የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 1/15 ገጽ 15-20
  • የይሖዋ በጎች በርኅራኄ መያዝ ያስፈልጋቸዋል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የይሖዋ በጎች በርኅራኄ መያዝ ያስፈልጋቸዋል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፈቃደኛ የመንጋው እረኞች
  • አዲሶች ለመስበክ ሲፈልጉ
  • ተጨማሪ ዕርዳታ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ
  • አንድ በቅርቡ የተጠመቀ ሰው ኃጢአት ቢሠራ
  • ወደ ‘ጉልምስና እንዲደርሱ’ እርዷቸው
  • እረኞች፣ ከሁሉ የላቁትን እረኞች አርዓያ ተከተሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • የምሥራቹ አገልጋዮች
    የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • የይሖዋን ውድ በጎች በጥንቃቄ መጠበቅ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 1/15 ገጽ 15-20

የይሖዋ በጎች በርኅራኄ መያዝ ያስፈልጋቸዋል

“እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ . . . እኛስ ሕዝቡ የማሰማሪያውም በጎች ነን።”—መዝሙር 100:3

1. ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚይዘው እንዴት ነው?

ይሖዋ ታላቅ እረኛ ነው። አገልጋዮቹ ከሆንን እንደ በጎቹ አድርጎ በመመልከት በርኅራኄ ይንከባከበናል። በሰማያት የሚኖረው አባታችን ያጽናናናል፣ መንፈሳችንን ያድስልናል፣ “ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ” ይመራናል። (መዝሙር 23:1-4) መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ካለው ከፍተኛ ፍቅር የተነሣ ነፍሱን እንኳ አሳልፎ ሰጥቷል።—ዮሐንስ 10:7-15

2. የአምላክ ሕዝቦች የሚገኙት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነው?

2 ይህ ሁሉ ርኅራኄ የተሞላበት እንክብካቤ ስለሚደረግልን ከመዝሙራዊው ጋር ሆነን እንደሚከተለው ለማለት እንችላለን፦ “በደስታም ለእግዚአብሔር ተገዙ በሐሴትም ወደፊቱ ግቡ። እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማሪያውም በጎች ነን።” (መዝሙር 100:2, 3) አዎን፣ ደስተኛና አስተማማኝ ጥበቃ የሚደረግልን ሕዝቦች ነን። ሁኔታችን በግንብ በታጠረ በረት ውስጥ ከክፉ አዳኝ ተሸሽገን ከመኖር ጋር ይመሳሰላል።።—ዘኁልቁ 32:16፤ 1 ሳሙኤል 24:3፤ ሶፎንያስ 2:6

ፈቃደኛ የመንጋው እረኞች

3. የተሾሙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ የሚይዙት እንዴት ነው?

3 የአምላክ በጎች በመሆናችን ብንደሰት አያስገርምም! የተሾሙ ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም በመሆን ይመሩናል። “በእኛ ላይ ራሳቸውን አለቃ” አያደርጉም፣ አይሰለጥኑብንም ወይም በእምነታችን ላይ የሚገዙ አይደሉም። (ዘኁልቁ 16:13፤ ማቴዎስ 20:25-28፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24፤ ዕብራውያን 13:7) ከዚህ ይልቅ የሚከተለውን የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር በሥራ ላይ የሚያውሉ አፍቃሪ እረኞች ናቸው፦ “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ።” (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ሐዋርያው ጳውሎስ ለመሰል ሽማግሌዎች እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “በገዛ ደሙ [“ልጁ ደም” አዓት] የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” እነዚህ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ወንዶች ‘መንጋውን በርኅራኄ የሚይዙ’ በመሆናቸው በጎቹ እንዴት አመስጋኞች ይሆኑ!—ሥራ 20:28-30

4. ቻርልስ ቲ ራስል ተለይቶ ይታወቅ የነበረው ከመንጋው ጋር በነበረው ምን ዓይነት ግንኙነት ነው?

