የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 23 ገጽ 157-ገጽ 159 አን. 3
  • የትምህርቱን ጥቅም ግልጽ ማድረግ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የትምህርቱን ጥቅም ግልጽ ማድረግ
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አዲስ ነገር የሚያሳውቅ፤ ግልጽ፣ የሚጨበጥ
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ግንዛቤ የሚያሰፋ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • በጉጉት ለማዳመጥ የሚጋብዝ መግቢያ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ትምህርቱን ለመስክ አገልግሎት እንደሚስማማ አድርጎ ማቅረብ
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 23 ገጽ 157-ገጽ 159 አን. 3

ጥናት 23

የትምህርቱን ጥቅም ግልጽ ማድረግ

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

አድማጮችህ የያዝከው መልእክት እነርሱን እንዴት እንደሚመለከት ወይም ቢሠሩበት እንዴት እንደሚጠቀሙ እንዲያስተውሉ እርዳቸው።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የምትናገረው ነገር ለእነርሱ ምን ጥቅም እንዳለው ካልገባቸው ፍላጎት የለኝም ሊሉ ወይም ደግሞ አንተን መስማት ትተው በሐሳብ ሊባዝኑ ይችላሉ።

ከአንድ ግለሰብ ጋር ስትወያይም ይሁን ንግግር ስትሰጥ አንተ በትምህርቱ ስለተማረክህ ብቻ አድማጮችም ተመሳሳይ ስሜት ያድርባቸዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። የያዝከው መልእክት በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ጥቅሙን ለአድማጮችህ ግልጽ ካላደረግህላቸው ብዙም ሳይቆይ አእምሮአቸው መባዘን ሊጀምር ይችላል።

ይህ አባባል በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ላሉ አድማጮችም ይሠራል። አዲስ ምሳሌ ስትጠቀም ወይም ከዚያ ቀደም ያልሰሙትን ተሞክሮ ስትናገር በጉጉት ያዳምጡህ ይሆናል። ስለሚያውቋቸው ነገሮች መናገር ስትጀምር ግን በተለይ ከምሳሌዎቹና ከተሞክሮዎቹ ጋር እያዛመድህ ካልሄድክ ሐሳባቸው እንደገና ሊባዝን ይችላል። እየተናገርህ ያለኸው ነገር እነርሱን የሚጠቅማቸው ለምንና እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ መርዳት ይኖርብሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ነገር ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ በጥበብ እንድናስብ ያበረታታናል። (ምሳሌ 3:​21) ሕዝቡን ‘ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ’ ይሖዋ መጥምቁ ዮሐንስን ተጠቅሞበታል። (ሉቃስ 1:17) ይህ ለይሖዋ ከሚኖረን ጤናማ ፍርሃት የሚመነጭ ጥበብ ነው። (መዝ. 111:​10) የዚህን ጥበብ አስፈላጊነት የሚገነዘቡ ሰዎች ዛሬ ሕይወታቸውን በተሳካ መንገድ ለመምራት ከመቻላቸውም በላይ መጪውን እውነተኛ ሕይወት ማለትም የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይችላሉ።​—⁠1 ጢሞ. 4:​8፤ 6:​19

አድማጮችን በሚጠቅም መንገድ ማቅረብ። የምታቀርበው ንግግር አድማጮችን የሚጠቅም እንዲሆን ስለ ትምህርቱ ብቻ ሳይሆን ስለ አድማጮችህም ጭምር ማሰብ ይኖርብሃል። ይህ ሲባል እንዲሁ በደፈናው ሳይሆን በተናጠል ስለ አድማጮችህ ማሰብ ማለት ነው። በአድማጮችህ መካከል የተለያዩ ግለሰቦችና ቤተሰቦች አሉ። ትናንሽ ልጆች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አንዳንድ አረጋውያንም ይኖሩ ይሆናል። እንግዶች ሌላው ቀርቶ አንተ ከመወለድህ በፊት ይሖዋን ያገለግሉ የነበሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንዶች በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሌሎቹ ደግሞ ገና አሁንም ከአንዳንድ የዓለም አስተሳሰቦችና ልማዶች ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቁ ሊሆኑ ይችላሉ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የማቀርበው ትምህርት በአድማጮቼ መካከል ያሉትን ሰዎች የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? ነጥቡን እንዲያስተውሉት ልረዳቸው የምችለው እንዴት ነው?’ ዋና ትኩረትህን ከላይ ከተዘረዘሩት አድማጮችህ መካከል በአንዱ ወይም በሁለቱ ላይ ማድረግ ትፈልግ ይሆናል። ይሁንና ሌሎችን ጭራሽ መርሳት አለብህ ማለት አይደለም።

