ሚያዝያ—‘ጠንክረን የምንሠራበትና የምንጋደልበት’ ወር
1 የመታሰቢያው በዓል ሰሞን የይሖዋ ሕዝቦች በጥልቅ የሚያሰላስሉበት ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ የክርስቶስ ሞት ስላከናወናቸው ነገሮችና በፈሰሰው በኢየሱስ ደም አማካኝነት አምላክ ስለሰጠን ተስፋ በጥልቅ የምናሰላስልበት ወቅት ነው። ያለፈውን ዓመት ሚያዝያ 19 መለስ ብላችሁ ስታስታውሱ ምን ትዝ ይላችኋል? በዚያን ዕለት ምሽት ያየሃቸውን ሰዎች፣ የመታሰቢያው በዓል ሲከበር የነበረው ልዩ መንፈሳዊ ሁኔታ፣ የቀረበው ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር እንዲሁም የቀረቡት ልባዊ ጸሎቶች ትዝ ይሉሃል? ምናልባትም ይሖዋና ኢየሱስ ላሳዩህ ፍቅር ያለህን ጥልቅ አድናቆት ይበልጥ በተግባር ለመግለጽ ቁርጥ ውሳኔ አድርገህ ይሆናል። እንዲህ ያለው ማሰላሰል በአሁኑ ጊዜ የሚነካህ እንዴት ነው?
2 የይሖዋ ሕዝቦች ምስጋናቸውን በቃላት በመግለጽ ብቻ እንደማይወሰኑ ግልጽ ነው። (ቆላ. 3:15, 17) በተለይ ባለፈው ሚያዝያ ራሳችንን ለክርስቲያናዊ አገልግሎት በማቅረብ ለይሖዋ የማዳን ዝግጅቶች አድናቆት እንዳለን ለማሳየት ጥረት አድርገናል። በኢትዮጵያ በሺህ የሚቆጠሩ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገላቸው በዚህ ረገድ ተመዝግቦ የነበረውን ከፍተኛ ቁጥር 35 በመቶ አሳድጎታል። የእነዚህና የሌሎቹ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የተቀናጀ ጥረት በሰዓት፣ መጽሔት በማበርከት እንዲሁም በተመላልሶ መጠየቅ ረገድ አዲስ ከፍተኛ ቁጥር እንዲመዘገብ አስችሏል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመጀመራቸውና አዲስ ከፍተኛ የመታሰቢያ በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር በመገኘቱ እጅግ ተደስተናል!
3 ተስፋችን እንደሚፈጸም ያለን እርግጠኝነት ለሥራ እንደሚያንቀሳቅሰን የታወቀ ነው። ሁኔታው ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ እንደጻፈው ነው:- “ይህን ለማግኘት እንደክማለንና [“ጠንክረን እንሠራለንና፣” NW ]፣ ስለዚህም እንሰደባለን [“እንጋደላለን፣” NW ]፤ ይህም ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ ነው።”—1 ጢሞ. 4:10
4 በዚህ የመታሰቢያ በዓል ሰሞን ይሖዋ ሕይወት እንድናገኝ ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት እንዳላችሁ የምታሳዩት እንዴት ነው? ባለፈው ሚያዝያ በአገራችን ከምንጊዜውም የበለጠ ከፍተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር አግኝተናል። በዚህ ዓመትስ ከዚያ የሚበልጥ ቁጥር ማግኘት እንችል ይሆን? ይህ በሚገባ ልንደርስበት የምንችል ግብ ነው። ሆኖም እያንዳንዱ የተጠመቀም ሆነ ያልተጠመቀ አስፋፊ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል። ብዙ አዲሶችም ተሳትፎ ለማድረግ ይበቁ ይሆናል። ስለሆነም በሚያዝያ ጠንክረህ ለመሥራትና ለመጋደል እቅድ በምታወጣበት ጊዜ አዲሶችንና ብዙም ልምድ የሌላቸውን ጨምሮ ሌሎች አብረውህ እንዲያገለግሉ ማነቃቃት የምትችልባቸውን መንገዶች አስቀድመህ ማሰብ ትችላለህ።
5 አንዳንዶች እንቅስቃሴያቸውን እንደገና እንዲጀምሩ መርዳት:- ለአንድ ወይም ለሁለት ወራት በመስክ አገልግሎት ያልተካፈሉ አንዳንድ አስፋፊዎች እንዳሉ የምታውቅ ከሆነ ልታበረታታቸውና አብረውህ በመስክ አገልግሎት እንዲካፈሉ ልትጋብዛቸው ትችል ይሆናል። በጉባኤው ውስጥ አገልግሎት ያቆሙ አንዳንድ አስፋፊዎች ካሉ ሽማግሌዎች እነርሱን ለመጎብኘትና በሚያዝያ እንደገና አገልግሎት እንዲጀምሩ ለማበረታታት ልዩ ጥረት ያደርጋሉ።
