የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • od ምዕ. 8 ገጽ 71-86
  • የምሥራቹ አገልጋዮች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የምሥራቹ አገልጋዮች
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አዲስ አስፋፊዎች
  • ብቃቶቹን ማሟላት
  • ልጆችን መርዳት
  • ራስን መወሰንና መጠመቅ
  • የአገልግሎት እንቅስቃሴን ሪፖርት ማድረግ
  • የግል የመስክ አገልግሎት ሪፖርት
  • የጉባኤ የአስፋፊ መዝገብ
  • የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ሪፖርት የምናደርገው ለምንድን ነው?
  • የግል ግብ ማውጣት
  • የይሖዋ በጎች በርኅራኄ መያዝ ያስፈልጋቸዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት አቅርቡ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
  • የጥያቄ ሣጥን
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2013
  • መልካም ለማድረግ የምትቀኑ ሁኑ!
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2003
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
od ምዕ. 8 ገጽ 71-86

ምዕራፍ 8

የምሥራቹ አገልጋዮች

ይሖዋ ፍጹም አርዓያ የሚሆነንን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮልናል። (1 ጴጥ. 2:21) አንድ ሰው የኢየሱስ ተከታይ ሲሆን የአምላክ አገልጋይ በመሆን ምሥራቹን ይሰብካል። ኢየሱስ የእሱ ተከታይ መሆን በመንፈሳዊ የሚያድስ መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” (ማቴ. 11:28, 29) ኢየሱስ፣ ያቀረበላቸውን ይህን ግብዣ የተቀበሉትን ሁሉ አላሳፈራቸውም!

2 ዋነኛው የአምላክ አገልጋይ የሆነው ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሆኑ ግብዣ ያቀረበላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ነበሩ። (ማቴ. 9:9፤ ዮሐ. 1:43) እነዚህን ሰዎች ለአገልግሎት ካሠለጠናቸው በኋላ እሱ ይሠራው የነበረውን ያንኑ ሥራ እንዲሠሩ ላካቸው። (ማቴ. 10:1–11:1፤ 20:28፤ ሉቃስ 4:43) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች እንዲያውጁ ሌሎች 70 ሰዎችን ላከ። (ሉቃስ 10:1, 8-11) ኢየሱስ እነዚህን ደቀ መዛሙርት ሲልካቸው እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እናንተን የሚሰማ ሁሉ እኔንም ይሰማል። እናንተን የማይቀበል ሁሉ ደግሞ እኔንም አይቀበልም። ከዚህም በላይ እኔን የማይቀበል ሁሉ የላከኝንም አይቀበልም።” (ሉቃስ 10:16) በዚህ መንገድ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ የተሰጣቸው ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገልጾላቸዋል። ኢየሱስንና ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላክ ወክለው የመናገር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል! ኢየሱስ “መጥተህ ተከታዬ ሁን” ሲል ላቀረበው ጥሪ ምላሽ የሚሰጡ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎችም ተመሳሳይ ኃላፊነት አለባቸው። (ሉቃስ 18:22፤ 2 ቆሮ. 2:17) ጥሪውን የሚቀበሉ ሁሉ የመንግሥቱን ምሥራች የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ መለኮታዊ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20

3 ኢየሱስ ተከታዮቹ እንድንሆን ላቀረበልን ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠታችን ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን “ማወቅ” ችለናል። (ዮሐ. 17:3) የይሖዋን መንገዶች ተምረናል። በእሱ እርዳታ አእምሯችንን ማደስ፣ አዲሱን ስብዕና መልበስና አኗኗራችንን ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ማስማማት ችለናል። (ሮም 12:1, 2፤ ኤፌ. 4:22-24፤ ቆላ. 3:9, 10) ይሖዋ ላደረገልን ነገሮች ያለን ልባዊ አድናቆት ሕይወታችንን ለእሱ እንድንወስን ብሎም ይህን ውሳኔያችንን በውኃ ጥምቀት እንድናሳይ አነሳስቶናል። ከተጠመቅንበት ሰዓት አንስቶ የተሾምን የአምላክ አገልጋዮች ሆነናል።

4 ለአምላክ የምታቀርበው አገልግሎት ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግክ ከክፋት የጸዱ እጆችና ንጹሕ ልብ ሊኖርህ እንደሚገባ ምንጊዜም ማስታወስ ያስፈልግሃል። (መዝ. 24:3, 4፤ ኢሳ. 52:11፤ 2 ቆሮ. 6:14–7:1) በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለን እምነት ንጹሕ ሕሊና አስገኝቶልናል። (ዕብ. 10:19-23, 35, 36፤ ራእይ 7:9, 10, 14) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሌሎችን ላለማደናቀፍ ሲሉ ማንኛውንም ነገር ለአምላክ ክብር ሊያደርጉ እንደሚገባ መክሯል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ጥሩ ምግባር ማሳየት አማኝ ያልሆኑ ሰዎች እውነትን እንዲቀበሉ ሊያደርግ እንደሚችል በመግለጽ እንዲህ ያለ ምግባር ማሳየት ያለውን ጥቅም አጉልቷል። (1 ቆሮ. 10:31, 33፤ 1 ጴጥ. 3:1) አንድ ሰው ከእኛ ጋር አብሮ የምሥራቹ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት እንዲያሟላ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?

