ዓለምን እየተቆጣጠረ ያለው ማን ነው?
ማን ይመስልሃል?
አምላክ?
የሰው ልጆች?
ወይስ ሌላ አካል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“መላው ዓለም ግን በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።”—1 ዮሐንስ 5:19
አዲስ ዓለም ትርጉም “የአምላክ ልጅ የተገለጠው የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው።”—1 ዮሐንስ 3:8
ይህን ማወቅህ ለአንተ ምን ጥቅም አለው?
ዓለም በችግር የተሞላው ለምን እንደሆነ አሳማኝ ምክንያት ታገኛለህ።—ራእይ 12:12
የተሻለ ዓለም ይመጣል ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት ታገኛለህ።—1 ዮሐንስ 2:17
መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ እምነት መጣል እንችላለን?
አዎ፣ ቢያንስ ሦስት ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦
የሰይጣን አገዛዝ ይጠፋል። ይሖዋ የሰውን ዘር ከሰይጣን ቁጥጥር ነፃ ለማውጣት ወስኗል። ይሖዋ ‘ዲያብሎስን እንዳልነበረ ለማድረግና’ ሰይጣን ያደረሰውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ ቃል ገብቷል።—ዕብራውያን 2:14
አምላክ ዓለምን እንዲገዛ ኢየሱስ ክርስቶስን መርጦታል። ኢየሱስ ጨካኝና ራስ ወዳድ ከሆነው የዚህ ዓለም ገዢ ፈጽሞ የተለየ ነው። አምላክ የኢየሱስን አገዛዝ አስመልክቶ ሲናገር “ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል፤ . . . ከጭቆናና ከግፍ ይታደጋቸዋል” ብሏል።—መዝሙር 72:13, 14
አምላክ ሊዋሽ አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ሊዋሽ እንደማይችል’ በግልጽ ይናገራል። (ዕብራውያን 6:18) ይሖዋ አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ሲገባ የተፈጸመ ያህል ልንቆጥረው እንችላለን! (ኢሳይያስ 55:10, 11) ስለዚህ “የዚህ ዓለም ገዢ . . . ይባረራል።”—ዮሐንስ 12:31