የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 27 ገጽ 174-ገጽ 178 አን. 2
  • በራስ አባባል መናገር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በራስ አባባል መናገር
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በራስ አገላለጽ የሚቀርብ ንግግርና ድንገተኛ የሆነ ንግግር
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • በአስተዋጽኦ መጠቀም
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ከአድማጮች ጋር ግንኙነት መፍጠርና የማስታወሻ አጠቃቀም
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 27 ገጽ 174-ገጽ 178 አን. 2

ጥናት 27

በራስ አባባል መናገር

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የምትጠቀምባቸውን ቃላት ሳትሸመድድ ሐሳቡን ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅተህ ተናገር።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

በራስ አባባል መናገር አድማጮች ትምህርቱን በትኩረት እንዲከታተሉና ለሥራ እንዲነሳሱ በማድረግ ረገድ በጣም ውጤታማ ዘዴ ነው።

ንግግርህን ለመዘጋጀት ብዙ ደክመህ ይሆናል። የተዘጋጀኸውም ንግግር ግንዛቤ የሚያሰፋና አሳማኝ ማስረጃዎችን የያዘ ሊሆን ይችላል። አቀላጥፈህም ልትናገር ትችላለህ። ይሁን እንጂ አድማጮችህ ሐሳባቸው የሚከፋፈል ከሆነና አልፎ አልፎ አንዳንድ ነገር ብቻ የሚያዳምጡ ከሆነ ከንግግርህ ምን ያህል ይጠቀማሉ? ሐሳባቸውን ሰብስበው ንግግርህን በትኩረት መከታተል ካልቻሉ ልባቸውን መንካት የምትችል ይመስልሃል?

ለዚህ ችግር ዋነኛው መንስኤ ምን ሊሆን ይችላል? ለችግሩ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም በአብዛኛው ግን ምክንያት የሚሆነው ተናጋሪው ንግግሩን በራሱ አባባል አለማቅረቡ ነው። በሌላ አባባል በተደጋጋሚ ከማስታወሻው እያነበበ ይናገራል ወይም አቀራረቡ ድርቅ ያለ ይሆናል ማለት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች ተናጋሪው ንግግሩን ከተዘጋጀበት መንገድ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው።

መጀመሪያ ላይ የንግግርህን እያንዳንዱን ዝርዝር ሐሳብ ጽፈህ በኋላ ያንኑ ወደ አስተዋጽኦ ለመቀየር ከሞከርህ በራስህ አባባል ማቅረብ እንደምትቸገር የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም የምትጠቀምባቸውን ቃላት አስቀድመህ መርጠሃል። ምንም እንኳ ንግግሩን የምታቀርበው አስተዋጽኦውን ተጠቅመህ ቢሆንም መጀመሪያ ዝርዝር ሐሳቡን ስትጽፍ የተጠቀምክባቸውን ቃላት ለማስታወስ መሞከርህ አይቀርም። አንድን ሐሳብ በጽሑፍ ስናሰፍር የምንጠቀምበት ቋንቋ በዕለት ተዕለት ንግግራችን ከምንጠቀምበት የተለየና የዓረፍተ ነገር አወቃቀሩም ከበድ ያለ ነው። ስለዚህ ንግግርህም ይህንኑ የጽሑፍ ቋንቋ ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።

የንግግሩን ሐሳብ አንድ በአንድ ለመጻፍ ከመሞከር ይልቅ የሚከተለውን ዘዴ ለመጠቀም ሞክር:- (1) ጭብጡንና ጭብጡን ለማዳበር የምትጠቀምባቸውን የርዕሰ ጉዳዩን ዋና ዋና ነጥቦች ምረጥ። ለአጭር ንግግር ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች በቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ንግግሩ ረዘም ያለ ሲሆን ደግሞ አራት ወይም አምስት ዋና ዋና ነጥቦች ሊኖሩት ይችላል። (2) እያንዳንዱን ዋና ነጥብ ለማዳበር የምትጠቀምባቸውን ጥቅሶች፣ ምሳሌዎችና ቁልፍ ሐሳቦች ከሥሩ አስፍር። (3) ንግግሩን ምን ብለህ እንደምትጀምር አስብ። ለዚህ እንዲረዳህ አንድ ወይም ሁለት ሐሳቦች ልትጽፍ ትችላለህ። እንዲሁም ንግግርህን ምን ብለህ እንደምትደመድም ተዘጋጅ።

