“አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?”
1 ይህ ጥያቄ በምድር ዙሪያ በሚኖሩት ሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚጉላላ ጥያቄ ነው። ምንም እንኳ ባለፉት መቶ ዓመታት የሰው ልጅ ብዙ ነገሮችን ያከናወነ ቢሆንም ሰውን በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲያስጨንቁ የኖሩት መሠረታዊ ችግሮች አሁንም እንዳሉ በመሆናቸው ሰዎች ግራ ተጋብተዋል። (ኢዮብ 14:1፤ መዝ. 90:10) የሰው ዘር እፎይታ ማግኘት የሚችለው ከየት ነው?
2 በጥቅምትና በኅዳር ወራት ጎረቤቶቻችን ለዚህ ጥያቄ መልስ እንዲያገኙ የመርዳት ልዩ መብት ተከፍቶልናል። እንዴት? የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን በማሰራጨት ነው። ርዕሱ “አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?” የሚል ነው። በጥቅምት ወር የመጀመሪያ አጋማሽ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን እናበረክታለን። ከዚያም ከሰኞ ጥቅምት 16 እስከ ዓርብ ኅዳር 17 የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን በስፋት እናሰራጫለን። በዘመቻው ወቅት በሥራ ቀናት የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን በማበርከት ላይ የምናተኩር ሲሆን ቅዳሜና እሁድ ወቅታዊ የሆኑ መጽሔቶችንም አብረን እናበረክታለን።
3 ሙሉ ተሳትፎ ታደርጋላችሁ? ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና አቅኚዎች ለዚህ ሥራ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉ እንደመሆናቸው መጠን በዚህ ዘመቻ ቀዳሚ ሆነው መገኘት ይፈልጋሉ። ብዙ አስፋፊዎች በአንዱ ወይም በሁለቱም የዘመቻ ወራት ረዳት አቅኚዎች ለመሆን ሁኔታዎቻቸውን አመቻችተዋል። ሌሎች ደግሞ በአገልግሎቱ ከበፊቱ የበለጠ ለመሥራት ዕቅድ አውጥተዋል።
4 የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች እያንዳንዱ የቡድኑ አባል የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን በማሰራጨት ረገድ ሙሉ ተሳትፎ እንዲያደርግ በማበረታታት በኩል ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል። በስብከቱ ሥራ ተሳትፎ ማድረግ ያቆሙ አንዳንድ አስፋፊዎች ይኖሩ ይሆናል። እነርሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለማወቅ ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉትን መጎብኘት ይኖርባቸዋል። በእነዚህ የዘመቻ ወራት ተሞክሮ ያለው አስፋፊ አገልግሎት ያቆመ እያንዳንዱን አስፋፊ ይዞ እንዲወጣ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል። እነዚህን ሰዎች እንደገና ንቁ አስፋፊዎች ለማድረግ የሚያስፈልገው የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን ለማበርከት ቀላል አቀራረብ መጠቀም ብቻ ሊሆን ይችላል።
5 በእውቀት መጽሐፍ አማካኝነት በጥናታቸው የገፉና በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ብቁ ሊሆኑ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን ይህ ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። ሌላው ቀርቶ ልጆችም በጣም አስደሳች በሆነው በዚህ ሥራ ጥሩ ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ።
6 የሚፈለገው ነገር ቀላል አቀራረብ መጠቀም ብቻ ነው። እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “ያለኝን ጊዜ ተጠቅሜ [የከተማውን ወይም የአካባቢውን ስም በመጥቀስ] ይህን በጣም አስፈላጊ መልእክት ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በማሰራጨት ላይ እገኛለሁ። ይህ የእርስዎ የግል ቅጂ ነው። ወስደው እንዲያነቡት እጋብዝዎታለሁ።” የመንግሥት ዜና ቁ. 36ን በምናሰራጭበት ጊዜ የአገልግሎት ቦርሳ አለመያዝ ይመረጥ ይሆናል።
7 ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸው የመስክ ስምሪት ስብሰባዎች:- ሽማግሌዎች የስምሪት ስብሰባዎች ለማድረግ የሚመርጡት ሰዓት አመቺና ተግባራዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል። እያንዳንዱ አስፋፊ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ እንዲችል በተለይ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ከቤት ወደ ቤትና በንግድ አካባቢዎች ለመሥራት እንዲቻል በቂ ክልል እንዲኖር ማድረግ ይኖርበታል። በተቻለ መጠን በሥራ ቀናት፣ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም ምሽት ላይ የመስክ ስምሪት ስብሰባዎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ተማሪዎች፣ የፈረቃ ሠራተኞችና ሌሎችም እንዲጠቀሙ አመሻሹ ላይ የስምሪት ስብሰባ ማዘጋጀት ይቻላል።
8 ቤታቸው ካልተገኙ ምን ማድረግ እንችላለን:- ግባችን በተቻለን መጠን ብዙ የቤት ባለቤቶችን በግል ማነጋገር ነው። ቤታቸው በምትሄድበት ጊዜ ማንንም ሰው ካላገኘህ አድራሻውን በማስታወሻህ ላይ ጽፈህ በሌላ ቀን ተመለስ። በዘመቻው የመጨረሻ ሳምንት ልታገኛቸው ሞክረህ ካልተሳካልህ በዚያ የሚያልፍ መንገደኛ እንዳያይ አድርገህ አንድ የመንግሥት ዜና ቁ. 36 በሩ ላይ ትተህ መሄድ ትችላለህ። የገጠር ክልሎች በሚሸፈኑበት ጊዜ ወይም ደግሞ በዚህ ዘመቻ መሸፈን ባለባቸው ሌሎች ክልሎች ውስጥ በሚሠራበት ወቅት በመጀመሪያ ቀን ቤታቸው ላልተገኙ ሰዎች አንድ የመንግሥት ዜና ቁ. 36 ትተውላቸው እንዲሄዱ ሽማግሌዎች ለጉባኤው መንገር ይችላሉ።
9 ጥሩ ተሳትፎ እናድርግ! ጉባኤዎች ከኅዳር 17 በፊት ክልላቸውን ለመሸፈን ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል። ጉባኤው በጣም ሰፊ ክልል ኖሮት ምቹና የማያሰጋ ከሆነ አንዳንድ አስፋፊዎች ብቻቸውን ማገልገል ይችላሉ። ይህ ዝግጅት መስማት የሚገባቸውን ብዙ ሰዎች ለማግኘት ይበልጥ ቀላል ይሆናል። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በሙሉ በጥሩ ሁኔታ በማስታወሻ ላይ መመዝገብ አትዘንጋ።
10 ለእያንዳንዱ ጉባኤ የተመደበው የመንግሥት ዜና ቁ. 36 ስለሚላክ ማዘዝ አያስፈልግም። ለልዩ፣ ለዘወትርና ለረዳት አቅኚዎች ለእያንዳንዳቸው 200 ቅጂዎች የሚደርሳቸው ሲሆን እያንዳንዱ አስፋፊ ደግሞ 50 ይሰጠዋል። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የቆዩ መጽሔቶችንም መስጠት ይቻላል። በዚህ ልዩ ዘመቻ ጥሩ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተሃል? አምላክ በቅርቡ ስለሚያመጣው ጊዜ ለጎረቤቶቻችን ማሳወቅ እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው!