የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ገጽ 39-ገጽ 42
  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ማጤን፣ መምረጥና ማደራጀት
  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • አርዕስቱንና ዋና ዋና ነጥቦችን ማጉላት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ገጽ 39-ገጽ 42

አስተዋጽኦ ማዘጋጀት

ብዙዎች አንድ ንግግር እንዲያቀርቡ ሲመደቡ ከመግቢያው አንስተው እስከ መደምደሚያው ድረስ ሁሉንም አንድ በአንድ ይጽፋሉ፤ ይህ ደግሞ አድካሚ ነው። በዚህ መንገድ አስተዋጽኦ ማዘጋጀት የንግግሩን ረቂቅ ብዙ መለዋወጥ ሊጠይቅባቸው ይችላል። ታዲያ ይህ የሚወስደው ጊዜ ቀላል አይደለም።

አንተስ ንግግርህን የምትዘጋጀው በዚህ መንገድ ነው? ይበልጥ ቀለል ያለ ዘዴ ማወቅ ትፈልጋለህ? አስተዋጽኦ ማዘጋጀት የሚቻልበትን መንገድ አንዴ ካወቅህ ሁሉንም ነገር መጻፍ አያስፈልግህም። ይህም የንግግሩን አቀራረብ ለመለማመድ በቂ ጊዜ እንድታገኝ ያስችልሃል። በዚህ መንገድ ከተዘጋጀህ ንግግሩን ማቅረብ የማትቸገር ከመሆኑም በላይ ንግግርህ ለአድማጮች ጆሮ የሚጥምና ለሥራ የሚያነሳሳ ይሆናል።

እርግጥ በጉባኤ ለሚቀርቡት የሕዝብ ንግግሮች ዋናው አስተዋጽኦ ተዘጋጅቶ ይሰጣል። ይሁን እንጂ ለአብዛኞቹ ሌሎች ንግግሮች አስተዋጽኦ ተዘጋጅቶ አይሰጥም። ምናልባት የሚሰጥህ የንግግርህ ርዕሰ ጉዳይ ወይም ጭብጥ ብቻ ይሆናል። ወይም ደግሞ ከአንድ የተወሰነ ጽሑፍ ላይ ንግግር እንድታቀርብ ልትጠየቅ ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጥቂት መመሪያ ብቻ ይሰጥህ ይሆናል። እንዲህ ላሉት ክፍሎች በሙሉ የራስህን አስተዋጽኦ ማዘጋጀት ያስፈልግሃል።

[በገጽ 41 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በገጽ 41 ላይ የሚገኘው ናሙና አጠር ያለ አስተዋጽኦ እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል ይጠቁምሃል። ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች በስተግራ በኩል ወጣ ብለው እንደሚጀምሩና ጎላ ብለው እንደተጻፉ ልብ በል። በእያንዳንዱ ዋና ነጥብ ሥር ያንን የሚደግፉ ሐሳቦች ተጠቅሰዋል። እነዚህን ሐሳቦች ለማዳበር የሚረዱ ተጨማሪ ነጥቦች ደግሞ ወደ ቀኝ ትንሽ ገባ ብለው ተጽፈዋል። ይህን አስተዋጽኦ በደንብ ተመልከተው። ሁለቱ ዋና ዋና ነጥቦች ከጭብጡ ጋር በቀጥታ እንደሚያያዙ አስተውል። ከሥር የተጠቀሱት ንዑስ ነጥቦችም ቢሆኑ እንዲያው የሚስቡ ስለሆኑ ብቻ እንዳልተጻፉ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ነጥብ ከላዩ ያለውን ዋና ነጥብ የሚደግፍ ነው።

የምታዘጋጀው አስተዋጽኦ ሙሉ በሙሉ ይህንን ናሙና የሚመስል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እስካሁን የተወያየንበት ነጥብ መሠረታዊ ሐሳብ ከገባህ ነጥቦችህን አደራጅተህ ሚዛናዊ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ጥሩ ንግግር ለማዘጋጀት ትችላለህ። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ማጤን፣ መምረጥና ማደራጀት

አንድ ጭብጥ ሊኖርህ ይገባል። የምትመርጠው ጭብጥ ግን በአንድ ቃል ሊገለጽ የሚችል ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ መሆን የለበትም። ጭብጡ ልታስተላልፈው የምትፈልገው ማዕከላዊ ሐሳብ ሲሆን ርዕሰ ጉዳዩን ከምን አቅጣጫ ለማብራራት እንዳቀድህ የሚያሳይ ነው። ጭብጡ ከተሰጠህ በዚያ ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ቃላት በሚገባ ለማጤን ሞክር። የተሰጠህን ጭብጥ በአንድ ጽሑፍ ላይ ተመሥርተህ የምታዳብረው ከሆነ ጭብጡን በአእምሮህ ይዘህ ጽሑፉን በሚገባ አጥና። ርዕሰ ጉዳዩ ብቻ ከተሰጠህ ደግሞ ጭብጡን የምትመርጠው አንተ ነህ ማለት ነው። ይሁን እንጂ ይህን ከማድረግህ በፊት አንዳንድ ምርምር ማድረጉ ጠቃሚ ነው። ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ሐሳቦች ለማግኘት ሰፋ አድርገህ ማሰብ ያስፈልግሃል።

