የጥያቄ ሣጥን
◼ በስልክ ስንመሠክር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚቻልበትን ዝግጅት መጥቀስ ይኖርብናል?
ሰዎችን በአካል ቀርበን በምናነጋግርበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ የሚካሄደው ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች መሆኑንና እንዲህ ዓይነቱን መዋጮ በደስታ እንደምንቀበል መግለጽ እንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በስልክ በምንመሠክርበት ወቅት ገንዘብ እንደማሰባሰብ ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም ስለሚችል መዋጮ ማድረግ ስለሚቻልበት ዝግጅት ምንም ነገር ማንሳት አይኖርብንም። የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎት ገንዘብ ማግኛ አይደለም።—2 ቆሮ. 2:17
◼ በስልክ ምሥክርነት ስንሰጥ አንድ ግለሰብ የይሖዋ ምሥክሮች በድጋሚ ቤቱ እንዲደውሉ እንደማይፈልግ ቢናገርስ?
የግለሰቡ ፍላጎት መከበር ይኖርበታል። አስፋፊዎች በዚያ ስልክ ቁጥር በድጋሚ እንዳይደውሉ ለማድረግ የግለሰቡ ስምና ይህን አቋሙን የገለጸበት ዕለት የተጻፈበት ማስታወሻ ከአገልግሎት ክልል ቅጹ ጋር ተያይዞ መቀመጥ አለበት። ቤታቸው እንድንደውል የማይፈልጉ ሰዎች ስም ዝርዝር በዓመት አንድ ጊዜ መታየት አለበት። የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ተሞክሮ ያካበቱ አስፋፊዎች እነዚህ ሰዎች አሁንም ተመሳሳይ አመለካከት እንዳላቸው ለማወቅ ደውለው እንዲያነጋግሯቸው ሊመደቡ ይችላሉ።—የሰኔ 1994 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣውን የጥያቄ ሣጥን ተመልከት።
◼ በወኅኒ ቤት ውስጥ ለሚገኙ እስረኞች ስንመሠክር ምን ጥንቃቄዎችን ማድረግ አለብን?
በዓለም ዙሪያ ቢያንስ 8 ሚልዮን እስረኞች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ለምሥራቹ ፍላጎት ያሳያሉ። (1 ጢሞ. 2:3, 4) አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ከእስረኞችና ከቤተሰቦቻቸው ጽሑፍ እንዲላክላቸው ወይም የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሯቸው የሚጠይቁ 1, 400 የሚያህሉ ደብዳቤዎች በየወሩ ይደርሱታል። አብዛኞቹ እስረኞች ለምሥራቹ የሚያሳዩት ፍላጎት ልባዊ ቢሆንም አንዳንዶቹ ግን በአምላክ ሕዝቦች ለመጠቀም የሚፈልጉ መሆናቸው ታይቷል። ከዚህ አኳያ ለእስረኞች መመሥከርን በሚመለከት ሁላችንም የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ ይኖርብናል።
ብዙውን ጊዜ ለእስረኞች ምሥክርነቱ የሚሰጠው በደብዳቤ ነው። ዓላማው በመንፈሳዊ ለመርዳት ቢሆንም እንኳ እህቶች ለወንድ እስረኞች ደብዳቤ መጻፍ እንደሌለባቸው በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን። እንዲህ መደረግ ያለበት ብቃት ባላቸው ወንድሞች ብቻ ነው። ጥሩ ችሎታ ያላቸው እህቶች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልባዊ ፍላጎት ካሳዩ ሴት እስረኞች ጋር እንዲጻጻፉ ሊመደቡ ይችላሉ። እስረኞች ቢጠይቁ እንኳን ገንዘብ ወይም ሌሎች ስጦታዎች መላክ አይገባም።
አንድ እስረኛ ለምሥራቹ ፍላጎት ካሳየ ስሙና አድራሻው በወኅኒ ቤቱ አቅራቢያ ላለው ጉባኤ መሰጠት አለበት። ብዙውን ጊዜ በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ብቃት ያላቸው ወንድሞች ሊያጋጥሙ የሚችሉ የተለያዩ ሁኔታዎችን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ያውቃሉ። ወኅኒ ቤቱ በየትኛው የጉባኤ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ ለማወቅ ካልተቻለ የእስረኛው ስምና አድራሻ ለቅርንጫፍ ቢሮው መላክ አለበት።
እስረኞችን እንዲያስጠኑ የተመደቡ ወንድሞች በርካታ እስረኞችን በአንድ ላይ አሰባስበው ማስጠናታቸው ምንም ችግር የለውም። ይሁን እንጂ አስፋፊዎችና እስረኞች ያለ ምንም ቁጥጥር በአንድ ላይ ተቀላቅለው ጊዜ የሚያሳልፉባቸው ልዩ ዝግጅቶች በወኅኒ ቤቱ ውስጥ መደረግ የለባቸውም። በተጨማሪም በቅድሚያ ዝግጅት ሳይደረግበት እንዲሁ ወደ አንድ ወኅኒ ቤት ጎራ ማለትም ሆነ ከእስረኞች ጋር ከልክ በላይ መቀራረብ የሚደገፍ ድርጊት አይደለም።
ምሥራቹን ለእስረኞች ስናካፍል “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች” መሆናችን ተገቢ ነው።—ማቴ. 10:16