“ጥሩ አቅኚ ሊወጣህ ይችላል!”
1. አንዲት እህት ስለ አቅኚነት ያላትን ስሜት የገለጸችው ምን በማለት ነው?
1 “እንደዚህ ያለ እርካታ ወይም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት የሚያስገኝልኝ ሌላ ሥራ ላገኝ አልችልም።” ይህን የተናገረችው ካቲ ፓልም የተባለች እህት ናት። ይህች እህት የራስዋን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ በደቡብ አሜሪካ በምትገኘው በቺሊ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ ድረስ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በአቅኚነት አገልግላለች። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ወንድሞች የሚያገኙትን አርኪ ሕይወት በማሰብ ምናልባት አንድ ሰው አንተንም “ጥሩ አቅኚ ሊወጣህ ይችላል!” ብሎህ ይሆናል።
2. በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ከፍተኛ እርካታ የሚያስገኘው እንዴት እንደሆነ አስረዳ።
2 እርካታ የሚያስገኝ የሕይወት ጎዳና፦ አርዓያችን የሆነው ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ መፈጸም እውነተኛ እርካታ አስገኝቶለት ነበር። (ዮሐ. 4:34) በመሆኑም ኢየሱስ ለተከታዮቹ እውነተኛ እርካታ የሚገኘው ከይሖዋ አምልኮ ጋር በተያያዘ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመካፈል መሆኑን ከልብ በመነጨ ስሜት አስተምሯል። የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝልን ሥራ ስንጠመድ ደስታ እናገኛለን። በተጨማሪም ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን ይበልጥ በሰጠን መጠን ደስታችን የዚያኑ ያህል ይጨምራል።—ሥራ 20:31, 35
3. በአገልግሎት ብዙ ሰዓት ካሳለፍን ምን አስደሳች በረከት ማግኘት እንችላለን?
3 በአገልግሎት ብዙ ሰዓት ባሳለፍን መጠን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማስጀመርና በመምራት የሚገኘውን ደስታ የማጣጣም ሰፊ አጋጣሚ ይኖረናል። በርካታ ሰዎች ግድ የለሽ ቢመስሉም እንኳ በአገልግሎት የበለጠ ተሞክሮና ችሎታ እያዳበርን ስንሄድ ክልላችንን መጀመሪያ ካሰብነው በተለየ ውጤታማ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። አቅኚዎች ለአንድ ዓመት በአቅኚነት ካገለገሉ በኋላ በአቅኚዎች የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ተካፍለው የቀሰሙትን እውቀት በሙሉ ሥራ ላይ የማዋል አጋጣሚ አላቸው። (2 ጢሞ. 2:15) በአገልግሎት ከጸናን ከጊዜ በኋላ ፍሬ የሚያፈራውን የእውነትን ዘር በሰዎች ልብ ውስጥ በጥሩ ሁኔታ መትከል እንችላለን።—መክ. 11:6
4. ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመጨረስ የተቃረቡ ወጣቶች ምን ነገር ማሰብ አለባቸው?
4 ወጣቶች፦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችሁን ከጨረሳችሁ በኋላ ወደፊት ስለምትመሩት ሕይወት በቁም ነገር አስባችኋል? እስከ አሁን ድረስ አብዛኛውን ጊዜያችሁን የያዘው ትምህርታችሁ ነው። ትምህርት ስትጨርሱ ጊዜያችሁን በምን ለማሳለፍ አስባችኋል? በሰብዓዊ ሥራ ከመጠመድ ይልቅ የዘወትር አቅኚ መሆን ትችሉ እንደሆነ ሁኔታውን በጸሎት ለምን አታስቡበትም? የተለያየ አስተዳደግ ላላቸው ሰዎች በመመሥከር፣ የሚያጋጥሟችሁን መሰናክሎች በመቋቋም፣ ራሳችሁን በመገሠጽና ሌሎችን በማስተማር የምታዳብሯቸው በርካታ ችሎታዎች በቀሪው የሕይወት ዘመናችሁ ይጠቅሟችኋል።
5. ወላጆችም ሆኑ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች ሌሎች አቅኚ እንዲሆኑ ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ እንዲገቡ የበኩላችሁን እያደረጋችሁ ነው? ንግግራችሁም ሆነ ጥሩ አርዓያ መሆናችሁ ልጆቻችሁ በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን እንዲያስቀድሙ በመርዳት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። (ማቴ. 6:33) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አቅኚነትን የጀመረው ሬይ “እናቴ አቅኚነት ከምንም ነገር በላይ እርካታ እንደሚያስገኝ ሁልጊዜ ይሰማት ነበር” ብሏል። በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ሌሎች አቅኚዎች እንዲሆኑ በንግግራቸውና በድርጊታቸው ማበረታታት ይችላሉ። በስፔን የሚኖረው ሆሴ የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤያችን የሚገኙ ወንድሞች አቅኚነትን ለወጣቶች ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ስለ አቅኚነት አገልግሎት የሚሰጡት ሐሳብም ሆነ ያላቸው አድናቆት እንዲሁም የሚያደርጉት ተግባራዊ እርዳታ አቅኚነት እንድጀምር ቀላል አድርጎልኛል።”
6. በአሁኑ ጊዜ አቅኚ የመሆን ፍላጎት ባይኖረን ምን ማድረግ እንችላለን?
