ጥናት 36
ጭብጡን ማዳበር
ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎች አንድ ጭብጥ ይዞ መናገር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ያውቃሉ። ንግግር በሚዘጋጁበት ጊዜ በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ብቻ በማተኮር በዚያ ላይ በጥልቀት እንዲያሰላስሉ ይረዳቸዋል። ይህም ብዙ ነጥቦችን ላይ ላዩን ጠቅሰው ከማለፍ ይልቅ አድማጮቻቸውን ይበልጥ በሚጠቅም መንገድ ትምህርቱን ለማዳበር ያስችላቸዋል። እያንዳንዱ ዋና ነጥብ ከጭብጡ ጋር የተያያዘና ጭብጡን የሚያዳብር በሚሆንበት ጊዜ አድማጮች ነጥቦቹን ለማስታወስና የተጠቀሱበትን ዓላማ ለመገንዘብ ቀላል ይሆንላቸዋል።
ጭብጡ የንግግርህ ርዕሰ ጉዳይ ነው ሊባል ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ የንግግርህ ጭብጥ የርዕሰ ጉዳዩ አንድ ነጥብ ብቻ መሆኑን ከተገነዘብህ ጥሩ ንግግር መስጠት ትችላለህ። የአምላክ መንግሥት፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትንሣኤ ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ብዙ ጭብጥ ሊወጣ ይችላል። ጥቂት ምሳሌዎችን እንጥቀስ:- “የአምላክ መንግሥት እውን መስተዳድር ነው፣” “የአምላክ መንግሥት ምድርን ገነት ያደርጋል፣” “መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአምላክ መንፈስ እርዳታ ነው፣” “መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን የሚሆን ጠቃሚ መመሪያ ነው፣” “የትንሣኤ ተስፋ በሐዘን የተደቆሱትን ያጽናናል” እንዲሁም “የትንሣኤ ተስፋ ስደት ሲያጋጥመን እንድንጸና ይረዳናል።” እነዚህን ሁሉ ጭብጦች የምናዳብርበት አቅጣጫ የተለያየ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር መጥቶ ሲያገለግል በስብከቱ ጎላ አድርጎ የገለጸው “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” የሚለውን ጭብጥ ነው ይህ ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ጋር ይስማማል። (ማቴ. 4:17) ይህ ጭብጥ እየተብራራና ግልጽ እየሆነ የሄደው እንዴት ነው? በአራቱ ወንጌሎች ውስጥ ስለ አምላክ መንግሥት ከ110 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። ይሁንና ኢየሱስ “መንግሥት” የሚለውን ቃል ደጋግሞ በመጥቀስ ብቻ አልተወሰነም። ትምህርቶቹም ሆኑ የፈጸማቸው ተዓምራት ይሖዋ መንግሥቱን የሚሰጠው የአምላክ ልጅና መሲሕ እርሱ መሆኑን የሚያረጋግጡ ነበሩ። በእርሱ አማካኝነት ሌሎችም የመንግሥቱ ወራሽ የመሆን አጋጣሚ እንደሚያገኙ ግልጽ አድርጓል። ይህንን መብት የሚያገኙ ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየት እንዳለባቸውም አስተምሯል። ባስተማራቸው ትምህርቶችና በፈጸማቸው ድንቅ ተዓምራት አማካኝነት የአምላክ መንግሥት የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት እንዴት እንደሚነካ ያሳየ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አጋንንትን ማውጣቱም ‘የአምላክ መንግሥት ወደ አድማጮቹ እንደደረሰች’ የሚያረጋግጥ መሆኑን አስረድቷል። (ሉቃስ 11:20) ኢየሱስ ተከታዮቹን ስለዚህ መንግሥት እንዲመሰክሩ አዝዟቸዋል።—ማቴ. 10:7፤ 24:14
