በስልክ መመስከር ብዙ ሰዎችን ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ነው
1 በምሥራቅ አፍሪካ በሚገኙ ትልልቅ ከተሞች የስልክ ግንኙነት በጣም የተለመደ ሆኗል። በየካቲት 15, 1987 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ላይ እንደተገለጸው የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ በስልክ መጠቀም አስደሳችና ውጤታማ የሆነ የመመስከሪያ መንገድ ነው።
2 ብዙ ምስክሮች በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ይበልጥ ልምድ እያገኙ ነው። ከቤት ወደ ቤት በምናደርገው ምስክርነት ልናገኛቸው ያልቻልነውን አንዳንድ ሰዎች በስልክ ልናገኛቸው እንችላለን። በስልክ የሚሰጥ ምስክርነት በጥንቃቄ፣ በደግነት፣ በዘዴና በጥበብ ከተከናወነ አንዳንዶች ጥሩ ተቀባይነት ያለው ሆኖ አግኝተውታል።
3 ከዚህ ቀደም ማኅበሩ ባለባቸው ሕመም ወይም አካለ ስንኩል በመሆናቸው ምክንያት ለጊዜው ወይም ለዘለቄታው ከቤት መውጣት የማይችሉ ወንድሞችና እኅቶች ምስክርነቱን ለመስጠት በስልክ እንዲጠቀሙ ሲያበረታታ ቆይቷል። ይህን በመሰለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እኅቶች በዚህ መልካም ሥራ ሊገፉበት ይገባል። በተጨማሪም ብዙ ወንድሞችና እኅቶች ረዳት አቅኚዎችና የዘወትር አቅኚዎችም ጭምር ከበር ወደ በር ከሚያደርጉት አገልግሎታቸው በተጨማሪ በስልክ እንደሚመሰክሩ የሚገልጹ ሪፖርቶች ደርሰውናል። ከዚህ ቀጥሎ በስልክ ስለመመስከር የሚገልጹ ጥቂት ሐሳቦች ተሰጥተዋል።
4 እንዴት መዘጋጀት እንደምንችል፦ በዚህ የአገልግሎት መብት ከሚካፈሉት ከሌሎች ጋር ተነጋገር፤ አንዳንድ ሐሳቦችንም አግኝ። ይሆናል የሚል አመለካከት ሁልጊዜ ይኑርህ። ይሖዋን የኃይልህና የጥንካሬህ ምንጭ አድርገህ ተመልከተው። እንዲሁም በጸሎት አማካኝነት በመንገድህ እንዲመራህ ጠይቅው። (መዝ. 27:14፤ ፊል. 4:13) እንደ ሌሎቹ የምስክርነት መስጫ መንገዶች ሁሉ በዚህ ሥራ በሙሉ ልብህ ለመሳተፍ ዕቅድ አውጣ። — ከማርቆስ 12:33 ጋር አወዳድር።
5 ስልክ በምንደውልበት ጊዜ ጠረጴዛ ወይም ዴስክ አጠገብ መቀመጥ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል በተሞክሮ ተረጋግጧል። በደረቅ ወንበር ላይ መቀመጥ በትክክል ለማሰብና አእምሮ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ይረዳል። ለመመስከር የምትጠቀምባቸውን ነገሮች ሁሉ ማለትም ትራክቶችን፣ በወቅቱ በመበርከት ላይ ያለውን ጽሑፍ፣ በቅርብ የወጡ መጽሔቶችን ወይም አንዳንድ ትኩረትን የሚስብ ሐሳብ ያላቸውን የቆዩ መጽሔቶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምክንያቱን ማስረዳት የተባለውን መጽሐፍ፣ የመንግሥት አዳራሹ አድራሻና ስብሰባ የሚደረግባቸው ሰዓታት የተመዘገበበት የስብሰባ መጋበዣ ካርድ፣ ብዕር ወይም እርሳስ እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽ ከፊት ለፊትህ አስቀምጥ። የምትጠቀምበትን ጽሑፍ አዘጋጅ፤ ምናልባትም አንድ የተወሰነ አርዕስት ላይ ገልጠህ አስቀምጠው። የምታደርገውን ውይይት በደንብ ተለማማድ። የምትደውልበት ዓላማ ምስክርነት ለመስጠትና በተቻለ ፍጥነት ግለሰቡን ሄደህ ለማነጋገር ዝግጅት ለማድረግ መሆኑን በአእምሮህ ያዝ።
