ወላጆች—ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሰልጥኗቸው
1 “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።” (ምሳሌ 22:6) ወላጆች ልጆቻችሁ ከእውነት መንገድ “ፈቀቅ” እንዳይሉ ከፈለጋችሁ ይህን ዓይነት ሥልጠና መስጠት መጀመር ያለባችሁ መቼ ነው? ከሕፃንነታቸው ነው!
2 ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ትምህርት ያገኘው ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ’ እንደነበር ሲናገር ከጨቅላነቱ ጊዜ አንስቶ ማለቱ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (2 ጢሞ. 3:14, 15) በውጤቱም ጢሞቴዎስ ጎበዝ መንፈሳዊ ሰው ሊሆን ችሏል። (ፊልጵ. 2:19-22) ወላጆች እናንተም ልጆቻችሁ “በእግዚአብሔር ፊት” ለማደግ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና ‘ከሕፃንነታቸው ጀምሮ’ መስጠት መጀመር አለባችሁ።—1 ሳሙ. 2:21
3 ለእድገት የሚያስፈልጋቸውን ውኃ አጠጧቸው:- ችግኞች ትልቅ ዛፍ ሆነው ለማደግ ቋሚ የሆነ የውኃ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ልጆች የጎለመሱ የአምላክ አገልጋዮች ሆነው ለማደግ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ውኃ በደንብ መጠጣት ያስፈልጋቸዋል። ልጆችን ስለ እውነት ለማስተማርና ከይሖዋ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲመሠርቱ ለመርዳት ዋነኛው መንገድ ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው። ነገር ግን ወላጆች እያንዳንዱ ልጅ በትኩረት እየተከታተለ መቆየት የሚችልበትን የጊዜ ርዝማኔ ግምት ውስጥ አስገቡ። ትናንሽ ልጆችን በአንድ ጊዜ ለረጅም ሰዓት ከማስተማር ይልቅ የትምህርቱ ጊዜ አጠር ያለ ግን ዘወትር የሚደረግ ቢሆን ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።—ዘዳ. 11:18, 19
4 የልጆቻችሁን ትምህርት የመቅሰም ችሎታ ፈጽሞ ዝቅ አድርጋችሁ አትገምቱ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላሉት ባለ ታሪኮች ተርኩላቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ሁኔታዎችን በሥዕል እንዲያስቀምጡ ወይም ክንውኖቹን በድራማ መልክ እንዲያሳዩ አድርጉ። የማኅበሩን ቪዲዮዎችና የቴፕ ክሮች (የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎችን ጭምር) በሚገባ ተጠቀሙባቸው። የቤተሰብ ጥናቱን ከልጆቻችሁ ዕድሜና ትምህርት የመቀበል ችሎታ ጋር እንዲመጣጠን አድርጉ። መጀመሪያ ላይ የሚሰጠው ሥልጠና መሠረታዊ በሆነ ትምህርት ላይ ያተኮረና መጠኑ አነስ ያለ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ልጁ እያደገ ሲሄድ ሥልጠናው ይበልጥ እየሰፋና ደረጃ በደረጃ እየጨመረ የሚሄድ መሆን ይኖርበታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቱ ሕያውና የማይሰለች እንዲሆን አድርጉ። ልጆቻችሁ ቃሉን ‘እንዲመኙ’ የምትፈልጉ ከሆነ የሚቻላችሁን ያህል ጥናቱን ማራኪ አድርጉት።—1 ጴጥ. 2:2
5 በጉባኤ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ አድርጓቸው:- ልጆቻችሁ በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ እንዲሳተፉ ደረጃ በደረጃ እያደጉ የሚሄዱ ግቦችን አውጡላቸው። የመጀመሪያ ግባቸው ምን ሊሆን ይችላል? ሁለት ትንንሽ ልጆች ያሏቸው ወላጆች እንዲህ ብለዋል:- “ለሁለቱም ልጆቻችን በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በጸጥታ ስለ መቀመጥ ሥልጠና መስጠት ጀመርን።” ከዚያም በስብሰባዎች ላይ በራሳቸው አባባል ሐሳብ እንዲሰጡ እርዷቸው፤ እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ለመመዝገብ ግብ እንዲያወጡ አድርጉ። በመስክ አገልግሎት ላይ ለሰዎች ትራክት ማበርከት፣ ጥቅስ ማንበብ፣ መጽሔት ማስተዋወቅና ከቤት ባለቤቶች ጋር ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ሊደረስባቸው የሚችሉ ጥሩ ግቦች ናቸው።
6 ቅንዓት ያላችሁ ምሳሌዎች ሁኗቸው:- ልጆቻችሁ በየቀኑ ስለ ይሖዋ ስትናገሩና ወደ እርሱ ስትጸልዩ ይሰማሉ? ቃሉን ስታጠኑ፣ በስብሰባዎች ስትገኙ፣ በመስክ አገልግሎት ስትካፈሉና የአምላክን ፈቃድ በደስታ ስትፈጽሙ ይመለከታሉ? (መዝ. 40:8) እንዲህ ስታደርጉ መመልከታቸውና አብራችሁ ከእነርሱ ጋር እንደዚህ ማድረጋችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። አንዲት ራሷን የቻለች ልጅ ስድስት ልጆቿን ታማኝ ምሥክሮች እንዲሆኑ አድርጋ ስላሳደገች እናቷ ስትናገር “በጎ ተጽዕኖ ያሳደረብን የእሷ ምሳሌነት ነው፤ ከቃሏ ይልቅ ተግባሯ የጎላ ድምፅ ነበረው” ብላለች። አንዲት የአራት ልጆች እናት ደግሞ “‘በሕይወታችን ውስጥ ይሖዋን ማስቀደም’ የሚለው አባባል ለእኛ እንዲያው የተለመደ ሐረግ ብቻ ሳይሆን በኑሯችን የሚንጸባረቅ ነገር ነበር” ብላለች።
7 ወላጆች ከአምላክ ቃል እውነቱን በማስተማር፣ ደረጃ በደረጃ እያደጉ የሚሄዱ ግቦችን በማውጣትና በተቻለ መጠን ግሩም ምሳሌ በመሆን ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምራችሁ አሰልጥኗቸው። እንዲህ ካደረጋችሁ ደስተኛ ትሆናላችሁ!