ወላጆች—ልጆቻችሁን እንዲሰብኩ አሰልጥኗቸው
1 ጉባኤዎቻችን አምላክን ለማገልገል ልባዊ ፍላጎት ባላቸው ብዙ ልጆች ተባርከዋል። (መክ. 12:1) ይሖዋ እሱን በማወደስ ተካፋይ እንዲሆኑ ከጋበዛቸው ሰዎች መካከል እነርሱም ይገኙበታል። (መዝ. 148:12-14) ስለሆነም ወላጆች ለልጆቻቸው በየዕለቱ የሚሰጡት ማሰልጠኛ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ እምነታቸውን ለሌሎች እንዴት ማካፈል እንደሚችሉ ማስተማርን ሊያካትት ይገባዋል።—ዘዳ. 6:6, 7
2 ልጆችን ደረጃ በደረጃ አሰልጥኗቸው፦ ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው ከወላጆቻቸው ጋር ወደ አገልግሎት አብሮ መሄድን መሰልጠን ይገባቸዋል። ልጆቻችሁ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ወደ አገልግሎት ከመሄዳቸው በፊት አዘጋጁአቸው። በሩ ላይ ሲደርሱ ምን እንዲያደርጉ እንደምትፈልጉባቸው አስቀድማችሁ አሳውቋቸው። በጣም ትንንሽ የሆኑ ልጆች ትራክቶችንና የጥሪ ወረቀቶችን ሊያበረክቱና ሰዎችን ወደ መንግሥት አዳራሽ ሊጋብዙ ይችላሉ። በደንብ ማንበብ የሚችሉ ልጆች ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲያነቡ ሊጋበዙ ይችላሉ። አጭር አቀራረብ በመጠቀም መጽሔቶችን ሊያበረክቱ ይችላሉ። ልምድ እያገኙ ሲሄዱ በአቀራረባቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጠቀሙ አሰልጥኗቸው። ብዙ ወጣት አስፋፊዎች የራሳቸውን የመጽሔት ደንበኞች አፍርተዋል፤ ዘወትርም ተመላልሶ መጠየቅ ያደርጋሉ። አንድ ልጅ ከሌላ ልጅ ጋር ከሚያገለግል ይልቅ ከአዋቂ ጋር ቢያገለግል የተሻለ ነው። አዋቂው ለቤቱ ባለቤት ወጣቱ ልጅ ለአገልግሎት በመሰልጠን ላይ እንዳለ ሊነግረው ይችላል።
3 አንዲት ትንሽ ልጅ የመንግሥቱ አስፋፊ ለመሆን እንድትችል የሽማግሌዎችን እርዳታ ጠየቀች። ምንም እንኳ በወቅቱ የልጅቷ ዕድሜ አምስት ዓመት ብቻ ቢሆንና ማንበብ ባትችልም የመንግሥቱን መልእክት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማቅረብ ችላ ነበር። የጥቅሶቹን ቦታ በቃሏ ስላጠናች የሚገኙበትን ቦታ ትገልጥና የቤቱን ባለቤት እንዲያነብ ከጠየቀችው በኋላ ታብራራለታለች።
4 ልጆች በአገልግሎት አዘውትረው ለመካፈል የሚያስችላቸውን ጥሩ ፕሮግራም የማውጣትን ጥቅም እንዲማሩ ወላጆች ምሳሌ ሊሆኗቸው ይገባል። ወላጆች ለአገልግሎት ቋሚ የሆነ ሳምንታዊ ፕሮግራም ሊያወጡና በፕሮግራማቸውም ሊጸኑ ይገባቸዋል። ይህ ደግሞ የትኛው የሳምንቱ ክፍል ሁልጊዜ ለአገልግሎት የተመደበ መሆኑን ልጆች እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።
5 ልጆች ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ ለአገልግሎት ፍቅር እንዲኖራቸውና በአገልግሎት እንዲደሰቱ በሚሰለጥኑበት ጊዜ ወደፊት ሌሎች መብቶች ላይ ለመድረስ ምናልባትም አቅኚ ለመሆን ይነሳሳሉ። (1 ቆሮ. 15:58) ሁላችንም በመካከላችን የሚገኙትን ልጆች የይሖዋ አወዳሾች በመሆን ጥሩ እድገት እንዲያደርጉ ልናበረታታቸው ይገባል።