በሚያዝያ ወር ‘መልካም ሥራዎችን ለመሥራት ቀናተኞች’ ሁኑ!
1 ባለፈው ዓመት በሚልዮን የሚቆጠሩ የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 ቅጂዎች በመላው ዓለም በተሰራጩበት ወቅት ይህ ነው የማይባል ምሥክርነት ተሰጥቷል። የጉባኤ አስፋፊዎችም ሆኑ አቅኚዎች በዚህ የሚያነቃቃ ሥራ በቅንዓት ተካፍለዋል። ከእነርሱ አንዱ ነበርክን? ከእነርሱ መካከል ከነበርክ በዚህ ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ዘመቻ ተካፋይ በመሆንህ በጣም እንደተደሰትክ አያጠራጥርም። በዚህ ዓመት ደግሞ ምን ‘መልካም ሥራ’ ይጠብቀን ይሆን? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።— ቲቶ 2:14
2 በሚያዝያ ወርና በግንቦት መጀመሪያ አካባቢ “ጦርነት የማይኖርበት ጊዜ” የሚል ርዕስ ያለውን የሚያዝያ—ሰኔ 1996 የንቁ! መጽሔት ልዩ እትም የማሰራጨት አስደሳች ሥራ ይጠብቀናል። ይህ ርዕስ ብዙ ሰዎችን የሚማርክ ስለሆነ በተቻለ መጠን መጽሔቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ በብዛት ለማሰራጨት እንጥራለን። ይህ የንቁ! መጽሔት እትም በውስጡ ከያዘው በጣም አስፈላጊ ትምህርት አንፃር እስኪያልቅ ድረስ በሚያዝያና በግንቦት መበርከት ይኖርበታል።
3 ግባችን ሁሉም አስፋፊዎች እንዲሳተፉ ነው፦ በዚህ አገር የሚገኙ አስፋፊዎች በሙሉ በሚያዝያ ወር በስብከቱ ሥራ መሳተፋቸው የሚያበረታታ ይሆናል። የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል በአእምሯችን በሚመላለስበት በዚህ ወር በመስክ አገልግሎት ቀጥተኛ የሆነ “የምስጋናን መሥዋዕት” በማቅረብ ለአምላክ ጥሩነት ያለንን አድናቆት ለማሳየት እንደምንፈልግ አያጠራጥርም።— ዕብ. 13:15
4 በሚያዝያ ወር በሚደረገው አገልግሎት ሁሉም በቅንዓት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሲባል የእያንዳንዱን የጉባኤ አባል ችግር ለመረዳት ትጋት የተሞላበት ጥረት መደረግ ይኖርበታል። (ሮሜ 15:1) የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች በቡድናቸው ውስጥ ያሉትን አስፋፊዎች ሁኔታ በሚገባ ተረድተው አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ተግባራዊ እርዳታ መስጠት ይኖርባቸዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያስፈልገው ሰው ይኖራልን? ይህን አገልግሎት ማን ሊሰጥ ይችላል? አንዳንዶች ፍርሃት ወይም ዓይን አፋርነት አለባቸውን? የበለጠ ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች ከእነርሱ ጋር ሊያገለግሉ ይችላሉን? የታመሙትስ እንዴት ሊረዱ ይችላሉ? በስልክ በመመሥከር፣ ደብዳቤ በመጻፍ ወይም በሌላ ውጤታማ በሆነ የአገልግሎት መስክ ሊሳተፉ ይችላሉን?
