ምዕራፍ 6
‘ኃያል ተዋጊ የሆነው ይሖዋ’—ለማጥፋት የሚጠቀምበት ኃይል
1-3. (ሀ) እስራኤላውያን ምን አስፈሪ ሁኔታ ገጥሟቸው ነበር? (ለ) ይሖዋ ለሕዝቦቹ የተዋጋው እንዴት ነው?
እስራኤላውያን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ምሕረት የለሹ የግብፅ ሠራዊት አሳድዶ ሊደመስሳቸው ከኋላ በመገስገስ ላይ ነው።a ወደፊት ሸሽተው እንዳያመልጡ ቀይ ባሕር አለ። ዙሪያ ገባው ደግሞ ቀጥ ያለ ተራራ ነው። ይሁንና ሙሴ ተስፋ እንዳይቆርጡ እያበረታታቸው ነው። “ይሖዋ ራሱ ስለ እናንተ ይዋጋል” በማለት ዋስትና ሰጣቸው።—ዘፀአት 14:14
2 ሆኖም ሙሴ ወደ ይሖዋ ሳይጮኽ አልቀረም። በዚህም የተነሳ አምላክ “ለምን ወደ እኔ ትጮኻለህ? . . . በትርህን አንሳና እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር፤ ባሕሩንም ክፈለው” አለው። (ዘፀአት 14:15, 16) ከዚያ በኋላ የተፈጸመውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይሖዋ ወዲያውኑ መልአኩን በማዘዝ የደመናው ዓምድ ከእስራኤላውያን ኋላ እንዲቆም አደረገ፤ ይህ የደመና ዓምድ እንደ ግድግዳ ሆኖ ግብፃውያኑን በመጋረድ ግስጋሴያቸውን ገትቶት መሆን አለበት። (ዘፀአት 14:19, 20፤ መዝሙር 105:39) ሙሴ እጁን ሲዘረጋ ኃይለኛ ነፋስ መጥቶ ባሕሩን ለሁለት ከፈለው። ውኃው ወደ በረዶነት የተለወጠ ያህል ረግቶ እንደ ግድግዳ በመቆሙ መላው የእስራኤል ሕዝብ ወለል ብሎ በተከፈተው ደረቅ መሬት ተሻገረ!—ዘፀአት 14:21፤ 15:8
3 ፈርዖን ይህን ተአምር ሲመለከት ወታደሮቹ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ማዘዝ ነበረበት። ይሁን እንጂ ትዕቢተኛው ፈርዖን ወታደሮቹ ጥቃት ለመሰንዘር ወደፊት እንዲገሰግሱ ትእዛዝ ሰጠ። (ዘፀአት 14:23) ግብፃውያኑ እስራኤላውያንን በማሳደድ ወደተከፈለው ባሕር ተንደርድረው ገቡ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ የሠረገሎቻቸው መንኮራኩሮች በመወላለቃቸው ትርምስምሳቸው ወጣ። እስራኤላውያን ሙሉ በሙሉ ከተሻገሩ በኋላ ይሖዋ ሙሴን “ውኃው በግብፃውያን፣ በጦር ሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ተመልሶ እንዲመጣባቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር” ሲል አዘዘው። እንደ ግድግዳ ቆሞ የነበረው ውኃ ተደርምሶ ፈርዖንንና ሠራዊቱን አሰጠማቸው!—ዘፀአት 14:24-28፤ መዝሙር 136:15
4. (ሀ) ይሖዋ በቀይ ባሕር ባከናወነው ነገር ምን ዓይነት አምላክ መሆኑን አሳይቷል? (ለ) ይህ አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ምን እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል?
4 አምላክ በቀይ ባሕር አጠገብ እስራኤላውያንን ለማዳን የወሰደው እርምጃ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከፈጸማቸው አስደናቂ ክንውኖች መካከል አንዱ ነው። በዚህም ይሖዋ “ኃያል ተዋጊ” መሆኑን አሳይቷል። (ዘፀአት 15:3) ይሁን እንጂ ይሖዋ ተዋጊ አምላክ መሆኑን ማወቅህ ስለ እሱ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ጦርነት በሰው ልጆች ላይ ብዙ መከራና ሥቃይ እንዳስከተለ አይካድም። አምላክ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሆኑ ወደ እሱ ከመቅረብ ይልቅ እንድትሸሸው ያደርግሃል?
