ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲያወድሱ አስተምሯቸው
1. ትንንሽ ልጆች ይሖዋን ማወደስ ይችላሉ?
1 መዝሙር 148:12, 13 ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች የይሖዋን ስም እንዲያወድሱ ያበረታታል። ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋን ስላወደሱ ልጆች የሚገልጹ በርካታ ምሳሌዎችን ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሳሙኤል ‘በይሖዋ ፊት ያገለግል የነበረው ብላቴና’ እያለ ነበር። (1 ሳሙ. 2:18) በእስራኤል የሚገኘው የይሖዋ ነቢይ ንዕማንን ከለምጹ ሊፈውሰው እንደሚችል ለንዕማን ሚስት የነገረቻት “አንዲት ልጃገረድ” ነበረች። (2 ነገ. 5:1-3) ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ታላላቅ ሥራዎችን ባከናወነበት ወቅት “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ የጮኹት “ልጆች” ነበሩ። (ማቴ. 21:15 የ1954 ትርጉም) ታዲያ ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያወድሱ ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
2. ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ መተዋቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ምሳሌ ሁኑ:- እስራኤላውያን አባቶች እውነትን በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ከመትከላቸው በፊት እነርሱ ራሳቸው ይሖዋን እንዲወዱና ሕጉን በልባቸው ውስጥ እንዲያኖሩ ታዝዘው ነበር። (ዘዳ. 6:5-9) ስለ አገልግሎት አዎንታዊ ነገር የምትናገሩ ከሆነና አገልግሎትን የሳምንታዊ ፕሮግራማችሁ አንዱ ክፍል ካደረጋችሁት ልጆቻችሁም ይህን ሥራ አስፈላጊና እርካታ የሚያስገኝ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።
3. አንዲት እህት በወላጆቿ ምሳሌነት የተጠቀመችው እንዴት ነበር?
3 አንዲት እህት የወላጆቿን ሁኔታ በማስታወስ ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “ልጅ ሳለሁ ቤተሰባችን ዘወትር ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል ቅዳሜና እሁድ በመስክ አገልግሎት መካፈል ይገኝበታል። ወላጆቼ አገልግሎት በጣም እንደሚያስደስታቸው ማስተዋል ችዬ ነበር። በአገልግሎት መካፈል አስደሳች እንቅስቃሴ መሆኑን እያየን ነበር ያደግነው።” ይህቺ እህት በሰባት ዓመቷ ያልተጠመቀች አስፋፊ የሆነች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 33ኛ ዓመቷን ይዛለች።
4. ለልጆች ቀጣይነት ያለው ሥልጠና መስጠት ሲባል ምን ማለት ነው?
4 ቀጣይነት ያለው ሥልጠና:- ልጆቻችሁን አገልግሎት ይዛችሁ ስትወጡ እነርሱም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አበረታቷቸው። ምናልባትም በር ሊያንኳኩ፣ ለቤቱ ባለቤት ትራክት ሊሰጡ አሊያም አንድ ጥቅስ ሊያነቡ ይችላሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ደስታቸውን የሚጨምርላቸው ከመሆኑም በላይ የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች የማካፈል ጥሩ ችሎታ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል። ከፍ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ በአገልግሎት የሚያደርጉት ተሳትፎም የዚያኑ ያህል መጨመር ይኖርበታል። በመሆኑም እድገት እንዲያደርጉና የአገልግሎታቸውን ጥራት ለማሻሻል የሚያስችሏቸውን መንፈሳዊ ግቦች እንዲያወጡ እርዷቸው።
5. አንድ ልጅ ያልተጠመቀ አስፋፊ እንዲሆን የሚያስፈልገው ብቃት ምንድን ነው?
5 ልጆቻችሁ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን ብቁ እንደሆኑ ከተሰማችሁና እነርሱም አገልግሎት ለመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው ከገለጹ ነገ ዛሬ ሳትሉ ከሽማግሌዎች ጋር ተነጋገሩ። አስፋፊ መሆናቸው ይሖዋን የማወደስ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስገነዝባቸዋል። አንድ ልጅ አስፋፊ ለመሆን የተጠመቁ አዋቂዎችን ያህል እውቀት እንዲኖረው እንደማይጠበቅበት አትርሱ። ልጃችሁ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በሚገባ ተረድቷል? የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች በጥብቅ ይከተላል? በአገልግሎት የመካፈልና የይሖዋ ምሥክር የመሆን ፍላጎት አለው? ይህ ከሆነ ሽማግሌዎች ልጁ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቁ መሆን አለመሆኑን ይወስናሉ።—የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የሚለውን መጽሐፍ ከገጽ 79-82 ተመልከቱ።
6. ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሠልጠን መጣራቸው የሚክስ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
6 ልጆች ከልባቸው ይሖዋን እንዲያወድሱ ማስተማር ጥረት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ ከመመልከት የበለጠ ደስታ የሚያስገኝላቸው ነገር የለም ለማለት ይቻላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ ልጆች ድንቅ ስለሆኑት ሥራዎቹ ሲናገሩ ማየት ያስደስተዋል።