መጽሔቶቻችንን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙባቸው
1 ብዙ ሰዎች የሚያነቡት ምንድን ነው? መጽሔቶችን ነው። ጥናቶች እንዳሳዩት ከ10 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉት አሥር ወጣቶች ውስጥ ዘጠኙ እንዲሁም ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው አዋቂዎች ቢያንስ በወር አንድ መጽሔት ያነባሉ። ሰዎች ለመጽሔት ፍቅር አላቸው።
2 ልበ ቅን ሰዎች ለመጠበቂያ ግንብ እና ለንቁ! መጽሔት ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረግ እንችላለንን? እኛ ራሳችን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን በንቃት የምንከታተል ከሆነ እንችላለን። እንዲህ ለማድረግ የሚረዳን ምንድን ነው? የሚከተሉትን ምክሮች ልብ በል:-
◼ መጽሔቶቹን አንብባቸው:- አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እርሱ በሚጎበኘው ወረዳ ውስጥ እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትም ከዳር እስከ ዳር የሚያነቡት በአማካይ ከሦስት አስፋፈዎች ውስጥ አንዱ ብቻ እንደሆነ ሪፖርት አድርጓል። አንተስ ታነባለህን? እያንዳንዱን ርዕስ ስታነብ ይህንን ትምህርት ‘አንዲት እናት፣ አንድ ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም የሚል ሐሳብ ያለው ሰው፣ አንድ ነጋዴ ወይም አንድ ወጣት እንዴት ይመለከቱታል? ’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። መጽሔቱን ስታስተዋውቅ ልትጠቀምባቸው ትችል ዘንድ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦችን በራስህ ቅጂ ላይ ምልክት አድርገህ ያዝ። ከዚያም በአንድ ወይም በሁለት ዓረፍተ ነገር ብቻ ሰዎች ለርዕሱ እንዴት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ እንደምትችል አስብ።
◼ የተወሰነ የመጽሔት ትእዛዝ ይኑርህ:- ከእያንዳንዱ እትም ምን ያህል መጽሔቶችን እንደምትፈልግ ለመጽሔት አገልጋዩ ንገረው፤ ልታበረክተው የምትችለውን ያክል ብቻ እዘዝ። በዚህ መንገድ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ በቂ መጠን ያላቸው መጽሔቶች ሳያቋርጡ ይደርሷችኋል።
◼ ቋሚ የመጽሔት ማበርከቻ ቀን መድብ:- ብዙ ጉባኤዎች በመጽሔት ምሥክርነት የሚሰጡበት የተወሰነ ቀን መድበዋል። በጉባኤው የመጽሔት ቀን መካፈል ትችላለህን? የማትችል ከሆነ በአገልግሎት ከምታሳልፈው ሰዓት የተወሰነውን በመንገድ ላይ በሚደረገው ምሥክርነት መጽሔት ለማበርከት እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ ለምታገኛቸው ሰዎችም ሆነ ለመጽሔት ደንበኞችህ በግልህ መጽሔቶችን ለማሰራጨት ሞክር።
◼ “መጠበቂያ ግንብ ” እና “ንቁ! ” መጽሔትን በንቃት ተከታተል:- በጉዞ ላይ ስትሆን ወይም ወደ ገበያ ስትሄድ መጽሔቶቹ አይለዩህ። ከሥራ ባልደረቦችህ፣ ከጎረቤቶችህ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞችህ ወይም ከአስተማሪዎችህ ጋር ስትነጋገር አበርክታቸው። ብዙ ጊዜ በአውሮፕላን የሚጓጓዙ አንድ ባልና ሚስት ከአጠገባቸው ከሚቀመጠው መንገደኛ ጋር ውይይት ለመጀመር በቅርቡ በወጡ መጽሔቶች ውስጥ በሚገኝ አንድ ነጥብ ይጠቀማሉ። ይህን በማድረጋቸው ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች አግኝተዋል። አንዳንድ ወጣቶች የአስተማሪዎቻቸውንና አብረዋቸው የሚማሩ ተማሪዎችን ትኩረት ይስባሉ ብለው ያሰቧቸውን ርዕሶች የያዙ መጽሔቶችን ሳያቋርጡ ወደ ትምህርት ቤት ይዘው ይሄዳሉ። ተልከህ ወጣ ስትል መጽሔቶች ይዘህ በመሄድ ሥራህን ከጨረስክ በኋላ ለነጋዴዎቹ አበርክትላቸው። ብዙዎቻችን ሁልጊዜ ነዳጅ እንቀዳለን፤ ታዲያ ለነዳጅ ማደያው ሠራተኞች ለምን መጽሔት አናበረክትላቸውም? ዘመዶችህን ስትጠይቅ፣ በሕዝብ መጓጓዣ ስትጠቀም ወይም የቀጠሮህ ሰዓት እስከሚደርስ ስትጠብቅ መጽሔቶች ከእጅህ አይለዩ። ሌሎች ተስማሚ አጋጣሚዎችን ልትገልጽ ትችላለህን?
