ጥናት 33
በአነጋገር ዘዴኛ መሆን
ዘዴኛ ሰው ሌሎችን ሳያስቀይም ተስማምቶ መኖር ይችላል። እንዴትና መቼ መናገር እንዳለበት ያውቃል። ይህ ማለት ግን ሌሎችን ላለማስቀየም ሲል ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ ይላል ወይም ሐቁን ያዛባል ማለት አይደለም። ዘዴኛ መሆንና ሰውን መፍራት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።—ምሳሌ 29:25
ዘዴኛ ለመሆን ዋናው መሠረቱ የመንፈስ ፍሬ ማፍራት ነው። በመሆኑም ፍቅር ያለው ሰው ሌሎችን መርዳት እንጂ ማስቆጣት አይፈልግም። ደግና የዋህ ሰው ሁሉንም ነገር የሚያደርገው በእርጋታና በማስተዋል ነው። ሰላማዊ የሆነ ሰው ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረው ይጥራል። ታጋሽ የሆነ ሰው መጥፎ ነገር ቢያደርጉበት እንኳ አይበሳጭም።—ገላ. 5:22, 23
ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በየትኛውም መንገድ ቢቀርብላቸው የሚቆጡ ሰዎች ይኖራሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ አይሁዳውያን ልባቸው ክፉ ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የእንቅፋት ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት’ ሆኖባቸዋል። (1 ጴጥ. 2:7, 8) የአምላክን መንግሥት የመስበክ ሥራውን አስመልክቶ ሲናገር “በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ” ብሏል። (ሉቃስ 12:49) ስለ ይሖዋ መንግሥት እየተነገረ ያለው መልእክት ዛሬም ቢሆን ሰዎች ምላሽ ሊሰጡበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የሰው ልጅ የፈጣሪውን ሉዓላዊነት መቀበል አለበት የሚለው ሐቅ የዚህ መልእክት አንዱ ክፍል ነው። የአምላክ መንግሥት ዛሬ ያለውን ክፉ ዓለም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ያጠፋዋል የሚለው መልእክት ብዙ ሰዎችን ያስቆጣቸዋል። እኛ ግን አምላክ ባዘዘን መሠረት መስበካችንን እንቀጥላለን። ይሁን እንጂ “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አንዘነጋም።—ሮሜ 12:18
ስንመሰክር በአነጋገራችን ዘዴኛ መሆን። ለሌሎች ስለ እምነታችን የምንናገርባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። አገልግሎት ወጥተን ከሰዎች ጋር የምንነጋገር ቢሆንም ለዘመዶቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን እንዲሁም አብረውን ለሚማሩ ልጆች መመስከር የምንችልበትን አጋጣሚ መፈለጋችን አይቀርም። በእነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች በአነጋገራችን ዘዴኛ መሆን ያስፈልገናል።
ሰዎች የሚያምኑበትን ነገር በሚያጣጥል መንገድ የመንግሥቱን መልእክት ልንነግራቸው ብንሞክር መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። ልታነጋግራቸው የሄድከው እነርሱ ጠይቀውህ ወይም የአንተ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተሰምቷቸው አይደለም። ስለዚህ ማስተካከል ያለባቸው ነገር እንዳለ ብትነግራቸው ሊበሳጩ ይችላሉ። የተሳሳተ ስሜት እንዳናሳድርባቸው ምን ማድረግ እንችላለን? በወዳጅነት መንፈስ የመወያየት ችሎታ ማዳበር ለዚህ ሊረዳ ይችላል።