አቀራረብህን መለማመድም በጣም አስፈላጊ ነው። ሆኖም በዚህ ጊዜ አስተዋጽኦውን አንድ በአንድ ለመሸምደድ መሞከር የለብህም። በራስህ አባባል መናገር እንድትችል አቀራረብህን ስትለማመድ ዋናው ትኩረትህ ሐሳቡ ላይ እንጂ ቃላቱ ላይ መሆን የለበትም። የሐሳቡ ቅደም ተከተል በአእምሮህ ቁልጭ ብሎ እስኪሳል ድረስ ደጋግመህ መከለስ ይኖርብሃል። ንግግሩ አሳማኝ በሆነ መንገድ የተዋቀረና በሚገባ የታሰበበት ከሆነ የነጥቡን ቅደም ተከተል በቀላሉ ማስታወስና ያለችግር መናገር ትችላለህ።

ጥቅሙን አስብ። በራስ አባባል የመናገር ትልቁ ጥቅም ትምህርቱን በቀላሉ በሚጨበጥ መንገድ ለማቅረብ ማስቻሉ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ንግግር ደግሞ አድማጮችን ለተግባር ያነሳሳል። አቀራረብህም ይበልጥ ሕያውና አድማጮችን የሚማርክ ይሆናል።

በራስህ አባባል የምትናገር ከሆነ አድማጮችህን እንደልብ ማየት ትችላለህ። እያንዳንዱን ዓረፍተ ነገር ከማስታወሻህ ለማየት ስለማትሞክር አድማጮችህ ርዕሰ ጉዳዩን በደንብ እንደምታውቀውና የምትናገረውንም ከልብህ እንደምታምንበት እንደሚሰማቸው የታወቀ ነው። በዚህ መንገድ ሞቅ ባለ የውይይት መልክ ለመናገርና የአድማጮችህን ልብ ለመንካት ትችላለህ።

ከዚህም በተጨማሪ በራስ አባባል መናገር እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ማድረግ ያስችላል። ንግግሩን ከማቅረብህ ትንሽ ቀደም ብሎ ከትምህርቱ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ የሚዛመድ ለየት ያለ ዜና ሰማህ እንበል። ይህንን ዜና መጥቀስህ ተገቢ አይመስልህም? ወይም ደግሞ ንግግሩን እየሰጠህ ሳለ በአድማጮችህ መካከል በትምህርት እድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች እንዳሉ አስተዋልክ እንበል። እነዚህ ወጣቶች ትምህርቱ እነርሱንም እንደሚመለከት እንዲያስተውሉ ለመርዳት ስትል በምትጠቀምባቸው ምሳሌዎች እንዲሁም ነጥቡን እንዴት ሊሠሩበት እንደሚችሉ በምትሰጠው ማብራሪያ ላይ ማስተካከያ ማድረግህ ጥሩ ይሆናል!

በራስ አባባል መናገር ያለው ሌላው ጥቅም ተናጋሪውን ይበልጥ የሚያበረታታ መሆኑ ነው። አድማጮች በአድናቆት እየተከታተሉህ እንዳሉ ስታይ ይበልጥ ግለትህ ይጨምርና ነጥቦቹን ሰፋ አድርገህ እያብራራህና አጽንዖት እየሰጠህ ትናገራለህ። አድማጮችህ በትኩረት እንደማይከታተሉህ ካስተዋልህ ነቃ ብለው እንዲያዳምጡህ ለማድረግ አንድ መላ ልትፈልግ ትችላለህ።

ልትጠነቀቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች። ካልተጠነቀቅህ በራስ አባባል መናገር አደጋ ሊኖረው እንደሚችል መዘንጋት የለብህም። አንዱ አደጋ ሰዓት ማሳለፍ ነው። ንግግሩን ስትሰጥ ብዙ ተጨማሪ ሐሳብ የምታክል ከሆነ በሰዓትህ ለመጨረስ ልትቸገር ትችላለህ። እያንዳንዱን የንግግሩን ክፍል በምን ያህል ደቂቃ ማቅረብ እንዳለብህ ማስታወሻህ ላይ ከጻፍህ እንዲህ ዓይነት ችግር አይገጥምህም። ከዚያም እያንዳንዱን ክፍል በመደብከው ደቂቃ መሠረት ለማቅረብ ጥረት አድርግ።

