የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 30 ገጽ 186-ገጽ 189 አን. 4
  • ለሰዎች አሳቢነት ማሳየት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለሰዎች አሳቢነት ማሳየት
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሰዎች ጋር የመወያየት ችሎታህን ማሻሻል
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ልብ ለመንካት መጣር
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • የትምህርቱን ጥቅም ግልጽ ማድረግ
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • ደቀ መዛሙርት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስን ኮርጅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 30 ገጽ 186-ገጽ 189 አን. 4

ጥናት 30

ለሰዎች አሳቢነት ማሳየት

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ሰዎች ሐሳባቸውን ሲገልጹ በቁም ነገር እንደምትከታተል ወይም ስለ ደህንነታቸው እንደምታስብ አሳይ።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ያሳየንን ፍቅር መኮረጅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ከመሆኑም ሌላ የሰዎችን ልብ ለመንካት ያስችለናል።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች በምንናገርበት ጊዜ ዓላማችን እንዲሁ እውቀት እንዲኖራቸው መርዳት ብቻ አይደለም። ልባቸውን መንካት ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ለአድማጮቻችን ልባዊ አሳቢነት ማሳየት ነው። እንዲህ ያለውን አሳቢነት ማሳየት የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ።

የአድማጮችህን አመለካከት ግምት ውስጥ አስገባ። ሐዋርያው ጳውሎስ የአድማጮቹን ባሕልና አስተሳሰብ ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። እንዲህ ሲል አስረድቷል:- “አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፣ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፣ ያለ እግዚአብሔር ሕግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፣ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ። በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ።” (1 ቆሮ. 9:​20-23) ታዲያ ዛሬ “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ” ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?

ሰዎችን ከማነጋገርህ በፊት አንዳንድ ሁኔታዎችን ለማስተዋል ትንሽ ጥረት እንኳ ካደረግህ ፍላጎታቸውና ሁኔታቸው ምን እንደሆነ የሚጠቁሙ ነገሮች ማግኘትህ አይቀርም። ሥራቸው ምን እንደሆነ መገመት ትችላለህ? ስለ እምነታቸው የሚጠቁም ነገር አስተውለሃል? ስለ ቤተሰብ ሕይወታቸውስ ምን ተገንዝበሃል? ከተመለከትኸው ሁኔታ አንጻር መግቢያህን ለእነርሱ እንደሚስማማ አድርገህ ማስተካከል ትችላለህ?

አቀራረብህ ይበልጥ ማራኪ እንዲሆን በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ምን ብለህ እንደምታነጋግር አስቀድመህ መዘጋጀት ያስፈልግሃል። በአንዳንድ አካባቢዎች በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ ያሉትን የውጭ አገር ዜጎችም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ የውጭ አገር ዜጎች የሚኖሩ ከሆነ ለእነርሱ ውጤታማ በሆነ መንገድ መመሥከር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ተዘጋጅተሃል? አምላክ ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና እውነትን እንዲያውቁ’ ስለሚፈልግ ለምታገኛቸው ሰዎች ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት ማራኪ በሆነ መንገድ የማቅረብ ግብ ሊኖርህ ይገባል።​—⁠1 ጢሞ. 2:​3, 4

በጥሞና አዳምጥ። ይሖዋ ሁሉን ማወቅ የሚችል ቢሆንም ሌሎች ሲናገሩ ያዳምጣል። ይሖዋ አንድን ጉዳይ በተመለከተ መላእክቱ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያመጡ ሲጠይቃቸው ነቢዩ ሚክያስ በራእይ ተመልክቷል። ከዚያም አንዱ መልአክ ያመጣውን የመፍትሔ ሐሳብ ራሱ እንዲያስፈጽም ልኮታል። (1 ነገ. 22:​19-22) አብርሃም በሰዶም ላይ የሚወሰደውን የቅጣት እርምጃ በተመለከተ ያደረበትን ስጋት ሲገልጽ ይሖዋ በደግነት አዳምጦታል። (ዘፍ. 18:​23-33) እኛስ በምናገለግልበት ጊዜ በማዳመጥ ረገድ የይሖዋን ምሳሌ እንደምንኮርጅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ሌሎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አበረታታ። ተስማሚ ጥያቄ ከጠየቅህ በኋላ መልስ እንዲሰጡ ልትፈቅድላቸው ይገባል። ሲናገሩ ከልብ አዳምጣቸው። በአሳቢነት የምታዳምጣቸው ከሆነ በነፃነት ለመናገር ይገፋፋሉ። ከንግግራቸው ይበልጥ ትኩረታቸውን የሚስበው ነገር እንዳለ ከተገነዘብህ በዘዴ ተጨማሪ ጥያቄዎችን አንሳ። ይበልጥ ስለ እነርሱ ለማወቅ ጣር። ይህ ማለት ግን ስለ ግል ሕይወታቸው አንድ በአንድ መመርመር አለብህ ማለት አይደለም። ከልብ ለማመስገን የሚያስችል ምክንያት ካገኘህ ስለሰጡት ሐሳብ አመስግናቸው። በተናገሩት ሐሳብ የማትስማማ እንኳ ቢሆን ምን ማለት እንደፈለጉ መረዳትህን ከመግለጽ ወደኋላ ማለት የለብህም።​—⁠ቆላ. 4:​6

ይሁን እንጂ ለሰዎች የምናሳየው አሳቢነት ከገደብ እንዳያልፍ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለሰዎች አሳቢነት እናሳያለን ማለት በግል ጉዳያቸው ውስጥ እንገባለን ማለት አይደለም። (1 ጴጥ. 4:​15) ተቃራኒ ፆታ ያለው ሰው በደግነት ተነሳስተን የምናሳየውን አሳቢነት በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዳው መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለአንድ ሰው የምታሳየው አሳቢነት ተገቢ የሚሆነው እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ ከአገር አገር አልፎ ተርፎም ከሰው ሰው ስለሚለያይ ማስተዋል ያስፈልጋል።​—⁠ሉቃስ 6:​31

አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ ጥሩ አዳማጭ ለመሆን ይረዳል። የምንናገረውን ነገር በደንብ የምናውቀው ከሆነ ሰውዬውን ዘና ብለን በጥሞና ልናዳምጠው እንችላለን። ይህም እንዲረጋጉ ከማስቻሉም ሌላ ከእኛ ጋር የመወያየት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ ይችላል።

ሰዎችን ማዳመጥ ለእነርሱ ያለንን አክብሮት የሚያረጋግጥ ነው። (ሮሜ 12:​10) የሚሰጡትን ሐሳብ እንደማንንቅና ለስሜታቸውም እንደምንጠነቀቅ ያሳያል። እኛም የምንናገረውን ነገር በጥሞና እንዲከታተሉ ሊያነሳሳቸው ይችላል። የአምላክ ቃል ‘ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ይሁን’ በማለት የሚመክረን ያለ ምክንያት አይደለም።​—⁠ያዕ. 1:​19

እድገት እንዲያደርጉ እርዳቸው። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ስናገኝ ስለ እነርሱ እንድናስብና ተመልሰን በመሄድ ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈልጋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንድናካፍላቸው የሚገፋፋን ለሰዎች ያለን አሳቢነት ነው። ዳግመኛ ተመልሰህ ለመሄድ ስታስብ ከዚህ በፊት ስለ እነርሱ የተገነዘብካቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል። እነርሱን በሚያሳስባቸው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተዘጋጅተህ ሂድ። እየተማሩት ያለው ነገር እንዴት እንደሚጠቅማቸው በግልጽ እንዲያስተውሉ እርዳቸው።​—⁠ኢሳ. 48:​17