4 ኢየሱስ የይሖዋን መንጋ በርኅራኄ የሚንከባከቡ “ፓስተሮች” ወይም እረኞች አድርጎ ‘ወንዶችን ስጦታ’ ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:8, 11 ኪንግ ጀምስ ቨርሽን) ከእነዚህ ወንዶች መካከል አንዱ የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚደንት የነበረው ቻርልስ ቲ ራስል ነው። ወንድም ራስል ከዋነኛው እረኛ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥር ሆኖ መንጋውን በእረኝነት ለመጠበቅ በሚሠራው ፍቅርና ርኅራኄ የተሞላበት ሥራ ምክንያት ፓስተር ራስል የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር። ዛሬ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚሾሙት በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ሲሆን “ፓስተር” “ሽማግሌ” ወይም “መምህር” የሚሉትን ቃላት ለእነርሱ እንደ ማዕረግ ስም አድርገን ላለመጠቀም እንጠነቀቃለን። (ማቴዎስ 23:8-12) ይሁንና ዛሬ ያሉት ሽማግሌዎች በይሖዋ ማሰማሪያ ውስጥ የሚገኙትን በጎች ለመጥቀም የፓስተርነት ወይም የእረኝነት ሥራ ይሠራሉ።

5. አዲሶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካሉት የተሾሙ ሽማግሌዎች ጋር መተዋወቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

5 ሽማግሌዎች እረኞች እንደመሆናቸው መጠን አዲሶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ጉልህ ድርሻ ያበረክታሉ። በመሆኑም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ በገጽ 168 ላይ እንደሚከተለው ይላል፦ “በጉባኤው ውስጥ ያሉትን የተሾሙ ሽማግሌዎች ተዋወቃቸው። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለበላይ ተመልካቾች ያወጣቸውን ብቃቶች የሚያሟሉ በመሆናቸው ከአምላክ የሚገኘውን እውቀት ሥራ ላይ በማዋል ረገድ ብዙ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9) ለማሸነፍ የምትታገለው ልማድ ወይም ከአምላክ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ጠባይ ካለህ ከመካከላቸው አንዱን ቀርበህ ከማነጋገር ወደኋላ አትበል። እነዚህ ሽማግሌዎች ‘የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ተናገሯቸው፣ ደካሞችን ደግፉ፣ ሁሉን ታገሡ’ የሚለውን የጳውሎስ ምክር ሥራ ላይ የሚያውሉ ሆነው ታገኛቸዋለህ።—1 ተሰሎንቄ 2:7, 8፤ 5:14 አዓት

አዲሶች ለመስበክ ሲፈልጉ

6. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አስፋፊ ለመሆን ሲፈልግ የምንከተለው አሠራር ምንድን ነው?

6 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እውቀት ካካበተና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመረ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ የመንግሥቱ አስፋፊ ማለትም የምሥራቹ ሰባኪ ለመሆን ይፈልግ ይሆናል። (ማርቆስ 13:10) በዚህ ጊዜ አስጠኚው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹን ቀርቦ ሊያነጋግረው ይገባል። ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹም በአገልግሎት ኮሚቴው ካሉት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ከሌላ ሽማግሌ ጋር ሆኖ አስጠኚውንና ተማሪውን እንዲያነጋግሯቸው ያደርጋል። ውይይቱ አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ በገጽ 98 እና 99 ላይ የተመሠረተ ይሆናል። እነዚህ ሁለት ሽማግሌዎች አዲሱ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች እንደሚያምንና ከአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ እንደሚኖር ካስተዋሉ ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት ለመካፈል ብቁ እንደሆነ ይነግሩታል።a የመስክ አገልግሎት ሪፖርቱን በመመለስ እንዳገለገለ ሲያሳውቅ ሪፖርቱ በስሙ በተዘጋጀ የአስፋፊዎች መመዝገቢያ ካርድ ላይ ይሠፍራል። ከዚህ በኋላ ይህ አዲስ ሰው ‘ቃሉን በደስታ ከሚሰብኩት’ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ሆኖ የምሥክርነት እንቅስቃሴውን ሪፖርት ማድረግ ይችላል። (ሥራ 13:5) ያልተጠመቀ አስፋፊ መሆኑ ለጉባኤው በማስታወቂያ ይነገራል።

7, 8. አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ በአገልግሎቱ አስፈላጊውን እርዳታ ሊያገኝ የሚችለው በምን መንገዶች ነው?