በተለይ ልምድ ያላቸውን ተናጋሪዎች ሊያጋጥም የሚችለው ሌላው አደጋ ከመጠን በላይ በራስ መተማመን ነው። አንዳንዶች ንግግር የማቅረብ ልምዱ ስላላቸው እንደምንም አንዳንድ ሐሳቦችን አገጣጥመው በመናገር ጊዜውን መሙላት እንደማይቸገሩ ይሰማቸው ይሆናል። ሆኖም ትህትናን ማዳበራችንና ታላቁ አስተማሪ ይሖዋ ራሱ ባዘጋጀው የትምህርት ፕሮግራም የምንካፈል መሆናችንን መገንዘባችን የሚሰጠንን እያንዳንዱን ክፍል በጸሎት እንድናስብበትና ጥሩ ዝግጅት እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል።​—⁠ኢሳ. 30:​20፤ ሮሜ 12:​6-8

በራሳቸው አባባል ንግግር በመስጠት ረገድ ብዙም ልምድ የሌላቸውን ተናጋሪዎች የሚያሳስባቸው ትልቁ ነገር ግን መናገር የፈለግሁትን ሐሳብ ልረሳው እችላለሁ የሚለው ፍርሃት ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ያለው ፍርሃት ጥሩ ተናጋሪ ለመሆን የሚረዳህን ይህንን የንግግር ባሕርይ ከማዳበር ወደኋላ እንዲጎትትህ ልትፈቅድ አይገባም። በደንብ ተዘጋጅ፤ እንዲሁም ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲረዳህ ጠይቀው።​—⁠ዮሐ. 14:​26

ሌሎች ተናጋሪዎች ደግሞ በራሳቸው አባባል ከመናገር ወደኋላ የሚሉት ስለሚጠቀሙባቸው ቃላት ከልክ በላይ ስለሚጨነቁ ነው። በመሠረቱ በራስህ አባባል ስትናገር የምትጠቀምባቸው ቃላት የተመረጡና ዓረፍተ ነገሮችህም ከሰዋስው ግድፈት የጠሩ ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ንግግርህ አድማጮችን በሚስብ መንገድ በውውይት መልክ መቅረቡ ይህንን በሚገባ ያካክሰዋል። ሰዎች ለመረዳት በማያስቸግሩ ቃላትና ባልተወሳሰቡ ዓረፍተ ነገሮች የሚነገረውን መልእክት መቀበል ይቀልላቸዋል። ጥሩ ዝግጅት ካደረግህ ብዙም ሳትጨነቅ ሐሳቡን በተገቢው መንገድ መግለጽ ትችላለህ። ይህንንም ማድረግ የምትችለው ደግሞ ስለሸመደድህ ሳይሆን ሐሳቡ በደንብ ስለገባህ ነው። በዕለት ተዕለት ውይይትህ ጥሩ የአነጋገር ልማድ ካለህ ንግግር ስትሰጥም አትቸገርም።

የምትጠቀምባቸው ማስታወሻዎች። ከጊዜ በኋላ ልምድ እያዳበርህ ስትሄድ አስተዋጽኦህ ላይ እያንዳንዱን የንግግሩን ነጥብ በጥቂት ቃላት ማስፈርን እየተማርክ ትሄዳለህ። እነዚህን አጫጭር ማስታወሻዎችና የምትጠቀምባቸውን ጥቅሶች በቀላሉ ለማየት እንዲመችህ በካርድ ላይ ወይም በወረቀት ላይ ልትጽፋቸው ትችላለህ። በአገልግሎት ለምታገኛቸው ሰዎች የምትናገረውን አጭር ሐሳብ ብዙውን ጊዜ በቃል ልትይዘው ትችላለህ። በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተዘጋጅተህ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ስትሄድ ግን ሐሳቡን በአጭሩ በማስታወሻ ጽፈህ መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ ልታደርገው ትችላለህ። አለዚያም ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱሳዊ የውይይት አርዕስት” በተባለው ቡክሌት ወይም ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በሚለው መጽሐፍ ላይ የሚገኝ አጭር ሐሳብ ልትጠቀም ትችል ይሆናል።