የሰውዬውን ትኩረት የሚስብ ርዕሰ ጉዳይ በማንሳት ውይይት ለመጀመር ሞክር። ግለሰቡ ዘመድህ፣ የሥራ ባልደረባህ ወይም አብሮህ የሚማር ልጅ ከሆነ ትኩረቱን የሚስበው ምን እንደሆነ ታውቅ ይሆናል። ሰውዬውን ከዚያ ቀደም አግኝተኸው የማታውቅ እንኳ ቢሆን በዜና የሰማኸውን ወይም በጋዜጣ ያነበብከውን ጉዳይ በማንሳት ውይይቱን መጀመር ትችል ይሆናል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ ርዕሰ ጉዳዮች ብዙ ሰዎችን የሚያሳስቡ ናቸው። ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ንቁ ሆነህ አንዳንድ ነገሮችን ለማስተዋል ሞክር። ቤት ውስጥ ያሉ ጌጣጌጦች፣ ግቢው ውስጥ የሚታዩ መጫዎቻዎች፣ ሃይማኖታዊ ቁሳቁሶች፣ መኪናቸው ላይ የተለጠፉ ነገሮች ትኩረታቸውን የሚስበው ምን እንደሆነ ሊጠቁሙህ ይችላሉ። ከሰውዬው ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ ሐሳቡን ሲገልጽ አዳምጠው። የሚሰነዝረው ሐሳብ ስለ እርሱ አመለካከት ወይም ዝንባሌ የነበረህን ግምት ሊያጠናክርልህ አሊያም እንድታስተካክል ሊያደርግህ ይችላል። እንዲሁም ለዚህ ሰው ለመመስከር ምን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለብህ እንድታስተውል ይረዳሃል።
በምትወያዩበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ውስጥ ያገኘሃቸውን ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር የሚዛመዱ ነጥቦች አካፍለው። ሆኖም አንተ ብቻ ተናጋሪ አትሁን። (መክ. 3:7) ሐሳቡን ለመግለጽ ፈቃደኛ ከሆነ እርሱም እንዲናገር ጋብዘው። ሐሳቡንና አስተያየቱን ሲገልጽ በጥሞና አዳምጠው። ይህም በምን ረገድ ዘዴኛ መሆን እንደሚያስፈልግህ ፍንጭ ሊሰጥህ ይችላል።
ከመናገርህ በፊት ሰውዬው እንዴት ሊሰማው እንደሚችል አስብ። ምሳሌ 12:8 [NW ] ‘በአንደበቱ አስተዋይ’ የሆነን ሰው ያወድሳል። እዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራበት የዕብራይስጡ አገላለጽ አርቆ ማሰብና ብልህነት የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ማስተዋል የሚለው ቃል አንድ ሰው ጥበብ የጎደለው ነገር ላለማድረግ ሲል በጉዳዩ ላይ በጥሞና በማሰብ ከአንደበቱ መቆጠቡን ያመለክታል። የዚሁ ምዕራፍ 18ኛ ቁጥር [አ.መ.ት ] ‘እንደ ሰይፍ ከሚዋጋ የግዴለሽነት አነጋገር’ እንድንቆጠብ ያስጠነቅቃል። ሰዎችን ሳናስከፋ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በትክክል ማስተላለፍ እንችላለን።
የምትጠቀምባቸውን ቃላት በማስተዋል መምረጥ ብቻ ለውይይታችሁ እንቅፋት የሚሆን ነገር እንዳይፈጠር ለማድረግ ሊረዳህ ይችላል። የምታነጋግረው ሰው “መጽሐፍ ቅዱስ” የሚለው ቃል ሲጠራ ደስ የማይለው ከሆነ “ቅዱሳን መጻሕፍት” ወይም “ዛሬ ከ2, 000 በሚበልጡ ቋንቋዎች የታተመ አንድ መጽሐፍ” ልትል ትችል ይሆናል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የምትጠቅስ ከሆነ ሰውዬው ያለውን አስተያየት ልትጠይቅና የእርሱን አመለካከት ግምት ውስጥ በማስገባት ልታወያየው ትችላለህ።