6 ሁላችንም ይሖዋ መንፈሱን በመስጠት በአገልግሎቱ እንዲያበረታን መጠየቃችንን መቀጠል ይገባናል። (ሉቃስ 11:13) መንፈሱን ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል አንብቡ። (2 ጢሞ. 3:16, 17) እንዲሁም በአምስቱም ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት [“ለጉባኤዎች፣” NW] የሚለውን” መስማት ይገባናል። (ራእይ 3:6) የማያዘወትሩና አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎች የጥናት ልማዳቸውን እንዲያሻሽሉና አዘውትረው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ መርዳት የሚቻልበት ተስማሚ ጊዜ አሁን ነው። (መዝ. 50:23) ይህንን የምናደርገው የራሳችንን መንፈሳዊ ደህንነት በንቃት መከታተላችንን በመቀጠል ነው። ሌላም የሚጠበቅብን ነገር አለ።
7 አምላክ “ለሚታዘዙት” መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። (ሥራ 5:32) እንደዚህ ያለው ታዛዥነት ‘ለሕዝብ እንድንሰብክና የተጣራ ምሥክርነት እንድንሰጥ’ የተሰጠንን ትእዛዝ መቀበልን የሚጨምር ነው። (ሥራ 1:8፤ 10:42) በርትተን እንድንሰብክ የአምላክ መንፈስ የሚያስፈልገን መሆኑ ባይካድም ይሖዋን ለማስደሰት ያለንን ፍላጎት በተግባር መግለጽ ስንጀምር እሱ በእጅጉ እንደሚረዳን የታወቀ ነው። በፈቃደኝነት መታዘዛችንን የሚያሳዩትን እነዚህን የመጀመሪያ እርምጃዎች መውሰድ ያለውን ጠቀሜታ አቅልለን አንመልከት!
8 ልጆችን መርዳት:- እናንተ ወላጆች፣ ልጆቻችሁ እውነትን ለሌሎች የመናገር ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ምልክት አይታችሁባቸው ይሆን? አብረዋችሁ መስክ አገልግሎት ይወጣሉ? በጠባያቸው ምሳሌ ናቸው? ከሆነ ለምን ታመነታላችሁ? የጉባኤያችሁ የአገልግሎት ኮሚቴ አባል ወደ ሆነ አንድ ሽማግሌ ቀርባችሁ በማነጋገር ልጃችሁ በሚያዝያ አስፋፊነት ለመጀመር ብቃቱን ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ አረጋግጡ። (አገልግሎታችን የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 99-100ን ተመልከት።) ልጆቻችሁ በዚህ የመታሰቢያ በዓል ሰሞን ለይሖዋ በሚቀርበው ከፍተኛ የውዳሴ ድምፅ በተለያዩ መንገዶች አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ አትዘንጉ።—ማቴ. 21:15, 16
9 በጆርጂያ ዩ ኤስ ኤ የምትኖር አንዲት ክርስቲያን እናት ልጅዋ ስለ ይሖዋ ለሌሎች እንድትናገር ሳታሰልስ ታበረታታት ነበር። ባለፈው ዓመት ይህች ትንሽ ልጅ ከእናቷ ጋር እያገለገለች እያለች ለአንድ ሰው አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለውን ብሮሹር አበርክታ ማውጫውን በአጭሩ አብራራችለት። ሰውዬው “ስንት ዓመትሽ ነው?” ሲል ጠየቃት። እሷም “ሰባት” በማለት መለሰችለት። ይህ ሰው እንደዚህ ያለ ግልጽ አቀራረብ በመጠቀሟ በጣም ተደነቀ። ሰውዬው በእውነት ቤት ውስጥ ያደገ ቢሆንም እውነትን የሕይወት መንገዱ አድርጎ በቁም ነገር አልያዘውም ነበር። ብዙም ሳይቆይ ለእርሱ፣ ለባለቤቱና ለሴት ልጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላቸው።
