የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 25 ገጽ 166-ገጽ 169 አን. 6
  • በአስተዋጽኦ መጠቀም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በአስተዋጽኦ መጠቀም
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ከአድማጮች ጋር ግንኙነት መፍጠርና የማስታወሻ አጠቃቀም
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • በራስ አባባል መናገር
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 25 ገጽ 166-ገጽ 169 አን. 6

ጥናት 25

በአስተዋጽኦ መጠቀም

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

መናገር የምትፈልገውን አንድ በአንድ ጽፈህ ከማንበብ ይልቅ ሐሳቡን በአእምሮህ አቀናብረህ ወይም በወረቀት ላይ አስተዋጽኦ አዘጋጅተህ ተናገር።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አስተዋጽኦ ማዘጋጀት ሐሳብህን ለማቀናበር ይረዳሃል። አስተዋጽኦ መጠቀም እንደወትሮህና ከልብህ መናገር እንድትችል ይረዳሃል።

ብዙ ሰዎች አስተዋጽኦ ይዞ ንግግር መስጠት የሚለው ሐሳብ ራሱ ያስፈራቸዋል። ከዚህ ይልቅ መናገር የሚፈልጉትን ሁሉ አንድ በአንድ ቢጽፉት ወይም በቃላቸው ቢሸመድዱት ይመርጣሉ።

ይሁንና በየዕለቱ ከሰዎች ጋር የምንነጋገረው የጻፍነውን እያነበብን አይደለም። ከቤተሰባችንና ከጓደኞቻችን ጋር ስንጫወት፣ በአገልግሎት ስንካፈል እንዲሁም በግላችንም ሆነ ሌሎችን ወክለን ልባዊ ጸሎት ስናቀርብ መናገር የምንፈልገውን ነገር በጽሑፍ ይዘን አንቀርብም።

ንግግር ስታቀርብ ሐሳቡን አንድ በአንድ ጽፈህ ማንበብህ ወይም ደግሞ አስተዋጽኦ መጠቀምህ ልዩነት ይኖረዋልን? መናገር የምትፈልገውን አንድ በአንድ ጽፈህ ማንበብህ እንዳትሳሳት ወይም የተመረጠ አነጋገር መጠቀም እንድትችል የሚረዳህ ቢሆንም የራሱ የሆነ ችግር አለው። ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ካነበብህ በኋላ ፍጥነትህና የድምፅ ቃናህ ከወትሮው የተለየና አንድ ወጥ ብቻ ይሆናል። ትኩረትህ አድማጮችህ ላይ ሳይሆን የምታነብበው ወረቀት ላይ ከሆነ ብዙዎቹ እንደምታስብላቸውና ትምህርቱን ለእነርሱ እንደሚስማማ አድርገህ እያቀረብህ እንዳለ ላይሰማቸውና በጥሞና ላያዳምጡህ ይችላሉ። አንድ ንግግር ይበልጥ ቀስቃሽ የሚሆነው በራስ አገላለጽ ሲቀርብ ነው።

ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለዕለት ተዕለት ሕይወታችንም የሚጠቅም ሥልጠና የምናገኝበት ዝግጅት ነው። ከወዳጆቻችን ጋር ስንገናኝ አነጋገራችን ጥሩ እንዲሆን ብለን ወረቀት ከኪሳችን እያወጣን ሐሳባችንን አናነብላቸውም። ስናገለግልም ቢሆን ለሰዎቹ ልናካፍላቸው የፈለግነውን አንዳንድ ነጥብ ልንረሳ እንችላለን በሚል ፍርሃት መልእክቱን በወረቀት ጽፈን አንሄድም። ለሰዎች ስትመሰክር የሚያሳዩ ሠርቶ ማሳያዎችን በትምህርት ቤቱ በምታቀርብበት ጊዜ በተቻለ መጠን የራስህን አነጋገር ተጠቅመህ መናገርን ተለማመድ። ብዙውን ጊዜ ነጥቦቹን በአእምሮህ በግልጽ ማስቀመጥ ወይም አስተዋጽኦ መጠቀም ልታነሳቸው ያሰብካቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ለማስታወስ በቂ ይሆናል። ይህ ግን ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ይጠይቃል። ይሁንና ከአስተዋጽኦ የመናገር ድፍረት ሊኖርህ የሚችለው እንዴት ነው?