ይሖዋ በቀይ ባሕር “ኃያል ተዋጊ” መሆኑን አሳይቷል
መለኮታዊ ጦርነት ከሰብዓዊ ግጭቶች ጋር ሲነጻጸር
5, 6. (ሀ) ይሖዋ “የሠራዊት ጌታ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መለኮታዊ ጦርነት ሰዎች ከሚያደርጉት ጦርነት የሚለየው እንዴት ነው?
5 አምላክ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሁለት መቶ ስልሳ ጊዜ ገደማ፣ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ ሁለት ጊዜ “የሠራዊት ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ሳሙኤል 1:11) ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን እጅግ ብዙ የሆነውን የመላእክት ሠራዊት ያዛል። (ኢያሱ 5:13-15፤ 1 ነገሥት 22:19) ይህ ሠራዊት ያለው የማጥፋት ኃይል እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ አይችልም። (ኢሳይያስ 37:36) ሰዎች ስለሚያደርሱት ጥፋት ማሰብ የሚያስደስት ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ የአምላክ ጦርነት በሰው ልጆች መካከል ከሚካሄዱት ግጭቶች ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። ወታደራዊም ሆኑ ፖለቲካዊ መሪዎች ማንኛውንም ጦርነት ለማካሄድ የሚነሱት የተቀደሰ ዓላማ ይዘው እንደሆነ ለማሳመን ቢሞክሩም የየትኛውም ሰብዓዊ ጦርነት መንስኤ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት ነው።
6 በአንጻሩ ግን ይሖዋ እንዲሁ በጭፍን ተነሳስቶ አይዋጋም። ዘዳግም 32:4 “እሱ ዓለት፣ የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ፍጹም ነው፤ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። እሱ ፈጽሞ ፍትሕን የማያጓድል ታማኝ አምላክ ነው፤ ጻድቅና ትክክለኛ ነው” ሲል ይገልጻል። የአምላክ ቃል ከቁጥጥር ውጭ የሆነን ቁጣ፣ ጭካኔንና ዓመፅን ያወግዛል። (ዘፍጥረት 49:7፤ መዝሙር 11:5) በመሆኑም ይሖዋ ያለበቂ ምክንያት እርምጃ አይወስድም። ያለውን ታላቅ ኃይል፣ ለማጥፋት የሚጠቀምበት በአግባቡ ከመሆኑም በላይ እንደ መጨረሻ አማራጭ አድርጎ ነው። “‘እኔ በክፉ ሰው ሞት ደስ እሰኛለሁ?’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘እኔ ደስ የምሰኘው ከመንገዱ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለም?’” ሲል በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት የተናገረው ቃል ይህን የሚያረጋግጥ ነው።—ሕዝቅኤል 18:23
7, 8. (ሀ) ኢዮብ ስለደረሰበት መከራ ምን የተሳሳተ ግምት አድሮበት ነበር? (ለ) ኤሊሁ፣ ኢዮብ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል የረዳው እንዴት ነው? (ሐ) በኢዮብ ላይ ከደረሰው ሁኔታ ምን ልንማር እንችላለን?
7 ታዲያ ይሖዋ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት የጻድቁን ሰው የኢዮብን ታሪክ መለስ ብለን ለመመልከት እንሞክር። በአንድ ወቅት ሰይጣን፣ ኢዮብ (እንዲያውም ማንኛውም ሰው) መከራ ቢደርስበት በታማኝነት ከአምላክ ጎን አይቆምም ሲል ተከራክሮ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ይህ አከራካሪ ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ ሲል ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት ፈቀደ። በዚህም የተነሳ ኢዮብ ጤንነቱን፣ ሀብቱንና ልጆቹን አጣ። (ኢዮብ 1:1 እስከ 2:8) ኢዮብ የተነሳውን ክርክር ስለማያውቅ አምላክ አላግባብ እየቀጣው እንዳለ ሆኖ ተሰምቶት ነበር። በዚህም ምክንያት ‘ለምን “ዒላማ” እና “ጠላት” አደረግኸኝ?’ ሲል አምላክን ጠይቋል።—ኢዮብ 7:20፤ 13:24
8 ኤሊሁ የተባለ አንድ ወጣት ኢዮብን “ትክክል እንደሆንክ በጣም እርግጠኛ ከመሆንህ የተነሳ ‘እኔ ከአምላክ ይበልጥ ጻድቅ ነኝ’ ትላለህ?” ብሎ በመውቀስ አስተሳሰቡ የተሳሳተ እንደሆነ ነግሮታል። (ኢዮብ 35:2) ‘ከአምላክ የተሻለ አውቃለሁ’ ወይም ደግሞ ‘አምላክ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ ትልቅ ስህተት ነው። ኤሊሁ “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!” ሲል ተናግሯል። በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከመረዳት ችሎታችን በላይ ነው፤ ኃይሉ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ፍትሑንና ታላቅ ጽድቁን አይጥስም።” (ኢዮብ 34:10፤ 36:22, 23፤ 37:23) አምላክ ያለበቂ ምክንያት እንደማይዋጋ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንግዲያው ይህን በአእምሯችን በመያዝ የሰላም አምላክ የሆነው ይሖዋ ተዋጊ እንዲሆን የሚያነሳሱትን አንዳንድ ምክንያቶች እንመርምር።—1 ቆሮንቶስ 14:33
የሰላም አምላክ ተዋጊ እንዲሆን የሚያስገድዱት ሁኔታዎች
9. ቅዱስ የሆነው አምላክ የሚዋጋው ለምንድን ነው?
