“የጌታ ሥራ የሚበዛላችሁ ሁኑ”
1 ከፊታችን በሚያዝያና በግንቦት በጉጉት የምንጠብቀው ሙሉ በሙሉ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የተያዘ ፕሮግራም ይጠብቀናል! ሚያዝያ 14 የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል እናከብራለን። በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች በዚያ ታላቅ ቀን እንዲገኙ ልናበረታታቸው ይገባል። ለምሳሌ:- የሥራ ባልደረቦቻችንን፣ የማያምኑ ዘመዶቻችንን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችንን፣ አዲስ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን በዚያ ቀን እንዲገኙ ጥረት ማድረግ አለብን። ልትጋብዟቸው ያሰባችኋቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ያዙ አንዲህ ካደረጋችሁ ማንንም ሳትረሱ ልትጋብዙ ትችላላችሁ።
2 በቀጣዩ ሳምንት በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ሁሉ ሚያዝያ 23 “የሐሰት ሃይማኖት ፍጻሜ ቀርቧል” በሚል ርዕስ የሚቀርበውን ልዩ የሕዝብ ንግግር እንዲያዳምጡ እናበረታታቸዋለን። ይህን ግልጽ መልእክት የሚሰሙ ብዙዎቹ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች እንዲህ ባሉ ልዩ አጋጣሚዎች ብቻ ሳይሆን አዘውትሮ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ ተብሎ ይገመታል።
3 ወደፊት የሚወጣው ልዩ የመንግሥት ዜና፦ ሚያዝያ 23 የሚደረገውን ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው እስከ ግንቦት 14 ድረስ በስፋት የምናሰራጨው ወቅታዊው ባለ አራት ገጽ የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 መውጣት ይሆናል። የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ወር አካባቢ ባሉት ጊዜያት ‘የጌታ ሥራ የሚበዛልን አይደለምን?’— 1 ቆሮ. 15:58
4 የሚሰራጨው የመንግሥት ዜና ለእያንዳንዱ ጉባኤ ይላካል። የመንግሥት ዜና የያዙት ካርቶኖች በደህና ቦታ መቀመጥ አለባቸው እንዲሁም ሚያዝያ 23 የሚደረገው ስብሰባ እስከሚደመደም ድረስ መከፈት የለባቸውም። በስብሰባው መጨረሻ ላይ የመንግሥት ዜና ለወንድሞችም ሆነ ለሕዝብ ይሰራጫል። ሚያዝያ 23 በሚደረጉ በጉባኤ ስብሰባዎች፣ በወረዳ ስብሰባዎች ወይም በልዩ ቀን ስብሰባዎች ላይ የተገኘ እያንዳንዱ ተሰብሳቢ አንዳንድ ቅጂ ያገኛል፤ ይህም የመንግሥት ዜና ከያዘው መልእክት ጋር እንዲተዋወቅና ለማሰራጨት ዝግጁ እንዲሆን ያስችለዋል።
5 ሽማግሌዎች ብዙ የሚሠሩት ሥራ ይኖራቸዋል፦ በዚህ ወር መግቢያ ላይ የሽማግሌዎች አካል ስለ ልዩ ዘመቻው ለመወያየት መሰብሰብ ይኖርበታል። ጉባኤዎች ከቤት ወደ ቤት በማገልገል የተሰጣቸውን የአገልግሎት ክልል ለመሸፈን መጣር ይኖርባቸዋል። ልዩ ዘመቻው ከመጠናቀቁ በፊት ባለፉት ስድስት ወራት ፈጽሞ ያልተሠራባቸውን የአገልግሎት ክልሎች ለመሸፈን ልዩ ጥረት አድርጉ። የሥራውን አስፈላጊነት ስንመለከት ለስብከቱ ሥራ የምንችለውን ያህል ጊዜ ለመመደብ እንፈልጋለን። ከወትሮው የበለጠ ብዙ አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም አዲስ የተሾሙ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች በመሆን በዚህ ሥራ እንደሚተባበሩን የታወቀ ነው። በጌታ ሥራ አብረን በመሥራት በጣም የሚያስደስት ጊዜ እናሳልፋለን!
