በተከፈተልህ “ታላቅ የሥራ በር” መግባት ትችላለህ?
1. ለሁላችንም የተከፈተልን “ታላቅ የሥራ በር” ምንድን ነው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “ታላቅ የሥራ በር” በተከፈተለት ወቅት ብዙዎች ይቃወሙት የነበረ ቢሆንም አጋጣሚውን የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማስፋፋት በሚገባ ተጠቅሞበታል። (1 ቆሮ. 16:9) በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ 642,000 የሚያህሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የዘወትር አቅኚዎች በመሆን በተከፈተላቸው ታላቅ የሥራ በር ገብተዋል።
2. ያለንበትን ሁኔታ በየጊዜው መገምገማችን ጥሩ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ሁኔታዎች ሊለወጡ ይችላሉ:- ምንም እንኳ አሁን ያለንበት ሁኔታ የምናደርገውን እንቅስቃሴ ሊገድብብን ቢችልም ይህ ሁኔታ ከጊዜ በኋላ ሊቀየር ይችላል። በመሆኑም ሁኔታችንን በየጊዜው መገምገማችን ጥሩ ይሆናል። ሆኖም ሁኔታው ሙሉ በሙሉ እስኪስተካከል ድረስ መጠበቅ አይኖርብንም። (መክ. 11:4) ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትህን በቅርቡ የምታጠናቅቅ ወጣት ነህ? ልጆችህ በቅርቡ ትምህርት ቤት ይገባሉ? ከመደበኛ ሥራህ በጡረታ የምትገለልበት ጊዜ ቀርቧል? እንዲህ ዓይነት ለውጦች ነጻ ጊዜ እንድታገኝና ወደ ዘወትር አቅኚነት አገልግሎት እንድትገባ ያስችሉሃል። ቀደም ሲል የጤና ችግር የነበረባቸው አንዲት አረጋዊ እህት በ89 ዓመታቸው የዘወትር አቅኚ ለመሆን ወሰኑ። ለምን? ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ሆስፒታል ስላልገቡ የጤንነታቸው ሁኔታ አቅኚ ለመሆን እንደሚያስችላቸው ስለተሰማቸው ነው።
3. አንዳንዶች የዘወትር አቅኚ ለመሆን ሲሉ ማስተካከያዎችን ያደረጉት እንዴት ነው?
3 የሐዋርያው ጳውሎስን ሁኔታ ብንመለከት መጀመሪያ አቅዶ የነበረው በቆሮንቶስ የነበሩ ወንድሞችን ለመጎብኘት ነበር። ይሁንና ምሥራቹን ለመስበክ ሲል በእቅዱ ላይ ማስተካከያ አድርጓል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ የዘወትር አቅኚዎችም አቅኚ ለመሆን ሲሉ ጥቂት የማይባሉ ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈልጓቸዋል። አንዳንዶች ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ያህል ለተወሰነ ሰዓት ብቻ በመሥራት ኑሯቸውን ቀላል አድርገዋል። በተሰማሩበት የአገልግሎት መብት ደስታ አግኝተዋል። (1 ጢሞ. 6:6-8) አንዳንድ ባልና ሚስቶች ደግሞ በአንድ ሰው ገቢ ብቻ ለመኖር የሚያስችሉ ለውጦችን በማድረግ ሚስት አቅኚ መሆን የምትችልበትን መንገድ አመቻችተዋል።
4. ከአቅኚዎች የሚጠበቀውን ሰዓት ማሟላት እንደማንችል ከተሰማን ምን ማድረግ እንችላለን?
4 ከአቅኚዎች የሚጠበቀውን የሰዓት ግብ ማሟላት አልችልም በሚል ፍርሃት ብቻ አቅኚ የመሆኑን ሐሳብ ከአእምሮህ ለማውጣት አትቸኩል። የሚያስፈልገው በቀን ከሁለት ሰዓት ትንሽ በለጥ ለሚል ጊዜ ማገልገል ብቻ ነው። ሰዓቱን ማሟላት መቻል አለመቻልህን እርግጠኛ ካልሆንክ 70 ሰዓት የማገልገል ግብ ይዘህ ለአንድ ወይም ለሁለት ወር ረዳት አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ሞክር። እንዲህ ማድረግህ በአቅኚነት የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም ያስችልሃል። (መዝ. 34:8) በአሁኑ ጊዜ በአቅኚነት እያገለገሉ ያሉትን አማክራቸው። ምናልባትም ከአንተ ጋር የሚመሳሰሉ ችግሮችን አሸንፈው ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 15:22) ይሖዋ አገልግሎትህን ለማስፋት የምታደርጋቸውን ጥረቶች እንዲባርክልህ ጠይቀው።—1 ዮሐ. 5:14
5. የዘወትር አቅኚነት ጠቃሚ ሥራ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
5 ጠቃሚ ሥራ:- የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል በርካታ በረከቶች ያስገኛል። በመስጠት የሚገኘውን ከፍተኛ ደስታ እንድታጣጥም ያስችልሃል። (ሥራ 20:35) አቅኚነት የአምላክን የእውነት ቃል በትክክል የማስረዳት ችሎታህን ያዳብርልሃል። (2 ጢሞ. 2:15) የይሖዋን እጅ የማየት አጋጣሚዎችህን ያሰፋልሃል። (ሥራ 11:21፤ ፊልጵ. 4:11-13) በተጨማሪም አቅኚነት ጽናትን የመሳሰሉ ባሕርያትን እንድታዳብር ከመርዳቱም ባሻገር ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ያስችልሃል። (ያዕ. 4:8) ታዲያ በዚህ ታላቅ የሥራ በር በመግባት የዘወትር አቅኚ መሆን ትችል ይሆን?