ጥናት 41
በቀላሉ የሚገባ
ስትናገር መልእክቱን ማስተላለፍህ ብቻ በቂ አይሆንም። አድማጮች በቀላሉ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ለማቅረብ መጣር ይኖርብሃል። ይህም ለወንድሞችም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ንግግር ስታቀርብ ሐሳብህን ጥሩ አድርገህ ለመግለጽ ይረዳሃል።
አንድ ንግግር ለአድማጮች በቀላሉ የሚገባ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ “ትምህርቱን መልክ ባለው መንገድ ማዋቀር” በሚለው ጥናት 26 ውስጥ ተገልጸዋል። “ለሰዎች አሳቢነት ማሳየት” በሚለው ጥናት 30 ውስጥም የተብራሩ አሉ። በዚህ ጥናት ውስጥም ጥቂት ተጨማሪ ነጥቦች ይብራራሉ።
ለመረዳት የማያስቸግሩ ቃላትና ቀላል የሆነ አቀራረብ። ለመረዳት የማያስቸግሩ ቃላትንና አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን መጠቀም ሐሳብን ጥሩ አድርጎ ለመግለጽ ይረዳል። የኢየሱስ የተራራ ስብከት አንድን ንግግር ማንኛውም ሰው በቀላሉ ሊረዳው በሚችል መንገድ እንዴት ማቅረብ እንደሚቻል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። ሐሳቡ ለአድማጮቹ አዲስ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ይናገር የነበረው ደስተኛ መሆን፣ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት፣ ጭንቀትን መቋቋምና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ስለሚቻልበት መንገድ ነው። እነዚህ ደግሞ ማንኛውንም ሰው የሚያሳስቡ ጉዳዮች ስለሆኑ ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ንግግሩን በቀላሉ መረዳት ይችላሉ። የተናገረበትም መንገድ ቢሆን በጣም ግልጽ ነበር። (ማቴ. ምዕ. 5-7) እርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያየ ርዝማኔና ብዙ ዓይነት አወቃቀር ያላቸው ዓረፍተ ነገሮች ይገኛሉ። ዓረፍተ ነገሩ ምንም ዓይነት ይሁን ምን ዋናው ቁም ነገር ሐሳቡ ግልጽና ለመረዳት የማያስቸግር ሆኖ መቅረቡ ነው።
ትምህርቱ ከባድ እንኳ ቢሆን አቀራረብህ ቀላል ከሆነ አድማጮች ሐሳቡን ለመረዳት አይቸገሩም። አቀራረብህን ቀላል ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አላስፈላጊ ዝርዝር ሐሳብ አታብዛ። ዋና ዋና ነጥቦችህን የሚያጎሉ ሐሳቦችን ብቻ ተጠቀም። የምትጠቀምባቸውን ቁልፍ ቃላት ምረጥ። ጥቅስ በጥቅስ ላይ ከማደራረብ ይልቅ የመረጥካቸውን ጥቅሶች እያነበብህ በደንብ አብራራ። ብዙ አላስፈላጊ ሐሳብ በመጠቀም ቁም ነገሩ እንዲድበሰበስ አታድርግ።
መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠናም እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ልትሠራባቸው ትችላለህ። ተማሪው ዋናው ነጥብ እንዲገባው አድርግ እንጂ እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር ለማብራራት አትሞክር። አንዳንዶቹን ዝርዝር ሐሳቦች ወደፊት የግል ጥናት ሲያደርግና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኝ ይማራቸዋል።
አንድን ትምህርት ቀላል አድርጎ ለማቅረብ ጥሩ ዝግጅት ያስፈልጋል። ትምህርቱ ለአድማጮችህ ግልጽ እንዲሆንላቸው ከፈለግህ በቅድሚያ ለአንተ ለራስህ ግልጽ ሊሆንልህ ይገባል። አንድን ጉዳይ በደንብ ካወቅኸው ምክንያቱን ጭምር ማስረዳት ትችላለህ። በራስህ አባባል ለመግለጽም አትቸገርም።
እንግዳ የሆኑ ቃላትን ትርጉም ማስረዳት። ንግግሩ በቀላሉ የሚገባ እንዲሆን አንዳንድ ጊዜ እንግዳ የሆኑ ቃላትን ትርጉም ለአድማጮች ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። አድማጮችህ ሁሉን ነገር እንደሚያውቁት በማሰብ ችላ ማለትም ሆነ አያውቁትም ብለህ እያንዳንዱን ነገር ለማብራራት መሞከር የለብህም። ‘ቀሪዎች፣’ “ታማኝና ልባም ባሪያ፣” “ሌሎች በጎች” እንዲሁም “እጅግ ብዙ ሰዎች” የሚሉት መግለጫዎች ምን ማለት እንደሆኑ እስካላብራራን ድረስ ለአዲሶች ግልጽ ላይሆንላቸው ይችላል። (ሮሜ 11:5፤ ማቴ. 24:45፤ ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 7:9) በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮችን ድርጅት በቅርብ የማያውቁ ሰዎች “አስፋፊ፣” “አቅኚ፣” “የወረዳ የበላይ ተመልካች” እንዲሁም “የመታሰቢያው በዓል” የሚሉትን ቃላት ላይረዷቸው ይችላሉ።
የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ጭምር ማብራራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ይኖራል። ብዙ ሰዎች “አርማጌዶን” የሚለው ቃል የኑክሌር እልቂትን የሚያመለክት ይመስላቸዋል። “የአምላክ መንግሥት” የሚለውን ቃል ሲሰሙ እውን መስተዳደር እንደሆነ አድርገው ከማሰብ ይልቅ በሰው ልብ ውስጥ ካለ ሐሳብ ወይም ከሰማያዊ ክንውን ጋር ብቻ ያያይዙት ይሆናል። “ነፍስ” የሚለው ቃል ደግሞ ሰው ሲሞት ከሥጋ ተለይታ የምትሄድን ረቂቅ መንፈሳዊ አካል እንደሚያመለክት ሊያስቡ ይችላሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “መንፈስ ቅዱስን” የሚረዱት ራሱን የቻለ ስብዕና ያለው የሥላሴ አካል እንደሆነ አድርገው ነው። ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ሕግጋት ስለማይመሩ መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ማብራራት ያስፈልግ ይሆናል።—1 ቆሮ. 6:18
መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብቡ ሰዎች ካልሆኑ “ጳውሎስ እንደጻፈው” ወይም “ሉቃስ እንደተናገረው” ብትል ስለ እነማን እየተናገርህ እንዳለህ ላይገባቸው ይችላል። ስለዚህ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ “ሐዋርያው” ወይም “ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ” የሚል መግለጫ መጠቀም ያስፈልግህ ይሆናል።
ዛሬ ያሉ አድማጮች ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ጥንታዊ መለኪያዎች ወይም አንዳንድ ልማዶች ለመረዳት ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል የኖኅ መርከብ ርዝመቷ 300 ክንድ፣ ወርድዋ 50 ክንድ፣ ከፍታዋ 30 ክንድ ነበር የሚለው መግለጫ ብዙም ግልጽ ላይሆንላቸው ይችላል። (ዘፍ. 6:15) ሆኖም አድማጮችህ የመርከቧን ግዝፈት በቀላሉ በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ የሚረዳ መግለጫ ልትጠቀም ትችላለህ።
በቂ ማብራሪያ ስጥ። ጉዳዩ ለአድማጮች ግልጽ እንዲሆን የአንድን ቃል ትክክለኛ ትርጉም መናገሩ ብቻ አይበቃም። በዕዝራ ዘመን ሕጉ ለሕዝቡ ከተነበበ በኋላ ይብራራላቸው ነበር። ሕዝቡ የሚነበበውን ነገር እንዲረዳ ሌዋውያኑ የሕጉን ትርጉምና እንዴት መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ያብራሩ ነበር። (ነህ. 8:8, 12) አንተም እንዲሁ አንድ ጥቅስ ስታነብብ ትርጉሙን ማብራራትና ለአድማጮች ያለውን ጠቀሜታ በደንብ ማስረዳት ይኖርብሃል።
ኢየሱስ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተነገሩት ትንቢቶች በእርሱ ላይ እንደተፈጸሙ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ግልጽ አድርጎላቸዋል። ስለ እነዚህ ነገሮች የመመሥከር ኃላፊነት እንዳለባቸውም ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ሉቃስ 24:44-48) ሰዎች የሚማሩት ነገር ይበልጥ ግልጽ የሚሆንላቸው ትምህርቱ በእነርሱ ሕይወት ውስጥ ያለውን ሚና እንዲያስተውሉ ስትረዳቸው ነው።
የልብ ዝንባሌ ወሳኝ ነው። የምትሰጠው ማብራሪያ ግልጽ ሊሆን ቢችልም ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ላይቀበሉት ይችላሉ። አንድ ሰው ሐሳቡን መቀበል የማይፈልግ ከሆነ ምን ማለት እንደተፈለገ ማስተዋል ሊሳነው ይችላል። (ማቴ. 13:13-15) ሁሉንም ነገር በሰብዓዊ ዓይን የሚመለከቱ ሰዎች መንፈሳዊ ነገር አይዋጥላቸውም። (1 ቆሮ. 2:14) አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካለው ለጊዜውም ቢሆን ውይይቱን ማቋረጡ የተሻለ ይሆናል።
ሆኖም አንዳንዶች በሕይወታቸው ከገጠማቸው መጥፎ ሁኔታ የተነሣ የምንነግራቸውን መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በተደጋጋሚ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚሰሙበት አጋጣሚ ካገኙ ልባቸው ሊለወጥ ይችላል። ኢየሱስ እንደሚገረፍና እንደሚገደል ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው ምን ማለቱ እንደነበር አላስተዋሉም። ለምን? ይህ ጨርሶ የማይጠብቁትና የማይፈልጉትም ነገር ስለነበር ነው። (ሉቃስ 18:31-34) ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ አሥራ አንዱ ሐዋርያት ኢየሱስ ባስተማራቸው መንገድ በመመላለስ ይህን ጉዳይ እንደተገነዘቡ አሳይተዋል።
ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚያስገኘው ውጤት። ሰዎች ጉዳዩ ይበልጥ ግልጽ የሚሆንላቸው በቃል ስንነግራቸው ብቻ ሳይሆን በተግባር ስናሳያቸው ጭምር ነው። ብዙ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንግሥት አዳራሽ ስለመጡበት ጊዜ ሲያስቡ ቶሎ ትዝ የሚላቸው በዚያ ያስተዋሉት እውነተኛ ፍቅር እንጂ የሰሙት ንግግር አይደለም። በተመሳሳይም በአገልግሎት ስንሰማራ ፊታችን ላይ የሚነበበው ደስታ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲቀበሉ ረድቷቸዋል። የይሖዋ አገልጋዮች እርስ በርስ ያላቸውን ፍቅር እንዲሁም ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች የሚያደርጉትን ደግነት በመመልከት አንዳንዶች እውነተኛውን ሃይማኖት የያዙት እነርሱ ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። እንግዲያው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያስተውሉ ለመርዳት ስትጥር ስለምታብራራበት መንገድ እንዲሁም ራስህ ምሳሌ ሆነህ ስለ መገኘትህ ልታስብ ይገባል።