ጥናት 37
ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ
የአንድ ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች የሚባሉት ምንድን ናቸው? እግረ መንገድህን ጠቀስ አድርገህ የምታልፋቸው ጥሩ ነጥቦች ሁሉ ዋና ነጥቦች አይደሉም። እነዚህ በንግግርህ ውስጥ በሰፊው የሚብራሩና የንግግርህን ዓላማ ለማሳካት ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ቁልፍ ሐሳቦች ናቸው።
የንግግሩ ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ነጥቦቹን በጥንቃቄ መምረጥና ማዋቀር ነው። ብዙውን ጊዜ አንድ ንግግር ለመዘጋጀት ምርምር ስታደርግ ብዙ ነጥቦች ታገኛለህ። ከእነዚህ ውስጥ የምትጠቀምባቸውን ነጥቦች ለመምረጥ ምን ሊረዳህ ይችላል?
በመጀመሪያ ስለ አድማጮችህ አስብ። አድማጮችህ የምታቀርበውን ትምህርት ምን ያህል ያውቁታል? አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ የሚሰጠውን ሐሳብ ይቀበላሉ? ወይስ የሚጠራጠሩ ይኖራሉ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ የሚሰጠውን ምክር ሥራ ላይ ለማዋል ሲጥሩ ምን ዓይነት ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል? በሁለተኛ ደረጃ ይህን ትምህርት ለአድማጮችህ የምታቀርብበት ዓላማ ምን እንደሆነ ግልጽ ሊሆንልህ ይገባል። ያሰባሰብካቸውን ነጥቦች ከእነዚህ ሁለት አቅጣጫዎች በመመዘን ተስማሚ ሆነው ያገኘሃቸውን ብቻ መርጠህ አስቀር።
ጭብጡንና ዋና ዋና ነጥቦችን የያዘ አስተዋጽኦ ከተሰጠህ ንግግርህ ከዚያ መውጣት የለበትም። ይሁን እንጂ እያንዳንዱን ዋና ነጥብ ስታዳብር ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነገሮች ግምት ውስጥ የምታስገባ ከሆነ ትምህርቱን ይበልጥ ለአድማጮች የሚጠቅም አድርገህ ማቅረብ ትችላለህ። አስተዋጽኦ ካልተሰጠህ ግን ዋና ዋና ነጥቦችን የምትመርጠው አንተ ነህ።
አንዴ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ግልጽ ከሆኑልህና በእነርሱ ሥር የምትጠቅሳቸውን ነጥቦች በደንብ ካዋቀርህ በኋላ ንግግሩን መስጠት አይከብድህም። አድማጮችህም ከንግግሩ ብዙ እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነው።
ትምህርቱን የምታዋቅርባቸው መንገዶች። ንግግርህን በተለያዩ መንገዶች ልታዋቅር ትችላለህ። እነዚህን መንገዶች በደንብ ካወቅሃቸው እንደ ንግግሩ ዓላማ ንግግርህን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማዋቀር የምትችልበት ከአንድ በላይ ምርጫ ይኖርሃል።
ነጥቦቹን በርዕስ በርዕስ ማስቀመጥ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግ የሚያስችል ዘዴ ነው። (እያንዳንዱ ዋና ነጥብ አድማጮችህ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያላቸውን እውቀት የሚጨምር ወይም የንግግርህን ዓላማ ለማሳካት የሚረዳ ስለሆነ በጣም አስፈላጊ ነው።) ሌላው መንገድ የጊዜ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ማዋቀር ነው። (ለምሳሌ ያህል ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረውን ሁኔታ ከጠቀስን በኋላ በ70 እዘአ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት ምን ዓይነት ሁኔታ እንደነበር ልንገልጽ እንችላለን። ከዚያም በዘመናችን ያለውን ሁኔታ እንጠቅሳለን።) ሦስተኛው መንገድ ደግሞ ምክንያቱንና ውጤቱን አቀናጅቶ ማቅረብ ነው። (እንደ ሁኔታው ከሁለቱ አንዱን ማስቀደም ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ዛሬ ያለውን ሁኔታ ማለትም ውጤቱን ከጠቀስህ በኋላ ምክንያቱን ልትገልጽ ትችላለህ።) አራተኛው መንገድ ተቃራኒ ነገሮችን እያነጻጸሩ ማቅረብ ነው። (መልካምና ክፉ ወይም አዎንታዊና አሉታዊ ነገሮችን ማነጻጸር ትችል ይሆናል።) አንድን ንግግር ለማዋቀር ከአንድ በላይ መንገዶችን ልትጠቀም ትችላለህ።