6 የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች ቅዳሜና እሁድ ለሚደረግ ምሥክርነት ቁርጥ ያለ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሁሉም ጥሩ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሊበረታቱ ይገባል። በዚህ ልዩ የዘመቻ ወቅት በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከምናደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ቢያንስ ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን በምሽት ለሚደረግ ምሥክርነት ፕሮግራም ሊወጣ ይገባል። አንዳንዶች ከትምህርት ቤት መልስ ተጨማሪ ተሳትፎ ለማድርግ የሚፈልጉትን ተማሪዎች ለመርዳት ከሰዓት በኋላ የአገልግሎት ስብሰባ ለማድረግ ይፈልጉ ይሆናል።
7 አስፋፊዎችም ሆኑ አቅኚዎች በእያንዳንዱ ቀን አገልግሎታቸውን ቀደም ብለው መጀመር እንዲችሉ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ፕሮግራም መውጣት ይኖርበታል። እነዚህ ስብሰባዎች አጠር ያሉ ሊሆኑ ይገባል። እያንዳንዱ ስብሰባ የመንግሥት ዜና እንዴት እንደሚበረከት የሚያሳይ አቀራረብ መግለጽ ይኖርበታል። የከሰዓት በኋለው የአገልግሎት ስብሰባ የመንግሥት ዜና የወሰዱትን ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግን የሚጠቁም አንድ ወይም ሁለት ሐሳቦችን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንድ አስፋፊዎች ጠዋትም ሆነ ከሰዓት በኋላ ማሰራጨቱን ይመርጡ ይሆናል። ለዚህ ዓላማ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ በቂ ክልል መኖሩን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ፍላጎት ያሳየ የማንኛውም ሰው ስምና አድራሻ ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያ ቅጽ ላይ መመዝገብ ይኖርበታል። አስተያየት በሚለው በኩልም ውይይታችሁ ባጭሩ ምን ይመስል እንደነበረ የሚጠቁም ሐሳብ መጨመር ይቻላል። ይህም ከሳምንት ወይም ከወር በኋላ ተመላልሶ መጠይቅ ለማድረግ መንገድ ይጠርጋል።
8 አንድ ጉባኤ ሌላው ጉባኤ ክልሉን አንዲሸፍን የሚረዳው ከሆነ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ስምና አድራሻ ክልሉ ለሚገኝበት ጉባኤ ማስረከብ ይኖርበታል።
9 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን ጥረት እያደረጉ ነውን? በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ በታረመ ፀባይ ያደጉ ልጆች ለብዙ ዓመታት ራሳቸውን ከወሰኑ ወላጆቻቸው ጋር ሲያገለግሉ እንደቆዩና ምንም እንኳ ገና የምሥራቹ አስፋፊዎች ባይሆኑም ውጤታማ እንደሆኑ ተስተውሏል። ወላጆች ልጆቻቸው በእርግጥ ለዚህ መብት ይበቁ ወይም አይበቁ እንደሆነ ሊመረምሩ ይገባቸዋል። ሁለት ሽማግሌዎች ከቤቱ ራስ ጋር ልጁ አስፋፊ እንዳይሆን ያገደውን ምክንያት ሊወያዩና ልጁ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ይበቃ ወይም አይበቃ እንደሆነ ሊወስኑ ይችላሉ።— አገልግሎታችን ገጽ 99–100
10 በጉባኤህ ክልል ለይሖዋ የምስጋና መሥዋዕት በትጋት የማያቀርቡ አስፋፊዎች አሉን? (ዕብ. 13:15) ምንም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎች ጋር ተጣብቀው የቀጠሉ ቢሆኑም አንዳንዶች የቀዘቀዙት ተስፋ መቁረጥ አሸንፏቸው ወይም የኑሮ ጫና ከብዷቸው ሊሆን ይችላል። በአንድ ሽማግሌ የሚደረግላቸው ወዳጃዊ ጉብኝት አዘውትረው ከጉባኤው ጋር ለመሰብሰብ እርምጃ እንዲወስዱ ሊያደርጋቸውና በተገቢው ጊዜም የአገልግሎት መንፈሳቸው እንዲታደስ ሊያደርጋቸው ይችላል።