10 ብዙ ልጆች አሁንም ቢሆን አስፋፊ ሆነው በአገልግሎት ከጎናችን ተሰልፈው ማየታችን ያስደስተናል። እነዚህ ልጆች እኩዮቻቸውን ሊገፋፉና ሊያበረታቱ ይችላሉ። ሆኖም ሚያዝያ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ አብሮ በመሥራት አንድነቱን ማጠናከርና መንፈሳዊነቱን መገንባት የሚችልበት ጥሩ አጋጣሚ ነው። በዚህ ረገድ የቤተሰብ ራሶች ቅድሚያውን መውሰድ ይገባቸዋል።—ምሳሌ 24:27
11 አዲሶችን መርዳት:- መጽሐፍ ቅዱስ የምታስጠኗቸውን አዳዲሶች በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? በሚያዝያ ወር ለሚደረገው ልዩ ጥረት አስተዋጽኦ ማበርከት ይችሉ ይሆን? እውቀት መጽሐፍ ምዕራፍ 2 አንቀጽ 22ን ወይም ምዕራፍ 11 አንቀጽ 14ን ባጠናችሁበት ወቅት እየተማሩ ያሉትን ነገር ለሌሎች መናገር እንደሚፈልጉ ገልጸውላችሁ ይሆናል። መጽሐፉን ወደ ማገባደድ ደርሳችሁ ከሆነ ምዕራፍ 18 አንቀጽ 8 ላይ “ምናልባት ለዘመዶችህ፣ ለወዳጆችህና ለሌሎች ሰዎች ስለምትማረው ነገር ለመናገር ትጓጓ ይሆናል። እንዲያውም ኢየሱስ እንዳደረገው ምሥራቹን ለሌሎች ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ መናገር ሳትጀምር አትቀርም። (ሉቃስ 10:38, 39፤ ዮሐንስ 4:6-15) አሁን ግን ከዚህም አልፈህ ለመሄድ ትፈልግ ይሆናል” የሚለውን ሐሳብ በግልጽ ለመወያየት ዝግጅት አድርጉ። የምታስጠኗቸው ሰዎች እንደዚህ ለማድረግ ዝግጁ ናቸውን?
12 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ በአምላክ ቃል ያምናልን? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ እያደረገ ነውን? ሕይወቱን ከመለኮታዊ የአቋም ደረጃዎች ጋር አስማምቷልን? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል? ይሖዋ አምላክን ማገልገል ይፈልጋል? ከሆነ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ በሚያዝያ ወር አብሮህ ለማገልገል ብቃቱን ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲወስኑ ሽማግሌዎችን እንዲያነጋግራቸው ለምን አታበረታታውም? (አገልግሎታችን የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 97-99ን ተመልከት።) ይህም ይሖዋን ለማገልገል በሚያደርገው ጥረት የይሖዋ ድርጅት ምን እርዳታ እንደሚያበረክትለት ለመመልከት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠዋል።
13 እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ተማሪዎች ከሌሎቹ ይልቅ ፈጣን እድገት ያደርጋሉ። ስለሆነም ሰኔ 2000 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 8 አንቀጽ 5-6 ላይ በወጣው መመሪያ መሠረት ብዙ ወንድሞችና እህቶች መጀመሪያ ላይ ጥሩ ፍላጎት ለነበራቸው ሆኖም እርምጃዎች ለመውሰድ ተጨማሪ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁለተኛ መጽሐፍ ሲያስጠኑ ቆይተዋል። እነዚህ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች “በአጭር ጊዜም ይሁን በረጅም ጊዜ” እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ስለሚችሉ ፈጽሞ ተስፋ አንቆርጥም። (ሥራ 26:29 የ1980 ትርጉም ) እነዚህን ሰዎች ለማስጠናት ያሳለፋችሁት ጊዜ ‘ረጅም’ የሚባል ዓይነት ከሆነ ተማሪያችሁ ለክርስቶስ ቤዛ ያለውን ጥልቅ አድናቆት በተግባር ማሳየት እንዲጀምር ይህ የመታሰቢያ በዓል ሰሞን ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንለት ይችላል?