5 ቀዝቅዘው የነበሩና ቋሚ መንፈሳዊ ማበረታቻ የተሰጣቸው አንዳንዶች እንደገና በስብከቱ ሥራ ለመሳተፍ ይገፋፉ ይሆናል። ልዩ እትም በሆነው ንቁ! መጽሔት የሚደረገው ዘመቻ እንዲነቃቁ ግሩም አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።
6 ልጆች ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሠልጥኗቸው፦ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ገና ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ባይሆኑም እንኳ ለበርካታ ዓመታት ከወላጆቻቸው ጋር ከቤት ወደ ቤት አገልግለዋል። አስፋፊ ሆነው ማገልገል የሚጀምሩበት ጊዜ አሁን ይሆን? ከልባቸው ተነሣስተው ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተዋልን? የቤተሰብ ራሶች ብቃት ያላቸው ልጆቻቸው እንደየዕድሜያቸውና እንደየችሎታቸው የተዘጋጁ አቀራረቦችን በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት እንዲለማመዱ ጊዜ መመደብ ያስፈልጋቸዋል። ትልልቆቹ ልጆች የሚያነጋግሩትን ሰው ፍላጎት ለመቀስቀስ አእምሮን የሚያመራምሩ ጥያቄዎችን ከተጠቀሙ በኋላ መልሱን ከመጽሔቱ ለማሳየት ሊመርጡ ይችላሉ። ትንንሽ ልጆች በጥቂት ቃላት ውጤታማ ምሥክርነት ሊሰጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የሚያነጋግሩትን ሰው “በዚህ ወር በመላው ዓለም እየተሰራጨ ያለውን ይህን ልዩ መጽሔት እንዲያነብ” ሊያበረታቱት ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ለሚያጋጥሙት የተቃውሞ ሐሳቦች እንዴት ምላሽ መስጠት እንደሚቻል የሚጠቁሙ አስተያየቶችን በቤተሰቡ ዝግጅት ውስጥ ማከል እንዳለባችሁ አትርሱ። ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ ብዙ ግሩም ሐሳቦችን ታገኛላችሁ። በምግብ ሰዓትና በሌሎች ተስማሚ ጊዜያት የቤተሰቡ አባላት በመስክ አገልግሎት ያገኙትን ተሞክሮ እንዲናገሩ አበረታቷቸው።
7 ብቃት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ኢየሱስ የሠራውን ሥራ ይሠራሉ፦ የኢየሱስ ትምህርት በመሠረተ ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም። ከተማሪዎቹ ጋር ወደ አገልግሎት በመውጣት እንዴት መስበክ እንደሚቻል አስተምሯቸዋል። (ሉቃስ 8:1፤ 10:1-11) ዛሬ ያለው ሁኔታስ ምንድን ነው? በመስካችን ከ5,000 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመመራት ላይ ናቸው። ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ብዙዎቹ ተገቢው ማበረታቻ ከተሰጣቸው የሥልጠናቸው ክፍል የሆነውን ቀጣይ እርምጃ በመውሰድ በሚያዝያ ወር ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነው ለማገልገል ብቃት ለማግኘት እንደሚችሉ አያጠራጥርም።
8 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ላይ ከሆንክ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው:- ተማሪው ከዕድሜውና ከችሎታው ጋር አብሮ የሚሄድ ዕድገት በማድረግ ላይ ነውን? እምነቱን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለሌሎች መግለጽ ጀምሯልን? “አዲሱን ሰው” በመልበስ ላይ ነውን? (ቆላ. 3:10) አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ ላይ ከገጽ 97 እስከ ገጽ 99 ድረስ የተዘረዘሩትን አንድ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሊያሟላቸው የሚገቡትን ብቃቶች አሟልቷልን? ብቃቶቹን እንደሚያሟላ ካመንክ ስለ ጉዳዩ ከእርሱ ጋር ለምን አትወያይም? አንዳንድ ተማሪዎች በሥራው ለመሳተፍ የሚያስፈልጋቸው በቀጥታ የቀረበ ግብዣ ብቻ ነው። እርግጥ ተማሪው ፈቃደኛ ከሆነ በመጀመሪያ እንደሌላው ጊዜ ከሁለት ሽማግሌዎች ጋር ውይይት እንዲደረግ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ዝግጅት ማድረጉ አስፈላጊ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪውን ያገደው አንድ ነገር ይኖር ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከሽማግሌዎቹ አንዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ላይ ሊገኝና ተማሪው ለእውነት ያለውን ስሜት እንዲገልጽ ሊያበረታታው ይችላል። ሽማግሌው ተማሪው የሚናገረውን ካዳመጠ በኋላ ቅዱስ ጽሑፋዊና ተግባራዊ ሐሳቦችን ሊሰጠው ይችል ይሆናል።