7 አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ የሽማግሌዎችና የሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እርዳታ ያስፈልገዋል። ለምሳሌ ያህል የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት መሪው ለዚህ ሰው መንፈሳዊ እድገት ትኩረት ይሰጣል። አዲሱ አስፋፊ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ውጤታማ በሆነ መንገድ መናገር አስቸጋሪ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። (ሥራ 20:20) በዚህ ረገድ የሚደረግለትን ድጋፍ በተለይ ደግሞ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ያስጠናው ሰው የሚያደርግለትን እርዳታ በደስታ እንደሚቀበል አያጠያይቅም። ይህ ዓይነቱ ተጨባጭ እርዳታ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት አዘጋጅቷቸዋል።—ማርቆስ 6:7-13፤ ሉቃስ 10:1-22

8 አገልግሎታችን ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በቅድሚያ ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ሁለቱ አስፋፊዎች በወርኃዊው የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጡትን አቀራረቦች ለመለማመድ ቀደም ብለው ሊገናኙ ይችላሉ። አገልግሎታቸውን ሲጀምሩም ተሞክሮ ያለው አስፋፊ የመጀመሪያዎቹን አንድ ወይም ሁለት በሮች ሊያንኳኳ ይችላል። ወዳጃዊ የመግቢያ ሐሳብ ካቀረበ በኋላ ሁለቱም አስፋፊዎች ምሥክርነቱን በመስጠት ሊካፈሉ ይችላሉ። ለጥቂት ሳምንታት በመስክ አገልግሎት አብረው በመሥራታቸው ጥሩ ተመላልሶ መጠየቆች ለማግኘትና ከዚያም አልፎ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ ጥናት ለማስጀመር ይችሉ ይሆናል። የበለጠ ተሞክሮ ያለው አስፋፊ ለጥቂት ጊዜ ጥናቱን ከመራ በኋላ ለአዲሱ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ ሊያስረክበው ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው አምላክ ለሚሰጠው እውቀት ያለውን አድናቆት በተግባር ሲገልጽ ሁለቱም አስፋፊዎች እንዴት ይደሰቱ!

9. አንድ አስፋፊ ለመጠመቅ ሲፈልግ ምን ዝግጅቶች ይደረጋሉ?

9 አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ በመንፈሳዊ እያደገ ሲሄድ በጸሎት ራሱን ለአምላክ ይወስንና መጠመቅ ይፈልግ ይሆናል። (ከማርቆስ 1:9-11 ጋር አወዳድር።) ለመጠመቅ እንደሚፈልግ ለጉባኤው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ማሳወቅ ይኖርበታል። ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹም አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 175 እስከ 218 ያሉትን ጥያቄዎች ከአስፋፊው ጋር የሚከልሱ ሽማግሌዎችን ይመድባል። ጥያቄዎቹ የሚገኙባቸው አራት ክፍሎች በሦስት ጊዜ ቢቻል በተለያዩ ሽማግሌዎች ሊሸፈኑ ይችላሉ። ያልተጠመቀው አስፋፊ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መጠነኛ እውቀት እንዳለውና በሌሎች መንገዶችም ብቁ እንደሆነ ከተስማሙ መጠመቅ እንደሚችል ይነግሩታል። ራሱን ወስኖ ሲጠመቅ ለመዳን የሚያበቃውን ‘ምልክት’ ያገኛል።—ሕዝቅኤል 9:4-6

ተጨማሪ ዕርዳታ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ

10. አንድ ሰው እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አጥንቶ ከጨረሰና ከተጠመቀ በኋላ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀቱን ሊያሳድግ የሚችለው እንዴት ነው?