አዲስ አስፋፊዎች

5 ፍላጎት ያሳየን አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ከጀመርክበት ጊዜ አንስቶ ስለሚማራቸው ነገሮች ለሌሎች እንዲናገር አበረታታው። ለዘመዶቹ፣ ለጓደኞቹ፣ ለሥራ ባልደረቦቹና ለሌሎች ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከር ይችላል። አዲሶች ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የምሥራቹ አገልጋዮች እንዲሆኑ በማስተማር ረገድ ይህ ወሳኝ እርምጃ ነው። (ማቴ. 9:9፤ ሉቃስ 6:40) ግለሰቡ በመንፈሳዊ እድገት እያደረገና መደበኛ ባልሆነ መንገድ የመመሥከር ችሎታ እያዳበረ ሲሄድ በመስክ አገልግሎት መካፈል እንደሚፈልግ መግለጹ አይቀርም።

ብቃቶቹን ማሟላት

6 አንድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት አብሮህ እንዲያገለግል ከመጋበዝህ በፊት አንዳንድ ብቃቶችን ማሟላቱን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። አንድ ሰው ከእኛ ጋር አብሮ አገልግሎት ከወጣ የሚያዩት ሰዎች የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። በመሆኑም አንድ ሰው ያልተጠመቀ አስፋፊ መሆን የሚችለው አኗኗሩን ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር እንዳስማማ በግልጽ ሲያሳይ ነው።

7 ግለሰቡን ስታስጠናውና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስታወያየው ስለቆየህ ስላለበት ሁኔታ በሚገባ ማወቅህ አይቀርም። ከተማረው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖረ መሆኑን አስተውለህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች የግለሰቡን አኗኗር በተመለከተ ሁለታችሁም በተገኛችሁበት ሊያነሷቸው የሚፈልጓቸው አንዳንድ ጉዳዮች ይኖራሉ።

8 የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ሁለት ሽማግሌዎች (አንደኛው የአገልግሎት ኮሚቴ አባል ነው) በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከአንተና ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ጋር እንዲወያዩ ዝግጅት ያደርጋል። በጣም ጥቂት ሽማግሌዎች ባሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ለዚህ ጉዳይ አንድ ሽማግሌና ጥሩ ችሎታ ያለው የጉባኤ አገልጋይ ሊመደቡ ይችላሉ። ይህን እንዲያደርጉ የተመደቡት ወንድሞች ቶሎ ቀጠሮ ይዘው ውይይቱን ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲያውም እነዚህ ወንድሞች ተማሪው አስፋፊ መሆን እንደሚፈልግ የተነገራቸው የጉባኤ ስብሰባ በሚያደርጉበት ቀን ከሆነ አስጠኚውንና ጥናቱን ከስብሰባው በኋላ ሊያነጋግሯቸው ይችላሉ። ውይይቱ ዘና ባለ መንፈስ መደረግ ይኖርበታል። ተማሪው ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ እንዲያገለግል የሚፈቀድለት የሚከተሉትን ብቃቶች ካሟላ ነው፦

  1. (1) መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነ ያምናል።—2 ጢሞ. 3:16

  2. (2) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ በእነዚህ ትምህርቶች ላይ ሙሉ እምነት አለው፤ በመሆኑም ጥያቄ ሲቀርብለት መልስ የሚሰጠው በራሱ ሐሳብ ወይም በሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ ነው።—ማቴ. 7:21-23፤ 2 ጢሞ. 2:15

  3. (3) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አብሮ መሰብሰብ እንዳለበት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ሁኔታው እስከፈቀደ ድረስ ለመታዘዝ ጥረት ያደርጋል።—መዝ. 122:1፤ ዕብ. 10:24, 25

  4. (4) መጽሐፍ ቅዱስ ምንዝርን፣ ከአንድ በላይ ማግባትንና ግብረ ሰዶምን ጨምሮ የፆታ ብልግናን በተመለከተ ምን እንደሚያስተምር ያውቃል፤ እንዲሁም አኗኗሩ ይህን ትምህርት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ያሳያል። ግለሰቡ የሥጋ ዘመዱ ካልሆነች ሴት ጋር አብሮ የሚኖር ከሆነ ሁለቱ በተገቢው መንገድ የተጋቡ መሆን አለባቸው።—ማቴ. 19:9፤ 1 ቆሮ. 6:9, 10፤ 1 ጢሞ. 3:2, 12፤ ዕብ. 13:4

  5. (5) ስካርን የሚከለክለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ያከብራል፤ እንዲሁም ለሕክምና ካልሆነ በቀር ማንኛውንም ሱስ የሚያስይዝ ወይም አስተሳሰብን የሚያዛባ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ንጥረ ነገር አይጠቀምም።—2 ቆሮ. 7:1፤ ኤፌ. 5:18፤ 1 ጴጥ. 4:3, 4

