ውጤታማ በሆነ የመንገድ ላይ ምሥክርነት ፍላጎት ያላቸውን ማግኘት
1 ኢየሱስ የመንግሥቱን ምሥራች መስማት የሚገባቸውን ሰዎች ፈልገው ያገኙ ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዟቸዋል። (ማቴ. 10:11) በአሁኑ ጊዜ ግን በብዙ አካባቢዎች ሰዎችን ቤታቸው አግኝቶ ማነጋገሩ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ታዲያ እኛ ያላገኘናቸውን መስማት የሚገባቸውን ሰዎች አግኝተን መልእክቱን ለማድረስ ምን ማድረግ ይቻላል?
2 የመንገድ ላይ ምሥክርነት ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ያላገኘናቸውን ሰዎች አግኝተን ለማነጋገር የሚያስችል ጥሩ መንገድ ሊሆን ይችላል። አውቶቡስ ፌርማታ ላይ፣ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው የመኖሪያ ሕንፃዎች አካባቢ፣ በሕዝብ መናፈሻዎችና ሰዎች ዕለታዊ ተግባራቸውን በሚያከናውኑባቸው ሌሎች አካባቢዎች የመንገድ ላይ ምሥክርነት መስጠት እንችላለን።
3 አንዳንዶች በመንገድ ላይ ምሥክርነት መስጠት ገና ሲነሣ ያስፈራቸዋል። ስለሚያፍሩ ወይም የመንግሥቱን መልእክት የሚጠሉ ሰዎች በማንቋሸሽ ላይቀበሉን ይችሉ ይሆናል በሚል ፍራቻ በዚህ ሥራ ለመካፈል ያመነቱ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ይህ ዓይነቱ ስጋት መሠረተ ቢስ ነው። በዚህ ሥራ ልምድ ያላቸው አስፋፊዎች ይህ ሥራ ከቤት ወደ ቤት የመመስከርን ያህል ቀላል እንደሆነ ሪፖርት አድርገዋል። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች ብዙውን ጊዜ መንገድ ላይ ሰዎች ለተለያዩ ጉዳዮች ቀርበው ስለሚያነጋግሯቸው በራቸውን አንኳኩተን ከምናነጋግራቸው ይልቅ መንገድ ላይ ስናነጋግራቸው ለመስማትም ሆነ ለመወያየት ይበልጥ ፈቃደኞች ሆነው አግኝተዋቸዋል። ስለዚህ ‘ደፍረን’ ብንጀምረው በምናገኘው ውጤት በጣም እንረካለን።—1 ተሰ. 2:2
4 ይበልጥ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ በመንገድ ላይ ምሥክርነት መስጠት የሚቻለው እንዴት ነው? በጣም ጥሩ የሆነው አንዱ መንገድ መጽሔቶቻችንን እንዲወስዱ በመጋበዝ ነው። በደንብ መዘጋጀትም በጣም አስፈላጊ ነው። ቀደም ብላችሁ መጽሔቶቻችንን አንብቧቸው። በምታነቡበትም ጊዜ የምታነጋግሯቸውን ሰዎች ሊማርክ ይችላል ብላችሁ የምታስቡትን አንድ ወይም ሁለት ነጥብ ምረጡ። አንድን ሰው ለ30 ሴኮንድ ብቻ ማነጋገር ይበቃል። ዓላማችን ከሌሎች ጋር በግል ተገናኝተን ለመነጋገር እንደመሆኑ መጠን ሰዎች በብዛት አዘውትረው የሚተላለፉበትን ቦታ ምረጡ። ምንም እንኳን አንድ ሌላ አስፋፊ በአካባቢው መኖሩ ጥሩ ቢሆንም ለየብቻ መሥራቱ ግን የተሻለ ነው። አብረው የሚቆሙ አስፋፊዎች ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ በማውራት ጊዜውን ወደማሳለፉ ሊያዘነብሉና የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ልብ ሳይሏቸው ሊቀሩ ይችላሉ።
5 አንድ ቦታ ላይ ቆሞ መጽሔቶችን ማሳየት፣ አንድን ግለሰብ ቀረብ ብሎ የማነጋገርን ያህል ውጤታማ አይደለም። ከሰውዬው ጋር እየተያያችሁ ለመነጋገር ሞክሩ። ውይይት ለመጀመር ስትጥሩ ሞቅ ያለና የወዳጅነት መንፈስ ያላችሁ ሁኑ፤ እንዲሁም ስለጉዳዩ በቀጥታ ተናገሩ። አንዳንድ ጊዜ ከሰውዬው ጋር እየተነጋገራችሁ ጥቂት እርምጃዎችን አብራችሁት ልትጓዙ ትችሉ ይሆናል። ሰውዬው መልእክቱን የሚቀበል ዓይነት ከሆነ መጽሔት እንዲወስድ ጋብዙት። መጽሔቱን ካልፈለገ ትራክት ልትሰጡት ትፈልጉ ይሆናል።
6 ብዙውን ጊዜ ጥያቄ ወይም ፍላጎት የሚቀሰቅስ ዐረፍተ ነገር ማዘጋጀት ጥሩ ነው። ጥሩ ምላሽ ካገኛችሁ ሰውዬውን ሌላ ጊዜ አግኝታችሁት ያሳየውን ፍላጎት መገንባት ትችሉ ዘንድ ስሙን፣ አድራሻውንና የስልክ ቁጥሩን ጭምር ልትጠይቁት ትችላላችሁ። እንዲህ ልትሉ ትችሉ ይሆናል፦ “የበለጠ ለማወቅ ከፈለጉ እቤትዎ መጥቼ ባነጋግርዎት ወይም ሌላ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግርዎት ባደርግ ደስ ይለኛል።”
7 አንድ ሽማግሌ የመንገድ ላይ ምሥክርነት እየሰጠ ሳለ አንዲት ወይዘሮ አግኝቶ ያነጋግራል። ሴትየዋ ከዚህ ቀደም አንድም ምሥክር ቤቷ መጥቶ አነጋግሯት እንደማያውቅ ነገረችው። ከዚያ አንድ መጽሐፍ ወሰደችና እሷ በሚመቻት ሰዓት አንዲት እህት እቤቷ መጥታ እንድታነጋግራት ተስማማች። ውጤታማ በሆነ ሁኔታ በመንገድ ላይ የምንመሰክር ከሆነ ሊሰሙ የሚገባቸውን ብዙ ሰዎች አግኝተን ልንረዳቸው እንደምንችል የተረጋገጠ ነው።—ሥራ 17:17