10 አንድ ግለሰብ ጥናቱን እውቀት በተባለው መጽሐፍ አጠናቆ ከተጠመቀ በኋላ እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነትb የተባለውን በመሰለ ሌላ ሁለተኛ መጽሐፍ ለእርሱ ጥናት መምራት አያስፈልግም። በቅርቡ የተጠመቀ አንድ ሰው ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ሲዘጋጅና በስብሰባዎቹ ላይ አዘውትሮ ሲገኝ ብዙ ነገሮችን እንደሚማር እሙን ነው። ለእውነት ያለው ጥማት በግሉ ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን እንዲያነብና እንዲያጠና እንዲሁም ከመሰል አማኞች ጋር ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት እንዲያደርግ ሲገፋፋው ተጨማሪ እውቀት ያገኛል። ይሁን እንጂ ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝስ?

11. (ሀ) ጵርስቅላና አቂላ አጵሎስን የረዱት እንዴት ነበር? (ለ) በቅርቡ ለተጠመቀና ለማግባት ለሚያስብ አንድ አስፋፊ ምን ዓይነት እርዳታ ሊሰጠው ይችል ይሆናል?

11 ‘ቅዱሳት መጽሐፍትን ጠንቅቆ’ የተማረውና ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ ትምህርት አግኝቶ የነበረው አጵሎስ እንኳ ተሞክሮ የነበራቸው ክርስቲያኖች ጵርስቅላና አቂላ “ወስደው የእግዚአብሔርን መንገድ ከፊት ይልቅ በትክክል” ሲያሳውቁት ተጠቅሟል። (ሥራ 18:24-26፤ ከሥራ 19:1-7 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ያህል አንድ በቅርቡ የተጠመቀ ወጣት ከተቃራኒ ጾታ ጋር ለመጠናናት ወይም ትዳር ለመመሥረት እያሰበ ነው እንበል። ተሞክሮ ያለው ክርስቲያን ስለ እነዚህ ጉዳዮች በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ውስጥ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲያገኝ ሊረዳው ይችል ይሆናል። ለምሳሌ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በሚለው መጽሐፍ ክፍል 7c ላይ እነዚህን ጉዳዮች የሚመለከቱ ጠቃሚ ነጥቦች ይገኛሉ። ቋሚ ጥናት አይሁን እንጂ አስጠኚው የነበረው አስፋፊ ይህንን ትምህርት ሊያወያየው ይችላል።

12. ችግር ለገጠማቸው በቅርቡ የተጠመቁ የትዳር ጓደኛሞች ምን ዓይነት እርዳታ ሊሰጣቸው ይችል ይሆናል?

12 ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። ምናልባት በቅርቡ የተጠመቁ የትዳር ጓደኛሞች አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ችግር ይኖርባቸው ይሆናል። በቅዱሳን ጽሑፎች ተጠቅሞ ለተወሰኑ ምሽቶች ሊያወያያቸውና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ትምህርቶችን ሊጠቁማቸው የሚችል ሽማግሌ ሊያማክሩ ይችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሽማግሌው ከእነዚህ ባልና ሚስት ጋር ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አይጀምርም።

አንድ በቅርቡ የተጠመቀ ሰው ኃጢአት ቢሠራ

13. የጉባኤ ሽማግሌዎች በቅርቡ የተጠመቀ አንድ ሰው ኃጢአት ቢፈጽምና ንስሐ ቢገባ ምሕረት ማሳየት የሚገባቸው ለምንድን ነው?