9 ሙሴ “ኃያል ተዋጊ” የሆነውን አምላክ ካወደሰ በኋላ “ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስናው ኃያል መሆኑን የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” ብሏል። (ዘፀአት 15:11) በተመሳሳይም ነቢዩ ዕንባቆም “ዓይኖችህ ክፉ የሆነውን ነገር እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን ናቸው፤ ክፋትንም ዝም ብለህ ማየት አትችልም” ሲል ጽፏል። (ዕንባቆም 1:13) ይሖዋ የፍቅር ብቻ ሳይሆን የጽድቅ፣ የፍትሕና የቅድስና አምላክ ነው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ባሕርያቱ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት እንዲጠቀምበት ያስገድዱታል። (ኢሳይያስ 59:15-19፤ ሉቃስ 18:7) ስለዚህ አምላክ በሚዋጋበት ጊዜ ቅድስናውን አያጎድፍም። ከዚህ ይልቅ የሚዋጋው ቅዱስ ስለሆነ ነው።—ዘፀአት 39:30
10. በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተተነበየው ጠላትነት ሊያከትም የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው? ይህስ ጻድቅ ለሆኑ የሰው ልጆች ምን ጥቅም ያስገኛል?
10 የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ካመፁ በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ ተመልከት። (ዘፍጥረት 3:1-6) ይሖዋ የዓመፅ ድርጊታቸውን ቸል ብሎ ቢያልፍ ኖሮ በሉዓላዊ ገዢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳ ይችል ነበር። ጻድቅ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በእነሱ ላይ የሞት ፍርድ ለመበየን ተገድዷል። (ሮም 6:23) በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ አምላክ በራሱ አገልጋዮችና ‘በእባቡ’ ማለትም በሰይጣን ተከታዮች መካከል ጠላትነት እንደሚኖር ገልጿል። (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:15) ይህ ጠላትነት ሊያከትም የሚችለው ሰይጣን ሲጨፈለቅ ብቻ ነው። (ሮም 16:20) ይህ የፍርድ እርምጃ የሰይጣንን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ምድር ወደ ገነትነት እንድትለወጥ ሁኔታዎችን የሚያመቻች በመሆኑ ጻድቅ ለሆኑ የሰው ልጆች ታላላቅ በረከቶች ያስገኛል። (ማቴዎስ 19:28) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ከሰይጣን ጎን የወገኑ ሁሉ በአምላክ ሕዝብ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ደህንነት ላይ ስጋት መፍጠራቸው አይቀርም። አልፎ አልፎ ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅ እጁን ጣልቃ ማስገባት ሊያስፈልገው ይችላል።
አምላክ ክፋትን ለማስወገድ እርምጃ ይወስዳል
11. አምላክ የጥፋት ውኃ ለማምጣት የተገደደው ለምንድን ነው?