9 ረዳት አቅኚ ለመሆን ‘ጊዜ ዋጁ’፦ በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አስፋፊዎች ለቤዛው ባላቸው አድናቆት ተነሣስተው በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ‘ጊዜያቸውን ይዋጃሉ።’ (ኤፌ. 5:15-17) ረዳት አቅኚነት አንዳንድ መሥዋዕቶችን መክፈል የሚጠይቅ ቢሆንም የሚያስገኘው ጥቅም ከፍተኛ ነው። የማይናቅ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የትምህርት ቤት እረፍት ጊዜያቸውን ረዳት አቅኚ ለመሆን ይጠቀሙበታል። ሙሉ ቀን የሚሠሩ አዋቂዎችም ምሽቶችንና ቅዳሜና እሑድን ተጠቅመው በዚሁ ሥራ ሙሉ በሙሉ ይሳተፋሉ። በዚህ መንገድ ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ችለዋል! በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ አብዛኞቹ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሁም ሚስቶቻቸው በረዳት አቅኚነት አገልግሎት ይሳተፋሉ። ሌሎች አስፋፊዎች የእነርሱን ቅንዓት የተሞላበት ምሳሌ መኮረጃቸው በሚያዝያ ወር አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት በረዳት አቅኚነት እንዲያገለግሉ ያስችላል።
10 ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ብትችልም ባትችልም በሚያዝያ ወር የመስክ አገልግሎትህን ከፍ ለማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ። ጥቂት ጥረት አድርገህ ልትደርስበት የምትችለውን የግል ግብ አውጣ። የግል ሁኔታዎችህ የሚፈቅዱልህን ያህል ለይሖዋ አገልግሎት ‘ራስህን ሙሉ በሙሉ ማቅረብህ’ የእርሱን በረከት ያስገኝልሃል።— 2 ቆሮ. 12:15 አዓት
11 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች፦ የንቁ! መጽሔት ዘመቻ በሚደረግበት በእያንዳንዱ ቀን አገልግሎት ቀደም ብሎ ለመጀመር የሚያስችል የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ መደረግ ይኖርበታል። በተጨማሪም ለምሽት ምሥክርነት ዝግጅት መደረግ ይኖርበታል። አብዛኞቹ አስፋፊዎች በመስክ አገልግሎት የሚሳተፉት ቅዳሜና እሑድ ስለሆነ ጉባኤዎች የንቁ! መጽሔት ልዩ ስርጭት በሚካሄድበት ወቅት ቅዳሜ ጠዋትና ከሰዓት በኋላ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ለማድረግ ፕሮግራም ማውጣት አለባቸው።
12 የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን የሚመሩት በቂ የአገልግሎት ክልሎች እንዳሉ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በቅርቡ ያልተሠራባቸው የአገልግሎት ክልሎች በመጀመሪያ መሸፈን ይኖርባቸዋል። በቅርቡ ያልተሸፈነ አንድ ወይም ሁለት የአገልግሎት ክልል አለህን? በዘመቻው ወቅት በእነዚህ ክልሎች ውስጥ ለማገልገል እርዳታ የሚያስፈልግህ ከሆነ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹን ወይም የክልል አገልጋዩን ወንድም አነጋግረው፤ እነርሱ እርዳታ የምታገኝበትን ዝግጅት ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው።
13 ስንት መጽሔቶች ታበረክታለህ? ይህ እያንዳንዱ ግለሰብ በግሉ የሚመልሰው ጥያቄ ነው። በዘመቻው ወቅት ምን ያህል መጽሔቶችን ማበርከት እንደምትችል ስትወስን የምትሠራበትን የአገልግሎት ክልል ዓይነት፣ ዕድሜህን፣ ጤንነትህን፣ በአገልግሎት የምታሳልፈውን ጊዜና ሌሎች ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ አስገባ። ሆኖም በጥር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ላይ የተሰጠውን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ልብ በል:- “ሐሳብ ለማቅረብ ያህል፣ አስፋፊዎች እንደየሁኔታቸው 10 መጽሔቶችን ለማበርከት ግብ ሊያወጡ ይችላሉ። አቅኚዎች ደግሞ 90 ለማበርከት ጥረት ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል።” አንተስ ተመሳሳይ ግብ ብታወጣ ልትደርስበት ትችላለህን?