በአነጋገር ዘዴኛ መሆን ብዙውን ጊዜ መቼ መናገር እንዳለብህ ማሰብንም ይጠይቃል። (ምሳሌ 15:23) ሰውዬው በሚናገረው ሁሉ ትስማማለህ ማለት ባይሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ ሐሳብ በሰነዘረ ቁጥር ሁሉንም ማረም አያስፈልግህም። በአንድ ጊዜ ሁሉንም ለመንገር አትሞክር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፣ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም” ብሏቸዋል።—ዮሐ. 16:12
የምታነጋግራቸውን ሰዎች እንደ አስፈላጊነቱ ከልብ አመስግናቸው። ግለሰቡ ተከራካሪ እንኳ ቢሆን እንድታመሰግነው የሚያደርግ ሐሳብ ይሰነዝር ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴና አርዮስፋጎስ ከነበሩ ፈላስፎች ጋር ሲነጋገር ያደረገው ይህንኑ ነው። ፈላስፋዎቹ “ይከራከሩት ነበር።” ታዲያ መልእክቱን እነርሱን በማያስቆጣ መንገድ ማስተላለፍ የቻለው እንዴት ነው? ትንሽ ቀደም ብሎ ለአማልክቶቻቸው የሠሯቸውን ብዙ መሠዊያዎች ተመልክቶ ነበር። የአቴናን ሰዎች በጣዖት አምላኪነታቸው ከማውገዝ ይልቅ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን በመጥቀስ አመስግኗቸዋል። “በማናቸውም ረገድ በጣም ሃይማኖተኞች መሆናችሁን አያለሁ” ብሏቸዋል። ይህን ማድረጉም ስለ እውነተኛው አምላክ የሚገልጸውን መልእክት ለማስተላለፍ አስችሎታል። ከዚህም የተነሣ አንዳንዶቹ ክርስትናን ተቀብለዋል።—ሥራ 17:18, 22, 34 አ.መ.ት
የተቃውሞ ሐሳብ ሲያነሳ ስሜታዊ አትሁን። ረጋ በል። ስለ ሰውዬው አመለካከት የበለጠ ለማወቅ የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ አድርገህ ተመልከተው። አመለካከቱን ስለገለጸልህ ልታመሰግነው ትችል ይሆናል። “የራሴ ሃይማኖት አለኝ” በማለት መወያየት እንደማይፈልግ ቢገልጽልህስ? “ከልጅነትዎ ጀምሮ ሃይማኖተኛ ነበሩ ማለት ነው?” ብለህ በዘዴ ልትጠይቀው ትችል ይሆናል። የሚሰጠውን መልስ ካዳመጥህ በኋላ “ሁሉም ሰው በአንድ ሃይማኖት ሥር የሚሰባሰብበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልዎታል?” ብለህ ጠይቀው። ይህም ውይይቱን ለመቀጠል በር ሊከፍት ይችላል።
ስለ ራሳችን ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት መያዛችን በአነጋገር ዘዴኛ ለመሆን ይረዳናል። የይሖዋ መንገድ ጽድቅ፣ ቃሉም እውነት ስለመሆኑ ሙሉ እምነት አለን። ስለ እነዚህ ነገሮች የምንናገረው እርግጠኛ ሆነን ነው። ይሁን እንጂ ራሳችንን የምናመጻድቅበት ምንም ምክንያት የለም። (መክ. 7:15, 16) እውነትን በማወቃችንና የይሖዋን በረከት በማግኘታችን አመስጋኞች ነን። ይሁን እንጂ የይሖዋን ሞገስ ያገኘነው በራሳችን ጽድቅ ሳይሆን ይገባናል በማንለው የእርሱ ደግነትና በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት አማካኝነት እንደሆነ እንገነዘባለን። (ኤፌ. 2:8, 9) ‘በእምነት እየኖርን እንደሆነና እንዳልሆነ ራሳችንን መመርመርና መፈተን’ እንዳለብን አንዘነጋም። (2 ቆሮ. 13:5) ስለዚህ የአምላክን ትእዛዝ መፈጸም አስፈላጊ መሆኑን ለሌሎች ስናስረዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለእኛም ጭምር እንደሚሠራ አድርገን በትሕትና እንናገራለን። በሰዎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን አልተሰጠንም። ይሖዋ ‘ፍርድን ሁሉ የሰጠው ለወልድ’ ስለሆነ ሁላችንም በእርሱ የፍርድ ወንበር ፊት ቆመን መልስ እንሰጣለን።—ዮሐ. 5:22፤ 2 ቆሮ. 5:10