◼ መጽሔት ለማበርከት የሚያስችል አጠር ያለ አቀራረብ ተዘጋጅ:- ጥቂት ነገር ብቻ ለመናገር ተዘጋጅ፤ የምትናገረው ነገር ግን ግልጽ ይሁን። ሞቅ ያለ ስሜት ይኑርህ። ልብ የምትነካ ሁን። በተወሰነ ነገር ላይ አተኩር። ከአንድ ርዕስ ውስጥ አንድ ሐሳብ መርጠህ በአጭሩ ከገለጽህ በኋላ መጽሔቶቹን አበርክት። ከሁሉ የተሻለ አቀራረብ ትኩረት በሚስብ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥያቄ አንስቶ ለጥያቄው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ ወደሚሰጥ አንድ ርዕስ መምራት ነው። ይህንን እንዴት ማድረግ እንደምንችል የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ተመልከት:-
3 ወንጀል እየከፋ ስለመሄዱ የሚናገር ርዕስ የምትጠቅስ ከሆነ እንዲህ በማለት መጠየቅ ትችላለህ:-
◼ “ወንጀል ይፈጸምብኛል ብለን ሳንሠጋ በሰላም መተኛት እንድንችል ምን መደረግ አለበት?” የምታነጋግረው ሰው ነገሮች እየተስተካከሉ ይሄዳሉ ብሎ አያስብ ይሆናል። ብዙ ሰዎች እንደዚህ እንደሚሰማቸው ልትገልጽለት ትችላለህ። እርሱን ሊያስደስተው ይችላል ብለህ የምታስበው አንድ ሐሳብ ልታካፍለው እንደምትፈልግ ልትነግረው ትችላለህ። ከዚያም ከርዕሱ ውስጥ አንድ ተስማሚ ነጥብ አሳየው።
4 ስለ ቤተሰብ ኑሮ የሚናገር ርዕስ ያለው መጽሔት ስታበረክት እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች መተዳደሪያ ማግኘትና ቤተሰባቸውን ማስተዳደር በጣም ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በርካታ መጽሐፎች ቢጻፉም መፍትሔ ተብለው በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ብዙ ምሁራን አይስማሙም። እምነት የሚጣልበት መመሪያ ማግኘት የምንችልበት ሌላ ምንጭ ይኖር ይሆን?” ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አንድ ሐሳብ ከመጽሔቱ ውስጥ አሳየው።
5 ስለ ማኅበራዊ ኑሮ ችግሮች የሚናገር ርዕስ ያለው መጽሔት ስታበረክት ይህንን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “ዛሬ አብዛኞቹ ሰዎች የተለያዩ ችግሮች አሉባቸው። አምላክ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድንኖር ዕቅድ አልነበረውም።” ከዚያም በርዕሱ ውስጥ የሠፈረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመቋቋም እንደሚረዳንና ወደፊት ስለሚያመጣው ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጠውንም ተስፋ አስረዳው።