11 ብቃት ያላቸው ሁሉ በዚህ አስደሳች ሥራ ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ፦ እናንት ልጆች ወይም በአሥራዎቹ እድሜ ላይ የምትገኙ ወጣቶች ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን አገልግሎት አስቸጋሪ ሆኖ አግኝታችሁታልን? በስብከቱ ሥራ የተወሰነ ልምድ ያላችሁ እናንት አዲሶችስ? በዚህ ልዩ የመንግሥት ዜና አማካኝነት የሚደረገውን የስብከት ሥራ የሚያስደስት ሆኖ ታገኙታላችሁ! የሚያስፈልገው ቀላል አቀራረብ ብቻ ነው።
እንዲህ ለማለት ትችላለህ :-
◼ “በዚህ ወር በዓለም ዙሪያ በ232 አገሮች አንድ በጣም አስፈላጊ መልእክት እያሰራጨን ነው። መልእከቱ በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ከፊታችን የተጋረጡብን ችግሮች መፍትሔ እንዳላቸው እንድናምን የሚያደርግ ተጨባጭ ማስረጃ ይሰጣል። እርስዎም የራስዎት ቅጂ እንዲኖርዎት እንፈልጋለን።”
ወይም ይህንን ልትሞክር ትችላለህ:-
◼ “በዚህ ወር ወደ አምስት ሚልዮን የሚሆኑ ፈቃደኞች አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ መልእክት በብዙ ቋንቋዎች እያሰራጩ ነው። በአሁኑ ጊዜ ሁላችንንም የሚያጋጥሙን ችግሮች ፍጻሜ አግኝተው ለማየት ለሚናፍቁ ሰዎች የተዘጋጀ ነው። ይህ የእርስዎ የግል ቅጂ ነው።”
ምናልባት በሚከተለው አቀራረብ መጠቀም ትመርጥ ይሆናል:-
◼ “እንዲህ የሚል ርዕስ ያለውን [የመንግሥት ዜናን ርዕስ አንብብ።] ጠቃሚ መልእክት ሰዎች ሁሉ እንዲያነቡት እያበረታታን ነው። እየጨመሩ የሚሄዱትን ችግሮች በተመለከተ በዚህ በገጽ 2 ላይ ምን እንደሚል ልብ ይበሉ . . .። [ከመንግሥት ምሥራች ላይ የተመረጠ አንድ ዓረፍተ ነገር አንብብ።] የቀረውን የዚህን ወቅታዊ መልእክት በማንበብ እንደሚደሰቱ እርግጠኞች ነን። ይህ የእርስዎ ቅጂ ነው።”
12 የመንግሥት ዜና የወሰዱትን ሁሉ ትኩረት ስጣቸው። ረጋ ብለህ በግልጽ ተናገር። አቀራረብህ የጥድፊያ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ክልላችንን በተሟላና በተጣራ መንገድ ለመሸፈንና የመንግሥት ዜና ለማንበብ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ሁሉ አንዳንድ የግል ቅጂ ሲደርሳቸው ለማየት እንፈልጋለን። በቤቱ ማንም ሰው ከሌለ ተስማሚ በሆነው ጊዜ ተመልሰህ የመንግሥት ዜና ማበርከት እንድትችል ከቤት ወደ ቤት መመዝገቢያህ ላይ በጥንቃቄ ምልክት አድርግ። አንድ ሰው ጽሑፉን ለማንበብ ፍላጎት ካሳየ የመንግሥት ዜናን በመንገድ ላይ ምሥክርነትም ልንጠቀምበት እንችላለን። ይሁን እንጂ ቅጂዎቹ የስብሰባ መጥሪያ ወረቀት ይመስል እጅ እንዳመጣ መታደል የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ቀረብ ብለህ አነጋግረውና እያስተዋወቅን ያለነውን መልእክት አስፈላጊነት ግለጽለት። የመንግሥት ዜናን መደበኛ ላልሆነ ምሥክርነትም ልንጠቀምበት እንችላለን። ለምሳሌ በትራንስፖርት ስትጓዝ ወይም በምሳ እረፍትህ ጊዜ ለሥራ ባልደረባህ ስትመሠክር እና በመሳሰሉ አጋጣሚዎች ተጠቀምበት። በሕመም ወይም በሌላ ምክንያት እቤት የዋሉ ሊጠይቋቸው ለመጡ፣ ለዶክተሮቻቸውና ለአስታማሚዎቻቸው፣ ዕቃ ለመሸጥ እቤታቸው ለሚመጡና ለሌሎችም ሊያበረክቱ ይችላሉ።
13 በዘመቻው ወቅት ምን ያህል ተመላልሶ መጠየቅ ታደርጋለህ? በመንግሥት ምሥራች ላይ ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ ተመልሰን ልንጠይቃቸው ስለሚገባ በጣም ብዙ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በመጀመሪያ ጉብኝታችን ወቅት የመንግሥት ዜና ማበርከቱ ላይ ብቻ ብናተኩር ይመረጣል። ከዚያም ተመልሰህ በምትመጣበት ጊዜ የመንግሥት ዜና ላይ የወጡት መልእክቶች ምን ያህል ወቅታዊ እንደሆኑ አንዳንድ ሐሳቦች አካፍለው። ሰውዬው ባነበበው ነገር ላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር በጥሞና አዳምጥ። የሚሰጠው ሐሳብ ወቅታዊ ከሆኑት መጽሔቶች የትኛውን ልታበረክትለት እንደሚገባና ምናልባትም ለቀጣዩ ውይይት ምን መዘጋጀት እንዳለብህ ለማወቅ ይረዳሃል። በተመላልሶ መጠየቁ አዎንታዊ ምላሽ ካገኘህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ጥረት አድርግ።— 1 ቆሮ. 3:6, 7
