜ እንደዚህ ቆም ብለህ መመልከትህ መድረክ ላይ እንደወጣህ የሚሰማህን የመረበሽ ስሜት ለማሸነፍ ሊረዳህ ይችላል። አድማጮችህም ቢሆኑ ፊትህ ላይ የሚነበበውን ስሜት በማየት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም አንተን በትኩረት ለመከታተል ዝግጁ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።
ንግግርህን እየሰጠህ አድማጮችህን ተመልከት። ይህ ሲባል በአጠቃላይ አድማጮችህን በዓይንህ ገረፍ ታደርጋለህ ማለት አይደለም። በአድማጮችህ መካከል ያሉትን ግለሰቦች ለማየት ጥረት አድርግ። በሁሉም ባሕል ውስጥ ለማለት ይቻላል አንድ የሕዝብ ተናጋሪ በተወሰነ መጠን አድማጮቹን ማየት ይጠበቅበታል።
አድማጮችህን ማየት ማለት ተሰብሳቢውን ከዳር እስከ ዳር መቃኘት ማለት አይደለም። አስፈላጊ ሆኖ ካገኘኸው ከአድማጮች መካከል አንዱን ሰው አክብሮት በተሞላበት መንገድ እያየህ አንድ ሙሉ ዓረፍተ ነገር ተናገር። ከዚያም ሌላ ሰው እያየህ ለዚያ ሰው ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገሮችን ተናገር። የትኛውንም ሰው ቢሆን እስኪያፍር ድረስ ትኩር ብለህ መመልከት የለብህም። እንዲሁም የምታየው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ መሆን የለበትም። በዚህ መንገድ በአድማጮችህ መካከል ያሉትን የተለያዩ ሰዎች ተራ በተራ እያየህ ስትናገር ዓይንህ ያረፈበት ሰው ከእርሱ ጋር እያወራህ እንዳለህ እንዲሰማው አድርገህ ተናገር። ዓይንህን ከመንቀልህ በፊት ስለተናገርከው ነገር ሰውዬው የተሰማውን ስሜት ለማንበብ ሞክር።
ብዙም ማቀርቀር ሳያስፈልግህ ማስታወሻህን አየት ለማድረግ እንዲያመችህ አትራኖሱ ላይ ልታስቀምጠው፣ በእጅህ ልትይዘው ወይም መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ ልታደርገው ይገባል። ማስታወሻህን ለማየት አንገትህን ማቀርቀር የሚያስፈልግህ ከሆነ አድማጮችህን በደንብ እያየህ ለመናገር ትቸገራለህ። ማስታወሻህን ምን ያህል ጊዜ ደጋግመህ እንደምትመለከትና የት ነጥብ ላይ ስትደርስ ማየት እንዳለብህ አስቀድመህ ማሰብ ይኖርብሃል። የአንድ ዋና ነጥብ ማጠቃለያ ላይ ስትደርስ ማስታወሻህን የምትመለከት ከሆነ አድማጮችህ ስለተናገርኸው ነገር ያላቸውን ስሜት ማንበብ ካለመቻልህም በላይ ንግግርህ በተወሰነ መጠን ይዳከማል። ማስታወሻህን አሁንም አሁንም የምትመለከት ከሆነም አድማጮችን ብዙ ማየት አትችልም።
ለአንድ ሰው ኳስ ስትወረውር ኳሱን መቅለብ አለመቅለቡን ማየት ትፈልጋለህ። በንግግርህ መሃል የምትሰነዝራቸው ሐሳቦችም እያንዳንዳቸው እንደ “ኳስ” ናቸው ሊባል ይችላል። አድማጮችህ የሰነዘርኸውን ሐሳብ እንደተቀበሉ የሚጠቁምህ ራሳቸውን በመነቅነቅ፣ ፈገግ በማለት ወይም በአትኩሮት በመመልከት የሚሰጡት ምላሽ ነው። አድማጮችህን በደንብ የምታያቸው ከሆነ ሐሳብህን መቀበል አለመቀበላቸውን ማስተዋል ትችላለህ።
በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንድታነብብ ተመድበህ ከሆነ በንባብህ መሃል ቀና እያልህ አድማጮችህን ለማየት መሞከር ይኖርብሃልን? አድማጮችህ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ንባብህን እየተከታተሉ ከሆነ ቀና ብለህ ብታይም አብዛኛዎቹ አያዩህም። ይሁንና አድማጮችህን መመልከት ፊታቸው ላይ የሚነበበውን ስሜት እንድትከታተል ስለሚረዳህ ንባብህን ይበልጥ ሕያው ለማድረግ ሊያነሳሳህ ይችላል። እንዲሁም ከአድማጮችህ መካከል መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ያላወጡና በሐሳብ የተወሰዱ ካሉ ከተናጋሪው ጋር ዓይን ለዓይን መጋጠማቸው እየተነበበ ያለውን ነገር እንዲከታተሉ ሊያነቃቸው ይችላል። እርግጥ ከጽሑፉ ላይ ዓይንህን ነቅለህ ብዙ መቆየት አትችልም። ደግሞም በዚህ ምክንያት ንባብህ መደነቃቀፍ የለበትም። ንባብህ ሳይደነቃቀፍ አድማጮችህን ማየት እንድትችል መጽሐፍ ቅዱስህን በእጅህ መያዝህና ከጭንቅላትህ ቀና ብለህ ማንበብህ ከሁሉ የተሻለ ይሆናል።
አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በንባብ የሚቀርብ ንግግር እንዲሰጡ ይመደቡ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን ንግግር ጥሩ አድርጎ ማቅረብ ልምድ፣ ጥሩ ዝግጅትና ብዙ ልምምድ ይጠይቃል። ንግግሩ በንባብ የሚቀርብ በመሆኑ አድማጮችን እንደልብ ማየት እንደማይቻል የታወቀ ነው። ሆኖም ተናጋሪው ጥሩ ዝግጅት ካደረገ ቦታው ሳይጠፋበት አለፍ አለፍ እያለ አድማጮቹን መመልከት ይችላል። በዚህ መንገድ አድማጮች በትኩረት እንዲከታተሉት ማድረግ ይችላል፤ ተሰብሳቢዎቹም ከሚቀርበው ግሩም መንፈሳዊ ትምህርት የተሟላ ጥቅም ያገኛሉ።