የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • lr ምዕ. 9 ገጽ 52-56
  • የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መቋቋም ያስፈልገናል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መቋቋም ያስፈልገናል
  • ከታላቁ አስተማሪ ተማር
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ ፈተናዎችን ከተቋቋመበት መንገድ መማር
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ዲያብሎስ ኢየሱስን ፈተነው
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ኢየሱስ ከቀረቡለት ፈተናዎች መማር
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • የዘላለም ሕይወት ጠላት
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
ለተጨማሪ መረጃ
ከታላቁ አስተማሪ ተማር
lr ምዕ. 9 ገጽ 52-56

ምዕራፍ 9

የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መቋቋም ያስፈልገናል

አንድ ሰው ስህተት የሆነ ነገር እንድታደርግ ጠይቆህ ያውቃል?— ‘እስቲ ልብ ካለህ ይህን አድርግ’ ብሎ አደፋፍሮህ ነበር? ወይም ደግሞ አድርግ ያለህን ነገር ብታደርግ እንደምትደሰት ደግሞም ብታደርገው ምንም ስህተት እንደሌለበት ነግሮህ ነበር?— አንድ ሰው እንዲህ የሚለን ከሆነ ስህተት እንድንሠራ እየገፋፋን ወይም እየፈተነን ነው ማለት ነው።

አንድ ሰው ስህተት እንድንሠራ ሲፈታተነን ምን ማድረግ ይኖርብናል? እሺ ብለን ስህተት የሆነ ነገር መሥራት ይኖርብናል?— እንዲህ ብናደርግ ይሖዋ አምላክ ደስ አይለውም። ስህተት እንድንሠራ የሚገፋፋንን ሰው ሰምተን ስህተት ብንሠራ ደስ የሚለው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— አዎ፣ ስህተት ብንሠራ ደስ የሚለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።

ሰይጣን የአምላክም የእኛም ጠላት ነው። እሱ መንፈስ ስለሆነ ልናየው አንችልም። እሱ ግን ሊያየን ይችላል። አንድ ቀን ዲያብሎስ ታላቁን አስተማሪ ኢየሱስን ያነጋገረው ሲሆን ስህተት እንዲሠራ ሊፈትነው ሞክሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን እንዳደረገ እንመልከት። ኢየሱስ ምን እንዳደረገ ማወቃችን ስህተት እንድንሠራ የሚገፋፋ ፈታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን ማድረግ ያለብንን ትክክለኛ ነገር እንድንገነዘብ ይረዳናል።

ኢየሱስ እንደተጠመቀ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ሲጸልይ

ኢየሱስ በተጠመቀ ጊዜ ምን ነገር ማስታወስ ጀምሮ ሊሆን ይችላል?

ኢየሱስ ሁልጊዜ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ይፈልግ ነበር። ይህንንም በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ በግልጽ አሳይቷል። ሰይጣን ኢየሱስን ሊፈትነው የሞከረው ወዲያው እንደተጠመቀ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰማያት ለኢየሱስ እንደተከፈቱለት’ ይናገራል። (ማቴዎስ 3:16) ሰማያት ተከፈቱ ማለት ኢየሱስ ቀደም ሲል ከአምላክ ጋር በሰማይ ስለ ነበረው ሕይወት ማስታወስ ጀመረ ማለት ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በሰማይ የነበረውን ሕይወቱን ማስታወስ ስለጀመረ ባስታወሳቸው ነገሮች ላይ ለማሰላሰል ወደ ምድረ በዳ ሄደ። በምድረ በዳም አርባ ቀንና ሌሊት ቆየ። ኢየሱስ በዚህ ሁሉ ጊዜ ምንም ምግብ ስላልበላ በጣም ራበው። ሰይጣን ሊፈትነው የሞከረው በዚህ ጊዜ ነበር።

ዲያብሎስ በድንጋዮች ተጠቅሞ ኢየሱስን ሲፈትነው

ዲያብሎስ ኢየሱስን ለመፈተን በድንጋዮች የተጠቀመው እንዴት ነው?