የምታነጋግረው ሰው የሚያስጨንቀው አንድ ሁኔታ ወይም ችግር እንዳለ ካጫወተህ በዚህ አጋጣሚ ምሥራቹን ንገረው። የተጨነቁ ሰዎችን አይቶ የማያልፈውን የኢየሱስን ምሳሌ ተከተል። (ማር. 6:​31-34) ቸኩለህ ‘ለምን እንዲህ አታደርግም’ ማለት ወይም ያልታሰበበት ምክር መስጠት የለብህም። እንዲህ ብታደርግ ከልብ ስለ እርሱ እንደማታስብ ሊሰማው ይችላል። ከዚህ ይልቅ ራስህን በእርሱ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክር። (1 ጴጥ. 3:​8) ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ተጠቅመህ ምርምር በማድረግ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችለውን ምክር አካፍለው። በሌላ በኩል ለሰውዬው ያለህ ፍቅራዊ አሳቢነት ለአንተ ያጫወተህን የግል ምሥጢሩን ሳያስፈልግ ለሌሎች ከመንዛት እንድትቆጠብም ያደርግሃል።​—⁠ምሳሌ 25:​9

በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ ለምናስጠናቸው ሰዎች ልባዊ አሳቢነት ልናሳይ ይገባል። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከምን አንፃር እገዛ እንደሚያስፈልገው በቁም ነገር ማሰብና ይህንኑ ጉዳይ ግምት ውስጥ በማስገባት መዘጋጀት ይኖርብሃል። ‘እሱ ወይም እሷ የማያቋርጥ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ቀጥሎ ምን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸዋል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። የምታስጠናው ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሉ እንዲያስተውል እርዳው። (ማቴ. 24:​45) አንዳንድ ጊዜ ማብራሪያ መስጠቱ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዴት ሊሠራባቸው እንደሚችል ለማስረዳት በተግባር ጭምር ማሳየት ያስፈልግህ ይሆናል።​—⁠ዮሐ. 13:​1-15

ሰዎች ሕይወታቸውን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ እንዲመሩ ለመርዳት ስንጥር ማስተዋል ሊኖረን ይገባል። የእያንዳንዳቸው አስተዳደግና ችሎታ የተለያየ ስለሚሆን መንፈሳዊ እድገት የሚያደርጉበትም ፍጥነት ይለያያል። ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር መጠበቅ የለብህም። (ፊልጵ. 4:​5 NW ) በሕይወታቸው ለውጥ እንዲያደርጉ ለማስገደድ አትሞክር። ለውጥ የሚያደርጉት በአምላክ ቃልና በመንፈሱ ተገፋፍተው መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ ሰዎች እንዲያገለግሉት የሚፈልገው በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት ነው። (መዝ. 110:​3 አ.መ.ት ) የግል ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲገጥማቸው የራስህን አመለካከት እንዳታስተላልፍ እንዲሁም በእነርሱ ቦታ ሆነህ ውሳኔ እንዳታደርግ መጠንቀቅ ይኖርብሃል።​—⁠ገላ. 6:​5

እርዳታ መስጠት። ኢየሱስ አብልጦ ያስብ የነበረው ስለ አድማጮቹ መንፈሳዊ ደህንነት ቢሆንም የሚያስፈልጓቸውን ሌሎች ነገሮች ችላ አላለም። (ማቴ. 15:​32) በቁሳዊ ነገር ለመርዳት ብዙም አቅም ባይኖረን እንኳን እርዳታ መስጠት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች ይኖራሉ።

