የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • sg ጥናት 27 ገጽ 133-138
  • አርዕስቱንና ዋና ዋና ነጥቦችን ማጉላት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አርዕስቱንና ዋና ዋና ነጥቦችን ማጉላት
  • ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • **********
  • ጭብጡን ማዳበር
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
sg ጥናት 27 ገጽ 133-138

ጥናት 27

አርዕስቱንና ዋና ዋና ነጥቦችን ማጉላት

1–4. የንግግር አርዕስት ምን ማለት እንደሆነ ግለጽ።

1 እያንዳንዱ ንግግር አቅጣጫ ይዞ እንዲጓዝና ሁሉንም ክፍሎች አንድ ላይ አስሮ መልክ እንዲያስይዝ ከተፈለገ የተወሰነ አርዕስት እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህ አርዕስት የያዘው መልዕክት ንግግሩን ከዳር እስከ ዳር ይሞላዋል። አርዕስቱ የንግግሩ ጭብጥ ነው። ምናልባት በአንድ ዓረፍተ ነገር መልክ ሊቀመጥ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም እያንዳንዱን የትምህርቱን ገጽታ ያካተተ ነው። የንግግሩ አርዕስት ለሁሉም አድማጮች ግልጽ መሆን ይኖርበታል፤ እንዲህ ሊሆን የሚችለው ግን በደንብ ካስጨበጥካቸው ነው።

2 የአንድ ንግግር አርዕስት ሁሉንም ነገሮች የሚዳስስ ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ አይደለም። ለምሳሌ “እምነት” የሚለው ቃል ብቻውን የንግግር አርዕስት ሊሆን አይችልም። ከዚህ ይልቅ የተወሰነ መልዕክት ለማስተላለፍ ርዕሰ ጉዳዩን ከአንድ አቅጣጫ ማብራራት ወይም ማስፋፋት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል የንግግሩ አርዕስት “እምነትህ እስከምን ድረስ ይሄዳል?” ወይም “አምላክን ለማስደሰት እምነት ያስፈልጋል” ወይም “የእምነት መሠረት” ወይም “በእምነት እያደጋችሁ ሂዱ” የሚል ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን እነዚህ አርዕስት ሁሉ በእምነት ላይ ያተኮሩ ቢሆኑም እያንዳንዱ ርዕሰ እምነትን ከተለያየ አቅጣጫ ይመለከተዋል። ስለሆነም እያንዳንዱ አርዕስት የተለየ መሥመር ተከትሎ ንግግሩን ማስፋፋትን ይጠይቃል።

3 አንዳንድ ጊዜ አርዕስቱን ከመምረጥህ በፊት ነጥቦችን ማሰባሰብ ሊያስፈልግህ ይችላል። ነገር ግን የንግግሩን አስተዋጽኦ ከማዘጋጀትህ ወይም ዋና ዋና ነጥቦችን ከመምረጥህ በፊት አርዕስቱ መወሰን ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መርተህ በጨረስክ ቁጥር ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ገለጻ ለማድረግ ትፈልግ ይሆናል። ይህ ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ ነው። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመርኩዘህ ምን ሐሳብ ማቅረብ እንዳለብህ ለመወሰን የአድማጮችህን ሁኔታና የንግግርህን ዓላማ ማሰብ ይኖርብሃል። ከዚህ በመነሣት አርዕስቱን ትመርጣለህ። አንድን አዲስ ሰው አገልግሎት ለማስጀመር እየሞከርህ ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ እንደሚከተሉ ማስረዳት እንዳለብህ ትወስን ይሆናል። ይህ የንግግርህ አርዕስት ይሆናል። በዚያ ወቅት የምታቀርበው ሐሳብ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ ከዚህ አንጻር የሚዳስስ ይሆናል።

4 በንግግርህ ውስጥ አርዕስቱን በደንብ ማስጨበጥ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ያሰብከውን ነገር የሚያሟላ ትክክለኛ አርዕስት መምረጥ ይኖርብሃል። ይህም በቅድሚያ መዘጋጀትን ይጠይቃል። አንድ አርዕስት መርጠህ በዚያ ላይ የተመሠረተ ንግግር ካዘጋጀህና ያን አስተዋጽኦ ተከትለህ ንግግር ከሰጠህ አርዕስቱ ቁልጭ ብሎ መታየቱ አይቀርም። ሆኖም ንግግሩን ስታቀርብ በአርዕስቱ ውስጥ ያሉትን ቁልፍ ቃላት ወይም ፍሬ ነገሮች አልፎ አልፎ በመጥቀስ አርዕስቱን በደንብ ማስያዝ ትችላለህ።

5, 6. የንግግሩ አርዕስት ተስማሚ መሆኑን ለመወሰን የምትችለው እንዴት ነው?

