የጥያቄ ሣጥን
◼ አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለጥምቀት ብቁ ከመሆኑ በፊት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በአገልግሎት መካፈል የሚኖርበት እስከ ምን ድረስ ነው?
ጥምቀት አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ እጅግ የላቀው ነው። በመሆኑም አንድ ሰው ለጥምቀት ብቁ ከመሆኑ በፊት አምላክ ከእሱ ስለሚጠብቀው ነገር ምክንያታዊ በሆነ መጠን ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም አምላክ ካወጣቸው መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እየኖረ መሆኑን ቀደም ብሎ ማሳየት ይኖርበታል።
ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰባቸውን ቸል እንዳይሉ ታዝዘዋል፤ በመሆኑም አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ረገድ ትጉህ መሆኑን አስቀድሞ ማሳየት አለበት። (ዕብ. 10:24, 25) በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ የማድረግ ልማድ ማዳበሩ ጠቃሚ ነው። ለመጠመቅ እንደ መሥፈርት ባይታይም በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ቢካፈል ጥሩ ይሆናል።
ክርስቲያኖች ምሥራቹን የመስበክና ደቀ መዝሙር የማድረግ ተልዕኮ ስለተሰጣቸው አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ ከመጠመቁ በፊት አዘውትሮ በአገልግሎት መካፈልም ይኖርበታል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ታዲያ ከመጠመቁ በፊት ስንት ወር ማገልገል ይኖርበታል? ግለሰቡ ከወር እስከ ወር አዘውትሮ በቅንዓት ለማገልገል መቁረጡን በግልጽ ለማየት በቂ ጊዜ ማለፍ እንደሚኖርበት የታወቀ ነው። (መዝ. 78:37) ይህ ማለት ግለሰቡ ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ረጅም ጊዜ መቆየት አለበት ማለት አይደለም፤ ጥቂት ወራት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። በየወሩ በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፈው ሰዓትስ ምን ያህል መሆን አለበት? በዚህ ረገድ የማይለዋወጥ ቋሚ ደንብ ማውጣት አይቻልም። ሽማግሌዎች የእያንዳንዱን አስፋፊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት እንዲሁም ምክንያታዊና ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋቸዋል።—ሉቃስ 21:1-4
የጥምቀት እጩውን የሚጠይቁት ሽማግሌዎች (ወይም የሽማግሌዎች እጥረት ባሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ የጉባኤ አገልጋዮች) የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታ እንደሚለያይ ማስታወስ እንዲሁም አስፋፊው ለጥምቀት ብቁ መሆን አለመሆኑን ሲወስኑ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም አለባቸው። ግለሰቡ የይሖዋ ምሥክር የመሆን ልባዊ ፍላጎት እንዳለው እንዲሁም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የመታቀፍና በአገልግሎት የመካፈል መብት ማግኘቱን እንደሚያደንቅ ማረጋገጥ አለባቸው። ይሁንና ሽማግሌዎቹ፣ ግለሰቡ ገና መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ እንዳልደረሰ ወይም ከአንድ የተጠመቀና ልምድ ያለው ወንጌላዊ ጋር የሚመጣጠን ችሎታ እንደሌለው ማስታወስ አለባቸው። ሽማግሌዎቹ እጩ ተጠማቂው ብቃቱን እንደማያሟላ ከተሰማቸው እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት በደግነት ሊገልጹለት ይገባል፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ድጋፍ እንዲያገኝ መርዳት ይኖርባቸዋል።