የምታቀርበው ንግግር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረተ ትምህርት የሚያብራራ ቢሆንስ? ትምህርቱን አድማጮችህ የሚያምኑበት ከሆነ ለእነርሱ የሚጠቅም አድርገህ ልታቀርበው የምትችለው እንዴት ነው? በጉዳዩ ላይ ያላቸውን እምነት ይበልጥ የሚያጠናክር አድርገህ ለማቅረብ ሞክር። እንዴት? ድጋፍ የሚሆኑትን ጥቅሶች በጥልቀት በማብራራት ነው። በተጨማሪም ለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር ልትረዳቸው ትችላለህ። ትምህርቱ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና ከይሖዋ ባሕርያት ጋር የሚጣጣመው እንዴት እንደሆነ በማብራራት ይህን ማድረግ ትችል ይሆናል። ይህን ትምህርት በማወቃቸው የተጠቀሙ እና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላቸውን አመለካከት ማስተካከል የቻሉ ሰዎችን እንደ ምሳሌ አድርገህ ጥቀስ።

ትምህርቱ ለአድማጮች ያለውን ጠቀሜታ የምትገልጸው የግድ በንግግርህ መደምደሚያ ላይ በምትሰጠው አጭር ማጠቃለያ መሆን የለበትም። ከንግግሩ መጀመሪያ አንስቶ እያንዳንዱ አድማጭ “ይህ ትምህርት ለእኔ ነው” በሚል ስሜት ሊከታተልህ ይገባል። ከዚህ በኋላ የንግግርህን እያንዳንዱን ዋና ነጥብ ስታብራራም ሆነ መደምደሚያህ ላይ ትምህርቱ ለአድማጮች ያለውን ጠቀሜታ ከመግለጽ ወደኋላ አትበል።

አድማጮች ትምህርቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የምታስረዳበት መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባል። ይህ ምን ማለት ነው? ፍቅር ልታሳያቸውና ራስህን በእነርሱ ቦታ ልታስቀምጥ ይገባል ማለት ነው። (1 ጴጥ. 3:​8፤ 1 ዮሐ. 4:​8) ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ስለነበረው ከባድ ችግር በጻፈበት ጊዜ እንኳ በዚያ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ያደረጉትን መንፈሳዊ እድገት በተመለከተ በጎ ጎናቸውን ሳይጠቅስ አላለፈም። የጻፈላቸውንም ምክር እንደሚሠሩበት ያለውን ትምክህት ገልጿል። (1 ተሰ. 4:​1-12) ይህ ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ነው!

የንግግርህ ዓላማ አድማጮች ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ እንዲሳተፉ ማበረታታት ነው? ለዚህ መብት አድናቆት እንዲያድርባቸውና በቅንዓት እንዲነሳሱ አድርግ። ይሁንና እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያደርገው ተሳትፎ መጠን እንደሚለያይና መጽሐፍ ቅዱስም ይህንኑ ጉዳይ ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ መዘንጋት አይኖርብህም። (ማቴ. 13:​23) ወንድሞችህ የጥፋተኛነት ስሜት እንዲያድርባቸው አታድርግ። ዕብራውያን 10:​24 ‘ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ’ ይመክረናል። ለፍቅር ካነሳሳናቸው ከልብ ተገፋፍተው ይሠራሉ። ሌሎችን በግፊት ለሥራ ለማነሳሳት ከመሞከር ይልቅ ይሖዋ ‘በእምነት የመታዘዝን’ መንፈስ በውስጣቸው እንድንኮተኩት እንደሚፈልግ መገንዘብ ይኖርብሃል። (ሮሜ 16:​26) የራሳችንንም ሆነ የወንድሞቻችንን እምነት ለማጠንከር ስንጥር ይህንን መዘንጋት አይኖርብንም።

