የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • jy ምዕ. 124 ገጽ 284-ገጽ 285 አን. 1
  • ክርስቶስ አልፎ ተሰጠ እንዲሁም ተያዘ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ክርስቶስ አልፎ ተሰጠ እንዲሁም ተያዘ
  • ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በይሁዳ ጠቋሚነት መያዝ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
  • ኢየሱስ ታሰረ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • ኢየሱስ በአንድ የአትክልት ቦታ
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
  • የጌታ ራት
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
jy ምዕ. 124 ገጽ 284-ገጽ 285 አን. 1
ጴጥሮስ የማልኮስን ጆሮ በመቁረጡ ኢየሱስ ገሠጸው፤ ወታደሮቹ ኢየሱስን ለመያዝ ተዘጋጅተዋል

ምዕራፍ 124

ክርስቶስ አልፎ ተሰጠ እንዲሁም ተያዘ

ማቴዎስ 26:47-56 ማርቆስ 14:43-52 ሉቃስ 22:47-53 ዮሐንስ 18:2-12

  • ይሁዳ በአትክልቱ ስፍራ ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠው

  • ጴጥሮስ የአንድን ሰው ጆሮ ቆረጠ

  • ኢየሱስ ተያዘ

እኩለ ሌሊት ካለፈ ቆይቷል። ካህናቱ፣ ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጣቸው ለይሁዳ 30 የብር ሳንቲሞች ለመክፈል ተስማምተዋል። ስለዚህ ይሁዳ የካህናት አለቆችንና ፈሪሳውያንን ያቀፈ ትልቅ ጭፍራ አስከትሎ ኢየሱስን መፈለግ ጀመረ። አንድ የሮም ወታደሮች ቡድንና የጦሩ አዛዥም አብረዋቸው ናቸው።

ይሁዳ ከፋሲካ ራት ላይ ተነስቶ እንዲሄድ ኢየሱስ ከነገረው በኋላ በቀጥታ ወደ ካህናት አለቆቹ እንደሄደ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። (ዮሐንስ 13:27) እነሱም የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችንና አንድ የወታደሮች ቡድን ሰበሰቡ። ይሁዳ መጀመሪያ የወሰዳቸው ኢየሱስና ሐዋርያቱ የፋሲካን በዓል ወዳከበሩበት ቤት ሊሆን ይችላል። ከይሁዳ ጋር ያለው ጭፍራ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ ወደ አትክልት ስፍራው ሄደ። ኢየሱስን ለማግኘት ቆርጠው የተነሱት እነዚህ ሰዎች ከመሣሪያ በተጨማሪ መብራትና ችቦ ይዘዋል።

ይሁዳ፣ ኢየሱስን የት እንደሚያገኘው እርግጠኛ በመሆን ሰዎቹን እየመራ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመላለሱ ብዙ ጊዜ ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ጎራ ይሉ ነበር። አሁን ጨለማ በመሆኑ የወይራ ዛፎቹ ኢየሱስን ሊሸፍኑት ይችላሉ። ወታደሮቹ ደግሞ ኢየሱስን አይተውት አያውቁ ይሆናል፤ ታዲያ እንዴት ሊለዩት ይችላሉ? ይሁዳ እነሱን ለመርዳት ምልክት ይሰጣቸዋል። “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙትና እንዳያመልጥ ተጠንቅቃችሁ ውሰዱት” አላቸው።—ማርቆስ 14:44

ይሁዳ ጭፍሮቹን እየመራ ወደ አትክልት ስፍራው ገባና ኢየሱስን ከሐዋርያቱ ጋር ሲመለከተው በቀጥታ ወደ እሱ ሄደ። ከዚያም “ረቢ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። ኢየሱስ ግን “ወዳጄ፣ እዚህ የተገኘህበት ዓላማ ምንድን ነው?” አለው። (ማቴዎስ 26:49, 50) ከዚያም “ይሁዳ፣ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህ?” በማለት ለራሱ ጥያቄ መልስ ሰጠ። (ሉቃስ 22:48) ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ለይሁዳ ትኩረት አልሰጠውም።

