ከጥቅምት 16 እስከ ኅዳር 12 የሚደረግ ልዩ ዘመቻ!
1 “የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!” ይህ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ለሚሰራጨው የመንግሥት ዜና ቁጥር 37 የተሰጠ ርዕስ ነው። በጥቅምት ወር የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እናበረክታለን። ከዚያም ከሰኞ ጥቅምት 16 እስከ እሁድ ኅዳር 12 የመንግሥት ዜና ቁ. 37ን በስፋት እናሰራጫለን። በዘመቻው ወቅት ቅዳሜና እሁድ ወቅታዊ የሆኑ መጽሔቶችንም አብረን እናበረክታለን።
2 እነማን መሳተፍ ይችላሉ? ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ላይ እየተካፈሉ ያሉ ሁሉ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ። ምናልባትም አንዳንዶቹ ረዳት አቅኚ መሆን ይችሉ ይሆናል። ጥሩ መንፈሳዊ እድገት እያደረጉ ያሉ ልጆች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉህ? ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነው ለማገልገል ብቃቱን ያሟሉ እንደሆነ ለማወቅ ሽማግሌዎችን እንዲያናግሩ እርዳቸው። ሽማግሌዎች ቅድሚያውን ወስደው አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎችን ቀርበው በማናገር በዘመቻው ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሊያበረታቷቸው ይገባል። ምናልባትም ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር ሊመድቧቸው ይችላሉ።
3 አስፋፊዎችም ሆኑ የዘወትር አቅኚዎች ቢያንስ 30 ቅጂ እንዲደርሳቸው የመንግሥት ዜና ቁ. 37 በበቂ መጠን ለሁሉም ጉባኤዎች ይላካል። አስፋፊዎች ባይሆኑም እንኳ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች፣ ለቤተሰባቸው ወይም ለጓደኞቻቸው የሚያበርክቱት አምስት ቅጂ ሊወስዱ ይችላሉ። አስፋፊዎችም ሆኑ አቅኚዎች ያበረከቱትን የመንግሥት ዜና መዝግበው በመያዝ የጥቅምትና የኅዳር ወር ሪፖርታቸውን በሚመልሱበት ወቅት በቅጹ ጀርባ ላይ ያበረከቱትን ብዛት መጻፍ አለባቸው። የጉባኤው ጸሐፊ ደግሞ ጉባኤው ያበረከተውን ጠቅላላ የመንግሥት ዜና ከደመረ በኋላ በእያንዳንዱ ወር መጨረሻ ላይ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ይልከዋል። ከዘመቻው የተረፈ የመንግሥት ዜና ካለ በየትኛውም የአገልግሎት ዘርፍ ማበርከት ይቻላል።
4 ስናበረክት ምን ማለት እንችላለን? መልእክቱን በስፋት ማሰራጨት እንዲያስችላችሁ አቀራረባችሁን አጭር አድርጉት። እንዲህ ማለት ትችላላችሁ:- “በዓለም ዙሪያ እየተሰራጨ ያለውን ይህንን በጣም አስፈላጊ መልእክት እኔም ለዚህ አካባቢ ሰዎች እያዳረስኩ ነው። ይህ የእርስዎ የግል ቅጂ ነው። እባክዎ ወስደው ያንብቡት።” የመንግሥት ዜና ቁ. 37ን በምናሰራጭበት ጊዜ የአገልግሎት ቦርሳ አለመያዛችን ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ያገኛችኋቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች መዝግባችሁ መያዛችሁን አትዘንጉ።
5 የአገልግሎት ክልልህን እንዴት መሸፈን ትችላለህ? የመንግሥት ዜናን በመንገድ ላይ በሚደረግ አገልግሎት ከማሰራጨት ይልቅ ከቤት ወደ ቤትና በንግድ አካባቢዎች ለማዳረስ ጥረት አድርጉ። ሰው ያልተገኘባቸውን ቤቶች መዝግባችሁ በመያዝ በሳምንቱ ውስጥ በሌላ ቀን ወይም በሌላ ሰዓት ተመልሳችሁ በመሄድ ባለቤቶቹን ለማግኘት ሞክሩ። ከሰኞ ኅዳር 6 ጀምሮ ግን በቤታቸው ለማታገኟቸው ሰዎች ትራክቱን ቤታቸው ትታችሁላቸው መሄድ ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ ጉባኤው ሰፊ የአገልግሎት ክልል ኖሮት በተወሰነው ጊዜ ውስጥ መሸፈን የማይችል ከሆነ ሽማግሌዎች በዘመቻው ወቅት በሙሉ የመንግሥት ዜና ቁ. 37ን ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች ትታችሁላቸው እንድትሄዱ ሊወስኑ ይችላሉ።
6 ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ ጥፋት በፍጥነት እየቀረበ ነው። ሙሉ በሙሉ ከመጥፋቷ በፊት ሰዎች ከእርሷ መውጣት ይኖርባቸዋል። (ራእይ 14:8፤ 18:8) ሁሉም ሰው የሐሰት ሃይማኖት ጥፋት መቅረቡን እንዲያውቅ በሚያስችለው በዚህ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ለመካፈል ከአሁኑ እቅድ አውጡ!