ከቤተሰባችንና ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት። ዘዴኛ መሆን ያለብን አገልግሎት ላይ ብቻ አይደለም። ዘዴኛ መሆን የመንፈስ ፍሬ ነጸብራቅ ስለሆነ ከቤተሰብ አባሎቻችን ጋር ባለን ግንኙነትም ልናሳየው የሚገባ ባሕርይ ነው። ፍቅር ለሌሎች ስሜት እንድንጠነቀቅ ያደርገናል። ንግሥት አስቴር ባሏ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ባይሆንም ለእርሱ አክብሮት የነበራት ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ አገልጋዮችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ወደ እርሱ የምታቀርበው በማስተዋል ነበር። (አስቴር ምዕ. 3-8) ከማያምኑ የቤተሰብ አባሎቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ዘዴኛ ለመሆን ስንል አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነታችን በቃል ከመግለጽ ይልቅ አኗኗራችን ስለ እውነት እንዲመሰክር ልናደርግ እንችላለን።—1 ጴጥ. 3:1, 2
በተመሳሳይም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች በደንብ ስለምናውቃቸው ብቻ እንደፈለግን ወይም ደግነት በጎደለው መንገድ እናነጋግራቸዋለን ማለት አይደለም። ጎልማሳ ስለሆኑ ምንም አይጎዱም ብለን ማሰብ አይኖርብንም። “እኔ እንግዲህ ባሕርዬ ነው” የሚል ሰበብ ማቅረብ የለብንም። አነጋገራችን ሌሎችን እንደሚያስቀይም ከተገነዘብን ለውጥ ለማድረግ መጣር ይኖርብናል። ‘እርስ በርስ አጥብቀን መዋደዳችን’ ‘ለእምነት ወንድሞቻችን መልካም እንድናደርግ’ ሊያነሳሳን ይገባል።—1 ጴጥ. 4:8, 15፤ ገላ. 6:10
ንግግር ስትሰጥ። ንግግር የሚሰጡም ቢሆኑ በአነጋገራቸው ዘዴኛ መሆን ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ አድማጭ አስተዳደጉና ሁኔታው የተለያየ ነው። መንፈሳዊ እድገታቸውም እንዲሁ የተለያየ ነው። አንዳንዶቹ ስብሰባ ላይ ሲገኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ሊሆን ይችላል። ሌሎቹ ደግሞ ተናጋሪው የማያውቀው የሚያሳስባቸው ችግር ይኖር ይሆናል። አንድ ተናጋሪ አድማጮቹን እንዳያስከፋ ምን ሊረዳው ይችላል?
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በሰጠው ምክር መሠረት ‘በማንም ላይ ክፉ ላለመናገርና ለሰው ሁሉ የዋህነትን ለማሳየት’ ጥረት አድርግ። (ቲቶ 3:1-3) ሌላውን ዘር፣ ቋንቋ ወይም ብሔር የሚያንቋሽሸውን የዓለም የአነጋገር ዘይቤ መኮረጅ የለብህም። (ራእይ 7:9, 10) የይሖዋ ትእዛዛት ምን እንደሆኑ በግልጽ ልትናገርና ትእዛዛቱን ማክበር ምን ጥቅም እንዳለው ቁልጭ አድርገህ ልታስረዳ ትችላለህ። ይሁን እንጂ ገና ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መንገድ መመላለስ ያልጀመሩትን ሰዎች የሚያንኳስስ ነገር መናገር የለብህም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲያስተውሉና እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር እንዲያደርጉ አበረታታቸው። የምትሰጠው ምክር ከልብ የመነጨ ምስጋና የታከለበት ሊሆን ይገባል። አነጋገርህና የድምፅህ ቃና እርስ በርስ ሊኖረን የሚገባውን የጠበቀ የወንድማማች መዋደድ የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል።—1 ተሰ. 4:1-12፤ 1 ጴጥ. 3:8