11 ይሖዋ በኖኅ ዘመን እንዲህ ያለ እርምጃ ወስዶ ነበር። ዘፍጥረት 6:11, 12 “ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር፤ ሰው ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር” ይላል። አምላክ በጎ ሥነ ምግባር ከምድር ላይ ጨርሶ እስኪጠፋ ድረስ ዝም ብሎ ይመለከት ይሆን? በፍጹም። ይሖዋ የዓመፅ መንፈስ የተጠናወታቸውንና ብልሹ ሥነ ምግባር የነበራቸውን ሰዎች በሙሉ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ለማምጣት ተገድዷል።
12. (ሀ) ይሖዋ የአብርሃምን “ዘር” በተመለከተ ምን ትንቢት ተናግሯል? (ለ) አሞራውያን መጥፋታቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
12 አምላክ በከነአናውያን ላይ የበየነው ፍርድም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ በአብርሃም ዘር አማካኝነት የምድር አሕዛብ ሁሉ ለራሳቸው በረከት እንደሚያገኙ ቃል ገብቶ ነበር። ይህን ዓላማ ዳር ለማድረስ፣ አሞራውያን የተባሉ ሕዝቦች የሚኖሩበትን የከነአን ምድር ለአብርሃም ተወላጆች ለማውረስ ወሰነ። አምላክ እነዚህን ሕዝቦች ከምድራቸው በኃይል ማስወጣቱ ፍትሐዊ ይሆናል? ይሖዋ “የአሞራውያን በደል ጽዋው [እስኪሞላ]” ድረስ ከምድራቸው እንደማይባረሩ አስቀድሞ የተናገረ ሲሆን ይህም 400 ዓመታት ገደማ እንደሚወስድ አመልክቷል።b (ዘፍጥረት 12:1-3፤ 13:14, 15፤ 15:13, 16፤ 22:18) በእነዚህ ዓመታት የአሞራውያን የሥነ ምግባር አቋም ይበልጥ እያዘቀጠ ሄደ። የከነአን ምድር በጣዖት አምልኮ፣ በደም መፋሰስና ልቅ በሆነ የፆታ ብልግና ተበከለች። (ዘፀአት 23:24፤ 34:12, 13፤ ዘኁልቁ 33:52) የምድሪቱ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ሳይቀር በእሳት በማቃጠል ለአማልክቶቻቸው መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል። ቅዱስ አምላክ የሆነው ይሖዋ አምላኪዎቹ እንዲህ ያለ ክፋት በሚፈጽሙ ሕዝቦች መካከል እንዲኖሩ ሊፈቅድ ይችላል? በፍጹም! “ምድሪቱ ረክሳለች፤ እኔም ለሠራችው ስህተት ቅጣት አመጣባታለሁ፤ ምድሪቱም ነዋሪዎቿን ትተፋቸዋለች” ሲል ተናግሯል። (ዘሌዋውያን 18:21-25) ይሁን እንጂ ይሖዋ እነዚህን ሰዎች በጅምላ ጠራርጎ አላጠፋም። እንደ ረዓብ እና እንደ ገባኦናውያን ያሉትን ጥሩ አመለካከት ያላቸው ከነአናውያን አላጠፋቸውም።—ኢያሱ 6:25፤ 9:3-27
ለስሙ ሲል ይዋጋል
13, 14. (ሀ) ይሖዋ ስሙን መቀደስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) ከእስራኤላውያን ጋር በተያያዘ ይሖዋ በስሙ ላይ የደረሰውን ነቀፋ ያስወገደው እንዴት ነው?
13 ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ ስሙም ቅዱስ ነው። (ዘሌዋውያን 22:32) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9) በኤደን የተነሳው ዓመፅ በአምላክና በአገዛዙ ላይ ጥያቄ ያስነሳ በመሆኑ የአምላክ ስም እንዲጎድፍ አድርጓል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ስም የማጥፋት ወንጀልና ዓመፅ ቸል ብሎ ሊያልፍ አይችልም። ስሙን ከነቀፋ ለማንጻት ሲል እርምጃ ለመውሰድ ተገድዷል።—ኢሳይያስ 48:11
14 እስቲ ወደ እስራኤላውያን ታሪክ እንመለስ። እስራኤላውያን ከግብፅ የባርነት ቀንበር እስካልተላቀቁ ድረስ አምላክ የምድር አሕዛብ በዘሩ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት እንደሚያገኙ ለአብርሃም የገባውን ቃል ሊፈጽም እንደማይችል የሚሰማቸው ይኖሩ ይሆናል። በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡን በብሔር ደረጃ ነፃ በማውጣትና በማደራጀት በስሙ ላይ የደረሰውን ነቀፋ አስወግዷል። ነቢዩ ዳንኤል ወደ አምላክ ሲጸልይ “ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በኃያል እጅ ያወጣህና እስከዚህ ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግክ አምላካችን ይሖዋ ሆይ” ያለው ለዚህ ነው።—ዳንኤል 9:15
15. ይሖዋ አይሁዳውያንን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ያወጣቸው ለምንድን ነው?