14 ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንዴት መርዳት ይቻላል? ኢየሱስ ሌሎች አገልግሎት እንዲጀምሩ ያሠለጠነበትን መንገድ በመመርመር ብቃቱን የሚያሟሉ ሰዎችን መርዳት የሚቻልባቸውን ዘዴዎች እንማራለን። እንዲያው ብዙ ሕዝብ ስላየ ብቻ ሐዋርያቱን በሉ ተናገሩ አላላቸውም። በመጀመሪያ የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ነገራቸው፣ አዘውትሮ የመጸለይ ዝንባሌ እንዲያዳብሩ አበረታታቸው፤ እንዲሁም ሦስት መሠረታዊ ዝግጅቶችን ይኸውም የአገልግሎት ጓደኛ፣ የአገልግሎት ክልልና የሚናገሩትን መልእክት ሰጣቸው። (ማቴ. 9:35-38፤ 10:5-7፤ ማር. 6:7፤ ሉቃስ 9:2, 6) እናንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላላችሁ። የምትረዱት የገዛ ልጃችሁንም ይሁን አዲስ ጥናት ወይም ለጥቂት ጊዜ አገልግሎት አቋርጦ የነበረ አስፋፊ የሚከተሉትን አስፈላጊ ነጥቦች ለመከተል ልዩ ጥረት ማድረጋችሁ ተገቢ ነው።
15 አስፈላጊነቱን አጉሉ:- የስብከቱን ሥራ አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጋችሁ ንገሩት። ለሥራው አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። ጉባኤው በአገልግሎት ምን እያከናወነ እንዳለ የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ንገሯቸው። ኢየሱስ በማቴዎስ 9:36-38 ላይ የገለጸውን ዓይነት መንፈስ አንጸባርቁ። ወደፊት አስፋፊ የመሆን ተስፋ ያለውን ወይም አገልግሎት አቁሞ የነበረውን ሰው እሱ ራሱ በአገልግሎት ስለሚያደርገው ተሳትፎም ሆነ በመላው ዓለም ለሚሠራው ሥራ ስኬታማነት እንዲጸልይ አበረታቱት።
16 መመሥከር ስለሚያስችሉ የተለያዩ አጋጣሚዎች እንዲያስብ አበረታቱት:- ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው ምሥክርነት ከመጽሐፍ ጥናት ቡድን ጋር መሰብሰብ እንደሚችል ግለጽለት። ከዘመዶቹና ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር ወይም በምሳ እረፍት ጊዜ ከሥራ ባልደረቦቹ ወይም በትምህርት ቤት አብረውት ከሚማሩ ጋር መወያየት እንደሚችል ንገረው። አንድ ሰው በትራንስፖርት በሚጓዝበት ጊዜ አብረዉት ለሚጓዙት መንገደኞች አሳቢነትን በማሳየት በቀላሉ ውይይት መጀመር ይችላል። እኛ ራሳችን ቅድሚያውን ወስደን ውይይት ከጀመርን ግሩም ምሥክርነት መስጠት የሚቻልበት ሰፊ አጋጣሚ ይከፈታል። በእርግጥም ተስፋችንን ‘ዕለት ዕለት’ ለሌሎች ለማካፈል የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች አሉ።—መዝ. 96:2, 3
17 ይሁን እንጂ አንተና አዲሱ አስፋፊ በተቻለ መጠን ወዲያውኑ ከቤት ወደ ቤት አብራችሁ ብታገለግሉ ይመረጣል። በሚያዝያ የአገልግሎት እንቅስቃሴህን ከፍ የማድረግ ግብ ካለህ የክልል አገልጋዩን ልትሠራበት የምትችል የአገልግሎት ክልል ይኖር እንደሆነ ጠይቀው። ካለ ክልሉን አጣርተህ የመሸፈን አጋጣሚ ታገኛለህ። ለምሳሌ አገልግሎትህን ስትጨርስ ወይም ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ወይም ወደ ሌላ ቦታ ስትሄድ ቀደም ሲል ቤታቸው ያልተገኙ ወይም ፍላጎት አሳይተው የነበሩ ሰዎች አሁን ቤት እንዳሉ ታስተውል ይሆናል። ከተቻለ ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን በሚችልበት ጊዜ ላይ ጎራ ብለህ አነጋግራቸው። እንዲህ ማድረጉ በአገልግሎቱ እርካታና ደስታ እንድታገኝ ይረዳሃል።
18 ማራኪ መልእክት አዘጋጁ:- አንድ ሰው የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማካፈል መፈለጉ አንድ ነገር ሲሆን ይህ ሰው በተለይ አዲስ ወይም ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ያልወጣ ከነበረ መልእክቱን በድፍረት መናገር መቻሉ ሌላ ነገር ነው። አዲሶችንና አገልግሎት አቁመው የነበሩትን እንዲዘጋጁ መርዳት በጣም ጠቃሚ ነው። የአገልግሎት ስብሰባና የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ጠቃሚ ሐሳብ ሊገኝባቸው ይችላል። ሆኖም ይህ በግል የሚደረገውን ዝግጅት ይተካል ማለት አይደለም።