14 ሽማግሌዎች ጥሩ እቅድ ማውጣት ይኖርባቸዋል፦ የሚቻል ከሆነ እያንዳንዱ የጉባኤው የአገልግሎት ክልል በሙሉ በልዩ ንቁ! መጽሔት እትሙ እንዲሸፈን አድርጉ። ለጉባኤው በተመደበ በማንኛውም የንግድ አካባቢ ለሚደረገው ሥራ ልዩ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል። በዚህ አካባቢ የሚያገለግሉ አስፋፊዎች ጥሩ ዝግጅት ማድረግና ንጹሕ ልብስ መልበስ አለባቸው። ሐተታ የበዛበት አቀራረብ መጠቀም አስፈላጊ አይደለም። በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ሰው ስታነጋግሩ ንግድ ቦታዎ ድረስ የመጣነው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ቤታቸው ስለማናገኛቸው የእርስዎን ትኩረት የሚስብ አንድ ርዕስ ልናሳይዎት ነው ልትሉ ትችላላችሁ። ከዚያም ከመጽሔቱ ስለ አንድ የተወሰነ ነጥብ በአጭሩ ልታወያዩት ትችላላችሁ። በተጨማሪም በጉባኤው የአገልግሎት ክልል ውስጥ በመንገድ ላይ በሚሰጠው ምሥክርነት መጽሔቶችን ማበርከት የሚቻልበት መንገድ በሚገባ መደራጀት ይኖርበታል። የመንገድ ላይ ምሥክርነት እጅግ ውጤታማ የሚሆነው ሰዎች ወደ እናንተ እስኪመጡ ድረስ ሳትጠብቁ ራሳችሁ ቀዳሚ በመሆን መንገደኞችን ቀርባችሁ ስታነጋግሩ ነው። በብዙ ሰዎች ዓይን ስለምትገቡ የሚያስከብር ልብስ መልበስ ይኖርባችኋል። በክልላችሁ ውስጥ በዘመቻው ወቅት ሊሠራባቸው የሚገቡ ሌሎች ቦታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ መናፈሻዎችና ገበያዎች ሊሠራባቸው ይችላሉ። በጉባኤው የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በእነዚህ ቦታዎች ለመመሥከር ምን ተገቢ ዝግጅቶች ሊደረጉ እንደሚችሉ የሽማግሌዎች አካል መወሰን ይኖርበታል።
15 ይሖዋ የማይታክት ሠራተኛ ነው። (ዮሐ. 5:17) ሰማይና ምድርንም ሆነ እፅዋትንና እንስሳትን ፈጥሯል፤ ሆኖም ሥራውን በመቀጠል በምድር ላይ የፍጥረታት ቁንጮ የሆነውን ሰው ፈጥሯል። ሕይወት ያገኘነው አምላክ ለመሥራት ፈቃደኛ በመሆኑ ነው። ‘አምላክን የምንመስል’ እንደመሆናችን መጠን ለእርሱ ባለን ፍቅር ተገፋፍተን ‘መልካም ሥራዎችን ለመሥራት ቀናተኞች’ መሆን ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:1 የ1980 ትርጉም፤ ቲቶ 2:14) ይሖዋ የምንችለውን ያህል ልናገለግለው የሚገባው በመሆኑና ውጤት ለማግኘት መመኘት የአንድ ቀናተኛ አገልጋይ መለያ ምልክት ስለሆነ በአገልግሎታችን ጥራት ያለው ሥራ ለማከናወን መጓጓት ይገባናል። እርግጥ ይሖዋ ለእርሱ ብለን የምንከፍለውን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ስለሚያደንቅ ሥራችን ፈጽሞ ከንቱ አይሆንም። (1 ቆሮ. 15:58) ስለዚህ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነትና በረከት እንደምናገኝ እንዲሁም በእጅጉ እንደሚሳካልን በመተማመን በአመስጋኝ ልብ ተገፋፍተን በሚያዝያ ወር ቅንዓት የተሞላበት ተግባር ለማከናወን ራሳችንን እናቅርብ!