ይሁን እንጂ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተደራራቢ የጉባኤ ክፍሎችና የሕዝብ ንግግሮች እንድታቀርብ ከተመደብህ ሰፋ ያለ ማስታወሻ መያዝ ያስፈልግህ ይሆናል። ለምን? ክፍሎችህን ከማቅረብህ በፊት ነጥቦቹን በቀላሉ ለመከለስ እንዲረዳህ ነው። ያም ሆኖ ንግግሩን ስታቀርብ በየዓረፍተ ነገሩ አሁንም አሁንም ማስታወሻህን በማየት እዚያ ላይ ያለውን በቀጥታ ለመናገር የምትጥር ከሆነ በራስህ አባባል ማቅረብ አትችልም። ሰፋ ያለ ማስታወሻ የምትጠቀም ከሆነ ቁልፍ የሆኑትን ጥቂት ቃላትና ጥቅሶች በንግግሩ ወቅት በቀላሉ ማየት እንድትችል አስቀድመህ ምልክት አድርግባቸው።

ብዙውን ጊዜ አንድ ልምድ ያለው ተናጋሪ ንግግሩን በዋነኝነት ማቅረብ ያለበት በራሱ አባባል ቢሆንም ሌሎች የአቀራረብ ዘዴዎችን ጣልቃ ማስገባት ጠቃሚ የሚሆንባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። በንግግሩ መግቢያና መደምደሚያ ላይ አድማጮችን በደንብ እያዩ ጠንከር ያሉና በተመረጡ ቃላት የተቀነባበሩ ሐሳቦችን መናገር ስለሚያስፈልግ ጥቂት ዓረፍተ ነገሮችን በቃል ማጥናቱ ውጤታማ ሊሆን ይችላል። ተጨባጭ እውነታዎችን፣ አኃዞችን፣ ከሌላ ምንጭ የተወሰዱ ሐሳቦችን ወይም ጥቅሶችን በምትጠቅስበት ጊዜ በቀጥታ ማንበቡ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል።

ለሌሎች ማብራሪያ መስጠት ሲያስፈልግ። አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነታችን ማብራሪያ እንድንሰጥ ድንገት ልንጠየቅ እንችላለን። ምናልባት አገልግሎት ላይ ያገኘነው ሰው የተቃውሞ ሐሳብ አንስቶ ሊሆን ይችላል። ከዘመዶቻችን፣ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ተመሳሳይ ጥያቄ ሊገጥመን ይችላል። የመንግሥት ባለ ሥልጣናትም ስለ እምነታችንና ስለ አቋማችን ማብራሪያ እንድንሰጥ ይጠይቁን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን” በማለት አጥብቆ ያሳስባል።​—⁠1 ጴጥ. 3:​15

በ⁠ሥራ 4:​19, 20 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ጴጥሮስና ዮሐንስ ለአይሁዳውያን የሳንሄድሪን ሸንጎ ምን ብለው እንደመለሱ ልብ በል። በሁለት ዓረፍተ ነገር አቋማቸውን በግልጽ አስረድተዋል። ጥያቄው እነርሱን ብቻ ሳይሆን ሸንጎውንም ሊያሳስብ እንደሚገባ በመጠቆም ተገቢውን መልስ ሰጥተዋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ እስጢፋኖስ በሐሰት ክስ ተወንጅሎ እዚሁ ሸንጎ ፊት ቀርቦ ነበር። እስጢፋኖስ በዚያው ቅጽበት ምን ዓይነት አሳማኝ መልስ እንደሰጠ የሐዋርያት ሥራ 7:​2-53 ላይ ማንበብ ትችላለህ። ሐሳቡን ያቀናበረው እንዴት ነው? ወደኋላ ተመልሶ የጠቀሳቸውን ክንውኖች በሙሉ ያስቀመጠው ታሪካዊ ቅደም ተከተላቸውን ጠብቆ ነበር። በተገቢው ቦታ ላይ ደግሞ የእስራኤል ብሔር ያሳየውን የዓመፀኝነት መንፈስ ጎላ አድርጎ መጥቀስ ጀመረ። ከዚያም መደምደሚያው ላይ ሲደርስ የሳንሄድሪን ሸንጎ የአምላክ ልጅ እንዲገደል በማድረግ ተመሳሳይ የዓመፀኝነት መንፈስ ማሳየቱን ጠቅሷል።