19 አዲሶች ለአገልግሎት ዝግጅት እንዲያደርጉ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? መጽሔት እንዴት ማበርከት እንደሚቻል በማሳየት መጀመር የምትችሉ ሲሆን አቀራረቡን ቀላልና አጭር አድርጉት! በዜና ከተነገሩት ነገሮች መካከል በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ይበልጥ ያሳሰበው የትኛው እንደሆነ እንዲያስብበት ካደረግህ በኋላ በወቅቱ ከሚበረከተው መጽሔት ላይ ከዚህ ጋር የሚስማማ አንድ ነጥብ ምረጥ። አቀራረቡን አብራችሁ ተዘጋጁ እንዲሁም በተቻለ መጠን ወዲያውኑ በአገልግሎት ላይ ተጠቀሙበት።
20 ለእድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እርምጃዎች መውሰድ:- ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር ከ14.8 ሚልዮን በላይ ነበር። በአስፋፊነት ሪፖርት የመለሱት ቁጥር ደግሞ ከስድስት ሚልዮን ትንሽ በለጥ የሚል ነው። በዚህ ልዩ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ትምህርት ሲብራራ ያዳመጡት ሰዎች ቁጥር 8.8 ሚልዮን እንደሚያክሉ ከዚህ መረዳት ይቻላል። እነዚህም ከአንዳንዶቻችን ጋር በግል መተዋወቃቸው ጥሩ ስሜት አሳድሮባቸው ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ብዙዎቹ በጣም ያደንቁናል፣ ለዓለም አቀፉ ሥራችን የበኩላቸውን ያደርጋሉ እንዲሁም እኛን ደግፈው ይከራከራሉ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እነዚህ ሰዎች ወደፊት ተጨማሪ እድገት ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማሉ። እነዚህ ሰዎች ተጨማሪ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?
21 በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት አብዛኞቹ አዳዲስ ሰዎች ይህን እርምጃ የወሰዱት ከመካከላችን አንዱ ስለጋበዛቸው ነው። ይህም ብዙውን ጊዜ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ቢያንስ አንድ የሚያውቁት ሰው መኖሩን ያሳያል። አንድ ሰው ግብዣችንን ተቀብሎ በቦታው ከተገኘ ባይተዋርነት እንዳይሰማውና ከፕሮግራሙ የተሟላ ጥቅም እንዲያገኝ የመርዳት ኃላፊነት አለብን። አዳራሹ ሊሞላ ስለሚችል መቀመጫ እንዲያገኝ እርዱት። መጽሐፍ ቅዱስህን አውሰው እንዲሁም የመዝሙር መጽሐፍህን አብሮህ እንዲመለከት ጋብዘው። ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች በሙሉ መልስ ስጠው። የምታሳየው ሞቅ ያለ አሳቢነት ፍላጎቱ እንዲያድግ ሊረዳው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ብንሆን አዲስ ሰው ካየን ሞቅ ያለ ሰላምታ የመስጠትና ቀረብ ብሎ የመተዋወቅ ኃላፊነት አለብን።
22 በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት በአንድ ሰው አስተሳሰብ ላይ ጉልህ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘቱ ሌላ ቦታ ፈልጎ ያላገኘው አንድ ነገር እንዳለ የሚጠቁም ከመሆኑም በላይ እኛ ዘንድ በጥልቀት ሊመረምረው የሚገባ ነገር አለ ብሎ እንደሚያስብ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ወሰን ስለሌለው የይሖዋ ፍቅር ጨርሶ ያልሰማ ሰው ስለ አስደናቂው የቤዛ ዝግጅት የተሰጠውን ማብራሪያ ሲሰማ ተአምር ሊሆንበት ይችላል። ከሌሎች የተለየን ይኸውም ቅኖች፣ ተግባቢዎች፣ አፍቃሪዎችና ሰው አክባሪዎች መሆናችንን በግልጽ ሊመለከት ይችላል። የመንግሥት አዳራሻችን እሱ ከሚያውቃቸው በሥዕሎች ከተሞሉትና ትርጉም የለሽ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ከሚካሄድባቸው አብያተ ክርስቲያናት ፈጽሞ የተለየ ነው። አዲሶች፣ ተሰብሳቢዎቹ ከተለያየ የኑሮ ደረጃዎች የመጡ መሆናቸውንና በስብሰባውም ላይ ሙዳየ ምጽዋት እንደማይዞር ማስተዋላቸው እንደማይቀር የታወቀ ነው። ይህም በሌላ ጊዜ ተመልሰው እንዲመጡ ሊገፋፋቸው ይችላል።