6 ስልክ በምትደውልበት ጊዜ፦ ዘና በል። እንደወትሮህ ተናገር። በስልክ ውጤታማ የሆነ ምስክርነት ለመስጠት ሞቅ ያለና ደስ የሚል አነጋገር ያስፈልጋል። በፊትህ ላይ የሚታየው ፈገግታ በድምፅህ ቃና ላይ ይንጸባረቃል። በቂ የሆነ የድምፅ መጠን በመጠቀም ረጋ ብለህ በግልጽ ተናገር። በትሕትና፣ በትዕግሥትና በወዳጅነት ተናገር። ተቃውሞ ያጋጥመኝ ይሆናል ብለህ አትፍራ። አንዳንድ ሰዎች ለምትነግራቸው መልእክት ፍላጎት ላይኖራቸው እንደሚችል ከመጀመሪያውኑ መቀበል ይኖርብሃል። በስልክ የምትሰጠውን ምስክርነት ዘወትር ከቤት ወደ ቤት ከምታደርገው አገልግሎት ባልተለየ መንገድ ተመልከተው።
7 በመግቢያህ ላይ ሙሉ ስምህን ተናገር። ምክንያቱን ማስረዳት በተባለው መጽሐፍ ላይ ያሉት ብዙ መግቢያዎች በውይይት መልክ በቀጥታ ሊነበቡ ይችላሉ። ገና በውይይቱ መጀመሪያ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቀም። በውይይቱ ሂደት ላይ የሆነ ነጥብ ላይ ስትደርስ አስፈላጊ መስሎ ከተሰማህ የይሖዋ ምስክር መሆንህን ግለጽላቸው። የሚያነጋግርህ ሰው በውይይቱ እንዲካፈል ፍቀድለት። ሰውዬው ሐሳቡን ሊያካፍልህ ቢፈልግ ከመስማት ወደ ኋላ አትበል። ለሰጣቸው ሐሳቦችና አስተያየቶች አመስግነው። ሰውዬውን ለማሞገስ ዝግጁ ሁን። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ብዙ እያወራ አላናግር ካለህ ወይም ክርክር ከጀመረህ ንግግሩን በዘዴ አቋርጠው። ልባቸውን ወደ አምላክ ያዘነበሉትን ሰዎች ለማግኘት በምታደርገው ፍለጋ የአምላክ መንፈስ እንዲመራህ ፍቀድለት።
8 ውይይቱን የቤቱ ባለቤት ከሚደመድመው ይልቅ አንት ብትደመድመው የተሻለ ነው። ሰውዬውን በመንግሥት አዳራሽ ለሚደረገው የሕዝብ ንግግር በመጋበዝና የመንግሥት አዳራሹን አድራሻና የስብሰባውን ጊዜ በመንገር ልትደመድም ትችላለህ። በተጨማሪም በተወያያችሁበት ሐሳብ ላይ የበለጠ ለመወያየት ቤቱ ድረስ ሄዶ ማነጋገር ይቻል እንደሆነ ያነጋገርከውን ሰው ልትጠይቀው ትችላለህ። በስልክ አማካኝነት ውጤታማ በሆነ መንገድ ጽሑፍ ማስተዋወቅ ይቻል ይሆናል። የመጽሔት ደንበኛ ለማግኘት ግብ በማድረግ መጽሔቶችን ዘወትር ልታመጣለት እንደምትችል ግለጽለት።
9 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የምስክርነቱን ሥራ ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ ለማስፋፋት ጥረት እንዲያደርጉ አዟቸዋል። (ሥራ 1:8) በአንዳንድ አካባቢዎች በስልክ በመመስከር ይህን ትዕዛዝ መፈጸም ይቻላል። እነዚህን ሐሳቦች የተከተሉ ወንድሞች በጣም የሚያበረታቱ ውጤቶች አግኝተዋል። በስልክ የሚሰጥ ምስክርነት ‘አገልግሎታቸውን የሚያከብሩበት’ አንዱ የተለየ ዘዴ ሆኖ አግኝተውታል። (ሮሜ 11:13) አንተም በስልክ በመመስከር ይህንኑ ደስታ አግኝ።