13 ሽማግሌዎች፣ “እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ . . . የተሰበረውን እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ” ሲል የተናገረውን ታላቁን እረኛ ይሖዋን ምሰሉት። (ሕዝቅኤል 34:15, 16፤ ኤፌሶን 5:1) ከዚህ መንፈስ ጋር በመስማማት ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ጥርጣሬ ያለባቸውን ወይም በኃጢአት የወደቁት ቅቡዓን በምሕረት እንዲይዟቸው አጥብቆ አሳስቧል። (ይሁዳ 22, 23 የ1980 ትርጉም) ተሞክሮ ካላቸው ክርስቲያኖች ብዙ መጠበቃችን ትክክል የሆነውን ያህል በኃጢአት ወድቀው ንስሐ ለሚገቡ ገና እንደ ጠቦት ላሉት አዲሶች ምሕረት ልናሳያቸው ይገባል። (ሉቃስ 12:48፤ 15:1-7) እንግዲያውስ ‘በይሖዋ ቦታ ሆነው የሚፈርዱት’ ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉትን በጎች በርኅራሄ ይንከባከቧቸዋል፣ በየዋህነት መንፈስም ያቀኗቸዋል።—2 ዜና መዋዕል 19:6፤ ሥራ 20:28, 29፤ ገላትያ 6:1d

14. በቅርቡ የተጠመቀ አንድ አስፋፊ ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም ምን መደረግ ይኖርበታል? እርዳታ ሊሰጠው የሚችለውስ እንዴት ነው?

14 ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል የመጠጥ ሱሰኛ የነበረ በቅርቡ የተጠመቀ አስፋፊ ከልክ በላይ በመጠጣት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ዳግም በዚያ ልማዱ ተሸነፈ እንበል። ወይም ደግሞ ለረጅም ጊዜ የነበረበትን የሲጋራ ሱስ ከተወ በኋላ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በስውር እንዲያጨስ ተፈትኖ ይሆናል። ምንም እንኳ አዲሱ ወንድማችን የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት ጸልዮ ሊሆን ቢችልም የፈጸመው ኃጢአት ልማድ እንዳይሆንበት ከአንድ ሽማግሌ እርዳታ ለማግኘት መጣር ይኖርበታል። (መዝሙር 32:1-5፤ ያዕቆብ 5:14, 15) ግለሰቡ የፈጸመውን ኃጢአት ከሽማግሌዎቹ ወደ አንዱ ቀርቦ ከተናገረ ይህ ሽማግሌ አዲሱን አስፋፊ በምሕረት ለማስተካከል መጣር ይኖርበታል። (መዝሙር 130:3) ከዚያ በኋላ ያለው አካሄዱ የተቃና እንዲሆን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መስጠቱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን 12:12, 13) ይህ ግለሰብ ምን ተጨማሪ እርዳታ ሊሰጠው እንደሚገባ ለመወሰን ሽማግሌው ጉዳዩን ከጉባኤው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ጋር ይወያይበታል።

15. አንድ የተጠመቀ ሰው ኃጢአት ሲፈጽም አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል?

15 አንዳንድ ጊዜ ከዚያ የበለጠ ነገር ማድረግም ያስፈልግ ይሆናል። ጉዳዩ በሰፊው የሚታወቅ ከሆነ፣ ለመንጋው አደገኛ ከሆነ ወይም ደግሞ አንድ ሌላ ከባድ ኃጢአት ከተፈጸመ የሽማግሌዎች አካል ጉዳዩን የሚያጣሩ ሁለት ሽማግሌዎች ይመድባል። እነዚህ ሽማግሌዎች የጉዳዩ ክብደት የፍርድ ኮሚቴ እንዲቋቋም የሚጠይቅ ሆኖ ካገኙት ለሽማግሌዎች አካል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከዚያ በኋላ የሽማግሌዎች አካል ኃጢአት የፈጸመውን ሰው ለመርዳት የፍርድ ኮሚቴ ይሰይማል። የፍርድ ኮሚቴው ግለሰቡን በርኅራኄ ሊይዘው ይገባል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ተጠቅመው ግለሰቡን ለማቅናት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። የፍርድ ኮሚቴው ለሚያደርገው የደግነት ጥረት ቀና ምላሽ ከሰጠ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ክፍል እንዳያቀርብ ወይም ሐሳብ እንዳይሰጥ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑንና አለመሆኑን ሊወስኑ ይችላሉ።