15 የሚያስገርመው ነገር ዳንኤል ይህን ጸሎት ያቀረበው አይሁዳውያን ይሖዋ ለስሙ ሲል ዳግመኛ እርምጃ እንዲወስድ ይጠብቁ በነበረበት ወቅት ነው። ዓመፀኛ የነበሩት አይሁዶች በዚህ ጊዜ በባቢሎን በግዞት ይገኙ ነበር። ዋና ከተማቸው ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ሆናለች። ዳንኤል አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለሳቸው የይሖዋን ስም እንደሚያስከብር በመገንዘብ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅር በል። ይሖዋ ሆይ፣ ትኩረት ስጥ፤ እርምጃም ውሰድ! አምላኬ ሆይ፣ ለራስህ ስትል አትዘግይ፤ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና።”—ዳንኤል 9:18, 19
ለሕዝቡ ሲል ይዋጋል
16. ይሖዋ ለስሙ ሲል የሚዋጋ መሆኑ ርኅራኄ የጎደለውና ራስ ወዳድ ነው ሊያሰኘው የማይችለው ለምን እንደሆነ አብራራ።
16 ይሖዋ ለስሙ ሲል ይዋጋል ሲባል ርኅራኄ የጎደለውና ራስ ወዳድ ነው ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ይልቁንም ከቅድስናውና ለፍትሕ ካለው ፍቅር ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ሕዝቡን ይጠብቃል። ዘፍጥረት ምዕራፍ 14ን ተመልከት። እዚህ ምዕራፍ ላይ አራት ወራሪ ነገሥታት የአብርሃምን የወንድም ልጅ ሎጥንና ቤተሰቡን ማርከው እንደወሰዱ የሚገልጽ ታሪክ እናገኛለን። አብርሃም በአምላክ እርዳታ በእነዚህ ኃያል ነገሥታት ላይ አስደናቂ ድል ተቀዳጀ! ይህ ድል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያልሰፈሩ አንዳንድ ወታደራዊ ክንውኖችንም እንደያዘ በሚገመተው “የይሖዋ የጦርነት መጽሐፍ” ላይ ከተመዘገቡት ታሪኮች የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። (ዘኁልቁ 21:14) ከዚያም በኋላ ቢሆን ሌሎች በርካታ ድሎች ተገኝተዋል።
17. እስራኤላውያን ወደ ከነአን ምድር ከገቡ በኋላ ይሖዋ እንደተዋጋላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው? አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ።
17 እስራኤላውያን ወደ ከነአን ምድር ከመግባታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ሙሴ “አምላካችሁ ይሖዋ በፊታችሁ ይሄዳል፤ የገዛ ዓይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ይዋጋላችኋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳግም 1:30፤ 20:1) በሙሴ እግር ከተተካው ከኢያሱ አንስቶ በመሳፍንትም ሆነ ታማኝ በነበሩት የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ ይሖዋ ለሕዝቡ በመዋጋት በጠላቶቻቸው ላይ በርካታ አስደናቂ ድሎች እንዲቀዳጁ አድርጓል።—ኢያሱ 10:1-14፤ መሳፍንት 4:12-17፤ 2 ሳሙኤል 5:17-21
18. (ሀ) ይሖዋ አለመለወጡ አመስጋኞች እንድንሆን የሚገፋፋን ለምንድን ነው? (ለ) በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ጠላትነት የሚያከትምበት ጊዜ ሲደርስ ምን ይከናወናል?