6 በመንገድ ላይ የሚደረገው ምሥክርነት ውጤታማ ነው፦ አስፋፊዎች በመጽሔቶች አማካኝነት ለሚደረገው የመንገድ ላይ ምሥክርነት በየሳምንቱ አንድ ቀን እንዲመድቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ማበረታቻ የተሰጣቸው ጥር 1940 በወጣው ኢንፎርማንት (መንግሥት አገልግሎታችን ) እትም ላይ ነበር። በመንገድ ላይ በሚደረገው ምሥክርነት በየጊዜው ትካፈላለህን? የምትካፈል ከሆነ የምትጠቀምበት ዘዴ በእርግጥ ውጤታማ ነውን? አንዳንድ አስፋፊዎች በሰው በተጨናነቁ የመንገድ ማዕዘኖች ላይ ቆመው እርስ በርሳቸው በማውራት በአጠገባቸው የሚያልፉትን ብዙ ሰዎች ችላ እንዳሉ ተስተውሏል። መጽሔቶችን ይዞ ጎን ለጎን ከመቆም ይልቅ ለየብቻ ሆኖ ሰዎችን ማነጋገር ይበልጥ ውጤታማ ነው። አዳዲስ ሰዎች አንድ ሰው ብቻውን ካነጋገራቸው ቆም ብለው ለጥቂት ጊዜ ሊያዳምጡት ይችላሉ፤ ነገር ግን ሞቅ ያለ ጨዋታ የያዙትን በቡድን የቆሙ ሰዎች ቀርቦ ለማነጋገር የሚደፍር የለም ለማለት ይቻላል። በመንገድ ላይ የሰዎችን ትኩረት በእጅጉ ስለምንስብ ለአምላክ አገልጋዮች የሚስማማ ጥሩ የፀጉር አበጣጠርና ልከኛ የሆነ አለባበስ ሊኖረን ያስፈልጋል።— 1 ጢሞ. 2:9, 10
7 የመጽሔት ደንበኞች፦ የመጽሔት ደንበኛ ያላቸው አስፋፊዎቸ የአገልግሎት ክልሎቹ በተደጋጋሚ የሚሸፈኑ ቢሆኑም እንኳ ብዙ መጽሔቶች ያበረክታሉ። የመጽሔት ደንበኞች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ምንጭ ናቸው።
8 መጽሔቶቹን ለማድረስ አዘውትረህ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ በአንተና በምታነጋግረው ሰው መካከል ያለው ፍቅርና ወዳጅነት እያደገ ይሄዳል። ይበልጥ በተዋወቃችሁ መጠን ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሶችን አንስቶ መነጋገሩ ያንኑ ያህል ቀላል ይሆንልሃል። ይህም ፍሬያማ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወደ መጀመር ሊመራ ይችላል። ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ለመጽሔቶቹ አድናቆት እንዳላቸው ከተገነዘብህ ኮንትራት እንዲገቡ ጋብዛቸው። ሰውዬውን ባነጋገርከው ቁጥር አንድ ተመላልሶ መጠየቅ ሪፖርት ማድረግ እንደምትችል አትርሳ።
9 አንዲት እህት ሳታቋርጥ ለአንዲት ሴት መጽሔቶች ትወስድላት ነበር። ሴትየዋ “የምትነግሪኝን ነገር አላምንበትም” ትበል እንጂ መጽሔቶቹን ለመውሰድ አንድ ቀንም እምቢ ብላ አታውቅም። አንድ ቀን እህት ስትሄድ የሴትየዋን ባል እቤት አገኘችው። መግባባት የሰፈነበት ውይይት ካደረጉ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ዝግጅት ተደረገ። እህት በጥናቱ ላይ ለመገኘት የመጡትን ሦስት ወንዶች ልጆች ተግባባቻቸው። በመጨረሻም እናትየውና ወንዶች ልጆችዋ ሕይወታችውን ለይሖዋ ወስነው ተጠመቁ። በአሁኑ ወቅት 35 የቤተሰቡ አባላት በእውነት ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ የተገኘው እህት ለመጽሔት ደንበኛዋ ተመላልሶ መጠየቅ ስላደረገች ነው!
