አዲሶች ዕድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው
1 ሚያዝያ 17 ቀን 1992 በዓለም ዙሪያ ወደ 11.5 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል ለማክበር ተሰብስበው ነበር። ይህም በይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ባሉት አስፋፊዎች በጠቅላላው ሁለት ተኩል በላይ ነው። ይህን የሚያክል ቁጥር ያለው ሕዝብ “ወደ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት ] ተራራ” ሲጐርፍ መመልከት እንዴት ያስደስታል! (ሚክ. 4:2) በአሁኑ ጊዜ ለእውነተኛው አምልኮ መጠነኛ ፍላጎት ያሳዩ ወደ ሰባት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች አሉ። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ይሖዋን በሕዝብ ፊት እያወደሱት አይደሉም። በእርግጥም “መከሩስ ብዙ ነው” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ያሁኑን ያህል ሙሉ ስሜት የሚሰጡ ሆነው አያውቁም! — ማቴ 9:37, 38
2 በሚያዝያ ወር በመስክ አገልግሎት ለመካፈል ብቁ የሆኑትን ሁሉ ለመርዳት ልዩ ጥረት እናደርጋለን። የጉባኤው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሪ በቡድኑ ውስጥ ባሉ ችሎታ ባላቸው ሌሎች አስፋፊዎችና አቅኚዎች በመታገዝ በዚህ ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይችላል። ሦስቱ ግቦቻችን:- (1) በዚህ ዓመት በሚሰጠው ልዩ የሕዝብ ንግግርና በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን አዳዲስ ሰዎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ዝግጅት ማድረግ፣ (2) እያጠኑ ያሉት ደግሞ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን የሚያስችሏቸውን ብቃቶች እንዲያገኙ ማበረታታትና (3) እኛም በመስክ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ መጨመር ናቸው።
3 እያንዳንዱ ሰው በስብሰባዎቻችን ላይ ለሚገኙት አዳዲስ ሰዎች ሰላምታ ለመስጠትና ለመተዋወቅ ልዩ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ፍላጎት ካላቸው ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ብዙዎቹ ቋሚ የሆነ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖራቸው ለማበረታታት ምን ልናደርግ እንችላለን?
4 በ1992 የአገልግሎት ዓመት በምሥራቅ አፍሪካ በየወሩ በአማካይ 29,750 የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል። አስፋፊዎች የመጽሐፍ ጥናት መሪያቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው ጋር ለመተዋወቅ እንዲችል አብሯቸው እንዲያስጠና ሊጋብዙት ይችላሉ። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አንዳንዶቹ በስብሰባዎች ላይ ይገኙ ይሆናል፤ እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ ተካፋይ ለመሆን የሚያስችል ብቃት ሊኖራቸው ይችላል። እነዚህ አዲሶች አዘውትረው መደበኛ ያልሆነ ምስክርነት ይሰጣሉን? አገልግሎታችን በተባለው መጽሐፍ በገጽ 50–52 (በእንግሊዝኛው በገጽ 97–99) ላይ በተገለጹት መሠረት ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች አሟልተዋልን? አሟልተው ከሆነ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ለመሆን ተቀባይነት ካገኙ በኋላ ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን አገልግሎት እንዴት ሊጀምሩ እንደሚችሉ አብራሩላቸው።
5 በምናደርጋቸው ክርስቲያናዊ ግንኙነቶች እርስ በርስ መበረታታችንን ችላ ማለት የለብንም። (ዕብ. 10:24, 25) በአገልግሎታቸው የቀዘቀዙ ቢኖሩ የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች ለእነርሱ እርዳታና ማበረታቻ ለመስጠት አንድ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ እነዚህን የቀዘቀዙ ሰዎች ለማበረታታት የሚያስፈልገው ነገር ወደ መስክ አገልግሎት አብረውን እንዲሄዱ ሞቅ ባለ መንፈስ መጋበዝ ብቻ ሊሆን ይችላል።
6 ሚያዝያ ከፍተኛ የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ የሚታይበት ወር እንዲሆን ለማድረግ የሁሉም ትብብር ያስፈልጋል። የመጽሐፍ ጥናት መሪው እያንዳንዱ የቡድኑ አባል በአገልግሎቱ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖረው በሚረዳበት ጊዜ በጋለ የአድናቆት ስሜት ቀዳሚ ሆኖ መምራቱ በዚህ ረገድ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ለአገልግሎት የሚረዱ ተጨማሪ ስብሰባዎች ሊዘጋጁ ይችሉ ይሆናል። በዕድሜ የገፉ ሰዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፤ ወጣቶችም ተግባራዊ በሆኑ መንገዶች እርዳታ ሊደረግላቸው ይችላል። በሚያዝያ ወር መላው ቤተሰብ በአገልግሎቱ እየተካፈለ መሆኑን ወላጆች ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ሁላችንም በዚህ የመከር ጊዜ ካለን ሁሉ ምርጡን ለይሖዋ ከሰጠን የእርሱን የተትረፈረፈ በረከት እናገኛለን።