የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚያስገኘው ደስታ
1 ወጣት ከሆንክ የወደፊት ሕይወትህ እንደሚያሳስብህ የታወቀ ነው። ምሳሌ 21:5 [አ.መ.ት ] “የትጉህ ሰው እቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” በማለት ይነግረናል። በሕይወትህ ውስጥ ስለምታወጣቸው ግቦች በቁም ነገር ማሰብህ ይጠቅምሃል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ዕቅድ ስታወጣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ከግምት ውስጥ አስገባ። ለምን?
2 ወጣት ሳሉ በአቅኚነት ያገለገሉ አንዳንዶች ምን ትዝታ እንዳላቸው ጠይቃቸው፤ ሁሉም “በሕይወቴ ውስጥ ፈጽሞ የማልረሳው ግሩም ጊዜ ነው!” የሚል ተመሳሳይ መልስ ይሰጡሃል። ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚያስገኘውን ደስታ የቀመሰ አንድ ወንድም በኋለኞቹ ዓመታት ላይ እንዲህ ብሏል:- “በወጣትነት ያሳለፉትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብሎ መመልከትና ‘በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ’ የሚለውን የጥበብ ምክር ተግባራዊ አድርጌዋለሁ ማለት መቻል ጥልቅ እርካታ ያመጣል።” (መክ. 12:1) በወጣትነታችሁ እንዲህ ዓይነት ደስታ የምታገኙበትን መንገድ ለመቀየስ ከእናንተም ሆነ ከወላጆቻችሁ ከወዲሁ የታሰበበት እቅድ ማውጣት ይፈለግባችኋል።
3 ወላጆች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን አበረታቱ፦ ይሖዋ አሳቢ አባት እንደመሆኑ መጠን በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለባችሁ ለይቶ ይነግራችኋል። (ኢሳ. 30:21) ይህን ዓይነት ፍቅራዊ አመራር በመስጠት በክርስቲያን ወላጅነታችሁ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ልጆቻችሁ በየትኛው መንገድ ቢሄዱ እንደሚበጃቸው ራሳቸው እንዲመርጡ ከመተው ይልቅ የይሖዋን በረከት ማግኘት በሚያስችላቸው ጎዳና እንዲሄዱ በጥበብ አሰልጥኗቸው። ከዚያም እየጎለመሱ ሲሄዱ ከእናንተ ያገኙት ሥልጠና “መልካሙንና ክፉውን ለመለየት” ይረዳቸዋል። (ዕብ. 5:14) አዋቂዎች በራሳቸው የማስተዋል ችሎታ ሊተማመኑ እንደማይችሉ ካሳለፉት የሕይወት ተሞክሮ ያውቃሉ፤ መንገዳቸውን ለማቅናት በይሖዋ ላይ መታመን አለባቸው። (ምሳሌ 3:5, 6) ብዙም የሕይወት ተሞክሮ ለሌላቸው ለወጣቶች ደግሞ ይህ ይበልጥ አስፈላጊ ነው።
4 ወላጆች ልጆቻችሁ ወደ አሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ሲቃረቡ ወይም ከዚያ ቀደም ብሎ የወደፊት ግባቸውን በተመለከተ ተጨባጭ እውነታውን መሠረት አድርጋችሁ አወያዩአቸው። የትምህርት ቤት መማክርት፣ መምህራንና የክፍል ጓደኞቻቸው ዓለማዊና ቁሳዊ ግቦችን ወደ ማሳደድ እንዲያዘነብሉ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ይሞክራሉ። ልጆቻችሁ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ችላ ሳይሉ በቁሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የሚያስችላቸውን የተግባር ሥልጠና የሚያገኙበትን የትምህርት ዓይነት እንዲመርጡ እርዷቸው። (1 ጢሞ. 6:6-11) አብዛኛውን ጊዜ አንድ ሰው የዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ሲጀምር ለሕይወት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በተጨማሪ የሙያ ትምህርት እና/ወይም ከትምህርት ጎን ለጎን በሥራ ቦታ የሚሰጥ ሥልጠና በቂ ሊሆን ይችላል።
5 ወጣቶች የነጠላነትን ስጦታ እንዲከታተሉ አበረታቷቸው። ከጊዜ በኋላ ለማግባት ቢወስኑ እንኳ በትዳር ውስጥ ያሉትን ከበድ ያሉ ኃላፊነቶች ለመሸከም ይበልጥ ዝግጁ ይሆናሉ። (በጥቅምት 2001 የመንግሥት አገልግሎታችን “ራስህን በፈቃደኝነት ልታቀርብ ትችላለህ?” የሚለውን ርዕስ አንቀጽ 8ን ተመልከት።) ወላጆች ስለ አቅኚነት፣ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ስለ ማገልገልና ስለ ቤቴል አገልግሎት አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመናገር በወጣቶች ውስጥ ገና በልጅነታቸው ይሖዋን በሚያስደስት፣ ሌሎችን በሚጠቅምና ለእነርሱም ደስታ በሚያስገኝላቸው መንገድ ሕይወታቸውን የመጠቀም ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርጉ።
6 ወጣቶች በሕይወታችሁ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን አስቀድሙ፦ ወጣቶች አቅኚነት ምን ይመስል ይሆን እያላችሁ ማሰብ አያስፈልጋችሁም። በትምህርት ወቅትም ሆነ ትምህርት ቤት ሲዘጋ በተቻለ መጠን ባላችሁ ትርፍ ጊዜ በረዳት አቅኚነት በማገልገል ልትሞክሩት ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ የአቅኚነት አገልግሎት ምን ያህል እርካታ የሚሰጥ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ! ካሁን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት በረዳት አቅኚነት ለማገልገል እቅድ ማውጣት ትችላላችሁ?
7 በቅርቡ የተጠመቅህ ወጣት ወንድም ከሆንክ ለጉባኤ አገልጋይነት ብቁ ለመሆን ስለመጣጣር በቁም ነገር አስብበት። (1 ጢሞ. 3:8-10, 12) እንዲሁም በቤቴል ስለ ማገልገል ወይም በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ስለ መካፈል ልታስብበት ትችላለህ። በአቅኚነት አገልግሎት የምታሳልፈው ሕይወት በፕሮግራም መመራትን፣ በግል በሚገባ መደራጀትን፣ ከሌሎች ጋር ተስማምቶ መኖርንና የኃላፊነት ስሜት ማዳበርን የመሳሰሉ ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስተምርሃል። እነዚህ ሁሉ ከጊዜ በኋላ ለምታገኛቸው የላቁ የአገልግሎት መብቶች ያዘጋጁሃል።
8 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስኬታማ ለመሆን ቁልፉ ከቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የታታሪነት መንፈስ መያዝ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ዓይነቱን ዝንባሌ ካበረታታ በኋላ በውጤቱም የሚገኙትን በረከቶች ጠቅሷል። “ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፣ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና።” (ቆላ. 3:23, 24) የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በሚያስገኘው የተትረፈረፈ ደስታ ይሖዋ እንዲባርካችሁ ምኞታችን ነው!