14 ‘ድካማችሁ ከንቱ አይሆንም’፦ ይህ ሁሉ ድካም የሚያስገኘው ውጤት ይኖራልን? ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎችን “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና” በማለት አረጋግጦላቸዋል። (1 ቆሮ. 15:58) ለበርካታ ዓመታት የመንግሥት ዜናን ለማሰራጨት ያደረግነው ጥረት በጣም ተባርኳል። ሁለት ባልና ሚስት ቤት ቀይረው ወደ አንድ ባዶ የመኖሪያ ሕንፃ ይዛወራሉ፤ ወደ ቤቱ ሲገቡ በመሳቢያው ውስጥ አንድ የቆየ የመንግሥት ዜና ያገኛሉ። በሕንፃው ውስጥ የቀረ ነገር ቢኖር ይህ ብቻ ነበር። ካነበቡት በኋላ በአካባቢው ከሚገኝ ጉባኤ ጋር ግንኙነት አደረጉ፤ ወዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ጠየቁ። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ፤ ከዚያም ለመጠመቅ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ። ምናልባት አንተም የምታበረክታቸው ቅጂዎች ተመሳሳይ ውጤት ያመጡ ይሆናል።— የእንግሊዝኛ መአ 11/74 ገጽ 1፤ በተጨማሪም የእንግሊዝኛ ንቁ! ኅዳር 8, 1976 ገጽ 15
15 ከፊታችን ሰፊ የሥራ መስክ ይጠብቀናል። ግባችን ከግንቦት 14 በፊት ወይም የመንግሥት ምሥራቹ ን የማሰራጫ ጊዜ ማራዘም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ እስከ ወሩ መጨረሻ ድረስ እያንዳንዱ ጉባኤ የተመደበለትን የአገልግሎት ክልል እንዲሸፍን ነው። አማርኛ፣ ኦሮምኛና ወላይትኛ ተናጋሪ በሆኑ አከባቢዎች ለእያንዳንዱ የዘወትርና ረዳት አቅኚ በግምት 100 የመንግሥት ዜና ቅጂዎች ለመላክ ዝግጅት ተደርጓል። እያንዳንዱ የጉባኤ አስፋፊም 50 ቅጂዎች ያህል ሊያገኝ ይችላል። አስፋፊዎችና አቅኚዎች ማሰራጨት የሚችሉትን ያህል ብቻ ሊወስዱና የተረፋቸውንም ትራክቶች ሌሎች እንዲጠቀሙበት ሊመልሱ ይገባቸዋል። በዚህ ረገድ የምናደርገው ጥሩ ትብብር ይህን ዋጋ ያለው መልእክት በስፋት ለማሰራጨት ያስችላል። የተመደበላቸው ክልል በጣም ሰፊ በመሆኑ ምክንያት እስከ ግንቦት አጋማሽ ድረስ ክልላቸውን ለመሸፈን ያልቻሉና አሁንም የቀሩ ቅጂዎች ያሏቸው ጉባኤዎች ካሉ ጎረቤት ጉባኤዎች እንዲያግዟቸው መጋበዙ ውጤታማ ይሆናል። በሌሎች ጉባኤዎች ምናልባት አስፋፊዎች ረዳት አቅኚ በመሆን ወይም በአገልግሎቱ አዘውትረው በመሳተፍ እንቅስቃሴያቸውን ከፍ የሚያደርጉት ከሆነ የአገልግሎት ክልሉ በራሱ በጉባኤው ሊሸፈን ይችላል። ትራክቶቹ ወደ ጉባኤያችሁ ዘግይተው የደረሱ ከሆነ ትራክቶቹ ልክ እንደደረሷችሁ የሦስት ሳምንት የዘመቻ ፕሮግራም ማውጣት ይገባችኋል፤ ግባችሁም የመጣላችሁን ሁሉ አሰራጭታችሁ ለመጨረስ መሆን አለበት።
16 ሥራችንን ውጤት ባለው መንገድ ለመፈጸም የምንፈልግ ከሆነ በሙሉ ነፍስ ለይሖዋ ያደርን መሆን ይፈለግብናል። (ቆላ. 3:23) የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት የሚነካ ጉዳይ ነው። ሰዎች አሁን በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ያሉት ሁኔታዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው ሊያጤኑት ይገባል። ጊዜው እየተሟጠጠ ነው። ለዚህ ዓለም ችግሮች የሰው ልጅ መፍትሔ ሊያስገኝ አይችልም፤ ሰዎች ይህንን ሐቅ አምነው መቀበል አለባቸው። የአምላክን በረከት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ከአምላክ ብቃቶች ጋር የሚስማማ አፋጣኝና ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል።
17 ልዩ ዘመቻው ግንቦት 14 ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ አለብንን? በፍጹም! ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት ከሰጠው ምክር ጋር በመስማማት የበለጠ ሥራ የበዛልን ሆነን እንቀጥላለን።