ተስማሚ ጭብጥ። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳለው አንድን ጭብጥ በሰፊው ማብራራት አይጠበቅብህም። ሆኖም ለንግግርህ ተስማሚ ጭብጥ መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው።
ጭብጡን የምትመርጠው አንተ ከሆንክ በመጀመሪያ የንግግርህ ዓላማ ምን እንደሆነ አስብ። በንግግርህ አስተዋጽኦ ውስጥ የምታካትታቸው ዋና ዋና ነጥቦች የመረጥከውን ጭብጥ የሚደግፉ መሆን ይኖርባቸዋል።
ጭብጡ ከተሰጠህ ትምህርቱን ከምን አቅጣጫ ማዳበር እንዳለብህ ለማወቅ በደንብ ልታጤነው ይገባል። ጭብጡ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነና እንዴት ሊዳብር እንደሚችል በደንብ ለመረዳት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። የተሰጠህን ጭብጥ ለማዳበር የሚረዱትን ነጥቦች የምትመርጠው አንተ ከሆንክ ጭብጡ እንዳይድበሰበስ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል። በሌላ በኩል ደግሞ ጭብጡን የሚያዳብሩት ነጥቦች ቀርበውልህ ከሆነ ከጭብጡ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዴት እንደምትጠቀምባቸው ማጤን ያስፈልግሃል። እንዲሁም ትምህርቱ ለአድማጮችህ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና የምታቀርብበት ዓላማም ምን እንደሆነ ማሰብ ይኖርብሃል። ይህ በንግግርህ አጽንዖት የምትሰጣቸውን ነጥቦች ለመምረጥ ይረዳሃል።
ጭብጡን ማጉላት የሚቻልበት መንገድ። ጭብጡን በተገቢው መንገድ ለማጉላት መሠረት መጣል ያለብህ ገና ነጥቦችህን ስትመርጥና ስታዋቅር ነው። ጭብጡን የሚደግፉ ነጥቦችን ብቻ ከተጠቀምህና ጥሩ አስተዋጽኦ ማዘጋጀት የሚቻልበትን መመሪያ ከተከተልህ ያለችግር ልታጎላው እንደምትችል የታወቀ ነው።
መደጋገም ጭብጡ ይበልጥ ጎላ ብሎ እንዲታይ ሊረዳ ይችላል። ጭብጥ እየተደጋገመ እንደሚመጣ የአንድ ዘፈን አዝማች ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። አዝማቹ የሚደገመው በተመሳሳይ መንገድ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አንድ ወይም ሁለት ሐረግ ብቻ ይደገም ይሆናል ወይም አዝማቹ ትንሽ ለውጥ ብቻ ይኖረዋል። ያም ሆነ ይህ የሙዚቃው አቀናባሪ አዝማቹ የሙዚቃው አካል ሆኖ እንዲዘልቅ ያደርጋል። የአንድ ንግግር ጭብጥም እንዲሁ መሆን አለበት። የጭብጡን ቁልፍ ቃላት መደጋገምን በዘፈን ውስጥ አለፍ አለፍ እያለ ከሚመጣው አዝማች ጋር ማመሳሰል ይቻላል። እነዚህን ቃላት በተመሳሳይ ቃላት እየተኩ መናገር ወይም ጭብጡን ትንሽ ለወጥ አድርጎ መግለጽ በተለያየ መንገድ ለመደጋገም ያስችላል። እንዲህ ካደረግህ ጭብጡ በአድማጮች አእምሮ ውስጥ ተቀርጾ ይቀራል።
እነዚህን ሐሳቦች ንግግር ስታቀርብ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ላይም ልትሠራባቸው ትችላለህ። ውይይቱ አጠር ያለ ቢሆንም እንኳ ጭብጡ ጎልቶ እንዲታይ ከተደረገ ሐሳቡ ቶሎ አይረሳም። መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና ጭብጡን ካጎላን ትምህርቱ በቀላሉ የሚታወስ ይሆናል። ተስማሚ ጭብጥ ለመምረጥና ያንን ለማዳበር የምታደርገው ጥረት ንግግር የመስጠትና የአምላክን ቃል የማስተማር ችሎታህን በማሻሻል ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።