10 የመጽሔት ደንበኛ ለማፍራት የሚያስችሉ ብዙ መንገዶች አሉ። ያበረከትክላቸውን ሰዎች በመመዝገብና አዳዲስ እትሞችን በየሁለት ሳምንቱ ይዘህ ለመሄድ ዝግጅት በማድረግ የመጽሔት ደንበኛ ማግኘት ትችላለህ። አንዱ መንገድ “በሚቀጥለው እትማችን” በሚለው ርዕስ ሥር የሚወጣውን ርዕስ መጠቀም ነው። ተመልሰህ ስትሄድ ባለፈው ጊዜ የጠቀስከውን ርዕስ የያዘ መጽሔት ይዘህለት እንደመጣህ ለምታነጋግረው ሰው ንገረው። ወይም ደግሞ ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ እንደዚህ ማለት ትችላለህ:- “ይህንን ርዕስ ሳነብ እርስዎም ይህንን ርዕስ ለማንበብ እንደሚፈልጉ ተሰምቶኛል . . .” ከዚያም በርዕሱ ላይ አጠር ያለ ሐሳብ ስጥና አበርክትለት። ተመላልሶ መጠየቁን ስትደመድም የሚከተሉትን አምስት ቀላል ነጥቦች ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽህ ላይ አስፍር:- (1) ያነጋገርከው ሰው ስም፣ (2) ያነጋገርከው ሰው አድራሻ፣ (3) ተመላልሶ መጠየቅ ያደረግህበት ቀን (4) ያበረከትክለት መጽሔት እትም እና (5) ያስተዋወቅኸውን ርዕስ። አንዳንድ አስፋፊዎች የመጽሔት ደንበኞች በማፍራት በኩል ተሳክቶላቸዋል፤ እስከ 40 የሚደርሱ ወይም ከዚያ የሚበልጡ ደንበኞች አሏቸው!
11 በንግድ አካባቢ የሚገኝ የአገልግሎት ክልል፦ በንግድ አካባቢ በሚገኝ የአገልገሎት ክልል የሚሠሩ አስፋፊዎች ብዙ መጽሔቶች አበርክተዋል። ከሱቅ ወደ ሱቅ ለማገልገል ሞክረህ ታውቃለህን? ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ የሚደረገው ተሳትፎ ውስን ነው። አንዳንዶች መጀመሪያ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ማነጋገር አስፈሪ ቢሆንባቸውም ለጥቂት ጊዜ ከሞከሩት በኋላ አስደሳችና የሚክስ ሆኖ አግኝተውታል። በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል እድትጀምር እገዛ እንዲያደርግልህ ለምን አንድ ተሞክሮ ያለው አስፋፊ ወይም አቅኚ አትጠይቅም?
12 ከሱቅ ወደ ሱቅ መመሥከር ብዙ ጥቅሞች አሉት። ሌላው ቢቀር በሥራ ሰዓት አብዛኞቹ ይገኛሉ! በንግድ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መነጋገር የማይፈልጉትም እንኳ ብዙውን ጊዜ ለሰው አክብሮት አላቸው። አገልግሎትህን በጠዋት ብትጀምር በጥሩ ሁኔታ ሊቀበሉህ ይችላሉ። ራስህን ካስተዋወቅህ በኋላ ብዙውን ጊዜ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ሰዎችን እቤታቸው ስለማታገኛቸው በቅርብ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች እንዲወስዱ በሥራ ቦታቸው እያወያየሃቸው እንዳለህ ልትነግራቸው ትችላለህ። በንግድ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች ምንም እንኳ ለንባብ ብዙ ጊዜ ባይኖራቸውም በዓለም ላይ ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማወቅ ስለሚፈልጉ ለመጽሔቶቻችን ከፍተኛ ዋጋ እንደሚሰጡ ግለጽ። መጽሔቶቹ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በንግዱ ዓለም ካለው አድልዎ ነፃ ከሆነ አዲስ አቅጣጫ አእምሮን የሚያመራምሩ ሐሳቦች ያቀርባሉ። በንግድ አካባቢ ባለ የአገልግሎት ክልል ውስጥ ከሚገኙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ውስጥ የመጽሔት ደንበኛ ማግኘት ይቻላል።