  6. (6) ከመጥፎ ጓደኝነት የመራቅን አስፈላጊነት ተገንዝቧል።—1 ቆሮ. 15:33

  7. (7) አባል ከነበረበት የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋርጧል። በዚህ ድርጅት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች መካፈል እንዲሁም ድርጅቱ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ወይም እነዚህን እንቅስቃሴዎች መደገፍ አቁሟል።—2 ቆሮ. 6:14-18፤ ራእይ 18:4

  8. (8) ከዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ነው።—ዮሐ. 6:15፤ 15:19፤ ያዕ. 1:27

  9. (9) በኢሳይያስ 2:4 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በሚገባ ያምንበታል፤ በመሆኑም ብሔራት በሚያደርጉት በየትኛውም ጦርነት አይካፈልም።

  10. (10) የይሖዋ ምሥክር የመሆን ልባዊ ፍላጎት አለው።—መዝ. 110:3

9 ሽማግሌዎቹ፣ ከተነሱት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተማሪው ስላለው አመለካከት እርግጠኛ ያልሆኑበት ነገር ካለ የተጠቀሱትን ጥቅሶች መሠረት አድርገው ተጨማሪ ጥያቄዎች ሊጠይቁት ይችላሉ። ተማሪው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በስብከቱ ሥራ የሚካፈሉ ሁሉ ከእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ጋር የሚስማማ አኗኗር ሊኖራቸው እንደሚገባ መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነው። ሽማግሌዎቹ ተማሪው ከሚሰጣቸው ሐሳቦች በመነሳት ተማሪው ከእሱ ምን እንደሚጠበቅ መገንዘብ አለመገንዘቡን እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ለመካፈል የሚያስችለውን ብቃት ምክንያታዊ በሆነ ደረጃ ማሟላት አለማሟላቱን ይወስናሉ።

10 ሽማግሌዎቹ ተማሪው ብቃቱን ማሟላት አለማሟላቱን ወዲያውኑ ሊነግሩት ይገባል። አብዛኛውን ጊዜ በውይይቱ መደምደሚያ ላይ ውሳኔያቸውን ሊያሳውቁት ይችላሉ። ተማሪው ብቃቱን ካሟላ ሽማግሌዎቹ አዲስ አስፋፊ አድርገው በደስታ ይቀበሉታል። (ሮም 15:7) ወዲያውኑ በመስክ አገልግሎት መካፈል እንዲጀምርና በወሩ መጨረሻ ላይ የአገልግሎት ሪፖርቱን እንዲመልስ ሊያበረታቱት ይገባል። ሽማግሌዎቹ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል ብቁ ሲሆንና የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመልስ የጉባኤ የአስፋፊ መዝገብ በስሙ እንደሚዘጋጅና በጉባኤው ፋይል ውስጥ እንደሚካተት ሊገልጹለት ይችላሉ። ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉ የግል መረጃዎችን የሚሰበስቡት ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉትን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በቅርበት መከታተል እንዲችል እንዲሁም አስፋፊው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈልና መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ለመርዳት ነው። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ማንኛውንም የግል መረጃ የሚጠቀሙት በjw.org ላይ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ የመረጃ ጥበቃ ፖሊሲ መሠረት እንደሆነ ለአዳዲስ አስፋፊዎች ሊያሳውቋቸው ይችላሉ።

11 ከአዲሱ አስፋፊ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ መጣራችንና የሚያደርገውን እድገት በትኩረት መከታተላችን በግለሰቡ ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። እንዲህ ማድረጋችን አዲሱ አስፋፊ የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን በየወሩ እንዲመልስና ይሖዋን ለማገልገል ይበልጥ ጥረት እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል።—ፊልጵ. 2:4፤ ዕብ. 13:2

12 ሽማግሌዎቹ በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ብቁ እንደሆነ ከወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለውን መጽሐፍ የግል ቅጂ ማግኘት ይችላል። ለመጀመሪያ ጊዜ የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን ሲመልስ ተማሪው ያልተጠመቀ አስፋፊ መሆኑን የሚገልጽ አጠር ያለ ማስታወቂያ ለጉባኤው ይነገራል።

ልጆችን መርዳት

13 ትናንሽ ልጆችም የምሥራቹ አስፋፊዎች ሆነው ለማገልገል ብቃቱን ሊያሟሉ ይችላሉ። ኢየሱስ ወደ እሱ የመጡትን ትናንሽ ልጆች በደስታ ተቀብሎ ባርኳቸዋል። (ማቴ. 19:13-15፤ 21:15, 16) ልጆችን የመርዳቱ ተቀዳሚ ኃላፊነት የወላጆች ቢሆንም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም በመንግሥቱ የስብከት ሥራ የመሳተፍ ልባዊ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ሊረዷቸው ይችላሉ። ወላጅ ከሆንክ በመስክ አገልግሎት ጥሩ ምሳሌ መሆንህ ልጆችህ ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት ቀናተኛ እንዲሆኑ በእጅጉ ሊያበረታታቸው ይችላል። መልካም ምግባር ያለው አንድ ልጅ ስለ እምነቱ ለሌሎች የመናገር ልባዊ ፍላጎት ካለው በዚህ ረገድ ምን ተጨማሪ እርዳታ ሊደረግለት ይችላል?