18 ይሖዋ አልተለወጠም፤ ይህችን ምድር ሰላም የሰፈነባት ገነት ለማድረግ ያለው ዓላማም ቢሆን አልተለወጠም። (ዘፍጥረት 1:27, 28) አምላክ አሁንም ቢሆን ክፋትን ይጠላል። ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቡን ከልብ ስለሚወድ ለእነሱ ሲል በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። (መዝሙር 11:7) እንዲያውም በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተገለጸው ጠላትነት በቅርቡ በአምላክ ሕዝብ ላይ ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ ከባድ ጥቃት እንዲሰነዘር ምክንያት ይሆናል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ስሙን ለመቀደስና ሕዝቡን ለመጠበቅ ሲል ዳግመኛ “ኃያል ተዋጊ” ሆኖ ይነሳል!—ዘካርያስ 14:3፤ ራእይ 16:14, 16
19. (ሀ) አምላክ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሆኑ ወደ እሱ እንድንቀርብ ሊያደርገን የሚችለው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) አምላክ ለእኛ ሲል የሚዋጋ መሆኑ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
19 ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክፉ አውሬ በአንድ ቤተሰብ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ሲል አባትየው በሕይወቱ ቆርጦ ከአውሬው ጋር በመፋለም ገደለው እንበል። ሚስቱና ልጆቹ ‘እንዴት አውሬውን ይገድለዋል?’ ብለው በማሰብ ለእሱ ጥላቻ የሚያድርባቸው ይመስልሃል? በፍጹም፤ እንዲያውም ለሕይወቱ ሳይሳሳ እነሱን ለማዳን ቆራጥ እርምጃ በመውሰዱ ይበልጥ እንደሚወዱት መገመት አያዳግትም። በተመሳሳይም አምላክ ያለውን ታላቅ ኃይል ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሆኑ እሱን እንድንሸሸው ሊያደርገን አይገባም። ከዚህ ይልቅ እኛን ለመጠበቅ ሲል የሚዋጋ መሆኑ ይበልጥ እንድንወደው ይገፋፋናል። በተጨማሪም ገደብ የለሽ ለሆነው ኃይሉ ያለን አድናቆት ሊጨምር ይገባል። ይህም “በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት፣ ተቀባይነት ባለው መንገድ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት” እንድናቀርብ ያደርገናል።—ዕብራውያን 12:28
“ኃያል ተዋጊ” ወደሆነው አምላክ ቅረብ
20. አምላክ ያከናወናቸውን ጦርነቶች በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዝርዝር መረጃ ባናገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?
20 እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአንዳንድ ሁኔታዎች ይሖዋን ለውጊያ ያነሳሱት ምክንያቶች ምን እንደሆኑ በዝርዝር አይገልጽም። ይሁን እንጂ ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ ይሖዋ ኃይሉን ፍትሕ በጎደለው ወይም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ አይጠቀምበትም። ብዙውን ጊዜ የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አውድ ወይም ሥረ መሠረት ጠለቅ ብለን መመርመራችን ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳናል። (ምሳሌ 18:13) ዝርዝር መረጃ በማናገኝበት ጊዜ እንኳ ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቃችንና ግሩም በሆኑት ባሕርያቱ ላይ ማሰላሰላችን በውስጣችን ሊፈጠር የሚችለውን ጥርጣሬ ለማስወገድ ይረዳናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በአምላካችን በይሖዋ ላይ ለመታመን የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት እናገኛለን።—ኢዮብ 34:12
21. ይሖዋ “ኃያል ተዋጊ” የሚሆንባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ምን ዓይነት አምላክ ነው?
21 ምንም እንኳ ይሖዋ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ “ኃያል ተዋጊ” ሆኖ የሚነሳ ቢሆንም ጦርነት ወዳድ ነው ማለት ግን አይደለም። ሕዝቅኤል ስለ ሰማያዊው ሠረገላ ባየው ራእይ ላይ ይሖዋ ከጠላቶቹ ጋር ለመዋጋት እንደተዘጋጀ ሆኖ ተገልጿል። ሆኖም ሕዝቅኤል አምላክን በራእይ የተመለከተው የሰላም ተምሳሌት በሆነው በቀስተ ደመና ተከብቦ ነው። (ዘፍጥረት 9:13፤ ሕዝቅኤል 1:28፤ ራእይ 4:3) ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ሰላማዊ አምላክ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክ ፍቅር ነው” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:8) ይሖዋ ባሕርያቱን በሙሉ የሚጠቀመው ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ነው። ይሖዋ ታላቅ ኃይል ያለው ቢሆንም አፍቃሪ ነው። እንዲህ ወዳለው አምላክ መቅረብ መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
a አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እስራኤላውያንን ያሳደዷቸው “600 ሠረገሎች፣ 50,000 ፈረሰኞችና 200,000 ገደማ የሚሆኑ በደንብ የታጠቁ እግረኛ ወታደሮች” እንደነበሩ ዘግቧል።—ጁዊሽ አንቲክዊቲስ፣ II, 324 [xv, 3]
b እዚህ ላይ “አሞራውያን” የሚለው ቃል በከነአን ምድር ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦችን በሙሉ እንደሚያመለክት ግልጽ ነው።—ዘዳግም 1:6-8, 19-21, 27፤ ኢያሱ 24:15, 18