13 በቤተሰብ መልክ ሆናችሁ አንድ ላይ ተዘጋጁ፦ በቤተሰብ ጥናታችሁ ወቅት በቅርብ ከወጡት መጽሔቶች ውስጥ የትኞቹ ርዕሶች ለአገልግሎት ክልላችሁ ተስማሚ እንደሚሆኑ ለመወያየት የተወሰነ ጊዜ መመደብ ይቻላል። ልጆችን ጨምሮ መላው የቤተሰቡ አባላት አቀራረባቸውንና “ሥራ አለብኝ፣” “የራሳችን ሃይማኖት አለን” ወይም “አልፈልግም” እንደሚሉት ለመሳሰሉ የተለመዱ የተቃውሞ ሐሳቦች ምን መልስ እንደሚሰጡ በየተራ ሊለማመዱ ይችላሉ። ጥሩ ትብብር ካለ መላው ቤተሰብ መጽሔት በማሰራጨቱ ሥራ ዘወትር መካፈል ይችላል።
14 የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ፦ የሚቻል ከሆነ በመጽሔት ቀን የሚደረገውን የመስክ ስምሪት ስብሰባ ጉባኤው አንድ ላይ ሆኖ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከማድረግ ይልቅ ስብሰባዎቹ የመጽሐፍ ጥናት በሚደረግባቸው ቦታዎች እንዲካሄዱ ዝግጅት አድርጉ። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎቹን እንዲመሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ለቡድኑ ተጨባጭ ሐሳቦችን ማቅረብ ይችሉ ዘንድ በሚገባ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ይህም ናሙና የሚሆን አንድ አቀራረብና በቅርቡ ከወጡ እትሞች ውስጥ በጉባኤው ክልል ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ፍላጎት የሚያነሳሱ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦችን መጥቀስ ሊያካትት ይችላል። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ቡድኑን ለአገልግሎት ማቀናጀትን ጨምሮ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁ አጭር ስብሰባዎች መሆን አለባቸው። የመጽሐፍ ጥናት ቡድኑ በአገልግሎት በሚያሳልፋቸው ሰዓታት በሙሉ ሥራ እንዳይፈታ የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች በቂ የአገልግሎት ክልል መኖሩን ማረጋገጥ ይገባቸዋል።
15 ለመጽሔቶቹ ያላችሁን አድናቆት አሳዩ፦ በሐምሌ 1993 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣው “በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በጥሩ ሁኔታ መጠቀም” የሚለው ርዕስ የሚከተለውን ጠቃሚ ነጥብ አስፍሯል:- “መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ከታተሙበት ቀን በአንድ ወይም በሁለት ወር ውስጥ ሁሉም መበርከት ባይችሉም እንኳን ያላቸውን ጠቃሚነት እንደማያጡ አስታውሱ። የያዟቸውን ሐሳቦች ጊዜ አይሽራቸውም፤ . . . የቆዩ መጽሔቶች እንዲከማቹ ማድረግና በፍጹም አለመጠቀም ለእነዚህ ጠቃሚ መሣሪያዎች አድናቆት እንደጎደለን ያሳያል። . . . የቆዩትን እትሞች ከማስቀመጥና ከመርሳት ይልቅ እነዚህን መጽሔቶች ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ለማበርከት ልዩ ጥረት ማድረግ አይሻልምን?”