የትምህርቱን ጠቀሜታ እንዲያስተውሉ መርዳት። በምትመሰክርበት ጊዜ ምሥራቹ ለእነርሱ ምን ትርጉም እንዳለው ጎላ አድርገህ ልትገልጽ ይገባል። ይህ ደግሞ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉት ሰዎች የሚያሳስባቸው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ ይጠይቅብሃል። ይህንን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በራዲዮ ወይም በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ዜናዎችን አዳምጥ። በጋዜጦች ላይ ትኩረት የተሰጣቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ተመልከት። እንዲሁም ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ዕድል መስጠትና ማዳመጥ ያስፈልግሃል። ሥራ ማጣት፣ የኪራይ ዋጋ መናር፣ ሕመም፣ የቤተሰብን አባል በሞት ማጣት፣ የወንጀል ፍርሃት፣ ባለ ሥልጣናት የሚፈጽሙት ግፍ፣ የትዳር መፍረስ፣ ልጆችን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ማሳደግና እነዚህን የመሳሰሉ ከባድ ችግሮች እንደሚያስጨንቋቸው ትገነዘብ ይሆናል። እነዚህን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳቸው ይችላል? ሊረዳቸው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።

ከአንድ ሰው ጋር ለመወያየት ስታስብ ልትነግረው የምትፈልገው ነገር እንደሚኖር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሰውዬውን ይበልጥ የሚያሳስበው ሌላ ጉዳይ እንዳለ ካስተዋልህ በተቻለ መጠን በዚህ ጉዳይ ላይ ለማወያየት ሞክር። ወይም በሌላ ጊዜ ጠቃሚ ሐሳቦችን ልታካፍለው እንደምትችል ንገረው። ይህን ስንል ‘በማይመለከተን ጉዳይ ውስጥ እንገባለን’ ማለት ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ምክር ከማካፈል ወደኋላ አንልም። (2 ተሰ. 3:​11) ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከእነርሱ ሕይወት ጋር የተያያዘ ምክር እንደሚሰጥ ሲያስተውሉ በጣም እንደሚነኩ የታወቀ ነው።

መልእክታችን እነርሱን በግል የሚጠቅማቸው እንዴት እንደሆነ ካልታያቸው ቶሎ ብለው ውይይቱን ሊያቋርጡ ይችላሉ። ቢያዳምጡን እንኳን ርዕሰ ጉዳዩ ለእነርሱ ያለውን ጥቅም ግልጽ ሳናደርግላቸው ከቀረን የምንነግራቸው ነገር ብዙም ልባቸውን ላይነካው ይችላል። በተቃራኒው ግን መልእክቱ ለእነርሱ ምን ትርጉም እንዳለው ግልጽ ካደረግንላቸው ውይይታችን በሕይወታቸው ውስጥ ወሳኝ ለውጥ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ሁልጊዜ ትምህርቱ ያለውን ጥቅም ለማጉላት መጣር ይኖርብሃል። (ምሳሌ 4:​7) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን፣ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዲሁም በይሖዋ መንገድ መመላለስ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል የሚረዷቸውን ምሳሌዎች ልብ እንዲሉ እርዳቸው። በይሖዋ መንገድ መመላለስ የሚያስገኝላቸውን ጥቅም ጠበቅ አድርገህ ግለጽ። (ኢሳ. 48:​17, 18) ይህም ተማሪዎቹ በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። ለይሖዋ ፍቅር እንዲኮተኩቱና እርሱን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርባቸው እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ሥራ ላይ የሚያውሉት ከልባቸው ተነሳስተው እንዲሆን አድርግ።

ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

  • አንድ ንግግር ስትዘጋጅ ስለ ንግግሩ ብቻ ሳይሆን ስለ አድማጮችህ ጭምር አስብ። እነርሱን ሊጠቅም በሚችል መንገድ አቅርበው።

  • ትምህርቱ ለአድማጮች ያለውን ጠቀሜታ የምትገልጸው የግድ በመደምደሚያህ ላይ መሆን የለበትም። በንግግርህ መሃል ሁሉ የትምህርቱ ጠቀሜታ ሊጎላ ይገባል።

  • ለመመስከር ስትዘጋጅ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉትን ሰዎች የሚያሳስባቸው ነገር ምን እንደሆነ ልብ ልትል ይገባል።

  • በአገልግሎት ሰዎችን ስታነጋግር ከልብ አዳምጣቸው። አቀራረብህንም እንደ ሁኔታው አስተካክል።

መልመጃ፦ የመንግሥት አገልግሎታችን ቅጂዎችህን በማገላበጥ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ላሉት ሰዎች ይበልጥ ተስማሚ ይሆናሉ የምትላቸውን አንድ ወይም ሁለት አቀራረቦች በመምረጥ በአገልግሎት ተጠቀምባቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