መናገር የምትፈልገውን ሐሳብ አቀናብር። ሐሳብህን በቅደም ተከተል ለመግለጽ በቅድሚያ በአእምሮህ ውስጥ ልታቀናብረው ይገባል። ይህ የምትናገራቸውን ቃላት መምረጥ ማለት አይደለም። ከመናገርህ በፊት ቆም ብለህ አስብ ማለት ነው።

ችኩል የሆነ ሰው ሳያመዛዝን ከተናገረ በኋላ ምነው ባልተናገርኩ ብሎ ይጸጸት ይሆናል። አንዳንዱ ደግሞ አንዱን ጥሎ ሌላውን ስለሚያነሳ ንግግሩ የማይጨበጥ ይሆናል። አንድ ሰው መናገር ከመጀመሩ በፊት ትንሽ ቆም ብሎ ነጥቦቹን በአእምሮው ለማቀናበር ከሞከረ እነዚህን ችግሮች ማስወገድ ይችላል። መናገር ከመጀመርህ በፊት አንደኛ ዓላማህ ምን እንደሆነ ወስን፣ ሁለተኛ የምትናገርበትን ቅደም ተከተል አስብ።

ለአገልግሎት በምትዘጋጅበት ጊዜ ምን ማድረግ አለብህ? በቦርሳህ የምትይዘውን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ሐሳብህንም በአእምሮህ በሚገባ ማቀናበር ያስፈልግሃል። የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጣ አንድ መግቢያ ለመጠቀም ካሰብህ ነጥቡ በደንብ እስኪገባህ ድረስ ደግመህ ደጋግመህ አንብበው። ዋናውን ፍሬ ሐሳብ በአንድ ወይም በሁለት አጭር ዓረፍተ ነገር ለመግለጽ ሞክር። አገላለጹን ለአንተ በሚመችህና ለአገልግሎት ክልልህ በሚስማማ መንገድ ማስተካከል ትችላለህ። የሐሳቡን ቅደም ተከተል በአእምሮህ ቁልጭ አድርገህ ማስቀመጥህ ጠቃሚ ነው። ይህ ምን ማድረግን ሊጨምር ይችላል? (1) በአካባቢህ ያሉ ብዙ ሰዎችን የሚያሳስባቸውን ጉዳይ እንደ መግቢያ አድርገህ ልትጠቅስ ትችላለህ። የምታነጋግረው ሰው አስተያየቱን እንዲሰጥ ጋብዘው። (2) አምላክ ይህን ችግር ለማስወገድ የሰጠውን ተስፋ የሚገልጹ አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችን ጨምሮ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ልትናገር የምትፈልገውን ነገር አስቀድመህ አስብ። አጋጣሚውን ካገኘህ ይሖዋ ይህን ተስፋ የሚፈጽመው በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሆነ ጎላ አድርገህ ግለጽ። (3) ከተወያያችሁበት ሐሳብ በመነሳት ግለሰቡ ቀጣይ እርምጃ እንዲወስድ አበረታታው። ጽሑፍ እንዲወስድ እና/ወይም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ልትጋብዘው እንዲሁም ቀጣይ ውይይት የምታደርጉበትን ቀጠሮ ልትይዝ ትችላለህ።