እስጢፋኖስ በሐሰት ተከስሶ በአይሁድ የሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረበ ጊዜ ነጥቦቹን በጊዜ ቅደም ተከተላቸው አደራጅቶ አሳማኝ የሆነ ንግግር አቅርቧል። ሥራ 7:2-53ን ስታነብብ የተጠቀመባቸው ነጥቦች በዓላማ የተመረጡ መሆናቸውን ልብ በል። እስጢፋኖስ ገና ሲጀምር አድማጮቹ ሊያስተባብሉት የማይችሉትን ታሪክ እየተናገረ እንዳለ ግልጽ አድርጓል። ከዚያም ዮሴፍን ወንድሞቹ በቅንዓት ተነሳስተው እንደ ሸጡት፣ አምላክ ግን ለሕዝቡ መዳን ለማምጣት እንደተጠቀመበት ገለጸ። ቀጥሎም አይሁዳውያን የአምላክ ወኪል የነበረውን ሙሴን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀሩ ጠቀሰ። በመጨረሻም መደምደሚያው ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገደሉት አይሁዳውያን የቀደመው ትውልድ ያሳየውን መንፈስ እንዳንጸባረቁ ጎላ አድርጎ ገልጿል።
ዋና ዋና ነጥቦችህ አይብዙ። አንድን ጭብጥ ለማዳበር የሚያስፈልጉት ነጥቦች ጥቂት ብቻ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ከአምስት አይበልጡም። ክፍልህ የ5 ደቂቃም ሆነ የ10 ደቂቃ ወይም የ30 ደቂቃ ወይም ከዚያ በላይ ዋና ዋና ነጥቦቹ ከዚህ አይበልጡም። በንግግርህ ውስጥ ጎልተው የሚታዩት ነጥቦች በጣም መብዛት የለባቸውም። አድማጮችህ ከአንድ ንግግር መጨበጥ የሚችሉት ጥቂት ነጥቦችን ብቻ ነው። ንግግሩ በረዘመ መጠን ዋና ዋናዎቹ ነጥቦችም የዚያኑ ያህል ይበልጥ ግልጽ መሆንና ቁልጭ ብለው መቀመጥ ይኖርባቸዋል።
የዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ብዛት ምንም ያህል ይሁን ምን እያንዳንዱ ነጥብ በደንብ መብራራት ይኖርበታል። አድማጮች እያንዳንዱን ዋና ነጥብ በሚገባ ማስታወስ እንዲችሉ በደንብ ልታብራራው ይገባል።
አቀራረብህ ለአድማጮች ቀላል ሊሆንላቸው ይገባል። በዚህ ረገድ ወሳኙ የትምህርቱ መብዛትና ማነስ አይደለም። የቱንም ያህል ብዙ ቢሆኑ በጥቂት ዋና ዋና ነጥቦች ሥር በሚገባ ከፋፍለህ ካቀረብካቸውና እነዚህን ዋና ዋና ነጥቦች ተራ በተራ ካብራራህ ንግግርህ ለመከታተል የማያስቸግር ከመሆኑም ሌላ ቶሎ አይረሳም።
ዋና ዋና ነጥቦችህ ጎልተው ይታዩ። የተዘጋጀሃቸው ነጥቦች በሥርዓት የተደራጁ ከሆኑ በንግግርህ ውስጥ ያላቸው ቦታ ጉልህ ሆኖ ይታያል።
በዋናው ነጥብ ላይ ያተኮሩ ማስረጃዎችን፣ ጥቅሶችንና ሌሎች ሐሳቦችን ማቅረብ ዋናው ነጥብ ጎላ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ የሚያስችል መሠረታዊ ዘዴ ነው። ሌሎቹ ንዑስ ነጥቦች በሙሉ ዋናውን ነጥብ የሚያብራሩ፣ የሚያጠናክሩ ወይም የሚያጎሉ ሊሆኑ ይገባል። ጥሩ እንደሆነ ስለተሰማህ ብቻ ከነጥቡ ጋር የማይሄድ ሐሳብ አትጥቀስ። ንዑሳን ነጥቦቹን ስታብራራ ዋናውን ነጥብ እንዴት እንደሚደግፉ ግልጽ ልታደርግ ይገባል። አድማጮች አስበው ይድረሱበት ብለህ ልትተወው አይገባም። የዋናውን ነጥብ ቁልፍ ቃላት ወይም ፍሬ ነገር አለፍ አለፍ እያልክ በመድገም በዋናውና በንዑስ ነጥቡ መካከል ያለውን ዝምድና ግልጽ ማድረግ ትችላለህ።
አንዳንድ ተናጋሪዎች ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች በቁጥር በመዘርዘር ጎላ ብለው እንዲታዩ ያደርጋሉ። ይህ ዘዴ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለማጉላት የሚረዳህ ቢሆንም ነጥቦቹን በጥንቃቄ መምረጥና አሳማኝ በሆነ ቅደም ተከተል ማደራጀትህ ግድ ነው።
ወደ ማብራሪያው ከመግባትህ በፊት ዋና ዋና ነጥቦችህን መጀመሪያ ላይ መዘርዘር ትፈልግ ይሆናል። ይህም አድማጮችህ ትምህርቱን በጉጉት እንዲጠብቁ ከማድረጉም በላይ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ጉልህ ሆነው እንዲታዩ ይረዳል። ነጥቡን በሚገባ አብራርተህ ከጨረስክ በኋላ በአጭሩ በመከለስ ይበልጥ ልታጎላው ትችላለህ።
በአገልግሎት። ከላይ የተወያየንባቸውን ሐሳቦች ለንግግር ብቻ ሳይሆን ለአገልግሎትም ይሠራሉ። ለአገልግሎት ስትዘጋጅ በአካባቢህ ያሉትን ሰዎች በጣም የሚያሳስባቸውን አንድ ጉዳይ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን ተስፋ እንደያዘ ለመግለጽ የሚያስችልህን አንድ ጭብጥ ምረጥ። ከዚያም ጭብጡን ለማዳበር የሚረዱህን ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ልትመርጥ ትችላለህ። እነዚህን ነጥቦች የሚደግፉ ጥቅሶች አዘጋጅ። ከዚያ ውይይቱን ምን ብለህ እንደምትጀምር አስብ። በዚህ መንገድ ከተዘጋጀህ በውይይቱ ወቅት ነጥቦችህን እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከል ትችላለህ። የምታነጋግረውም ሰው ነጥቡን ለማስታወስ ቀላል ይሆንለታል።