16. ሽማግሌዎች ኃጢአት የፈጸመውን ሰው ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

16 ኃጢአት የፈጸመው ሰው ቀና ምላሽ ሰጥቶ ከሆነ በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ ከነበሩት ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ወይም ሁለቱ እምነቱን ለማጠንከርና ለአምላክ የጽድቅ ደረጃዎች ያለውን አድናቆት ለማሳደግ የታቀዱ የእረኝነት ጉብኝቶች ሊያደርጉለት ይችላሉ። አልፎ አልፎም አብረውት በመስክ አገልግሎት ሊሠሩ ይችላሉ። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በመጠቀም የተወሰኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶችን ሊያደርጉለት ይችላሉ፤ ግን ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመሩለታል ማለት አይደለም። ኃጢአት የፈጸመው ሰው በዚህ ርኅራኄ የተሞላበት እንክብካቤ አማካኝነት ወደፊት የሥጋ ድካሙን ለመቋቋም የሚረዳውን ጥንካሬ ማግኘት ይችል ይሆናል።

17. አንድ የተጠመቀ ሰው ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ ንስሐ ካልገባና ከኃጢአት መንገዱ ካልተመለሰ ምን እርምጃዎች ይወሰዳሉ?

17 እርግጥ ነው በቅርብ ጊዜ የተጠመቀ መሆኑ ንስሐ ሳይገባ ኃጢአት ለመፈጸም ሰበብ አይሆንም። (ዕብራውያን 10:26, 27፤ ይሁዳ 4) የኃጢአት ድርጊት የፈጸመ ማንኛውም የተጠመቀ ግለሰብ ንስሐ ካልገባና የኃጢአት ድርጊቱን ካልተወ ከጉባኤው ይወገዳል። (1 ቆሮንቶስ 5:6, 11-13፤ 2 ተሰሎንቄ 2:11, 12፤ 2 ዮሐንስ 9-11) ይህን እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአገልግሎት ኮሚቴው የፍርድ ኮሚቴ ይሰይማል። ግለሰቡ የሚወገድ ከሆነ የሚከተለው አጭር ማስታወቂያ ይነገራል፦ “ . . . ተወግዷል።”e

ወደ ‘ጉልምስና እንዲደርሱ’ እርዷቸው

18. በቅርቡ የተጠመቁ አዲሶችም ሆኑ ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲሁም ስለ ፈቃዱ ገና ብዙ የሚማሩት ነገር ይኖራቸዋል ብለን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

18 አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች ከመንጋው ሳይነጠሉ ይዘልቃሉ። ከዚህ ሌላ የሚያስደስተው ደግሞ እያንዳንዳችን ዘወትር ስለ ሰማያዊ አባታችንና ስለፈቃዱ መማር ስለምንችል ይበልጥ ወደ እርሱ መቅረብ እንችላለን። (መክብብ 3:11፤ ያዕቆብ 4:8) በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት የተጠመቁት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ገና የሚማሩት ብዙ ነገር እንደነበር አይካድም። (ሥራ 2:5, 37-41፤ 4:4) ምንም ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ያልነበራቸው አሕዛብም እንዲሁ ብዙ ነገር መማር ነበረባቸው። ለምሳሌ ጳውሎስ በአቴንስ አርዮስፋጎስ በተባለ ቦታ ከሰጠው ምሥክርነት በኋላ የተጠመቁት ሰዎች ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። (ሥራ 17:33, 34) ዛሬም እንዲሁ በቅርቡ የተጠመቁ አዲሶች ገና የሚማሯቸው ብዙ ነገሮች ከመኖራቸውም በላይ በአምላክ ዓይን ቅን የሆነውን ነገር እያደረጉ ለመቀጠል የደረሱበትን ውሳኔ እንዲገፉበት ጊዜና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።—ገላትያ 6:9፤ 2 ተሰሎንቄ 3:13

19. የሚጠመቁት አዲስ ሰዎች ‘ወደ ጉልምስና እንዲደርሱ’ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

