ለልጆቻችሁ ምን ዓይነት ግቦች አውጥታችሁላቸዋል?
1 የሕይወት ስኬታማነት ጊዜና ጉልበት ቢጠፋላቸው የማይቆጩ ግቦችን ከፊታችን በማስቀመጥና እነዚህ ግቦች ላይ ተጣጥረን በመድረስ ላይ የተመካ ነው። ከንቱና የማይደረስባቸው ግቦች ከፊታቸው የሚያስቀምጡ ሰዎች ያሰቡት ነገር ስላልተፈጸመ ከመከፋታቸውም በላይ ርካታ አያገኙም። የትኞቹን ግቦች ብንከታተል ‘እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን ለመያዝ’ እንደምንችል መገንዘብ ጥበብ ይጠይቃል። (1 ጢሞ. 6:19 አዓት ) ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለብን በትክክል ስለሚመራን ምንኛ አመስጋኞች ነን!— ኢሳ. 30:21
2 ይሖዋ ይህንን የመሰለ ፍቅራዊ መመሪያ በማዘጋጀት ለወላጆች ጥሩ ምሳሌ ትቶላቸዋል። ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ከሁሉ የተሻለው መንገድ የትኛው እንደሆነ ተሞክሮ የሌላቸው ልጆቻቸው ራሳቸው እንዲመርጡ ከመተው ይልቅ በየትኛው መንገድ መሄድ እንደሚገባቸው ያሰለጥኗቸዋል። ‘በሸመገሉ ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይሉም።’ (ምሳሌ 22:6) ክርስቲያን ወላጆች በራሳቸው ማስተዋል መደገፍ እንደማይችሉ ከተሞክሮ አውቀዋል። በይሖዋ መታመን አለባቸው። (ምሳሌ 3:5, 6) ውስን እውቀትና ተሞክሮ ያላቸው ልጆች ደግሞ እንዲህ ማድረጋቸው ይበልጥ አስፈላጊ ነው።
3 ወላጆች ልጆቻቸው ‘ይበልጥ በሚሻለው ነገር’ ላይ እንዲያተኩሩ የሚረዳቸው ጊዜና ጉልበት ቢጠፋለት የማይቆጭ ግብ ሊያወጡላቸው ይችላሉ። (ፊልጵ. 1:10) ልጆች የቤተሰብ ጥናቱን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡና ከጥናቱም እንዲማሩ በማበረታታት ሊጀምሩ ይችላሉ። ልጆች ለጉባኤ ስብሰባዎች ቀደም ብሎ የመዘጋጀትና በራሳቸው አባባል ሐሳብ ለመስጠት ዝግጁ የመሆንን ልማድ ቢያዳብሩ ጥሩ ነው። በስብከቱ ሥራ አዘውትረው መካፈላቸውም አስፈላጊ ነው። ትንንሽ ልጆች ትራክቶች በማበርከት፣ ጥቅስ በማንበብ ወይም መጽሔቶችን በማስተዋወቅ ሊካፈሉ ይችላሉ። ማንበብ ሲችሉ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ቢመዘገቡ መንፈሳዊ እድገታቸውን ሊያፋጥንላቸው ይችላል። ያልተጠመቀ አስፋፊ መሆን ወይም ለጥምቀት ተቀባይነት ማግኘት ወደ ፊት ለመግፋት የሚያስችል አንድ ትልቅ እርምጃ ነው።
4 ወላጆች ልጆቻቸው ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ሲቃረቡ ወይም ከዚያ ቀደም ብሎ ሥራን በተመለከተ ስለሚያወጧቸው ግቦች ከእነርሱ ጋር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መነጋገር አለባቸው። የትምህርት ቤት አማካሪዎችና የክፍል ጓደኞቻቸው ዓለማዊና ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዲከተሉ በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ይችላሉ። የመንግሥቱን ጉዳዮች መሥዋዕት ሳያደርጉ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት የሚያስችላቸውን ጠቃሚ ሥልጠና የሚያስገኝ የትምህርት ዓይነት እንዲመርጡ ወላጆች ሊረዷቸው ይገባል። (1 ጢሞ. 6:6–10) የነጠላነትን “ስጦታ” ግባቸው እንዲያደርጉ ማበረታታት ይቻላል። በኋላ ለማግባት ቢወስኑ እንኳ ከባድ የሆኑትን የትዳር ኃላፊነቶች ለመሸከም የሚያስችላቸው አቋም ይኖራቸዋል። (ማቴ. 19:10, 11፤ 1 ቆሮ. 7:36–38) ወላጆች ስለ አቅኚነት፣ የምሥራቹ አገልጋዮች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ስለማገልገል፣ ስለ ቤቴል አገልግሎት ወይም ስለ ሚስዮናዊነት ሥራ የሚያበረታቱ ነገሮችን በመናገር ልጆቻቸው በሕፃንነታችው ሕይወታቸውን ይሖዋን በሚያስደስት፣ ሌሎችን በሚጠቅምና ለራሳቸው በረከት በሚያስገኝ መንገድ የመጠቀሙን ምኞት በውስጣቸው ሊተክሉ ይችላሉ።
5 በዛሬው ጊዜ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ክርስቲያናዊ የሥነ ምግባር አቋም ያላቸውና ቲኦክራሲያዊ ግቦች ከፊታቸው ያስቀመጡ በጣም ብዙ ወጣቶች መገኘታቸው እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ ነገር አይደለም። የተሳካላቸው በአፍቃሪ ወላጆቻቸው ጥረት ነው ለማለት ይቻላል። ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ ወዴት እያመሩ ነው? በመንግሥቱ ጉዳዮች ላይ ወዳተኮረ ሕይወት ለመድረስ ደረጃ በደረጃ እየተጓዙ ነውን? ማድረግ ከምትችላቸው አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዱ በልጆችህ ውስጥ እውነትን መትከል እንደሆነ አስታውስ። በየቀኑ ስለ እውነት ተናገር። በታማኝነት ይሖዋን የሚያገለግል ቤተሰብ በማግኘት የተባረክህ ልትሆን ትችላለህ።— ዘዳ. 6:6, 7፤ ኢያሱ 24:15