14 የልጁ ወላጅ የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ከሆኑት ሽማግሌዎች መካከል ወደ አንዱ ቀርቦ ልጁ አስፋፊ ሆኖ የማገልገል ፍላጎት እንዳለው መናገር ይኖርበታል፤ ከዚያም ሽማግሌዎች ልጁ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል ብቁ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ እሱን የሚያነጋግሩበት ዝግጅት ያደርጋሉ። የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ሁለት ሽማግሌዎች (አንደኛው የአገልግሎት ኮሚቴ አባል ነው) ከልጁና አማኝ ከሆነው ወላጁ (ወላጆቹ) አሊያም ከአሳዳጊው ጋር ተገናኝተው እንዲነጋገሩ ዝግጅት ያደርጋል። ልጁ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሠረታዊ እውቀት ካለውና በአገልግሎት መካፈል የሚፈልግ ከሆነ ይህ ጥሩ እድገት ማድረጉን ያመለክታል። ሁለቱ ሽማግሌዎች እነዚህንና በዕድሜ ጎልማሳ ከሆኑ ሰዎችም ጭምር የሚጠበቁ ሌሎች ብቃቶችን ካመዛዘኑ በኋላ ልጁ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል ብቁ መሆን አለመሆኑን ይወስናሉ። (ሉቃስ 6:45፤ ሮም 10:10) ሽማግሌዎች አንድን ትንሽ ልጅ ሲያነጋግሩ በአብዛኛው ጎልማሳ ከሆኑ ሰዎች ጋር የሚያነሷቸውንና ልጁን የማይመለከቱትን ጉዳዮች አንስተው መወያየት አያስፈልጋቸውም።

15 በውይይቱ ወቅት ሽማግሌዎቹ፣ ላደረገው እድገት ልጁን ሊያመሰግኑትና የመጠመቅ ግብ እንዲያወጣ ሊያበረታቱት ይገባል። የልጁ ወላጆችም ቢሆኑ በልጃቸው ልብ ላይ እውነትን ለመትከል ጠንክረው ስለሠሩ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። ወላጆች ለልጃቸው ተጨማሪ ድጋፍ መስጠት እንዲችሉ ለመርዳት ሽማግሌዎቹ ከገጽ 179-181 ላይ የሚገኘውን “ለክርስቲያን ወላጆች” የሚለውን ርዕስ እንዲያነቡ ሊነግሯቸው ይችላሉ።

ራስን መወሰንና መጠመቅ

16 ይሖዋን ካወቅክ፣ ለእሱ ፍቅር ካዳበርክ እንዲሁም መለኮታዊ ብቃቶችን አሟልተህ በመስክ አገልግሎት መሳተፍ ከጀመርክ ከእሱ ጋር የመሠረትከውን የግል ዝምድና ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ራስህን ለአምላክ በመወሰንና ይህን እርምጃ መውሰድህን በውኃ ጥምቀት በማሳየት ነው።—ማቴ. 28:19, 20

17 ራስን መወሰን የሚለው አገላለጽ ለአንድ ቅዱስ ዓላማ ራስን መለየትን ያመለክታል። ራስን ለአምላክ መወሰን ማለት ሕይወትን ለእሱ አገልግሎት ለማዋልና በመንገዶቹ ለመጓዝ በጸሎት ቃል መግባት ማለት ነው። በሌላ አባባል ለዘላለም እሱን ብቻ ማምለክ ማለት ነው። (ዘዳ. 5:9) ይህ በግልህ ልታደርገው የሚገባ ውሳኔ ነው። ሌላ ሰው ይህን ውሳኔ ሊያደርግልህ አይችልም።

18 ይሁን እንጂ የእሱ ንብረት መሆን እንደምትፈልግ ለይሖዋ በጸሎት መግለጽህ ብቻ በቂ አይደለም። ራስህን ለአምላክ መወሰንህን ለሌሎች ማሳየት ያስፈልግሃል። ኢየሱስ እንዳደረገው አንተም በውኃ በመጠመቅ ራስህን ለአምላክ መወሰንህን ለሌሎች ታሳውቃለህ። (1 ጴጥ. 2:21፤ 3:21) ይሖዋን ለማገልገልና ለመጠመቅ ከወሰንክ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ይህን ፍላጎትህን ለሽማግሌዎች አካል አስተባባሪው ማሳወቅ ይኖርብሃል። እሱም ለጥምቀት የሚያስፈልጉትን መለኮታዊ ብቃቶች የምታሟላ መሆንህን ለማረጋገጥ የተወሰኑ ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩህ ዝግጅት ያደርጋል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ መጽሐፍ ከገጽ 182-184 ላይ የሚገኘውን “ላልተጠመቀ አስፋፊ” የሚለውን ርዕስና ከገጽ 185-207 ላይ የሚገኘውን “መጠመቅ ለሚፈልጉ የቀረቡ ጥያቄዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