በዚህ ጊዜ በጽሑፍ የሰፈረ አስተዋጽኦ መያዝ አያስፈልግህም። የሐሳቡን ቅደም ተከተል በአእምሮህ በግልጽ ማስቀመጥ ብቻ በቂ ነው። የመጀመሪያውን ሰው ከማነጋገርህ በፊት የምትናገረውን ሐሳብ ለመከለስ ስትል አስተዋጽኦ የምትይዝ ከሆነ መግቢያህ ላይ የምትጠቀምባቸውን ጥቂት ቃላት፣ አንድ ወይም ሁለት ጥቅሶችና መደምደሚያህ ላይ ምን እንደምትል የሚጠቁም አጭር ነገር ብቻ የያዘ መሆን ይኖርበታል። ጥሩ ዝግጅት ማድረግና እንዲህ ዓይነት አስተዋጽኦ መጠቀም ዙሪያ ጥምጥም መሄድ ሳያስፈልገን ሐሳባችንን ቁልጭ አድርገን ለመግለጽ ያስችለናል።

በጉባኤው የአገልግሎት ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ወይም የተቃውሞ ሐሳብ ካለ በዚያ ጉዳይ ላይ ምርምር ማድረጉን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። በአብዛኛው ሁለት ወይም ሦስት መሠረታዊ ነጥቦችና እነርሱን የሚደግፉ ጥቅሶች ካገኘህ በቂ ነው። “መጽሐፍ ቅዱሳዊ የውይይት አርዕስት” ከተባለው ቡክሌት ወይም ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ላይ ከሚገኙት ጎላ ብለው የተጻፉ ንዑስ ርዕሶች የምትፈልገውን ነጥብ የያዙ አጫጭር አስተዋጽኦዎችን ማግኘት ትችላለህ። ከሌላ ጽሑፍ ያገኘኸውንም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ጥሩ ሐሳብ መጨመር ትፈልግ ይሆናል። ይህንን ያካተተ አጠር ያለ አስተዋጽኦ በወረቀት አዘጋጅና ለአገልግሎት ከምትጠቀምባቸው ጽሑፎች ጋር አብረህ አስቀምጠው። የምታነጋግረው ሰው ይህንኑ ጥያቄ ወይም የተቃውሞ ሐሳብ በሚያነሳበት ጊዜ ስለምታምንበት ነገር ለማስረዳት አጋጣሚውን በማግኘትህ ደስ እንዳለህ ግለጽለት። (1 ጴጥ. 3:​15) ከዚያም አስተዋጽኦህን በመጠቀም ለጥያቄው መልስ ስጥ።

ቤተሰብህን፣ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኑን ወይም ጉባኤውን ወክለህ ስትጸልይም ቢሆን ልትጠቅሰው የምትፈልገውን ሐሳብ አስቀድመህ በአእምሮህ ማቀናበርህ ጠቃሚ ነው። በ⁠ሉቃስ 11:​2-4 ላይ እንደምናነበው ኢየሱስ ትርጉም ያለው ጸሎት ለማቅረብ የሚረዳ አጭር ሐሳብ ለሐዋርያቱ ነግሯቸዋል። ሰሎሞን በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አገልግሎት ሲወሰን ረጅም ጸሎት አቅርቧል። ስለምን ጉዳይ እንደሚጸልይ አስቀድሞ አስቦበት እንደነበር ግልጽ ነው። በመጀመሪያ ያተኮረው በይሖዋና እርሱ ለዳዊት በገባው የተስፋ ቃል ላይ ሲሆን ከዚያ በኋላ ስለ ቤተ መቅደሱ ቀጥሎም በተወሰኑ ሁኔታዎችና ወገኖች ላይ ያተኮሩ ሐሳቦችን አንድ በአንድ ጠቅሷል። (1 ነገ. 8:​22-53) ከእነዚህ ምሳሌዎች እኛም ትምህርት መቅሰም እንችላለን።

አስተዋጽኦህ ቅልብጭ ያለ ይሁን። አስተዋጽኦውን ያዘጋጀኸው ንግግር ለመስጠት ነው? ከሆነ ምን ያህል ነጥቦች ሊያካትት ይገባል?