ለሰዎች አሳቢነት እንድናሳይ የሚገፋፋን ችግራቸውን እንደ ራሳችን ችግር አድርገን መመልከታችን ነው። ለምሳሌ ያህል የምታነጋግረው ሰው የአየሩ ሁኔታ እንዳልተስማማው ካስተዋልህ ቦታ ልትቀይሩ ወይም ሌላ ቀጠሮ ይዛችሁ ልትለያዩ ትችላላችሁ። ጎረቤትህ ወይም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያሳየ ሰው ከታመመ ወይም ሆስፒታል ከገባ ካርድ በመላክ ወይም አጭር ደብዳቤ በመጻፍ አለዚያም ሄደህ በመጠየቅ አሳቢነትህን አሳይ። ከቻልክ ምግብ ይዘህ ልትጠይቀው ወይም ሌላ የሚፈልገውን ነገር ልታደርግለት ትችላለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እድገት እያደረጉ ሲሄዱ እንደ በፊቱ ከድሮ ጓደኞቻቸው ጋር ስለማይቀራረቡ ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። እንደ ጓደኛ አድርገህ አቅርባቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ በኋላም ይሁን በሌላ ጊዜ የምትጫወቱበት አጋጣሚ ሊኖር ይገባል። ጥሩ ባልንጀሮች እንዲያፈሩ አበረታታቸው። (ምሳሌ 13:​20) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ እርዳቸው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከሚሰጠው ትምህርት ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ አብረሃቸው ልትቀመጥና ልጆቻቸውን በመያዝ ልትረዳቸው ያስፈልጋል።

ከልብ የመነጨ አሳቢነት አሳያቸው። ለሌሎች አሳቢ መሆን በልምድ የምታዳብረው ዘዴ ሳይሆን ከልብ የሚመነጭ ባሕርይ ነው። ከልብ የመነጨ መሆን አለመሆኑ በተለያዩ መንገዶች ይገለጻል። የምናዳምጥበት መንገድና የምንናገረው ነገር የአሳቢነታችንን ጥልቀት የሚያረጋግጥ ነው። ለሌሎች በምናሳየው ደግነትና አዘኔታም ይገለጻል። ምንም ባንናገርና ምንም ባናደርግ እንኳ በሁኔታችንና ፊታችን ላይ በሚነበበው ስሜት ይንጸባረቃል። ሰዎች የምናስብላቸው ከሆነ ይህን በቀላሉ ማስተዋል አይቸገሩም።

ለሰዎች ልባዊ አሳቢነት እንድናሳይ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት የሰማያዊ አባታችንን ፍቅርና ምህረት ለመኮረጅ ያለን ፍላጎት ነው። ይህም አድማጮቻችን ይሖዋን እንዲወድዱና መልእክቱን እንዲቀበሉ ይረዳቸዋል። እንግዲያው ምሥራቹን ለሌሎች ስታካፍል “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስታውስ።​—⁠ፊልጵ. 2:4

ከልብ የመነጨ አሳቢነት ማሳየት የሚቻልበት መንገድ

  • ሰውዬው ሲናገር በጥሞና አዳምጥ። አመለካከቱን በመግለጹ አመስግነው። ሐሳቡን ይበልጥ በግልጽ መረዳት እንድትችል አንዳንድ ጥያቄዎች ጠይቀው።

  • ከተለያያችሁ በኋላ ስለ ሰውዬው አስብ። ብዙ ሳትቆይ ተመልሰህ ሂድ።

  • እርሱን ይበልጥ ስለሚያሳስበው ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ንገረው።

  • አሁንም ይሁን ወደፊት የሚያስፈልገውን ነገር ግምት ውስጥ በማስገባት ጠቃሚ እገዛ አድርግለት።

መልመጃ፦ (1) የጉባኤ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ለአንድ ሰው አሳቢነት ለማሳየት ሞክር። ሰላምታ ከመስጠት አልፈህ ከእርሱ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ ጥረት አድርግ። ይህ የዘወትር ልማድህ ሊሆን ይገባል። (2) በአገልግሎት ለምታገኘው ሰው አሳቢነት አሳይ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መመስከርህ ብቻ በቂ አይሆንም። ስለ ሰውዬው ይበልጥ ለማወቅ ሞክር። የምትናገረውም ሆነ የምታደርገው ነገር ስለ እርሱ ካገኘኸው ግንዛቤ ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ፈልግ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