ኢየሱስ የችቦና የመብራቱ ብርሃን ወዳለበት ቦታ ወጣ ብሎ ሰዎቹን “ማንን ነው የምትፈልጉት?” አላቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስ በድፍረት “እኔ ነኝ” አለ። (ዮሐንስ 18:4, 5) ሰዎቹ ምን ሊያደርግ እንደሆነ ስላላወቁ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።

ኢየሱስ በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ጨለማውን ተገን አድርጎ ከመሸሽ ይልቅ ማንን እንደሚፈልጉ በድጋሚ ጠየቃቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” ብለው እንደገና ሲመልሱ ኢየሱስ ረጋ ብሎ “እኔ ነኝ አልኳችሁ እኮ። የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው ይሂዱ” አለ። በዚህ አስጨናቂ ጊዜም እንኳ ኢየሱስ፣ ከሐዋርያቱ መካከል አንዳቸውም እንደማይጠፉበት ቀደም ሲል የተናገረውን ሐሳብ አልዘነጋም። (ዮሐንስ 6:39፤ 17:12) ኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያቱን ጠብቋቸዋል፤ “ከጥፋት ልጅ” ይኸውም ከይሁዳ በቀር አንዳቸውም አልጠፉበትም። (ዮሐንስ 18:7-9) በመሆኑም አሁን ሰዎቹ፣ ታማኝ ተከታዮቹን እንዲተዉአቸው ጠየቀ።

ወታደሮቹ ተነስተው ኢየሱስን ለመያዝ ሲሞክሩ ሐዋርያቱ ምን እየተከናወነ እንዳለ ገባቸው። በመሆኑም “ጌታ ሆይ፣ በሰይፍ እንምታቸው?” በማለት ጠየቁት። (ሉቃስ 22:49) ኢየሱስ መልስ ከመስጠቱ በፊት ጴጥሮስ ሐዋርያቱ ይዘዋቸው ከነበሩት ሁለት ሰይፎች መካከል አንደኛውን መዘዘ። ከዚያም የሊቀ ካህናቱ ባሪያ የሆነውን ማልኮስን መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠው።

ኢየሱስ ግን የማልኮስን ጆሮ በመዳሰስ ፈወሰው። ከዚያም ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎ በማዘዝ ጠቃሚ ትምህርት ሰጠ። ኢየሱስ ሰዎቹ እንዲይዙት ፈቃደኛ መሆኑን አሳይቷል፤ ምክንያቱን ሲገልጽ “እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉት ቅዱሳን መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 26:52, 54) አክሎም “አብ የሰጠኝን ጽዋ መጠጣት አይኖርብኝም?” አለ። (ዮሐንስ 18:11) ኢየሱስ፣ አምላክ ለእሱ ያለውን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል ለመሞት እንኳ ፈቃደኛ ነው።

ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ አስተምር ነበር፤ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም። ይህ ሁሉ የሆነው ግን በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።”—ማቴዎስ 26:55, 56

በዚህ ጊዜ ወታደሮቹና የጦር አዛዡ እንዲሁም የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። ሐዋርያቱ ይህን ሲመለከቱ ሸሹ። ሆኖም “አንድ ወጣት” (ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም) በሰዎቹ መካከል ቀርቶ ኢየሱስን መከተል ጀመረ። (ማርቆስ 14:51) ይሁን እንጂ ሰዎቹ ማንነቱን ሲያውቁ ሊይዙት ሞከሩ፤ በዚህ ጊዜ የለበሰውን በፍታ ጥሎ ሸሸ።

  • ይሁዳ ኢየሱስን ለማግኘት ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ የሄደው ለምንድን ነው?

  • ጴጥሮስ ኢየሱስን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲል ምን እርምጃ ወሰደ? ሆኖም ኢየሱስ ይህን በተመለከተ ምን አለ?

  • ኢየሱስ፣ አምላክ ለእሱ ካለው ፈቃድ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ ያሳየው እንዴት ነው?

  • ሐዋርያቱ ኢየሱስን ጥለው ሲሸሹ እዚያው የቀረው ማን ነው? ምንስ አጋጠመው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