ለመስበክ ጊዜው አሁን ነው!
1. ለመስበክ ጊዜው አሁን ነው የምንለው ለምንድን ነው?
1 “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት።” ይህ መልእክት፣ በመላእክት መሪነት “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ” እየታወጀ ነው። መታወጅ ያስፈለገው ለምንድን ነው? “ምክንያቱም [የአምላክ] የፍርዱ ሰዓት ደርሶአል።” የምንኖረው ‘የፍርዱ ሰዓት’ በደረሰበት ወቅት ላይ ሲሆን ይህ ፍርድ ደግሞ በዚህ ሥርዓት ጥፋት ይደመደማል። ሰዎች “ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው [መስገዳቸው]” በጣም አስፈላጊ ነው። በዛሬው ጊዜ የሚከናወን ማንኛውም ሥራ ቢሆን “የዘላለም ወንጌል” ከማወጁ ሥራ ጋር በአስፈላጊነቱም ሆነ በአጣዳፊነቱ ሊወዳደር አይችልም። በእርግጥም፣ ለመስበክ ጊዜው አሁን ነው!—ራእይ 14:6, 7
2. የይሖዋ አገልጋዮች የጊዜውን አጣዳፊነት እንደተገነዘቡ ያሳዩት እንዴት ነው?
2 የይሖዋ አገልጋዮች ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የአምላክን መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ወደ 12 ቢሊዮን የሚጠጋ ሰዓት አሳልፈዋል። ብዙዎች ለመንፈሳዊው የመከር ሥራ የበለጠ ጊዜ ለማግኘት ሲሉ በአኗኗራቸው ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን አድርገዋል። (ማቴ. 9:37, 38) ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በየወሩ በአማካይ ከ850,000 በላይ የሚሆኑ አስፋፊዎች አቅኚ ሆነው አገልግለዋል። ይህም ሲባል የዘወትር አቅኚዎች በስብከቱ ሥራ በየወሩ በአማካይ 70 ሰዓት ማሳለፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ረዳት አቅኚዎች ደግሞ በወር 50 ሰዓት ማገልገል አለባቸው።
3. አስፋፊዎች አቅኚ ለመሆን ብዙውን ጊዜ ምን ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?
3 አቅኚ ለመሆን ምን ያስፈልጋል? አቅኚዎች “ዘመኑ አጭር” መሆኑን በመገንዘብ ኑሯቸውን ቀላል ለማድረግ ይጥራሉ። (1 ቆሮ. 7:29, 31) ሰብዓዊ ሥራ በመሥራት ብዙ ጊዜ ላለማጥፋት ብለው ወጪዎቻቸውን ለመቀነስ የሚያስችሏቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ። ለምሳሌ አንዳንዶች አነስ ወዳለ ቤት ተዛውረዋል። ሌሎች ደግሞ የማያስፈልጉ ዕቃዎችን አስወግደዋል። (ማቴ. 6:19-21) ብዙውን ጊዜ የግል ጉዳዮቻቸውን ለመተው ይገደዳሉ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ለአገልግሎት የበለጠ ጊዜና ትኩረት ለመስጠት ሲሉ ነው። (ኤፌ. 5:15, 16) በርካታ አስፋፊዎች ያልተቋረጠ ጥረት በማድረግ፣ የራሳቸውን ጥቅም በመሠዋት እንዲሁም በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ በመታመን አቅኚ ሆነው ለማገልገል የሚያስችላቸውን ፕሮግራም ማውጣት ችለዋል።
4. የአቅኚነት ግብ ላይ ለመድረስ ምን ተግባራዊ የሆኑ እርምጃዎች ሊረዱህ ይችላሉ?
4 አቅኚ መሆን ትችላለህ? በአገልግሎታቸው የተዋጣላቸውን አቅኚዎች እንዴት እንደተሳካላቸው ለምን ቀረብ ብለህ አትጠይቃቸውም? የደስታቸው ተካፋይ ለመሆን አብረሃቸው በመስክ አገልግሎት ተካፈል። በጽሑፎቻችን ላይ ስለ አቅኚነት የሚናገሩትን ርዕሶች አንብብ። ለአቅኚነት መሸጋገሪያ ድልድይ ሊሆኑህ የሚችሉ ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አውጣ። አሁን አቅኚ ሆነህ እንዳታገለግል እንቅፋት የሆኑብህ ችግሮች ካሉ መቋቋም እንድትችል እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው።—ምሳሌ 16:3
5. አቅኚነት በአገልግሎት ችሎታችንን እንድናሻሽል የሚረዳን እንዴት ነው?
5 የምናገኘው በረከትና ደስታ:- አቅኚነት በአምላክ ቃል የመጠቀም ችሎታችንን ለማሻሻል ይረዳናል፤ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ደስታ ያስገኝልናል። አንዲት ወጣት አቅኚ እንዲህ ብላለች:- “የአምላክን የእውነት ቃል በትክክል መጠቀም መቻል ትልቅ በረከት ነው። አቅኚ ከሆናችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጠቀም ሰፊ አጋጣሚ ይኖራችኋል። ከቤት ወደ ቤት ሳገለግል ለእያንዳንዱ ሰው የሚስማማ ጥቅስ ወዲያውኑ ትዝ ይለኛል።”—2 ጢሞ. 2:15
6. አቅኚነት ምን ዓይነት ሥልጠና እንድናገኝ ይረዳናል?
6 አቅኚነት ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚሆን ብዙ ጠቃሚ ነገሮችንም ያስተምረናል። ወጣቶች ጊዜያቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙ፣ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ጠንቃቆች እንዲሆኑና ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ሊረዳቸው ይችላል። ብዙዎች አቅኚ ሆነው ማገልገላቸው በሕይወታቸው ውስጥ ይበልጥ መንፈሳዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። (ኤፌ. 4:13) በተጨማሪም አቅኚዎች የይሖዋን እጅና በረከት በሕይወታቸው የመመልከት ልዩ መብት አግኝተዋል።—ሥራ 11:21፤ ፊልጵ. 4:11-13
7. አቅኚነት ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?
7 አቅኚ መሆን ከሚያስገኘው በረከት ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር እንድንቀራረብ የሚረዳን መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በፈተናዎች ጊዜ እንድንጸና ያስችለናል። አንዲት እህት በአስቸጋሪ ጊዜያት እንዴት እንደጸናች ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “አቅኚ በነበርኩበት ጊዜ ከይሖዋ ጋር የመሠረትኩት የጠበቀ ዝምድና በችግር ጊዜ እንድጸና ረድቶኛል። በወጣትነት ዕድሜዬ ይሖዋን በሙሉ ጊዜዬ ለማገልገል በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ራሴን ማቅረብ እችላለሁ ብዬ ፈጽሞ ባላሰብኩባቸው መንገዶች ለማገልገል አስችሎኛል።” (ሥራ 20:35) እኛም በተመሳሳይ እጅግ አስፈላጊ በሆነው የስብከት ሥራ አቅማችን የፈቀደውን ያህል በመሥራት የተትረፈረፈ በረከት እናግኝ።—ምሳሌ 10:22