የአስተዋጽኦ ዓላማ ሐሳቡን እንድታስታውስ መርዳት ብቻ እንደሆነ መዘንጋት የለብህም። እንደ መግቢያ የምትጠቀምበትን ሐሳብ በጥቂት ዓረፍተ ነገሮች ጽፈህ ብትይዝ ጠቃሚ እንደሚሆን ይሰማህ ይሆናል። ከዚህ በኋላ ያለውን የአስተዋጽኦ ክፍል በተመለከተ ግን መጨነቅ ያለብህ ስለምትጠቀምባቸው ቃላት ሳይሆን ሐሳቡን ስለማስፈርህ ብቻ ነው። ሐሳቡን በዓረፍተ ነገር መልክ ማስቀመጥ ከመረጥህ አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን ተጠቀም። በንግግርህ የምታዳብራቸው ጥቂት ዋና ዋና ነጥቦች በአስተዋጽኦህ ላይ ጎላ ብለው ሊታዩ ይገባል። ለዚህ ስትል ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ልታሰምርባቸው ወይም በሌላ ቀለም ልትጽፋቸው ትችላለህ። ከዚያ ደግሞ በእያንዳንዱ ዋና ነጥብ ሥር ሐሳቡን ለማዳበር የምትጠቀምባቸውን ነጥቦች ዘርዝር። ልታነብባቸው ያሰብካቸውን ጥቅሶች ጻፍ። ብዙውን ጊዜ ጥቅሶቹን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ ማንበቡ የተሻለ ነው። ልትጠቀምበት ያሰብከውን ምሳሌ የሚጠቁም ማስታወሻ አስፍር። ከመጽሐፍ ቅዱስና ታማኝና ልባም ባሪያ ከሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ውጭ ያገኘኸውን ከነጥቡ ጋር የሚስማማ ጠቃሚ ሐሳብ መጨመር ትፈልግ ይሆናል። ከጉዳዩ ጋር የሚዛመደውን እያንዳንዱን ነጥብ በሚገባ ማቅረብ እንድትችል አስተዋጽኦህ ላይ የምታሰፍረው ማስታወሻ ግልጽ መሆን ይኖርበታል። ንግግሩን ስታቀርብ እንዳትቸገር አስተዋጽኦህ በሥርዓት የተጻፈ መሆን ይኖርበታል።

አንዳንዶች ዋና ዋናውን ነጥብ ብቻ የያዘ አስተዋጽኦ ይጠቀማሉ። አንድ አስተዋጽኦ ቁልፍ የሆኑትን ቃላት፣ ተናጋሪው በቃሉ የሚጠቅሳቸውን ጥቅሶችና አንዳንድ ሐሳቦችን እንዲያስታውስ የሚረዱ ምልክቶችና ሥዕሎች ብቻ የያዘ ሊሆን ይችላል። አንድ ተናጋሪ ይህንን ቀላል ማስታወሻ ብቻ በመያዝ ትክክለኛ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በራሱ አገላለጽ ንግግሩን መስጠት ይችላል። የዚህ ምዕራፍ ዓላማም ይህንኑ ማስተማር ነው።

በዚህ መጽሐፍ ከገጽ 39 እስከ 42 ላይ “አስተዋጽኦ ማዘጋጀት” በሚል ርዕስ የቀረበ ሐሳብ ታገኛለህ። “በአስተዋጽኦ መጠቀም” በሚለው በዚህ ጥናት ለመሥራት ስትጥር ከላይ በተጠቀሰው ርዕስ ሥር ያለውን ሐሳብ ማንበብህ ጠቃሚ ይሆናል።

የአስተዋጽኦ አጠቃቀም። አሁን ትኩረት እንድትሰጠው የተፈለገው ነጥብ ግን አስተዋጽኦ ማዘጋጀት ሳይሆን አስተዋጽኦውን ጥሩ አድርጎ መጠቀም ነው።