23 ከመታሰቢያው በዓል በኋላ፣ በበዓሉ ላይ የተገኙ አዲሶችን ተከታትለን ለመርዳት ንቁዎች መሆን ይኖርብናል። አዳዲስ ሰዎችን ጋብዛችሁ ከነበረ የጋበዛችኋቸውን ሰዎች ተከታትላችሁ የመርዳቱ ኃላፊነት የእናንተ ነው። ወደየቤታቸው ከመሄዳቸው በፊት በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ስለሚደረጉት ሌሎች ስብሰባዎች ሳትረሱ መንገር ይኖርባችኋል። የሚቀጥለውን የሕዝብ ንግግር ርዕስ ንገሯቸው። በአቅራቢያቸው ያለው የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት የት እና በስንት ሰዓት እንደሚደረግ ንገሯቸው። መላው ጉባኤ በቅርቡ በአካባቢያቸው በሚደረግ የወረዳ እና የልዩ ስብሰባ ቀን ላይ ለመገኘት እቅድ የሚያወጣበትን ምክንያት አስረዳቸው።
24 ቤታቸው ሄደህ ለመጠየቅ የሚያስችልህን ዝግጀት አድርግ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች ጋር የሚያስተዋውቋቸውን ጽሑፎች ይኸውም አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር እና እውቀት መጽሐፍ እንዲኖራቸው አድርጉ። እስከ አሁን ጥናት ካልጀመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ጋብዟቸው። በድርጅት መልክ እንዴት እንደምንንቀሳቀስ በግልጽ እንዲረዱ የይሖዋ ምሥክሮች ወይም የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉ የተባለውን ብሮሹር እንዲያነብቡ ሐሳብ አቅርብላቸው። የሚቻል ከሆነ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የቪዲዮ ክሮች ለምሳሌ ያህል መላው የወንድማማች ማኅበር የተባለውን ቪዲዮ እንዲያዩ ጋብዛቸው። በጉባኤ ውስጥ ካሉ ከሌሎች ጋር እንዲተዋወቁ አድርግ። በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ ከአዳዲሶቹ ሰዎች ጋር ያለህ ግንኙነት እንዳይቋረጥ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤውን ሲጎበኝ ወይም በወረዳ ወይም በልዩ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋብዛቸው። ‘ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው’ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሁሉ እንዲያገኙ እርዳቸው!—ሥራ 13:48
25 ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይችላሉ? በሚያዝያ የተጠናከረ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ለማከናወን የሚደረገው ጥረት ስኬታማነት በአብዛኛው የተመካው በሽማግሌዎች ላይ ነው። የመጽሐፍ ጥናት መሪ ከሆንክ በቡድንህ ውስጥ የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው በዚህ ልዩ እንቅስቃሴ እንዲሳተፍ ለመርዳት ማድረግ የምትችላቸውን ነገሮች በማስታወሻህ ላይ አስፍር። በቡድንህ ውስጥ ወጣቶች፣ አዲሶች፣ የማያዘወትሩ ወይም አገልግሎት ያቆሙ ይኖሩ ይሆን? ወላጆቻቸው፣ አቅኚዎች ወይም ሌሎች አስፋፊዎች ቅድሚያውን ወስደው ይረዷቸው እንደሆነና እንዳልሆነ አረጋግጥ። አንተም በበኩልህ በምትችለው ሁሉ እርዳቸው። ለሁለት ዓመታት በመስክ አገልግሎት አዘውታሪ ያልነበረች አንዲት እህት ባለፈው ሚያዝያ በአገልግሎት ላይ ከ50 ሰዓት በላይ አሳልፋለች። እንዲህ ያለ ለውጥ እንድታደርግ የረዳት ምንድን ነው? ሽማግሌዎች ገንቢ የእረኝነት ጉብኝት ስላደረጉላት እንደሆነ ተናግራለች።