የአገልግሎት እንቅስቃሴን ሪፖርት ማድረግ

19 ንጹሕ አምልኮ በዓለም ዙሪያ ምን ያህል እንደተስፋፋ የሚገልጹ ሪፖርቶችን መስማት ምንጊዜም ቢሆን ለይሖዋ ሕዝቦች የብርታት ምንጭ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥራቹ በመላው ምድር ላይ እንደሚሰበክ ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገረበት ጊዜ አንስቶ እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህ ሥራ እንዴት እንደሚከናወን በከፍተኛ ጉጉት ሲከታተሉ ቆይተዋል።—ማቴ. 28:19, 20፤ ማር. 13:10፤ ሥራ 1:8

20 የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በስብከቱ ሥራ ስለተገኙ ስኬቶች የሚገልጹ ሪፖርቶችን መስማት ያስደስታቸው ነበር። (ማር. 6:30) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንድ ላይ ተሰብስበው በነበሩ 120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ እንደፈሰሰባቸው ይገልጻል። ብዙም ሳይቆይ የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር አድጎ 3,000 ገደማ የደረሰ ሲሆን ከዚያም ወደ 5,000 ገደማ ከፍ ብሏል። ‘ይሖዋ የሚድኑ ሰዎችን በየዕለቱ በእነሱ ላይ ይጨምር እንደነበር’ እንዲሁም ‘በጣም ብዙ ካህናት ይህን እምነት እንደተቀበሉ’ የሚገልጽ ሪፖርት ቀርቧል። (ሥራ 1:15፤ 2:5-11, 41, 47፤ 4:4፤ 6:7) ደቀ መዛሙርቱ ስለ እነዚህ ጭማሪዎች የሚገልጸውን ዜና ሲሰሙ በእጅጉ ተበረታተው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! በአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ቆስቋሽነት ከባድ ስደት ተነስቶባቸው የነበረ ቢሆንም እነዚህን አስደሳች ሪፖርቶች መስማታቸው የተሰጣቸውን መለኮታዊ ተልእኮ ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸው መሆን አለበት!

21 ከ60-61 ዓ.ም. ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ምሥራቹ በመላው ዓለም እየተስፋፋና ፍሬ እያፈራ እንደሆነ” እንዲሁም “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ [እንደተሰበከ]” ሪፖርት አድርጓል። (ቆላ. 1:5, 6, 23) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለቃሉ ታዛዥ ነበሩ፤ መንፈስ ቅዱስም የአይሁድ ሥርዓት በ70 ዓ.ም. ከማብቃቱ በፊት የስብከቱን ሥራ በስፋት እንዲያከናውኑ ኃይል ሰጥቷቸዋል። እነዚያ ታማኝ ክርስቲያኖች ምን እየተከናወነ እንዳለ የሚገልጹ ሪፖርቶች ሲሰሙ ምንኛ ተበረታተው ይሆን!

መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የስብከቱ ሥራ በተሟላ ሁኔታ እንዲከናወን የበኩልህን አስተዋጽኦ እያበረከትክ ነው?

22 በዛሬው ጊዜ ያለው የይሖዋ ድርጅትም “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በሚለው የማቴዎስ 24:14 ጥቅስ ፍጻሜ መሠረት እየተከናወነ ያለውን ሥራ የሚገልጹ መረጃዎችን መዝግቦ ለመያዝ ይጥራል። ራሳችንን የወሰንን የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን አጣዳፊ ሥራ ተሰጥቶናል። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የስብከቱ ሥራ በተሟላ ሁኔታ እንዲከናወን እያንዳንዳችን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን። ይሖዋ ለስብከቱ ሥራ ክትትል በማድረግ ይህ ሥራ ዳር እንዲደርስ ያደርጋል፤ እኛም በዚህ ሥራ ከተካፈልን የእሱን ሞገስ እናገኛለን።—ሕዝ. 3:18-21

የግል የመስክ አገልግሎት ሪፖርት

23 ለመሆኑ ሪፖርት የምናደርገው ምንድን ነው? ሪፖርት የምናደርጋቸው ነገሮች ዝርዝር ድርጅቱ ባዘጋጀው የመስክ አገልግሎት ሪፖርት መመለሻ ቅጽ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ከዚህ ቀጥሎ ጠቅለል ተደርገው የቀረቡት ሐሳቦች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

24 “ያበረከትከው ጽሑፍ (የታተሙና ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች)” በሚለው ሥር የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ሰዎች ያበረከትካቸውን የታተሙም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የሚገኙ ጽሑፎች ጠቅላላ ብዛት ትመዘግባለህ። “ያሳየኸው ቪዲዮ” በሚለው ሥር ደግሞ ቪዲዮዎቻችንን ምን ያህል ጊዜ ለሰዎች እንዳሳየህ ትጽፋለህ።