5 ተስማሚ አርዕስት። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ተስማሚ አርዕስት የመምረጥ ችግር አይኖርብህም፤ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ የንግግሩ አርዕስት ተወስኖ ይሰጥሃል። ይሁን እንጂ ንግግር እንድታቀርብ ስትጠየቅ ሁልጊዜ እንደዚያ ያለ ሁኔታ አያጋጥምህም። ስለዚህ የንግግርን አርዕስት ጉዳይ በጥንቃቄ መመርመሩ ጥሩ ነው።

6 አንድን የንግግር አርዕስት ተስማሚ የሚያደርገው ምንድን ነው? ሦስት አራት ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል። አድማጮችህን፣ ለማከናወን ያሰብከውን ዓላማ እንዲሁም እንድትሸፍነው የተመደበልህ ጽሑፍ ካለ እርሱንም ጭምር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ጎልቶ የሚታይ አርእስት ከሌለ ምናልባት ንግግርህን በአንድ ማዕከላዊ ሐሳብ ዙሪያ አልገነባኸው ይሆናል። ለንግግሩ አርዕስት ምንም አስተዋጽኦ የማያደርጉ ብዙ ነጥቦች በንግግሩ ውስጥ አካተህ ሊሆን ይችላል።

7, 8. አርዕስቱን ማጉላት የሚቻልባቸውን መንገዶች ግለጽ።

7 የአርዕስቱን ቃላት ወይም ሐሳብ መደጋገም። የንግግሩ ክፍሎች በሙሉ አርዕስቱን በማጉላት ረገድ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ የሚቻልበት አንዱ መንገድ የአርዕስቱን ቃላት ወይም ማዕከላዊ ሐሳብ መደጋገም ነው። በሙዚቃ ላይ መላልሶ የሚሰማ የአዝማቹ ዜማ አለ። ይህ ዜማ በጠቅላላው የሙዚቃ ቅንብር ውስጥ ይገኛል። ተደጋግሞ ስለሚሰማም አብዛኛውን ጊዜ ገና ሲጀምር ወዲያው ይታወቃል። ይህ የአዝማቹ ዜማ ሁልጊዜ በአንድ ዓይነት ድምፅ አይቀርብም። አንዳንድ ጊዜ የዜማው አንድ ወይም ሁለት ዓይነት ድምፅ ብቻ ይሰማል፤ ብዙ ጊዜም ትንሽ ለወጥ ብሎ ይቀርባል። የሙዚቃው አቀናባሪ በዚያም ሆነ በዚህ የአዝማቹን ዜማ በሙዚቃው ውስጥ በብልሃት አቀነባብሮ ያስገባውና የጠቅላላው ሙዚቃ መታወቂያ እስኪሆን ድረስ በተደጋጋሚ ይሰማል።

8 የአንድ ንግግር አርዕስትም እንደዚሁ መሆን አለበት። በአንድ የሙዚቃ ቅንብር ውስጥ እንዳለ ተደጋጋሚ ዜማ ሁሉ ቁልፍ የሆኑት ቃላት ወይም ዋናው ሐሳብም ይደጋገማል። የአርዕስቱን አቀራረብ ትንሽ ለወጥ ለማድረግ በተመሳሳይ ቃላት ወይም አነጋገር መጠቀም ይቻላል። ይህን ዘዴ እስኪሰለች ድረስ ሳይሆን ሳይበዛ ከተጠቀምክበት አርዕስቱ የጠቅላላው ንግግር መታወቂያ ምልክት እስኪሆን ድረስ ይደምቃል፤ እንዲሁም አድማጮችህ ይዘውት የሚሄዱት ጭብጥ ይሆናል።

**********

9–13. የአንድ ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች ምን ማለት እንደሆኑ ግለጽ። በምሳሌ አስረዳ።

9 የንግግርህ አርዕስት ምን መሆን እንዳለበት ከወሰንክ በኋላ በዝግጅትህ ውስጥ የምትወስደው የሚቀጥለው ርምጃ ንግግሩን በየትኞቹ ዋና ነጥቦች አዋቅረህ ማስፋፋት እንዳለብህ መምረጥ ይሆናል። በንግግር ምክር መስጫው ቅጽህ ውስጥ ይህ ጉዳይ “ዋና ዋና ነጥቦችን መለያየት” ተብሎ ተጠቅሷል።