26 ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በቂ የአገልግሎት ክልሎች፣ መጽሔቶችና ሌሎች ጽሑፎች እንዲኖሩ ለማድረግ እርስ በርስ መተባበር ይገባቸዋል። ተጨማሪ የመስክ ስምሪት ስብሰባዎች ማዘጋጀት ይቻል ይሆን? ከሆነ ሌሎች ስለ ልዩ ዝግጅቱ እንዲያውቁ አድርጉ። ከሁሉም በላይ በግልህም ሆነ በሕዝብ ፊት በምትጸልይበት ጊዜ ይሖዋ ተጨማሪ የመንግሥት እንቅስቃሴ የምናደርግበትን ወር እንዲባርክ ለምነው።—ሮሜ 15:30, 31፤ 2 ተሰ. 3:1
27 ባለፈው ሚያዝያ በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ሽማግሌዎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ማበረታቻ ሰጥተዋል። በየሳምንቱ በስብሰባዎች ላይ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ መሆን ይችሉ እንደሆነ በጸሎት እንዲያስቡበት አበረታትተዋል። በእያንዳንዱ አጋጣሚ የአገልጋዮች አካል በሚያዝያ ከምንጊዜውም የተሻለ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ስለማድረግ በግለት ይናገር ነበር። በዚህ ምክንያት ሽማግሌዎቹንና የጉባኤ አገልጋዮቹን ጨምሮ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አስፋፊዎች በአቅኚነት አገልግለዋል!
28 ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ የሚገኝ ደስታ:- በአገልግሎት ‘ጠንክረን በመሥራታችንና በመጋደላችን’ ምን በረከቶችን እናገኛለን? (1 ጢሞ. 4:10) ከላይ የተጠቀሱት ሽማግሌዎች ባለፈው ሚያዝያ ጉባኤያቸው በቅንዓት ያከናወነውን እንቅስቃሴ አስመልክተው ሲጽፉ “ወንድሞችና እህቶች በመስክ አገልግሎት ላይ ይበልጥ መሥራት ከጀመሩ ወዲህ ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ ምን ያህል እንዳፋቀራቸውና እንዳቀራረባቸው ይናገራሉ” ብለዋል።
29 እንደልብ መንቀሳቀስ የማይችል አንድ ወጣት ወንድም ባለፈው ሚያዝያ በተደረገው ልዩ እንቅስቃሴ የመካፈል ከፍተኛ ፍላጎት አድሮበት ነበር። ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት እቅድ በማውጣትና በእናቱ እንዲሁም በመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ እርዳታ በረዳት አቅኚነት ውጤታማ ወር ሊያሳልፍ ችሏል። ስላጋጠመው ነገር ምን ተሰምቶታል? “በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ጤንነት እንዳለው ሰው እንደሆንኩ ያክል ተሰምቶኛል” በማለት ተናግሯል።
30 ይሖዋ ስለ ንጉሣዊ አገዛዙ የመናገር መብታቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎችን አብዝቶ እንደሚባርክ ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 145:11, 12) የጌታችንን የሞቱን መታሰቢያ በዓል ስናከብር ለአምላክ ያደሩ መሆን ወደፊት የበለጠ በረከት እንደሚያስገኝ እንገነዘባለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ዘላለማዊ የሕይወት ሽልማት የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት ተጠባብቋል። ሆኖም ይህ ሽልማት እንዲያው እጁን አጣጥፎ ተስፋ በማድረግ ብቻ እንደማይገኝ ገብቶት ነበር። “ለዚህም ነገር፣ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፣ እደክማለሁ” በማለት ጽፏል። (ቆላ. 1:29) ይሖዋ በኢየሱስ በኩል ለጳውሎስ ኃይል በመስጠት ሕይወት አድን አገልግሎቱን እንዲያከናውን እንዳደረገው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ለእኛም እንዲሁ ማድረግ ይችላል። በሚያዝያ ይህ ሁኔታ በአንተም ላይ ይፈጸም ይሆን?
[ሣጥን]
አንተስ አገልግሎት እንዲጀምር ማንን ማበረታታት ትችላለህ?
ልጅህን?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን?
አገልግሎት ያቆመን አንድ ሰው?