ዓይን ለዓይን ለመተያየት በመጣር ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት አሳዩ
1 ሰዎች በሚበዙበት አካባቢም ይሁን ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል አብዛኛውን ጊዜ ማነጋገር ከመጀመራችን በፊት ከሰዎቹ ጋር ዓይን ለዓይን እንተያያለን። በዚያች ቅጽበት፣ ልናነጋግራቸው በመፈለጋችን ምን እንደተሰማቸው ሌላው ቀርቶ በምን ዓይነት ስሜት ውስጥ እንዳሉ ከፊታቸው ላይ ማንበብ እንችል ይሆናል። እነርሱም በተመሳሳይ ስለ እኛ ብዙ ነገር መገንዘብ ይችላሉ። አንዲት ሴት ቤቷ መጥታ ስላነጋገረቻት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች:- “ፈገግታ በተሞላው ፊቷ ላይ የመረጋጋት ስሜት ይነበብ እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ ደግሞ የማወቅ ፍላጎቴን ጨምሮልኛል።” በሴትየዋ ውስጥ የተፈጠረው ስሜት ምሥራቹን እንድታዳምጥ መንገድ ከፍቶላታል።
2 በመንገድ ላይ ስንመሠክርም ሆነ ሰው በሚበዛበት ቦታ ስናገለግል የምናነጋግራቸውን ሰዎች በሚገባ ማየት ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የሚረዳ ውጤታማ መንገድ ነው። አንድ ወንድም ሊያናግራቸው ያሰባቸው ሰዎች ወደ እርሱ ሲቀርቡ ዓይን ዓይናቸውን ይመለከታል። ከዚያም እነርሱ ሲያዩት ፈገግ ይልና የያዘውን መጽሔት ያስተዋውቃቸዋል። ወንድም ይህን አቀራረብ መጠቀሙ አስደሳች የሆኑ ውይይቶችን እንዲያደርግና ብዙ ጽሑፎችን እንዲያበረክት አስችሎታል።
3 የሰዎችን ስሜት ተረዱ:- ሰዎችን ዓይን ዓይናቸውን እያዩ ማናገር ስሜቶቻቸውን ለመረዳት ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ያነሳንለትን ነጥብ መረዳት እንደቸገረው ወይም በሐሳባችን እንዳልተስማማ ከፊቱ ሊነበብ ይችላል። ሥራ ላይ መሆኑን አሊያም ትዕግሥቱ እያለቀ መሄዱን ከፊቱ ማንበብ እንችላለን። ይህም አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው እንድንለውጥ ወይም ንግግራችንን እንድናሳጥር ይረዳናል። ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንዳለን ከምናሳይባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ የሌሎችን ስሜት መረዳት ነው።
4 ቅንነትና ጽኑ እምነት:- በበርካታ ባሕሎች ውስጥ ዓይን ዓይን እያየ የሚናገር ሰው ቅን እንደሆነ ተደርጎ ይታሰባል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ “እንግዲያስ ማን ሊድን ይችላል?” ብለው ሲጠይቁት መልስ የሰጠበትን መንገድ ልብ በሉ። የመጽሐፍ ቅዱሱ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እየተመለከታቸው፣ ‘ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል’ አላቸው።” (ማቴ. 19:25, 26) ኢየሱስ ጽኑ እምነት እንደነበረው ከፊቱ ስለሚነበብ የተናገራቸው ቃላት ይበልጥ አሳማኝ እንደሚሆኑ አያጠራጥርም። ስለዚህ የሰዎችን ዓይን እያዩ መናገር ቅንነትና ጽኑ እምነት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ የመንግሥቱን መልእክት እንድናስተላልፍ ይረዳናል።—2 ቆሮ. 2:17፤ 1 ተሰ. 1:5