16 በጊዜያችን እውነትን የሚፈልጉ ብዙ ልበ ቅን ሰዎች አሉ። እነርሱን ወደ እውነት ለመምራት የሚያስፈልገው ነገር በአንዷ መጽሔት ውስጥ ያለው ሐሳብ ብቻ ሊሆን ይችላል! ይሖዋ አስደሳች መልእክት እንድናውጅ አዞናል፤ መልእክቱን ለሌሎች ለማድረስ ደግሞ መጽሔቶቻችን ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። ወደፊት መጽሔት ለማሰራጨቱ ሥራ ይበልጥ ትኩረት ትሰጠዋለህን? ከሚከተሉት ምክሮች አንዳንዶቹን ከፊታችን ባሉት ቅዳሜና እሑድ ትጠቀምባቸዋለህን? እንደዚህ ካደረግህ በእጅጉ ትባረካለህ።
የሚሠሩ ሐሳቦች፦
◼ መጽሔቶቹን ቀደም ብለህ በማንበብ ከርዕሶቹ ጋር ተዋወቅ።
◼ የአካባቢህ ሰዎች በጋራ ስለሚያሳስባቸው ነገር የሚያወሳ ርዕስ ምረጥ።
◼ ለተለያዩ ሰዎች ይኸውም ለወንዶች፣ ለሴቶችም ሆነ ለወጣቶች የሚስማማ አቀራረብ ተዘጋጅ። መጽሔቱ ከምታነጋግረው ሰው ሁኔታ ጋር የሚስማማበትን መንገድና መላው ቤተሰቡ እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚችል ግለጽለት።
◼ አብዛኞቹ ሰዎች እቤት በሚገኙበት ሰዓት አገልግሎት ለመውጣት ዕቅድ አውጣ። አንዳንድ ጉባኤዎች መጽሔቶችን በመጠቀም ምሽት ላይ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጅት አድርገዋል።
◼ አቀራረብህ አጭርና አስፈላጊውን ነጥብ ብቻ የሚጠቅስ ይሁን።
◼ ስትናገር በጣም አትፍጠን። አድማጭህ ፍላጎት ከሌለው ቶሎ ቶሎ መናገርህ ጥቅም የለውም። ዘና ለማለትና የምታነጋግረው ሰው ሐሳቡን እንዲገልጽ አጋጣሚ ለመስጠት ሞክር።
መጽሔቶችን ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማበርከት፦
◼ ወዳጃዊ ፈገግታና ደግነት የተላበሰ የድምፅ ቃና ይኑርህ።
◼ ስለ መጽሔቶቹ ስትናገር ግለት ይኑርህ።
◼ ዝግ ብለህ ግልጽ በሆነ መንገድ ተናገር።
◼ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ብቻ ተናገር፤ የምታነጋግረውን ሰው ፍላጎት የሚቀሰቅስ አጭር ነገር ተናግረህ መጽሔቱ እንዴት እንደሚጠቅመው ግለጽለት።
◼ የመጽሔቱን አንድ ርዕስ ብቻ ጎላ አድርገህ ግለጽ።
◼ አንድ መጽሔት ብቻ አስተዋውቀህ ሌላውን ከዚያ መጽሔት ጋር አያይዘህ አበርክት።
◼ መጽሔቶቹን ለምታነጋግረው ሰው ስጠው።
◼ ያነጋገርከው ሰው ተመልሰህ ለመምጣት ዕቅድ እንዳለህ ይወቅ።
◼ መጽሔቶቹን አልወስድም ካለ ውይይትህን ወዳጃዊና ገንቢ በሆነ ስሜት ደምድም።
◼ ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽህ ላይ ፍላጎት ያሳዩትንና ያበረከትክላቸውን ሰዎች ሁሉ መዝግብ።
መጽሔት ለማበርከት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች፦
◼ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ምሥክርነት
◼ በመንገድ ላይ በሚደረግ ምሥክርነት
◼ ከሱቅ ወደ ሱቅ በሚደረገው ምሥክርነት
◼ የመጽሔት ደንበኛ
◼ ምሽት ላይ በሚደረገው ምሥክርነት
◼ ተመላልሶ መጠየቆች ስታደርግ
◼ ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና የነበረ ሰው ስታነጋግር
◼ በጉዞ ላይ ስትሆንና ገበያ ስትገበይ
◼ ከዘመዶችህ፣ ከሥራ ባልደረቦች፣ ከጎረቤቶችህ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞችህ፣ ከአስተማሪዎችህ ጋር ስትነጋገር
◼ በሕዝብ መጓጓዣዎችና ወረፋ ስትጠብቅ