ዲያብሎስ “እስቲ የአምላክ ልጅ ከሆንክ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። ኢየሱስ ዳቦ ቢያገኝ እንዴት ደስ ባለው! ለመሆኑ ግን ኢየሱስ ድንጋዩን ወደ ዳቦ መቀየር ይችል ነበር?— አዎ፣ ይችል ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ልዩ ኃይል ነበረው።

ዲያብሎስ አንተን ድንጋዩን ዳቦ አድርገው ቢልህ ታደርገው ነበር?— ኢየሱስ ርቦት ነበር። ታዲያ አንድ ጊዜ ብቻ ድንጋዩን ዳቦ ቢያደርግ ምን አለበት?— ኢየሱስ ኃይሉን ለራሱ ጥቅም ማዋሉ ስህተት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ይሖዋ ይህን ኃይል የሰጠው ሰዎችን ወደ አምላክ ለመሳብ እንዲጠቀምበት እንጂ ለራሱ ጥቅም እንዲያውለው አልነበረም።

ስለዚህ ኢየሱስ ሰይጣን የተናገረውን ከመፈጸም ይልቅ ‘ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውን ለሰይጣን ነገረው። ይሖዋን የሚያስደስት ነገር ማድረግ ምግብ ከመብላት ይበልጥ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር።

ሆኖም ዲያብሎስ እንደገና ኢየሱስን ለመፈተን ሙከራ አደረገ። ኢየሱስን ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደውና በቤተ መቅደሱ ጫፍ ላይ አቆመው። ከዚያም ሰይጣን ‘የአምላክ መላእክት ራስህን እንዳትጎዳ ይጠብቁሃል ተብሎ ስለተጻፈ የአምላክ ልጅ ከሆንክ ራስህን ወደ ታች ወርውር’ አለው።

ሰይጣን ይህን የተናገረው ለምንድን ነው?— ሰይጣን ይህን የተናገረው ኢየሱስ የሞኝነት ድርጊት እንዲፈጽም ለመገፋፋት ብሎ ነው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ ሰይጣን ያለውን አላደረገም። ኢየሱስ ሰይጣንን “‘አምላክህን ይሖዋን አትፈታተነው’ ተብሎም ተጽፏል” አለው። ኢየሱስ ሕይወቱን አደጋ ላይ በመጣል ይሖዋን መፈታተን ስህተት እንደሆነ ያውቅ ነበር።

በዚህ ጊዜም ቢሆን ሰይጣን ተስፋ ቆርጦ አልተወውም። ቀጥሎ ደግሞ ኢየሱስን በጣም ትልቅ ተራራ ላይ አወጣው። እዚያም የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው። ከዚያም ሰይጣን ኢየሱስን “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።

ዲያብሎስ ለኢየሱስ ያቀረበለትን ስጦታ እስቲ አስብ። እነዚህ ሁሉ የሰው መንግሥታት በእርግጥ የሰይጣን ናቸው?— አዎ፣ ኢየሱስ የሰይጣን መሆናቸውን አልካደም። የሰይጣን ባይሆኑ ኖሮ ኢየሱስ ‘የአንተ አይደሉም’ ይለው ነበር። አዎ፣ ሰይጣን በእርግጥም የዓለም መንግሥታት ሁሉ ገዥ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም ገዥ” ብሎ ይጠራዋል።—ዮሐንስ 12:31

ሰይጣን ለኢየሱስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ እንደሚሰጠው ቢነግረውም አልተቀበለውም

ሰይጣን ለኢየሱስ እነዚህን ሁሉ መንግሥታት ሊያቀርብለት የቻለው ለምንድን ነው?

ዲያብሎስ እሱን ካመለክኸው አንድ ነገር እንደሚሰጥህ ቃል ቢገባልህ ምን ታደርግ ነበር?— ኢየሱስ ምንም ዓይነት ሽልማት ቢያስገኝለት ዲያብሎስን ማምለክ ስህተት መሆኑን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለው:- ‘አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክህን ብቻ ማምለክና እሱን ብቻ ማገልገል እንዳለብህ ይናገራል።’—ማቴዎስ 4:1-10፤ ሉቃስ 4:1-13

አንዲት ትንሽ ልጅ ኬክ አይታ ስትጓጓ

አንተ ስህተት የሆነ ነገር እንድታደርግ ብትፈተን ምን ታደርጋለህ?