25 “ተመላልሶ መጠየቅ” በሚለው ሥር ሪፖርት የምታደርገው አንድ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ሰው ያሳየውን ፍላጎት ለማሳደግ ስትል ግለሰቡን ደግመህ ያነጋገርክባቸውን ጊዜያት ድምር ነው። ያነጋገርነውን ግለሰብ ድጋሚ በአካል በማግኘት፣ ደብዳቤ በመጻፍ፣ ስልክ በመደወል፣ የጽሑፍ መልእክት ወይም ኢሜይል በመላክ አሊያም ጽሑፍ በማድረስ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ይቻላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በተመራ ቁጥር አንድ ተመላልሶ መጠየቅ ተብሎ ሊቆጠር ይችላል። ያልተጠመቀ ልጅ ያለው አንድ ወላጅ፣ ልጁ ባለበት የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራሙን የሚመራ ከሆነ በሳምንት አንድ ተመላልሶ መጠየቅ መቁጠር ይችላል።

26 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በአብዛኛው በየሳምንቱ የሚመራ ቢሆንም በወር ውስጥ ሪፖርት የሚደረገው አንድ ጥናት ተብሎ ነው። አስፋፊዎች በወር ውስጥ ያስጠኗቸውን የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዛት ይመዘግባሉ። ራሳቸውን ወስነው በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን ስናስጠና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብለን ሪፖርት እናደርጋለን። በተጨማሪም ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ አጥንቶ ላልጨረሰ አዲስ ተጠማቂ የምንመራውን ጥናት አሊያም ከአገልግሎት ኮሚቴ አባላት አንዱ በሰጠን መመሪያ መሠረት የምናስጠናውን የቀዘቀዘ ወንድም ወይም እህት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብለን መቁጠር እንችላለን።

27 “ሰዓት” በሚለው ሥር ሪፖርት የምታደርገው አኃዝ ትክክል መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ሪፖርት የምታደርገው ከቤት ወደ ቤት በማገልገል፣ በመንገድ ላይ በመመሥከር፣ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት አሊያም ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ ምሥክሮች ላልሆኑ ሰዎች መደበኛ በሆነ ወይም ባልሆነ መንገድ ምሥክርነት በመስጠት የምታሳልፈውን ጊዜ ነው። ሁለት አስፋፊዎች አብረው ሲያገለግሉ ሁለቱም ሰዓቱን መቁጠር የሚችሉ ቢሆንም ተመላልሶ መጠየቁን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ሪፖርት የሚያደርገው ግን አንደኛው ብቻ ነው። በቤተሰብ አምልኮ ምሽት ላይ ሁለቱም ወላጆች ልጆቻቸውን በጋራ የሚያስተምሩ ከሆነ እያንዳንዳቸው በሳምንት ውስጥ እስከ አንድ ሰዓት ድረስ መያዝ ይችላሉ። የሕዝብ ንግግር የሚሰጡ ወንድሞች ሰዓቱን መቁጠር ይችላሉ። የሕዝብ ንግግር የሚያስተረጉሙም ቢሆኑ ሰዓቱን መቁጠር ይችላሉ። ይሁንና ሰዓት የማትቆጥርባቸው ሌሎች አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች አሉ። ለምሳሌ ወደ መስክ አገልግሎት ለመሄድ በመዘጋጀት፣ በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ በመገኘት፣ እግረ መንገድህን ዕቃ እንደመግዛት ያሉ ሌሎች ጉዳዮችን በማከናወን እና በመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች በመካፈል የምታሳልፈውን ሰዓት መቁጠር አይኖርብህም።

28 እያንዳንዱ አስፋፊ ለምሥክርነቱ ሥራ ያዋለውን ሰዓት ሲቆጥር በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናው የሚነግረውን መስማት አለበት። አንዳንድ አስፋፊዎች የሚሰብኩት ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሲሆን ሌሎች ደግሞ ጥቂት ነዋሪዎች ባሉባቸውና ነዋሪዎቹን ለማግኘት ብዙ መጓዝ በሚጠይቅባቸው አካባቢዎች ይሰብካሉ። አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ይለያል፤ አስፋፊዎች ሰዓት የሚይዙበት መንገድም ቢሆን የተለያየ ነው። የበላይ አካሉ የመስክ አገልግሎት ሰዓት የሚቆጠርበትን መንገድ በተመለከተ የራሱን ሕሊና ተጠቅሞ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጉባኤዎች ሊከተሉት የሚገባ ደንብ አያወጣም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የቱ ትክክል እንደሆነ የመፍረድ ሥልጣን የተሰጠው ማንም ሰው የለም።—ማቴ. 6:1፤ 7:1፤ 1 ጢሞ. 1:5

