ልጆቻችሁ የምሥራቹ አገልጋዮች እንዲሆኑ አሠልጥኗቸው
1. መዝሙር 148:12, 13 ክርስቲያን ወላጆች ምን እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል?
1 ይሖዋ እሱን እንዲያመሰግኑት ለልጆች ግብዣ አቅርቦላቸዋል። (መዝ. 148:12, 13) በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችንና የአምላክን የሥነ ምግባር ሕጎች በማስተማር ብቻ አይወሰኑም። የምሥራቹ አገልጋዮች እንዲሆኑም ያሠለጥኗቸዋል። ታዲያ እንዲህ ያለውን ሥልጠና ደረጃ በደረጃ መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው?
2. ወላጆች የሚተዉት ጥሩ ምሳሌ በልጆቻቸው ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል?
2 ጥሩ ምሳሌ ሁኑ፦ መስፍኑ ጌዴዎን አብረውት ለነበሩት 300 ሰዎች “እኔን ተመልከቱ” ብሏቸው ነበር። (መሳ. 7:17) ልጆች በተፈጥሯቸው ወላጆቻቸውን የማየትና እነሱን የመምሰል ዝንባሌ አላቸው። ሌሊት ላይ የሚሠራ አንድ ወላጅ ጠዋት ከሥራ ሲገባ በጣም ቢደክመውም ቅዳሜ ቅዳሜ ግን ከመተኛት ይልቅ ልጆቹን ይዞ አገልግሎት ይወጣል። ይህ ወላጅ ምንም መናገር ሳያስፈልገው አገልግሎት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ለልጆቹ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:33) ልጆቻችሁ ጸሎት እንደማቅረብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደማንበብ፣ በጉባኤ ተሳትፎ እንደማድረግና በስብከቱ ሥራ እንደመካፈል ባሉ የተለያዩ የአምልኮ እንቅስቃሴዎች በደስታ ስትካፈሉ ይመለከቷችኋል? እርግጥ ነው፣ ፍጹም ምሳሌ መሆን አትችሉም። ይሁንና ልጆቻችሁ ይሖዋን በትጋት ስታገለግሉ የሚመለከቷችሁ ከሆነ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ እነሱን ለማስተማር ለምታደርጉት ጥረት በጎ ምላሽ የመስጠታቸው አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል።—ዘዳ. 6:6, 7፤ ሮም 2:21, 22
3. ወላጆች የልጆቻቸውን ዕድሜ ግምት ውስጥ በማስገባት የትኞቹ መንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲደርሱ ሊረዷቸው ይገባል?
3 እንደ አቅማቸው ግቦችን እንዲያወጡ እርዷቸው፦ ወላጆች ልጆቻቸው መራመድ እንዲጀምሩ፣ አፋቸውን እንዲፈቱ፣ በራሳቸው መልበስ እንዲችሉና ሌሎች ነገሮችን እንዲያከናውኑ ለማሠልጠን የማያሰልስ ጥረት ያደርጋሉ። ወላጆች የልጆቻቸውን እድገት ግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ግቦችን ያወጡላቸዋል። ክርስቲያን ወላጆች ደግሞ የልጆቻቸውን ዕድሜና አቅም መሠረት በማድረግ ልጆቹ መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡና እነዚህ ግቦች ላይ እንዲደርሱ ይረዷቸዋል። (1 ቆሮ. 9:26) ልጆቻችሁ በራሳቸው አባባል መልስ እንዲሰጡና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተሰጣቸውን ክፍል በራሳቸው እንዲዘጋጁ እየረዳችኋቸው ነው? (መዝ. 35:18) በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ እንዲካፈሉስ እያሠለጠናችኋቸው ነው? ለመጠመቅና ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ግብ እንዲያወጡ እየረዳችኋቸው ነው? ሊያበረታቷቸው ከሚችሉ ደስተኛና ቀናተኛ ወንጌላውያን ጋር እንዲቀራረቡ ጥረት ታደርጋላችሁ?—ምሳሌ 13:20
4. ወላጆች ልጆቻቸውን ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ የሚያሠለጥኗቸው ከሆነ ልጆቹ ምን ጥቅም ያገኛሉ?
4 መዝሙራዊው “አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 71:17) ልጆቻችሁን ገና ከጨቅላነታቸው ጀምሮ የምሥራቹ አገልጋዮች እንዲሆኑ አሠልጥኗቸው። ልጆቻችሁ በእናንተ ድጋፍ ከወዲሁ መንፈሳዊ መሠረት የሚጥሉ ከሆነ ወደፊት ትልቅ ሲሆኑ እንደሚጠቅማቸው ምንም ጥርጥር የለውም!—ምሳሌ 22:6