እኛም ስህተት እንድንሠራ የሚገፋፉ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። አንዳንዶቹ ፈተናዎች ምን እንደሆኑ ታውቃለህ?— አንድ ምሳሌ እንመልከት። እናትህ አንድ የምትወደውን ምግብ ወይም ኬክ ሠርታለች እንበል። ‘ሰዓቱ ሲደርስ ትበላለህ፤ እስከዚያ ድረስ ምንም እንዳትነካ’ ብላ ነግራህ ይሆናል። አንተ ግን በጣም ርቦህ ይሆናል፤ ስለዚህ ለመብላት ልትፈተን ትችላለህ። በዚህ ጊዜ እናትህን ትታዘዛለህ?— ሰይጣን እናትህን እንዳትታዘዝ ይፈልጋል።

ኢየሱስን አስታውስ። እሱም በጣም ተርቦ ነበር። ነገር ግን አምላክን ማስደሰት ከመብላት ይበልጥ አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ያውቅ ነበር። አንተም እናትህ የምትነግርህን ስታደርግ እንደ ኢየሱስ መሆን እንደምትፈልግ ታሳያለህ።

ሌሎች ልጆች የሆነ ክኒን እንድትውጥ ሊነግሩህ ይችላሉ። ‘ይህን ክኒን ብትውጠው በጣም ደስ እንዲልህ ያደርግሃል’ ብለው ይነግሩህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ክኒን አደንዛዥ መድኃኒት ሊሆን ይችላል። ክኒኑን ብትውጥ በጣም ሊያሳምምህና አልፎ ተርፎም ሊገድልህ ይችላል። ወይም ደግሞ አንድ ልጅ ሲጋራ ይሰጥህ ይሆናል። ሲጋራም ቢሆን በውስጡ አደንዛዥ ዕፅ አለበት። ታዲያ ልጁ ሲጋራውን እንድታጨስ ቢያደፋፍርህ ምን ታደርጋለህ?—

አንድ ልጅ ለሁለት ትናንሽ ልጆች ሲጋራ ሲሰጣቸው፤ አንደኛው ልጅ ሲቀበል ሌላው ግን ትቶት ይሄዳል

ኢየሱስን አስታውስ። ሰይጣን ኢየሱስን ከቤተ መቅደሱ ጫፍ ላይ ራሱን ወደ ታች እንዲወረውር በመንገር ሕይወቱን አደጋ ላይ እንዲጥል የሚያደርግ ፈተና አቅርቦለት ነበር። ኢየሱስ ግን ይህን አላደረገም። ታዲያ አንተ አንድ ሰው አንድ አደገኛ ነገር እንድታደርግ ቢያደፋፍርህ ምን ታደርጋለህ?— ኢየሱስ ሰይጣንን አልሰማውም። አንተም ብትሆን ስህተት የሆኑ ነገሮችን እንድታደርግ የሚያደፋፍርህን ሰው መስማት አይኖርብህም።

መቁጠሪያ የያዘች ልጅ

ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?

አንተም አንድ ቀን ምስሎችን እንድታመልክ ጥያቄ ይቀርብልህ ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ይህን ማድረግ እንደሌለብን ይናገራል። (ዘፀአት 20:4, 5) በትምህርት ቤት በሚደረግ አንድ ሥነ ሥርዓት ላይ ምስሎችን እንድታመልክ ትጠየቅ ይሆናል። ምስሎችን አላመልክም ካልክ ትምህርት ቤት ገብተህ መማር እንደማትችል ይነገርህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ?—

ሁሉም ሰው ትክክል የሆነውን ነገር በሚያደርግበት ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ቀላል ነው። ነገር ግን ሌሎች ስህተት የሆነውን ነገር እንድናደርግ በሚገፋፉን ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። እነሱ እያደረጉ ያሉት ነገር ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ይናገሩ ይሆናል። ነገር ግን ትልቁ ጥያቄ፣ አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? የሚለው ነው። የተሻለውን ነገር የሚያውቀው እሱ ነው።

ስለዚህ ሌሎች ምንም ቢሉ፣ አምላክ ስህተት ናቸው የሚላቸውን ነገሮች ፈጽሞ ማድረግ የለብንም። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ አምላክን ሁልጊዜ እናስደስተዋለን፤ ዲያብሎስን ግን ፈጽሞ አናስደስተውም።

ስህተት የሆነውን ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋ ፈተና ሲያጋጥመን እንዴት መቋቋም እንደምንችል የሚገልጹ ተጨማሪ ሐሳቦች በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ይገኛሉ:- መዝሙር 1:1, 2፤ ምሳሌ 1:10, 11፤ ማቴዎስ 26:41፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:22

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