ይህን ስታደርግ ‘ይህ ትምህርት ለአድማጮች አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ዓላማዬ ምንድን ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ዓላማህ እንዲሁ ትምህርቱን ማቅረብ ወይም ንግግርህን ማራኪ ማድረግ ሳይሆን አድማጮችህን አንድ ጠቃሚ ሐሳብ ማስጨበጥ መሆን አለበት። የንግግርህ ዓላማ ፈር ከያዘ በኋላ በጽሑፍ አስፍረው። በምትዘጋጅበት ጊዜ ይህን የንግግርህን ዓላማ መርሳት የለብህም።

የንግግርህን ዓላማ ካወቅህና ከዚያ ጋር የሚስማማ ጭብጥ ከመረጥህ በኋላ (ወይም የተሰጠህ ጭብጥ ከዚህ ዓላማህ ጋር እንዴት እንደሚጣጣም ካጤንክ በኋላ) በተፈለገው ነጥብ ላይ ያተኮረ ምርምር ማድረግ ትችላለህ። ለአድማጮችህ ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናል የምትለውን ሐሳብ ፈልግ። እንዲሁ በደፈናው ብዙ ነገር በሚዳስስ ሐሳብ ሳይሆን ግንዛቤ በሚያሰፋና ጠቃሚ በሆነ ተጨባጭ ነጥብ ላይ አተኩር። አብዛኛውን ጊዜ ልትጠቀምበት ከምትችለው በላይ ብዙ ሐሳብ ስለምታገኝ የምታደርገውን ምርምር በተመለከተ ሚዛናዊና መራጭ መሆን ያስፈልግሃል።

ጭብጥህን ለማዳበርና ዓላማህን ዳር ለማድረስ የምትጠቀምባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ለይ። እነዚህ ነጥቦች የአስተዋጽኦህ መዋቅር ወይም መሠረት ይሆናሉ ማለት ነው። ዋና ዋና ነጥቦቹ ምን ያህል መሆን ይኖርባቸዋል? አጠር ላለ ንግግር ምናልባት ሁለት ዋና ነጥቦች በቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ለአንድ ሰዓት ንግግር እንኳ በአብዛኛው አምስት ዋና ዋና ነጥቦች በቂ ናቸው። ዋና ዋና ነጥቦቹ ጥቂት ከሆኑ አድማጮችህ በቀላሉ ሊያስታውሷቸው ይችላሉ።

ጭብጡና ዋና ዋና ነጥቦቹ ምን እንደሆኑ ካወቅህ በኋላ ምርምር አድርገህ ያገኘሃቸውን ሐሳቦች በቅደም ተከተል አስቀምጥ። ከዋና ዋና ነጥቦችህ ጋር በቀጥታ የሚዛመደው ነጥብ የትኛው እንደሆነ ለይ። አድማጮች ንግግርህን በጉጉት እንዲያዳምጡት የሚያስችሉ ዝርዝር ማብራሪያዎችን አክልበት። ለዋና ዋና ነጥቦችህ ድጋፍ የሚሆኑ ጥቅሶች በምትመርጥበት ጊዜ የጥቅሶቹን መልእክት በደንብ ለማብራራት የሚያስችሉ ሐሳቦችን በአእምሮህ ያዝ። እያንዳንዱ ሐሳብ ከየትኛው ዋና ነጥብ ሥር መቀመጥ እንዳለበት ከለየህ በኋላ በቦታ ቦታው አስቀምጥ። ምርምር ስታደርግ ካገኘሃቸው ሐሳቦች ውስጥ አንዳንዱ አድማጮችን ሊማርክ የሚችል ቢሆንም ከዋና ዋና ነጥቦችህ መካከል ከየትኛውም ጋር የማይዛመድ ከሆነ አውጣው። ወይም በሌላ ጊዜ እንድትጠቀምበት በፋይል አስቀምጠው። የተሻሉ ናቸው ያልካቸውን ብቻ መርጠህ አስቀር። ብዙ ነጥቦችን ለማካተት ከሞከርክ መጣደፍህ ስለማይቀር ንግግርህን ጥልቀት ባለው መንገድ ማቅረብ ትቸገራለህ። በተመደበልህ ጊዜ ውስጥ አድማጮችህን የሚጠቅሙ ጥቂት ነጥቦችን ብቻ ጥሩ አድርገህ ማቅረቡ የተሻለ ነው።

