መንፈሳዊ ግቦችህ ላይ እንዴት መድረስ ትችላለህ?
1. ብዙ ወጣት ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መንፈሳዊ ግቦች አውጥተዋል?
1 ወጣት ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና ኢየሱስ ‘መንግሥቱን አስቀድሙ’ ሲል የተናገራቸው ቃላት በሕይወትህ ውስጥ በምታወጣቸው ግቦች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴ. 6:33) ምናልባት ግብህ አቅኚ በመሆን አገልግሎትህን ማስፋት ወይም የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ተዛውረህ ማገልገል ይሆናል። አንዳንዶች በዓለም አቀፉ የግንባታ ሥራ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው ለማገልገል፣ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ለመሥራት ወይም ሚስዮናዊ ለመሆን አሊያም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ለመሄድ ያስቡ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ግቦች አርኪና የሚያስመሰግኑ ናቸው!
2. መንፈሳዊ ግቦችህ ላይ መድረስ እንድትችል ምን ሊረዳህ ይችላል?
2 መንፈሳዊ ግቦችህ ላይ መድረስ እንድትችል ግቦችህን በጽሑፍ ማስፈር ጠቃሚ ነው። የሐምሌ 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል:- ‘አንድ ያሰብከውን ነገር በቃላት ለመግለጽ ስትሞክር ይበልጥ ግልጽ ይሆንልሃል። አንተም ያወጣሃቸውን ግቦች፣ እነዚህ ግቦች ላይ እንዴት መድረስ እንደምትችል፣ ያጋጥሙኛል ብለህ የምታስባቸውን መሰናክሎችና እነዚህን መሰናክሎች እንዴት መወጣት እንደምትችል በጽሑፍ ማስፈር ትችላለህ።’ በተጨማሪም የአጭር ጊዜ ግቦች ማውጣት ምን ደረጃ ላይ እንደደረስህ ራስህን ለመገምገም የሚያስችልህ ከመሆኑም በላይ የረጅም ጊዜ ግብህ ላይ ትኩረት እንድታደርግ ይረዳሃል።
3. አንድን ሰው ለጥምቀት እንዲበቃ የሚረዱት የአጭር ጊዜ ግቦች የትኞቹ እንደሆኑ ተናገር።
3 የአጭር ጊዜ ግቦች:- ያልተጠመቅህ ከሆንክ እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ እንዳለብህ አስብ። ምናልባት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርት ይበልጥ መረዳት ያስፈልግህ ይሆናል። ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በሙሉ አውጥተህ በማንበብ መጽሐፉን በሚገባ ለማጥናት ግብ አድርግ። (1 ጢሞ. 4:15) ቤቴላውያንና የጊልያድ ተማሪዎች እንደሚፈለግባቸው ሁሉ አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራእይ ለማንበብ ግብ አውጣ። ከዚያ በኋላ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ። (መዝ. 1:2, 3) እንዲህ ማድረግህ በመንፈሳዊ ምን ያህል እድገት ለማድረግ እንደሚረዳህ አስብ! እያንዳንዱን የጥናት ክፍለ ጊዜ ስትጀምርም ሆነ ስትደመድም ከልብ የመነጨ ጸሎት አቅርብ። እንዲሁም የተማርከውን በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ።—ያዕ. 1:25
4. አንድ ክርስቲያን ቤቴል ገብቶ ማገልገልንና ሚስዮናዊ መሆንን የመሳሰሉ የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ ለመድረስ ምን የአጭር ጊዜ ግብ ማውጣት ይችላል?
4 የተጠመቅህ ከሆንክ ምን ተጨማሪ ግቦች ልታወጣ ትችላለህ? የስብከት ችሎታህን ማሻሻል ያስፈልግህ ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ በመስክ አገልግሎት ላይ የአምላክን ቃል በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ግብ ማውጣት ትችላለህ? (2 ጢሞ. 2:15) አገልግሎትህን እንዴት ማስፋት ትችላለህ? ከዕድሜህና ከሁኔታህ ጋር የሚስማሙ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ግቦችህ ላይ እንድትደርስ የሚረዱህን ግቦች አውጣ።
5. አንድ ወንድም ያወጣቸው የአጭር ጊዜ ግቦች ቤቴል ገብቶ ማገልገል እንዲችል የረዱት እንዴት ነው?
5 የተሳካ ምኞት:- የ19 ዓመቱ ቶኒ የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ በጎበኘበት ወቅት በዚያ ገብቶ የማገልገል ጉጉት አደረበት። ነገር ግን አኗኗሩ ሥነ ምግባር የጎደለው ከመሆኑም በላይ ራሱን ለአምላክ ወስኖ አልተጠመቀም ነበር። ይሁን እንጂ ቶኒ ሕይወቱን ከይሖዋ መንገዶች ጋር ለማስማማትና ለጥምቀት የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ግብ አወጣ። እዚህ ግብ ላይ ከደረሰ በኋላ ደግሞ ረዳት አቅኚ ከዚያም የዘወትር አቅኚ ለመሆን የሚፈልግበትን ጊዜ በቀን መቁጠሪያው ላይ ምልክት በማድረግ ሌሎች ግቦች አወጣ። አቅኚ ሆኖ ካገለገለ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቅርንጫፍ ቢሮ ገብቶ እንዲያገለግል ሲጠራ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን ገምት!
6. መንፈሳዊ ግቦችህ ላይ እንድትደርስ ምን ሊረዳህ ይችላል?
6 አንተም የአምላክን መንግሥት ጥቅሞች ማስቀደምህን ከቀጠልህ ያወጣሃቸው መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ ትችላለህ። “የምታደርገውን ሁሉ” በጸሎት ለይሖዋ ንገረው። ከዚያም በትጋት ፈጽማቸው።—ምሳሌ 16:3፤ 21:5