10 የንግግር ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው? እግረ መንገድህን የምትጠቅሳቸው ደስ የሚሉ ሐሳቦች ወይም ነጥቦች አይደሉም። በተወሰነ ርዝመት የሚስፋፉ የንግግሩ ዐበይት ክፍሎች ናቸው። የምግብ ሸቀጥ ባለበት ሱቅ ውስጥ በየመደርደሪያው ላይ እንደተለጠፉት ጽሑፎች ወይም ምልክቶች ናቸው። ጽሑፉ ወይም ምልክቱ ያ መደርደሪያ ምን ነገር እንደያዘ ለመለየት የሚረዳ ሲሆን በዚያ ውስጥ ምን ዓይነት ዕቃ መቀመጥ እንዳለበት ወይም እንደሌለበት ይወስናል። ለምሳሌ ያህል ጥራጥሬ የሚል ጽሑፍ በተለጠፈበት መደርደሪያ ውስጥ ማርና ማርማላታ መገኘት የለባቸውም፤ ቢገኙ ግን ሰውን ያደናግራሉ። ሻይና ቡና የሚል ጽሑፍ ባለበት መደርደሪያ ላይ ሩዝ ቦታው አይደለም። ዕቃው ከመከመሩ ወይም በላይ በላዩ ከመጫኑ የተነሣ የመደርደሪያው ጽሕፈት በግልጽ ሊታይ ካልቻለ ምንም ነገር ማግኘት አስቸጋሪ ይሆናል። ምልክቶቹ በግልጽ መታየት ከቻሉ ግን ገበያተኛው ከፊቱ ምን ዕቃ እንዳለ ወዲያው ማወቅ ይችላል። የንግግርህ ዋና ነጥቦች ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። እነዚህ ዋና ነጥቦች ሊስተዋሉና በአእምሮ ውስጥ ሊቀመጡ እስከቻሉ ድረስ አድማጮችህ እስከ ንግግሩ መደምደሚያ ድረስ ብዙም ማስታወሻ መውሰድ ሳያስፈልጋቸው አንተን ለመከታተል አይቸገሩም።

11 ሌላም ጉዳይ አለ። የትኞቹን ዋና ነጥቦች መምረጥና መጠቀም እንዳለብህ የሚወስነው የአድማጮችህ ሁኔታና የንግግርህ ዓላማ ነው። በዚህ ምክንያት የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ትክክለኛ ዋና ነጥቦች መምረጥህን የሚገመግመው ቀደም ብሎ ራሱ የትኞቹ ጉዳዮች ዋና ነጥቦች መሆን እንዳለባቸው ወስኖ በመምጣት ሳይሆን ተማሪው የመረጣቸውን ዋና ነጥቦች እንዴት እንደተጠቀመባቸው መሠረት በማድረግ መሆን ይኖርበታል።

12 መቅረት የማይችሉትን ነጥቦች ብቻ ምረጥ። ስለዚህ አንድን ነጥብ መቅረት የማይችል እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው? እያልክ ራስህን ጠይቅ። ይህ ነጥብ ባለመኖሩ የንግግርህ ዓላማ የሚኰላሽ ከሆነ ነጥቡ መቅረት አይችልም ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ስለ ቤዛ ምንም አውቀት ለሌለው ሰው ቤዛን የተመለከተ ውይይት ማድረግ ቢኖርብህ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሰው እንደነበረ ማስረዳቱ አስፈላጊ ይሆናል። አለበለዚያ የመሥዋዕቱን ተመጣጣኝነት ማስረዳት የማይቻል ነገር ይሆናል። ስለዚህ ይህን ነገር በንግግርህ ውስጥ ከዋና ዋናዎቹ ነጥቦች አንዱ አድርገህ ትወስደዋለህ ማለት ነው። ነገር ግን የሥላሴ ትምህርት ሐሰት እንደሆነ ለዚህ ሰው ቀደም ሲል አረጋግጠህለት ከነበረ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ስለመምጣቱ የምትሰጠው ማብራሪያ አስፈላጊነቱ ሁለተኛ ደረጃ ብቻ ይሆናል፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል ተቀብሎታል። በተጨማሪም በዚህ ምክንያት የተነሣ የኢየሱስ ቤዛ ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው መሆኑን ማስረዳት ቀላል ይሆናል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ኢየሱስ ሰብአዊ አካል እንደነበረው ማስረዳቱ መቅረት የማይችል ነገር አይደለም ማለት ነው።

