በአቅኚነት አገልግሎት ተጨማሪ ወንድሞች ያስፈልጋሉ
1 ጳውሎስ “የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” በማለት አበረታቷል። (1 ቆሮ. 15:58) ይህም ለብዙዎች በአቅኚነት አገልግሎት መጠመድን የሚጠይቅ ነው። ባለፈው መስከረም ከ90 የሚበልጡ ተጨማሪ አቅኚዎች ተገኝተዋል!
2 በአሁኑ ጊዜ በእዚህ አገር አቅኚ ሆነው ከሚያገለግሉት መካከል ብዙዎቹ እህቶች ናቸው። (መዝ. 68:11 አዓት) ተጨማሪ ወንድሞች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቢካፈሉ ለጉባኤ ምን ያህል ደስታ ያመጣ ይሆን! (መዝ. 110:3 አዓት) ብዙ ወንድሞች ከባድ የሆነ ሥጋዊ ሥራና የቤተሰብ ኃላፊነት እንዳላቸው ግልጽ ነው። ሌሎች ደግሞ የጉባኤውን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ጠንክረው ይሠራሉ። ለመንግሥቱ ሲሉ የሚደክሙትን እንደነዚህ ያሉትን ወንዶች እናደንቃቸዋለን።— 1 ጢሞ. 4:10
3 ቢሆንም ግን ከእናንተ መካከል ተጨማሪ ወንድሞች በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል ይችሉ ይሆን? ሚስትህ አቅኚ ከሆነች አንተም አብረሃት አቅኚ መሆን ትችላለህ? ጡረታ የወጣህ ከሆንክ ጊዜህን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከማዋል የበለጠ የሚያስደስት ነገር የለም ቢባል አትስማማም? በቅርብ ጊዜ ትምህርት የጨረስክ ከሆንክ ለተጨማሪ መብቶች መሸጋገሪያ ድልድይ እንዲሆንልህ አቅኚ ለመሆን በጥንቃቄና በጸሎት አስበህበታል?— ኤፌ. 5:15-17
4 አንድ ወንድም ጥሩ ገቢ የሚያስገኝለትን የንግድ ሥራውን ከሸጠ በኋላ አቅኚ መሆን አንዲችል የትርፍ ሰዓት ሥራ ያዘ። ቀዳሚ ሆኖ በማገልገሉ ምክንያት ከአራቱ ልጆቹ መካከል ሦስቱ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ አቅኚ ሆኑ። አራተኛውም አብሯቸው አቅኚ የሚሆንበትን ጊዜ በጉጉት እየተጣባበቀ ነበር። ይህ ወንድምና ቤተሰቡ ብዙ በረከቶች አግኝተዋል።
5 ትልቅ በር ተከፍቷል፦ የአቅኚነት አገልግሎት “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” ሊከፍት ይችላል። (1 ቆሮ. 16:9) አቅኚ የሆኑ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ብዙ ሥራዎችን ሊያከናውኑ ይችላሉ። ቅንዓት የሞላበት አገልግሎት መንፈሳዊ ጉልምስናቸውና ቲኦክራሲያዊ እድገታቸው ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ ያደርጋል። አቅኚ መሆን ለተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች በር ሊከፍት ይችላል። ልዩ አቅኚ ለመሆን ወይም ለቤቴል አገልግሎት መሸጋገሪያ ድልድይ ሊሆን ይችላል። ለአንድ ዓመት በአቅኚነት ከተሳተፉ በኋላ በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት የመካፈል በረከት አለ። ነጠላ የሆኑ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል ሊጣጣሩ ይችላሉ። አዎን፣ አቅኚ ሆኖ ማገልገል በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ባሉት በእነዚህ ታላላቅ መብቶች ለመካፈል በር ይከፍታል።
6 በዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ለመካፈል ሁኔታቸውን ያስተካከሉ ወንድሞች ብዙ መስጠት የሚያስገኘውን ታላቅ ደስታ ሊቀምሱ ይችላሉ።— ሥራ 20:35