6 እንቅፋቶችን ማሸነፍ፦ ይሁንና አቅኚ የመሆን ፍላጎት ባይኖርህስ? መጀመሪያ ላይ እንዲህ ያለ ስሜት ከተሰማህ ለይሖዋ ‘አቅኚነት ለእኔ የሚሆን ሥራ ይሁን አይሁን አላውቅም፤ ግን አንተን የሚያስደስትህን ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ’ በማለት የሚሰማህን ነገር በጸሎት መንገር ትችላለህ። (መዝ. 62:8፤ ምሳሌ 23:26) ከዚያም በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ሞክር። በርካታ የዘወትር አቅኚዎች በመጀመሪያ ረዳት አቅኚ በመሆን አቅኚነትን ‘የቀመሱ’ ሲሆን ያገኙት ደስታ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገቡ አነሳስቷቸዋል።—መዝ. 34:8
7. በወር የሚጠበቅብንን 70 ሰዓት ማሟላት መቻላችንን በተመለከተ ያለንን ጥርጣሬ ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?
7 በወር የሚጠበቅባችሁን 70 ሰዓት ማሟላት እንደምትችሉ እርግጠኛ ባትሆኑስ? ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ያላቸውን አቅኚዎች ለምን አታማክሩም? (ምሳሌ 15:22) ከዚያም ሰዓታችሁን ለማሟላት የሚያስችሏችሁን በርካታ አማራጭ ፕሮግራሞችን አውጡ። እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ለአገልግሎት የሚሆን ጊዜ መግዛት ስትችሉ የሰዓት ግባችሁን ማሟላት ካሰባችሁት በላይ ቀላል ሆኖ ታገኙታላችሁ።—ኤፌ. 5:15, 16
8. በየጊዜው ሁኔታችንን መለስ ብለን መገምገም ያለብን ለምንድን ነው?
8 ሁኔታችሁን እንደገና ገምግሙ፦ ያለንበት ሁኔታ ብዙ ጊዜ ይለዋወጣል። በመሆኑም ያላችሁበትን ሁኔታ በየጊዜው መለስ ብላችሁ መገምገማችሁ ጥሩ ነው። ለምሳሌ፣ ከሰብዓዊ ሥራችሁ ጡረታ የምትወጡበት ጊዜ ተቃርቧል? ቀደም ብሎ ጡረታ የወጣ ራንዲ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ይህን ውሳኔ ማድረጌ ከባለቤቴ ጋር የዘወትር አቅኚ እንድሆን አስችሎኛል፤ ይህ ደግሞ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል ጥሩ አጋጣሚ ከፍቶልናል። እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በማድረጌ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን በረከቶች አግኝቻለሁ፤ ከሁሉም የሚበልጠው በረከት ግን ጥሩ ሕሊና ማግኘት ነው።”
9. ባልና ሚስቶች ስለ ምን ነገር ማሰብ አለባቸው?
9 አንዳንድ ባልና ሚስቶች ሁኔታቸውን ከገመገሙ በኋላ ሁለቱም የሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራ መሥራት እንደሌለባቸው ተገንዝበዋል። እውነት ነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ አኗኗርን ቀላል ማድረግ ሊጠይቅ ይችላል፤ ሆኖም እንዲህ ያለ መሥዋዕትነት መክፈል ከሚያስገኘው በረከት አንጻር የሚያስቆጭ አይደለም። አገልግሎቷን ለማስፋት ስትል በቅርብ ጊዜ የሙሉ ቀን ሰብዓዊ ሥራዋን የለቀቀች የትዳር ጓደኛ ያለችው ጆን “ባለቤቴ የቀኑን ክፍለ ጊዜ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንደምታሳልፍ ማወቅን የመሰለ የሚያስደስተኝ ነገር የለም” ብሏል።
10. ክርስቲያኖች አቅኚ ለመሆን እንዲያስቡ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?
10 የፍቅርና የእምነት መግለጫ፦ ይሖዋ፣ ማናችንም ብንሆን ልንሠራው ከምንችለው ማንኛውም ሥራ የሚበልጠውን የስብከቱን ሥራ ሰጥቶናል። ይህ አሮጌ ሥርዓት በቅርቡ የሚጠፋ ሲሆን ከዚህ ጥፋት የሚድኑት የይሖዋን ስም የሚጠሩ ብቻ ናቸው። (ሮም 10:13) ለይሖዋ ያለን ከልብ የመነጨ ፍቅርና ላደረገልን ነገሮች ያለን አድናቆት፣ ልጁ በቅንዓት እንድንሰብክ የሰጠንን ተልዕኮ እንድንፈጽም ያነሳሳናል። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ዮሐ. 5:3) በተጨማሪም በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እንደምንኖር ያለን እምነት በዓለም ሙሉ በሙሉ ከመጠቀም ይልቅ በቀረው ጊዜ በአገልግሎቱ የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል።—1 ቆሮ. 7:29-31
11. አንድ ሰው ጥሩ አቅኚ ሊወጣን እንደሚችል ቢነግረን ሐሳቡን እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
11 የዘወትር አቅኚነት ረጅም ሰዓት በአገልግሎት የማሳለፍ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የምናሳይበት ነው። ስለሆነም አንድ ሰው ጥሩ አቅኚ ሊወጣህ እንደሚችል ሲነግርህ መልካም ነገር እየተመኘልህ እንደሆነ ሊሰማህ ይገባል። በተጨማሪም በዚህ እርካታ በሚያስገኝ የአገልግሎት ዘርፍ ከሚካፈሉ ሰዎች ጎን ለመሰለፍ ጉዳዩን በጸሎት አስብበት።
[ከገጽ 4 የተቀነጨበ ሐሳብ]
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ እንዲገቡ የበኩላችሁን እያደረጋችሁ ነው?
[ከገጽ 5 የተቀነጨበ ሐሳብ]
ይሖዋ፣ ማናችንም ብንሆን ልንሠራው ከምንችለው ማንኛውም ሥራ የሚበልጠውን የስብከቱን ሥራ ሰጥቶናል።