13 ስለዚህ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ። ስለዚህ ጉዳይ አድማጮቼ ቀደም ሲል ምን ያውቃሉ? የንግግሬ ዓላማ ግቡን እንዲመታ ከምን ተነሥቼ ማስረዳት ይኖርብኛል? የመጀመሪያውን ጥያቄ መልስ የምታውቅ ከሆነ የሁለተኛውን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ነጥቦችህን ካሰባሰብክ በኋላ እነርሱን በማንገዋለል በአድማጮችህ ዘንድ የታወቁትን ሐሳቦች ለጊዜው ወደ ጎን ትተውና ቀሪዎቹን ነጥቦች በዓይነት በዓይነታቸው በመደልደል ጥቂት ክፍሎች ብቻ እንዲቀሩ ማድረግ አለብህ። እነዚህ ቀሪ ክፍሎች ለአድማጮችህ ምን መንፈሳዊ ምግብ እንደምታቀርብ የሚጠቁሙ ምልክቶች ይሆኑልሃል። እነዚህ ምልክቶች ወይም ዋና ነጥቦች በፍጹም መድበስበስ ወይም መሰወር የለባቸውም። ፍንትው ብለው መታየት ያለባቸው ዋና ነጥቦችህ ናቸው።

14–17. ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ማብዛት የማይኖርብን ለምን እንደሆነ ግለጽ።

14 ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች አይብዙ። በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ መቅረት የማይችሉት ነጥቦች ጥቂት ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ በአንድ እጅ ላይ ባሉት ጣቶች ሊቆጠሩ ይችላሉ። ነጥቦቹን ለማቅረብ የተመደበው ጊዜ የቱንም ያህል ረጅም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይሆንም። ብዙ ነጥቦች ጎልተው እንዲታዩ ለማድረግ አትሞክር። ይህ ብዙዎችን የሚያጋጥም ወጥመድ ነው። የምግብ ሸቀጥ የሚያቀርብ ሱቅ ከመጠን በላይ ሲሰፋ የዕቃዎቹ ዓይነት እንደዚሁ ብዛት ይኖራቸዋል። ስለዚህ ሰዎቹ የፈለጉትን ዕቃ ጠይቀው ለማግኘት ይገደዳሉ። የአድማጮችህ አእምሮ በአንድ ስብሰባ ላይ ብዙ ዓይነት ሐሳቦችን ለመቀበል ያለው አቅም የተወሰነ ነው። ንግግርህ ረጅም ከሆነም ይበልጥ ቀለል ባለ መንገድ መቅረብ ይኖርበታል። ቁልፍ የሆኑት ነጥቦችህም ይበልጥ መደርጀትና ቁልጭ ብለው መታየት አለባቸው። ስለዚህ አድማጮችህ ከአቅማቸው በላይ ብዙ ነገሮችን በአእምሮአቸው እንዲይዙ ለማድረግ አትሞክር። አድማጮችህ የግድ ይዘዋቸው መሄድ እንዳለባቸው የተሰሙህን ነጥቦች ምረጥ። ከዚያ በኋላ ጊዜህን በሙሉ ስለነዚህ ነጥቦች በመናገር አሳልፍ።

15 ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች መብዛት አለመብዛታቸውን የሚወስነው ምንድን ነው? በቀላሉ ለመግለጽ ያህል አንዱ ሐሳብ ቢቀርና አሁንም የንግግርህ ዓላማ ግቡን የሚመታ ከሆነ ያ ነጥብ ቁልፍ ነጥብ አይደለም ማለት ነው። ንግግርህን በይበልጥ የተሟላ ለማድረግ ያን ነጥብ እንደ ማያያዣ ወይም ማስታወሻ አድርገህ ልትጠቀምበት ትችላለህ።

16 ሌላም ነገር አለ። እያንዳንዱን ነጥብ በተሳካ ሁኔታ አስፋፍተህ ለመግለጽና ለመደምደም በቂ ጊዜ እንዲኖርህ ያስፈልጋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሐሳብ መቅረብ ካለበት አድማጮች የሚያውቋቸውን ነጥቦች ከአስተዋጽኦው በጣም ቀንስ። ለአድማጮች አዲስ ከሆኑት ሐሳቦች በስተቀር ሌሎቹን ሁሉ አበጥረህ አውጣ። የቀሩትን ነጥቦች ግን አድማጮች እንደማይረሷቸው አድርገህ ግልጽ አድርጋቸው።