ስለ እምነትህ ማብራሪያ እንድትሰጥ ድንገት በምትጠየቅበት ጊዜ ጥሩ መልስ ለመስጠት የሚረዳህ ምንድን ነው? ንጉሥ አርጤክስስ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ከመስጠቱ በፊት በልቡ ጸሎት ያቀረበውን የነህምያን ምሳሌ ተከተል። (ነህ. 2:​4) ከዚያም የምትሰጠውን መልስ ጊዜ ሳታጠፋ በአእምሮህ አቀናብረህ ለማስቀመጥ ሞክር። ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች መነሻ አድርገህ ልትጠቀምባቸው ትችል ይሆናል:- (1) በማብራሪያህ ልታካትታቸው የሚገቡ አንድ ወይም ሁለት ነጥቦች ምረጥ (ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱ ነጥቦችን መጠቀም ትፈልግ ይሆናል።) (2) ላነሳኻቸው ነጥቦች ማስረጃ አድርገህ የምትጠቀምባቸውን ጥቅሶች አስብ። (3) ጠያቂህ በጥሞና እንዲያዳምጥህ ማብራሪያህን እንዴት ብለህ እንደምትጀምር አስብ። ከዚህ በኋላ መልስ መስጠት ልትጀምር ትችላለህ።

ድንገት የሚያፋጥጥ ጥያቄ ቢቀርብልህ ምን ማለት እንዳለብህ ግራ ይገባህ ይሆን? ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸዋል:- “የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፣ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።” (ማቴ. 10:​19, 20) ይህ ማለት ግን እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ‘በጥበብ የመናገር’ ችሎታ በተዓምራዊ መንገድ ይሰጥሃል ማለት አይደለም። (1 ቆሮ. 12:​8) ይሁን እንጂ ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ለአገልጋዮቹ የሚሰጠውን ትምህርት አዘውትረህ የምትከታተል ከሆነ መንፈስ ቅዱስ አስፈላጊ የሆነውን ሐሳብ እንድታስታውስ ሊረዳህ ይችላል።​—⁠ኢሳ. 50:​4

በራስ አባባል መናገር በጣም ውጤታማ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በጉባኤ ክፍል ስታቀርብ ሁልጊዜ በዚህ መንገድ መናገርን ከተለማመድህ ድንገት ጥያቄ ሲቀርብልህም አጥጋቢ መልስ መስጠት አትቸገርም። በራስ አባባል መናገርን ከመለማመድ ወደኋላ አትበል። በዚህ መንገድ የመናገር ችሎታ ካዳበርህ በአገልግሎትህ ውጤታማ ትሆናለህ። በተጨማሪም በጉባኤ የሕዝብ ንግግር የማቅረብ መብት ካለህ አድማጮችህ በትኩረት እንዲከታተሉህ ማድረግ እንዲሁም ልባቸውን መንካት ትችላለህ።

ይህንን ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው?

  • በመጀመሪያ በራስ አባባል መናገር ጥቅም እንዳለው ልታምንበት ይገባል።

  • ንግግርህን አንድ በአንድ ከመጻፍ ይልቅ አጭር አስተዋጽኦ አዘጋጅ።

  • የንግግሩን አቀራረብ ስትለማመድ እያንዳንዱን ዋና ነጥብ በተናጠል በአእምሮህ ከልስ። ስለ ቃላቱ አቀማመጥ ከልክ በላይ ከመጨነቅ ይልቅ የሐሳቡን ቅደም ተከተል በአእምሮህ ለመቅረጽ ሞክር።

መልመጃ፦ (1) ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት በምትዘጋጅበት ጊዜ ሙሉ ዓረፍተ ነገሮችን ሳይሆን ቁልፍ የሆኑ ቃላትን ብቻ ማስመርን ተለማመድ። በራስህ አባባል መልስ። (2) በሚቀጥለው ጊዜ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚሰጥህን ክፍል አቀራረብ ስትለማመድ የትምህርቱን ጭብጥና ሌሎች ሁለት ወይም ሦስት ነጥቦች በመከለስ ጀምር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