29 በመስክ አገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ ሪፖርት ስናደርግ ቅጹ ላይ ማስፈር ያለብን ሙሉ ሰዓታትን እንጂ ደቂቃዎችን አይደለም። ከዚህ የተለየ አሠራር የምንከተለው አንድ አስፋፊ በዕድሜ መግፋት ምክንያት እንደልቡ የማይንቀሳቀስ፣ ከቤት መውጣት የማይችል፣ ከእንክብካቤ መስጫ ተቋም የማይወጣ ወይም በሌላ ምክንያት ነፃነቱ የተገደበ ከሆነ ነው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ሥር የሚገኝ አንድ አስፋፊ በአገልግሎት ያሳለፋቸውን ደቂቃዎች በ15 ደቂቃ ከፋፍሎ (15፣ 30 ወይም 45 ደቂቃ) ሪፖርት ማድረግ ይችላል። በወር ውስጥ ያገለገለው 15 ደቂቃ ብቻ ቢሆንም ይህን ሪፖርት ማድረግ ይኖርበታል። በዚህ መንገድ አዘውታሪ የመንግሥቱ አስፋፊ ተደርጎ ይቆጠራል። ይህ ዝግጅት በከባድ በሽታ ወይም ጉዳት ሳቢያ ለተወሰነ ጊዜ ምናልባትም ለአንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ መንቀሳቀስ ላልቻለ አስፋፊም ይሠራል። ይህ ዝግጅት የተደረገው የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ ለተገደበ አስፋፊዎች ብቻ ነው። አንድ አስፋፊ በዚህ ዝግጅት መጠቀም ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ የሚወስነው የአገልግሎት ኮሚቴው ነው።

የጉባኤ የአስፋፊ መዝገብ

30 በየወሩ የምትመልሰው የመስክ አገልግሎት ሪፖርት በጉባኤ የአስፋፊ መዝገብ ላይ ይመዘገባል። እነዚህ መዝገቦች አስፋፊው ያለበት ጉባኤ ንብረት ናቸው። ወደ ሌላ ጉባኤ ለመዛወር ካሰብክ ይህን ለሽማግሌዎችህ ማሳወቅህን አትዘንጋ። ጸሐፊው መዝገብህ ለአዲሱ ጉባኤህ እንዲላክ ያደርጋል። ይህም የዚያ ጉባኤ ሽማግሌዎች አንተን የጉባኤው አስፋፊ አድርገው እንዲቀበሉህና መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲያደርጉልህ ያስችላቸዋል። ከጉባኤህ ርቀህ የምትቆየው ከሦስት ወር ላነሰ ጊዜ ከሆነ እባክህ የመስክ አገልግሎት ሪፖርትህን ለጉባኤህ ላክ።

የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያችንን ሪፖርት የምናደርገው ለምንድን ነው?

31 የመስክ አገልግሎት ሪፖርትህን መመለስ የምትረሳበት ጊዜ አለ? ሁላችንም አልፎ አልፎ ማሳሰቢያ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሪፖርት ማድረግን በተመለከተ ተገቢውን አመለካከት ካዳበርንና እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ከተረዳን የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን አስታውሶ መመለስ ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል።

32 አንዳንዶች “ይሖዋ በአገልግሎት ላይ የማደርገውን እንቅስቃሴ ያውቃል፤ ታዲያ ለጉባኤው ሪፖርት ማድረግ የሚያስፈልገኝ ለምንድን ነው?” ብለው ይጠይቃሉ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ እያንዳንዳችን የምናከናውነውን ሥራም ሆነ አገልግሎታችን የሙሉ ነፍስ ይሁን የይስሙላ በሚገባ ያውቃል። ሆኖም ይሖዋ፣ ኖኅ በመርከቡ ውስጥ ለምን ያህል ቀናት እንደቆየ እንዲሁም እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለምን ያህል ዓመታት እንደተጓዙ እንዲመዘገብ እንዳደረገ አስታውስ። በዚያን ወቅት፣ ታማኝ ሆነው የጸኑትም ሆነ በእሱ ላይ ያመጹት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ተመዝግቧል። በተጨማሪም እስራኤላውያን የከነአንን ምድር አንድ በአንድ የያዙት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ታማኝ የነበሩት የእስራኤል መሳፍንት ምን ነገሮችን እንዳከናወኑ በጽሑፍ እንዲሰፍር አድርጓል። አዎ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ ያከናወኗቸው ነገሮች በዝርዝር እንዲጻፉ አድርጓል። ይሖዋ በመንፈሱ መሪነት እነዚህ ዘገባዎች እንዲጻፉ ማድረጉ ትክክለኛ መዝገቦችን ስለመያዝ ያለውን አመለካከት በግልጽ እንድንገነዘብ ያስችለናል።

33 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ክንውኖች የይሖዋ ሕዝቦች የመዘገቧቸው መረጃዎችና የሚይዟቸው መዝገቦች ምን ያህል ትክክል እንደሆኑ ያሳያሉ። በአብዛኞቹ ዘገባዎች ላይ ቁጥሩ በትክክል ባይገለጽ ኖሮ ታሪኩ ያን ያህል ልባችንን አይነካውም ነበር። በዘፍጥረት 46:27፣ ዘፀአት 12:37፣ መሳፍንት 7:7፣ 2 ነገሥት 19:35፣ 2 ዜና መዋዕል 14:9-13፣ ዮሐንስ 6:10፣ 21:11፣ የሐዋርያት ሥራ 2:41 እንዲሁም 19:19 ላይ የሚገኙትን ዘገባዎች እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል።

