ወጣቶች—መንፈሳዊ ግቦቻችሁ ምንድን ናቸው?
1 ይሖዋ ትርጉም ያለው ሥራ እና ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች ለደስታ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ያውቃል። (ዘፍጥረት 1:28ን፤ 2:15, 19ን ተመልከት።) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ የመስበክና የማስተማር ሥራ ሰጥቷል። በተጨማሪም በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የመውረስ የመጨረሻ ግብ አለን። እስከዚያው ድረስ ግን ኃይላችንንና ጥሪታችንን በተሳሳተ መንገድ እንዳንጠቀምበት ከፈለግን ቀስ በቀስ እያደጉ የሚሄዱ መንፈሳዊ ግቦችን ማውጣት ይኖርብናል።— 1 ቆሮ. 9:26
2 ለወጣቶች የሚሆኑ ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች:- ወጣቶች እንደየግል ችሎታቸው ሊደረስባቸው የሚችሉ ቲኦክራሲያዊ ግቦችን ሊያወጡ ይገባቸዋል። (1 ጢሞ. 4:15) አንዳንድ ትንንሽ ልጆች ማንበብ ከመቻላቸው በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በቃላቸው ለመውጣት የሚያስችላቸው ግብ ላይ ደርሰዋል። ልጆች በቤተሰብ ጥናት አማካኝነት ለስብሰባዎች መዘጋጀትን በመማር ትርጉም ያለው ሐሳብ ለመስጠትና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመመዝገብ የሚያስችላቸው ግብ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ወደ መስክ አገልግሎት በሚሄዱበት ጊዜ ምሥክርነት በመስጠቱ ሥራ ተሳትፎ ማድረግን ስለሚማሩ ቀስ በቀስ ያልተጠመቁ አስፋፊ የመሆን ግብ ላይ ይደርሳሉ። ወላጆች ለልጆቻቸው ራስን የመወሰንና የመጠመቅ ግብ ሊያወጡላቸው ይገባል።
3 በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ከሆንክ መንፈሳዊ ግቦችህ ምን ነገሮችን ያጠቃልላሉ? በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ በሆኑ ግቦች ላይ በማተኮር “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ።” (መክ. 12:1፤ መዝ. 71:17) ትምህርት ቤት በሚዘጋባቸው ወራት ለምን ረዳት አቅኚ አትሆንም? ዘወትር አቅኚ በመሆን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት አስበህ ታውቃለህ? ወደፊት በአካባቢህ በሚገኝ የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪዎች ቡድን ወይም ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል አለዚያም ወደ ሌላ ቦታ ሄደህ እርዳታ ለማበርከት እንድትችል አዲስ ቋንቋ ለመማርስ አስበሃል? በአሁኑ ጊዜ በቤቴል፣ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት፣ ወይም በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉ ብዙዎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግብ ያወጡት ገና ትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር። አንተስ ለምን እንዲሁ አታደርግም?
4 ገና በለጋ እድሜ ላይ እያላችሁ የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ተጣጣሩ። እሱ ገና የ12 ዓመት ወጣት በነበረበት ጊዜ እንኳ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች በግልጽ ተናግሯል። (ሉቃስ 2:42-49, 52) የግል ጥናት ለማድረግ፣ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብና ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር አዘውትሮ በስብሰባና በአገልግሎት ለመካፈል ጠቃሚ ግቦችን ማውጣት ኢየሱስ ባስተማረበት መንገድ ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች የማስተማር ችሎታ እንድታዳብር ይረዳሃል።