ነጥቦችህን ገና በቅደም ተከተል አላደራጀህ ከሆነ አሁን እንደዚያ ማድረግ ትችላለህ። የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የሚዛመዱ ብዙ ሐሳቦች ካሰባሰበ በኋላ ‘እንደ ቅደም ተከተላቸው’ በማስቀመጥ ይህን አድርጓል። (ሉቃስ 1:​3 አ.መ.ት ) ነጥቦችህን በጊዜ ቅደም ተከተላቸው ወይም በርዕስ በርዕሳቸው አደራጅተህ ምናልባትም መንስዔውንና ውጤቱን ወይም ችግሩንና መፍትሔውን በማፈራረቅ ዓላማህን ለማሳካት ውጤታማ ሆኖ ባገኘኸው መንገድ ልታቀርባቸው ትችላለህ። አድማጮችህ ከአንዱ ነጥብ ወደሌላው መሸጋገርህን ማስተዋል እስኪቸገሩ ድረስ በድንገት ከአንዱ ሐሳብ ወደሌላው ማለፍ የለብህም። የምታቀርባቸው ማስረጃዎች አድማጮች ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ የሚያደርጉ መሆን ይኖርባቸዋል። ነጥቦችህን ስታደራጅ አድማጮች ንግግርህን እንዴት እንደሚከታተሉት አስብ። ንግግርህን አንድ በአንድ መከታተል ይችላሉ? ይዘኸው ከተነሳኸው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለሥራ ያነሳሳቸዋል?

በመቀጠል ደግሞ አድማጮችህ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ እንዲሁም የምታቀርበው ንግግር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲያስተውሉ የሚረዳ መግቢያ አዘጋጅ። እንዲህ በምታደርግበት ጊዜ የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ዓረፍተ ነገሮች መጻፍህ ጥሩ ሊሆን ይችላል። በመጨረሻም የተነሳህበትን ዓላማ ዳር ለማድረስ የሚያግዝ ቀስቃሽ መደምደሚያ አዘጋጅ።

አስተዋጽኦህን ቀደም ብለህ ካዘጋጀህ ንግግሩን ከማቅረብህ በፊት አንዳንድ ጥቃቅን ማስተካከያዎችን በማድረግ ንግግሩን ይበልጥ ለማሻሻል የሚያስችል ጊዜ ታገኛለህ። ለአንዳንዶቹ ነጥቦች ድጋፍ የሚሆኑ አኃዛዊ መረጃዎች፣ ምሳሌዎች ወይም ተሞክሮዎች እንደሚያስፈልግህ ይሰማህ ይሆናል። አንድ በቅርቡ የተፈጸመ ሁኔታ ወይም የአድማጮችህን ትኩረት ሊስብ የሚችል ከአካባቢህ የተገኘ መረጃ መጠቀም አድማጮችህ የትምህርቱን አስፈላጊነት በቀላሉ እንዲያስተውሉ ሊረዳቸው ይችላል። ንግግርህን ስትከልስ ትምህርቱን ለአድማጮችህ እንደሚስማማ አድርገህ ማቅረብ የምትችልባቸው አጋጣሚዎች ይበልጥ ግልጽ ይሆኑልህ ይሆናል። ነጥቦቹን እንደገና ማጤንና አንዳንድ ማሻሻያዎችን ማድረግ አንድን ትምህርት ጠቃሚና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ወሳኝነት አለው።

አንዳንድ ተናጋሪዎች ከሌሎቹ ይበልጥ በዛ ያለ ማስታወሻ መያዝ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ትምህርቱን ያዋቀርከው በጥቂት ዋና ነጥቦች ላይ ብቻ ከሆነ እነዚህን ዋና ነጥቦች ለመደገፍ የግድ የማያስፈልጉትን ሐሳቦች በማውጣት ነጥቦቹን በቅደም ተከተላቸው አስቀምጥ። በዚህ ረገድ ተሞክሮ እያዳበርክ ስትሄድ ሁሉንም ነገር መጻፍ እንደማያስፈልግህ ትገነዘባለህ። ይህ ጊዜ በጣም ይቆጥብልሃል፤ የንግግርህም ጥራት ይሻሻላል። እንዲህ ስታደርግ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና እየተጠቀምህ እንዳለህ በግልጽ ይታያል።

አስተዋጽኦ ማዘጋጀት የሚቻለው እንዴት ነው?

  • የመረጥኸው ርዕሰ ጉዳይ ለአድማጮችህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና የተነሳህበት ዓላማ ምን እንደሆነ አስብ

  • አንድ ጭብጥ ምረጥ፤ ጭብጡ ከተሰጠህ ደግሞ በደንብ አጢነው

  • ግንዛቤ የሚያሰፋና ጠቃሚ ሐሳቦችን አሰባስብ

  • ዋና ዋና ነጥቦችህን ለይ

  • ነጥቦችህን አደራጅ፤ ይበልጥ የተሻሉ ናቸው የምትላቸውን ብቻ ምረጥ

  • አድማጮች የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ መግቢያ አዘጋጅ

  • ቀስቃሽ መደምደሚያ አዘጋጅ

  • ንግግርህን ከልስ፤ አንዳንድ ማሻሻያዎችን አድርግ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