19 በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ አዲሶች ይጠመቃሉ። እነዚህ አዲሶች ‘ወደ ጉልምስና እንዲያድጉ’ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ዕብራውያን 6:1-3) በቃል እያበረታታችኋቸው፣ በድርጊታችሁ ምሳሌ በመሆንና በአገልግሎት ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት አዲሱን ሰውነት እንዲለብሱና ‘በእውነት መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ’ ልትረዷቸው ትችሉ ይሆናል። (3 ዮሐንስ 4፤ ቆላስይስ 3:9, 10) ተሞክሮ ያለህ አስፋፊ ከሆንክ ሽማግሌዎች አንድን አዲስ መሰል አማኝ በአገልግሎት እንድትረዳ ወይም ደግሞ በአምላክ ላይ ያለው እምነት እንዲጠናከር፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ያለው አድናቆት እንዲያድግና ለመሳሰሉት ነገሮች ጥቂት ሳምንታት አብረኸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት እንድታደርግ ይጋብዙህ ይሆናል። እረኞች ከመንጋው ጋር ያላቸው ግንኙነት አባት በምክር እናት በየዋህነት ልጆቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8, 11) ይሁንና ጥቂት ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ብቻ ጉባኤው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ሊሸፍኑ አይችሉም። ሁላችን እርስ በርስ እንደሚደጋገፍ የአንድ ቤተሰብ አባላት ነን። እያንዳንዳችን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት አንድ ነገር ማድረግ እንችላለን። አንተ ራስህ ማበረታቻ ለመስጠት፣ የተጨነቁትን ለማጽናናት፣ የደከሙትን ለማበርታት ትችላለህ።—1 ተሰሎንቄ 5:14, 15

20. አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ለማሰራጨትና በይሖዋ ማሰማሪያ ውስጥ የሚገኙትን በጎች በርኅራኄ ለመንከባከብ ምን ልታደርግ ትችላለህ?

20 የሰው ልጅ አምላክ የሚሰጠው እውቀት ያስፈልገዋል። የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን ይህን እውቀት በማሰራጨቱ ሥራ በደስታ መካፈል ትችላለህ። የይሖዋ በጎች በርኅራኄ መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ይህን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ፍቅራዊ ድርሻ ልታበረክት ትችላለህ። ይሖዋ አገልግሎታችሁን እንዲባርክላችሁና በማሰማሪያው ውስጥ ያሉትን በጎች ለመርዳት ለምታደርጉት ልባዊ ጥረት ብድራታችሁን ይከፍላችሁ ዘንድ እንመኛለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በዚህ ጊዜ ይህ አዲስ አስፋፊ አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የተባለው መጽሐፍ አንድ ቅጂ ሊሰጠው ይችላል።

b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኀበር የታተመ

c ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ

d ላልተጠመቁ አስፋፊዎች የተደረገውን ይህን መሰል ዝግጅት “አምላክን እንዲያመልኩ ሌሎችን መርዳት” በሚለው ርዕስ ሥር በመጠበቂያ ግንብ 22-109 ገጽ 15-20 ላይ ተገልጿል።

e የውገዳ ውሳኔ ተላልፎ ግለሰቡ ይግባኝ ካለ ማስታወቂያው ሳይነገር ይቆያል። አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 147-8 ተመልከቱ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ይሖዋ በጎቹን የሚይዘው እንዴት ነው?

◻ አዲሶች ለመስበክ ሲፈልጉ ምን ይደረጋል?

◻ አዲሶች ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሆኖ ሲገኝ መሰል አማኞች ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ ሽማግሌዎች ኃጢአት ፈጽመው ንስሐ ለገቡት ሰዎች ምን እርዳታ ሊሰጧቸው ይችላሉ?

◻ በቅርቡ የተጠመቀ አንድ ሰው ‘ወደ ጉልምስና እንዲደርስ’ እንዴት ልትረዳው ትችላለህ?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቻርልስ ቲ ራስል የመንጋው አፍቃሪ እረኛ በመሆኑ ይታወቅ ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ርኅሩኅ እረኞች የአምላክን መንጋ የሚይዙት በእንክብካቤ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