ከጥቅምት 20 እስከ ኅዳር 16 የሚካሄድ ልዩ የትራክት ዘመቻ!
1 ከሰኞ ጥቅምት 20 ጀምሮ ለአራት ሙሉ ሳምንታት እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የሚል ርዕስ ያለውን አዲስ ትራክት ለማሰራጨት ልዩ ዘመቻ እናካሂዳለን። በመላው ዓለም የሚካሄደው ይህ ልዩ ዘመቻ ብዙ ሰዎች የእውነት ብቸኛ ምንጭ ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል የሚል እምነት አለን።—ዮሐ. 17:17
2 ትራክቱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሚከተሉት ስድስት አስፈላጊ ጥያቄዎች የሚሰጠውን ግልጽ መልስ ይዟል፦ “አምላክ በእርግጥ ያስብልናል?” “ጦርነትና መከራ ማብቂያ ይኖራቸው ይሆን?” “ስንሞት ምን እንሆናለን?” “ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?” “አምላክ እንዲሰማኝ እንዴት መጸለይ ይኖርብኛል?” እንዲሁም “በሕይወቴ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?” አብያተ ክርስቲያናት ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት አልቻሉም። ከሕዝበ ክርስትና ውጪ ያሉ የሌሎች እምነቶች ተከታዮችም እንኳ እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፤ ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ መልስ እንደያዘ አያውቁ ይሆናል። በመሆኑም ይህ መልእክት የብዙ ሰዎችን ቀልብ እንደሚስብ ተስፋ እናደርጋለን።
3 የአገልግሎት ክልላችሁን ሸፍኑ፦ ከቤት ወደ ቤት በማገልገል በተቻለ መጠን አብዛኛውን ክልላችሁን ለመሸፈን ጥረት አድርጉ። ክልላችሁ ሰፊ ከሆነ፣ ሽማግሌዎች ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች ትራክቱን መጀመሪያ በሄዳችሁ ዕለት በራቸው ላይ እንድታስቀምጡላቸው ሊወስኑ ይችላሉ። ትራክቱን ለጎረቤቶቻችሁ፣ ለዘመዶቻችሁ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ለምታውቋቸው ሰዎች እንዲሁም ዘወትር ለምታነጋግሯቸው ሌሎች ሰዎች መስጠት እንደሚኖርባችሁ አትርሱ። ምናልባት በጥቅምት ወይም በኅዳር ወር ረዳት አቅኚ ሆናችሁ ለማገልገል እቅድ ማውጣት ትችሉ ይሆናል። ጥሩ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ላይ የሚገኝ ልጅ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አላችሁ? ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ በዘመቻው ለመካፈል የሚያስችለውን ብቃትስ ያሟላል? ከሆነ ሁኔታውን ለሽማግሌዎች አሳውቁ።
4 ምን ማለት ትችላለህ? መልእክቱን ለበርካታ ሰዎች ለማድረስ አቀራረብህን አጭር እንዲሆን ማድረግህ በጣም የተሻለ ነው። የቤቱን ባለቤት በትራክቱ የመጀመሪያ ገጽ ላይ ከሚገኙት ስድስት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱን መጠየቅ ትችላለህ፤ ከዚያም በትራክቱ ላይ የሚገኘውን መልስ አሳየው። ይህም ሁሉም አስፋፊዎች አቀራረባቸውን እንደ ክልላቸው ሁኔታ እንዲቀያይሩ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ፍላጎት ያለው ሰው ካጋጠመህ ማስታወሻ በመያዝ በሌላ ጊዜ ተመልሰህ አነጋግረው። ቅዳሜና እሁድ ከትራክቱ ጋር ወቅታዊ መጽሔቶችን እናበረክታለን። ዘመቻው ኅዳር 16 ካበቃ በኋላ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ ይበረከታል። የተረፈው ትራክት እንደማንኛውም ትራክት ጥቅም ላይ ይውላል።
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀምር፦ ይህ ትራክት በዋነኝነት የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ማስጀመር እንድንችል እኛን ለመርዳት ነው። ፍላጎት ላሳየ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ በትራክቱ ላይ ከተገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መካከል የትኛው እንዳጽናናው ወይም እፎይታ እንዳስገኘለት ልትጠይቀው ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ስለተደረገው ዝግጅት የሚናገረውን በገጽ 4 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አሳየውና ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ስጠው። የሚቻል ከሆነ እሱ የመረጠውን ርዕሰ ጉዳይ ይበልጥ ከሚያብራራው ምዕራፍ ውስጥ አንድ ወይም ሁለት አንቀጾችን በአጭሩ ተወያዩበት።
6 ይሖዋ እሱን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ የሚፈልጉ ሰዎችን እየሰበሰበ ነው። (ዮሐ. 4:23) ሰዎች እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ለመርዳት ሁላችንም በዚህ ልዩ ዘመቻ እንካፈል!