17 በመጨረሻም ንግግርህ ያልተደነጋገረ፣ በቀላሉ መንገድ የቀረበ መሆን አለበት። ይህም ሁልጊዜ በትምህርቱ ብዛት ላይ የተመካ አይደለም። ችግሩ የነጥቦችህ አለመቀነባበር ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ወደ አንድ ሱቅ ብትገባና ሁሉም ዕቃ ወለሉ ላይ ተከምሮ ብታይ መላ ቅጡ የጠፋበትና አደናጋሪ ይሆንብሃል። ምንም ነገር ለማግኘት ትቸገራለህ። ነገር ግን ሁሉም ነገር በሥርዓት ቢቀመጥና ተመሳሳይ ዕቃዎች አንድ ላይ ቢደረደሩ እንዲሁም መደርደሪያው የጽሑፍ ምልክት ቢለጠፍበት ለዓይን ደስ ከማለቱም ሌላ የተፈለገውን ዕቃ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። አንተም በተመሳሳይ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን በጥቂት ዋና ዋና ነጥቦች ሥር በመደርደር ንግግርህን ቀላል አድርገው።

18. ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች መቅረብ ያለባቸው እንዴት ነው?

18 ዋና ዋና ሐሳቦችን ለየብቻ ማስፋፋት። እያንዳንዱ ዋና ሐሳብ ነጠል ብሎ መቀመጥ ይኖርበታል። እያንዳንዱ ለየብቻው መስፋፋት አለበት። ይህም ሲባል ግን በንግግርህ መግቢያ ወይም መደምደሚያ ላይ የንግግሩን ዋና ዋና ርዕሶች ጨምቀህ ልታቀርብ አትችልም ማለት አይደለም። በንግግሩ ሐተታ ላይ ግን በአንድ ጊዜ ስለ አንድ ዋና ሐሳብ ብቻ መናገር አለብህ። አንዳንድ ጊዜ ብቻ ሐሳቦችን ለማያያዝ ወይም ለማጉላት ስትል ከኋላ ያሉትን ነጥቦች ማምጣት ትችላለህ። አርዕስታዊ አስተዋጽኦ ማዘጋጀትን መማርህ ዋና ዋና ነጥቦችን ለየብቻ ለማስፋፋት ከፍተኛ ርዳታ ያደርግልሃል።

19–21. ንዑስ ነጥቦችን ልንጠቀምባቸው የሚገባን እንዴት ነው?

19 ንዑስ ነጥቦች በዋናዎቹ ሐሳቦች ላይ ያተኩራሉ። ለማስረጃነት የሚቀርቡ ነጥቦች፣ ጥቅሶች ወይም ሌሎች ነጥቦች በዋናው ሐሳብ ላይ ማተኮርና እርሱን ማዳበር ይኖርባቸዋል።

20 በምትዘጋጅበት ጊዜ ንዑስ ነጥቦችን አንድ በአንድ አመዛዝናቸው። ከዚያም ዋና ነጥቡን ለማብራራት፣ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ወይም ለማዳበር በቀጥታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ነጥቦች ብቻ አስቀር። ምንም ለውጥ የማያመጣ ነጥብ ካለ መውጣት አለበት። ቁም ነገሩን ከማደነጋገር አልፎ የሚፈይደው ነገር የለም።

21 ከዋናው ሐሳብ ጋር ተዛማጅነት ያለው ማንኛውም ነጥብ አንተ ከምትናገረው ሐሳብ ጋር በቀጥታ መያያዝ አለበት። ሁለቱን ሐሳቦች ማያያዙን ለአድማጮች አትተወው። የሚያገናኛቸውን ነገር ግልጽ አድርገው። ያ ተዛማጅነት ምን እንደሆነ ተናገር። ሳይነገር የቀረ ነገር አብዛኛውን ጊዜ ለሰሚው ግልጽ አይሆንም። ይህንን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን ዋናውን ሐሳብ የሚገልጹ ቁልፍ ቃላትን መድገም ወይም የዋናውን ነጥብ ሐሳቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ መደጋገም ትችላለህ። ንዑስ ነጥቦች በዋናዎቹ ሐሳቦች ላይ እንዲያተኩሩ የማድረግንና እያንዳንዱን ዋና ነጥብ ከንግግሩ አርዕስት ጋር የማስተሳሰርን ጥበብ ካዳበርክ በየጊዜው የምትሰጣቸው ንግግሮች ያልተወሳሰቡና ጥሩ መልክ ያላቸው ስለሚሆኑ ለማቅረብ የሚቀሉና ቶሎ የማይረሱ ይሆናሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