ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት አቅርቡ
1 ወደር የሌለው ልዩ መብት አለን። ይህም የይሖዋ ምሥክር የመሆን መብት ነው። እስካሁን ከተከናወነው ሁሉ በላቀ ሁኔታ ስለ መንግሥቱ ለማወጅ ይሖዋ እየተጠቀመበት ያለው ዓለም አቀፍ የወንጌላውያን ድርጅት አባል ነን! (ማር. 13:10) ያለንበትን ጊዜ አጣዳፊነት ግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ሥራ የቻልነውን ያህል ሙሉ በሙሉ እየተካፈልን ነውን?
2 ለስብከታችን ቀና ምላሽ የሚሰጡት ምን ያህል ሰዎች እንደሆኑ አናውቅም። “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሚሆኑ ይሖዋ አረጋግጦልናል። እነዚህም ‘ቀንና ሌሊት ለእርሱ ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ’ ተለይተው ይታወቃሉ። (ራእይ 7:9, 15 አዓት) በአምላክ አገልግሎት የተጠመዱ ከአምስት ሚልዮን በላይ የሆኑት ምሥክሮች ፍላጎት ያላቸው አድማጮች ወይም ተሰብሳቢዎች ብቻ አይደሉም። ምሥራቹን በመላው ዓለም የሚያውጁ ሠራተኞች ናቸው!
3 በየዕለቱ በመስክ አገልግሎትም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። ሁላችንም በየዕለቱ ቢያንስ ለአንድ ሰው እውነትን ብናካፍል ሊሰጥ የሚችለውን ሰፊ ምሥክርነት አስብ። ለይሖዋ ያለን አድናቆት ስለ እርሱ በቅንዓት እንድናውጅ ሊያንቀሳቅሰን ይገባል።— መዝ. 92:1, 2
4 ሌሎች ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ እርዷቸው፦ ይሖዋ ጭማሪ እንድናገኝ በማድረግ እኛን መባረኩን ቀጥሏል። (ሐጌ 2:7) ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በየወሩ በአማካይ 4,866 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል። እነዚህን ሰዎች ስናስጠና ግባችን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ብዙዎቹ በስብሰባዎቸ ላይ አዘውትረው በመገኘት ጥሩ እድገት አሳይተዋል። የተማሩትን “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ” ለሚያውቋቸው ሰዎች መናገር ጀምረዋል። (ሥራ 2:11) ለሕዝብ በሚደረገው አገልግሎት እንዲካፈሉ ግብዣ ሊቀርብላቸው ይችላልን?
5 በሚያዝያ ወር በመስክ አገልግሎት አብረውን ለመካፈል ብቁ የሆኑ አዳዲስ ሰዎችን ለመጋበዝ ልዩ ጥረት ማድረግ አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ በዚህ ሥራ ለመካፈል እንደሚፈልግ ነግሮሃልን? ነግሮህ ከሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን አሟልቷልን? (አገልግሎታችን መጽሐፍ ገጽ 97-9 ተመልከት።) ተማሪው በመስክ አገልግሎት መካፈል ሲፈልግ ስለ እርሱ ሁኔታ ከሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ጋር ተወያዩ። ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ጉዳዩን እንዲመረምሩ ሁለት ሽማግሌዎች ይመድባል። ተማሪው ያልተጠመቀ አስፋፊ እንዲሆን ተቀባይነት ካገኘ አብሮህ እንዲያገለግል ጋብዘው። በተለይ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾችና የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች በሚያዝያ ወር አስፋፊ የሚሆኑትን በመርዳት በኩል ንቁ መሆን አለባቸው።
6 ወላጆች ልጆቻቸው ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን ብቁ እንደሆኑና እንዳልሆኑ መመርመር ይችላሉ። (መዝ. 148:12, 13) ልጅህ በመንግሥቱ አገልግሎት መካፈል የሚፈልግ ከሆነና ጥሩ ጠባይ ካለው የአገልግሎት ኮሚቴ አባል ከሆኑ ሽማግሌዎች መካከል ከአንዱ ጋር ስለ ሁኔታው መወያየት ትችላለህ። ሁለት ሽማግሌዎች አንተንና ልጁን ካነጋገሩ በኋላ እንደ አስፋፊ ሆኖ ለመቆጠር ብቁ መሆኑንና አለመሆኑን ይወስናሉ። ልጆች ይሖዋን በማወደሱ ሥራ ሲተባበሩን ልዩ ደስታ ይሰማናል!
7 ቅዱስ አገልግሎት ሊቀርብለት የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው። (ሉቃስ 4:8) ሁላችንም ይሖዋን ‘በእጅጉ’ የማወደስ አስደናቂ መብታችንን እንጠቀምበት።— መዝ. 109:30፤ 113:3