34 ሪፖርታችን በይሖዋ አምልኮ የምናከናውነውን ነገር ሁሉ እንደማያጠቃልል የታወቀ ነው፤ ያም ሆኖ ሪፖርት መመለሳችን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ለሚከናወነው ሥራ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ሐዋርያት ከስብከት ዘመቻ ሲመለሱ “ያደረጉትንና ያስተማሩትን ነገር ሁሉ” ለኢየሱስ ሪፖርት አድርገው ነበር። (ማር. 6:30) አንዳንድ ጊዜ ሪፖርቶች የተወሰኑ የአገልግሎታችን ገጽታዎች ልዩ ትኩረት እንደሚያሻቸው ሊጠቁሙ ይችላሉ። አኃዞቹ በአንዳንድ እንቅስቃሴዎቻችን ጥሩ እድገት መደረጉን፣ በአንጻሩ ደግሞ በሌሎች መስኮች ለምሳሌ ከአስፋፊ ቁጥር ጭማሪ ጋር በተያያዘ እድገቱ አዝጋሚ መሆኑን ሊጠቁሙ ይችላሉ። በመሆኑም ማበረታቻ መስጠት ወይም ለችግሮቹ መፍትሔ ማበጀት ሊያስፈልግ ይችላል። ኃላፊነት ያላቸው የበላይ ተመልካቾች ሪፖርቶቹን በማጤን የግለሰቦችን ወይም የጠቅላላውን ጉባኤ እድገት የገታውን ማንኛውንም ሁኔታ ለማስተካከል ይጥራሉ።

35 ከዚህም በላይ ሪፖርቶች፣ ድርጅቱ በየትኛው አካባቢ ተጨማሪ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ማወቅ እንዲችል ይረዳሉ። የበለጠ ፍሬያማ የሆኑት የትኞቹ አካባቢዎች ናቸው? ብዙም እድገት የሌለው የት አካባቢ ነው? ሰዎች እውነትን እንዲማሩ ለመርዳት የትኞቹ ጽሑፎች ያስፈልጋሉ? ድርጅቱ የሚደርሱት ሪፖርቶች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለስብከቱ ሥራ የሚያስፈልጉትን ጽሑፎች አስቀድሞ እንዲያውቅና ያንን ፍላጎት ለማሟላት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርግ ያስችሉታል።

36 ሪፖርቶችን መስማት በጣም ያበረታታል። ወንድሞቻችን በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን ለመስበክ እያከናወኑ ስላለው ሥራ ስንሰማ እጅግ አንደሰትም? በዓለም ዙሪያ ስላለው እድገት የሚገልጹ ሪፖርቶች፣ የይሖዋ ድርጅት ምን ያህል እየሰፋ እንዳለ አጠቃላይ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዱናል። ተሞክሮዎች እንድንበረታታና የስብከት ሥራችንን በተሟላ ሁኔታ እንድናከናውን ያነሳሱናል። (ሥራ 15:3) የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን በመመለስ ረገድ የትብብር መንፈስ ማሳየታችን ከፍተኛ ጥቅም ያለው ከመሆኑም ሌላ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወንድሞቻችን ያለንን አሳቢነት ያሳያል። እንዲህ ባለ ቀላል ሊመስል በሚችል ጉዳይ ታዛዥ በመሆን ለይሖዋ ድርጅታዊ አሠራር እንደምንገዛ እናሳያለን።—ሉቃስ 16:10፤ ዕብ. 13:17

የግል ግብ ማውጣት

37 በመስክ አገልግሎት የምናደርገውን እንቅስቃሴ ከሌላ አስፋፊ እንቅስቃሴ ጋር የምናወዳድርበት ምንም ምክንያት የለም። (ገላ. 5:26፤ 6:4) እያንዳንዱ ግለሰብ ያለበት ሁኔታ የተለያየ ነው። በአንጻሩ ግን ልንደርስባቸው የምንችላቸው የግል ግቦች ማውጣታችን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን በአገልግሎት ምን ያህል እድገት እንዳደረግን ለማወቅ ይረዳናል። በተጨማሪም እነዚህ ግቦች ላይ መድረሳችን እርካታ ያስገኝልናል።

38 በእርግጥም ይሖዋ “ታላቁን መከራ” በሕይወት የሚያልፉ ሰዎችን የመሰብሰቡን ሥራ እያፋጠነው እንዳለ በግልጽ ማየት ይቻላል። የምንኖረው ኢሳይያስ የተናገረው የሚከተለው ትንቢት እየተፈጸመ ባለበት ዘመን ነው፦ “ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል። እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ።” (ራእይ 7:9, 14፤ ኢሳ. 60:22) ታሪካዊ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የምሥራቹ አገልጋይ መሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ማቴ. 24:14

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