አስተዋጽኦህን ለመጠቀም የመጀመሪያው እርምጃ ንግግሩን ለማቅረብ መዘጋጀት ነው። ጭብጡን ተመልከት ከዚያም እያንዳንዱን ዋና ዋና ነጥብ አንብብና ከጭብጡ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አስብ። እያንዳንዱን ዋና ነጥብ ለማብራራት ምን ያህል ጊዜ እንደሚያስፈልግ ጊዜ መድብ። ከዚያ እንደገና ተመልሰህ የመጀመሪያውን ዋና ነጥብ አጥና። ነጥቡን ለማዳበር የምትጠቀምባቸውን ሐሳቦች፣ ጥቅሶችና ምሳሌዎች ከልስ። ይህ የንግግሩ ክፍል በደንብ እስኪዋሃድህ ድረስ ደግመህ ደጋግመህ አጥናው። ቀሪዎቹን ዋና ነጥቦችም እንዲሁ ተራ በተራ አጥናቸው። በሰዓትህ መጨረስ እንድትችል አንዳንድ ነጥቦች መቀነስ ካስፈለገህ የትኞቹን ነጥቦች እንደምትቀንስ ምረጥ። ከዚያም ንግግሩን በሙሉ ከልሰው። ትኩረትህ ሐሳቡ ላይ እንጂ ቃላቱ ላይ መሆን የለበትም። ንግግሩን በቃልህ አትሸምድድ።

ንግግሩን በምታቀርብበት ጊዜ አድማጮችህን በደንብ ልታያቸው ይገባል። አንድ ጥቅስ ካነበብህ በኋላ ብዙውን ጊዜ ማስታወሻህን ማየት ሳያስፈልግህ መጽሐፍ ቅዱስህን ተጠቅመህ ማብራራት መቻል ይኖርብሃል። በተመሳሳይም ምሳሌ የምትጠቀም ከሆነ በቀጥታ ከማስታወሻህ ከማንበብ ይልቅ ለጓደኛህ እንደምትተርክ አድርገህ ተናገር። በምትናገርበት ጊዜ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ላይ ማስታወሻህን አትይ። የሚያዳምጡህን ሰዎች ልብ መንካት የምትችለው ከልብህ የምትናገር ከሆነ ነው።

አስተዋጽኦ ተጠቅሞ የመናገርን ችሎታ በሚገባ ማዳበርህ የተዋጣለት የሕዝብ ተናጋሪ በመሆን ረገድ ትልቅ ዕድገት እንዳደረግህ የሚያሳይ ይሆናል።

አስተዋጽኦ መጠቀም የሚቻለው እንዴት ነው?

  • አስተዋጽኦ ተጠቅሞ መናገር ጥቅም እንዳለው ራስህን አሳምን።

  • በዕለት ተዕለት ውይይትህ፣ መናገር የምትፈልገውን ሐሳብ አስቀድመህ በአእምሮህ አቀናብር።

  • በአስተዋጽኦ ተጠቅመህ ለመናገር ድፍረት እንድታገኝ ወደ ይሖዋ ጸልይ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ተሳትፎ አድርግ።

  • አስተዋጽኦህ ቅልብጭ ያለና ጥርት ብሎ የሚነበብ ይሁን።

  • አስተዋጽኦውን ስትዘጋጅ ዓላማህ ሐሳቡን መከለስ እንጂ ቃላቱን መሸምደድ መሆን የለበትም።

መልመጃ:- በዚህ ሳምንት አገልግሎት ከመውጣትህ በፊት ልትናገረው ያሰብከውን መልእክት በቅደም ተከተል በአእምሮህ አስቀምጥ። (ገጽ 167 አንቀጽ 3ን ተመልከት።) ከዚያም በመስክ አገልግሎት ስትካፈል በተዘጋጀኸው ነጥብ ከሰዎች ጋር ምን ያህል ጊዜ እንደተወያየህ ወይም ቢያንስ ዋናውን ሐሳብ መጥቀስ እንደቻልክ ቁጠር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