የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • od ምዕ. 6 ገጽ 53-58
  • የጉባኤ አገልጋዮች ጠቃሚ ሥራ ያከናውናሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የጉባኤ አገልጋዮች ጠቃሚ ሥራ ያከናውናሉ
  • የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች
  • ምን ዓይነት አገልግሎቶች ያከናውናሉ?
  • የጉባኤ አገልጋዮች ምን ሚና ይጫወታሉ?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
  • በሽማግሌዎችና በዲያቆናት መካከል ያለውን ስምምነት መጠበቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የጉባኤ አገልጋዮች ጠቃሚ አገልግሎት ያበረክታሉ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1999
  • ሽማግሌዎች—ኃላፊነት እንዲሸከሙ ሌሎችን አሠልጥኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
od ምዕ. 6 ገጽ 53-58

ምዕራፍ 6

የጉባኤ አገልጋዮች ጠቃሚ ሥራ ያከናውናሉ

ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበረው ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያዎች ከሆኑት ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፣ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን ጨምሮ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ቅዱሳን ሁሉ።” (ፊልጵ. 1:1) በዚህ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ ለጉባኤ አገልጋዮች ሰላምታ ማቅረቡን አስተዋልክ? እነዚህ ወንዶች በዚያን ጊዜ በጉባኤው ውስጥ የነበሩትን ሽማግሌዎች በመርዳት ትልቅ እገዛ ያበረክቱ እንደነበር ግልጽ ነው። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። የጉባኤ አገልጋዮች የሚያከናውኗቸው ሥራዎች ለበላይ ተመልካቾች እርዳታ የሚያበረክቱ ከመሆኑም ሌላ ጉባኤው የተደራጀ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

2 በጉባኤህ ውስጥ ያሉትን የጉባኤ አገልጋዮች ታውቃቸዋለህ? ለአንተም ሆነ ለጉባኤው ጥቅም ሲሉ የሚያከናውኑትን ሥራስ ታውቃለህ? ይሖዋ እነዚህ ወንዶች የሚያከናውኑትን ሥራ በአድናቆት እንደሚመለከት ምንም ጥያቄ የለውም። ጳውሎስ “በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግሉ ወንዶች ለራሳቸው መልካም ስም የሚያተርፉ ከመሆናቸውም በላይ በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ስላላቸው እምነት አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የሚያስችል ነፃነት ያገኛሉ” ሲል ጽፏል።—1 ጢሞ. 3:13

የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች

3 አንድ የጉባኤ አገልጋይ ንጹሕ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመራ፣ ኃላፊነት የሚሰማውና የተመደበለትን ሥራ በአግባቡ የሚያከናውን እንዲሆን ይጠበቅበታል። ጳውሎስ የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን በተመለከተ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ስንመለከት ይህ ግልጽ ይሆንልናል፦ “የጉባኤ አገልጋዮችም በተመሳሳይ ቁም ነገረኞች፣ በሁለት ምላስ የማይናገሩ፣ ብዙ የወይን ጠጅ የማይጠጡ፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይስገበገቡ፣ የእምነትን ቅዱስ ሚስጥር በንጹሕ ሕሊና አጥብቀው የሚይዙ መሆን ይገባቸዋል። በተጨማሪም ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅድሚያ ይፈተኑ፤ ከዚያም ከክስ ነፃ ሆነው ከተገኙ አገልጋይ ሆነው ያገልግሉ። የጉባኤ አገልጋዮች የአንዲት ሚስት ባል እንዲሁም ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድሩ ሊሆኑ ይገባል።” (1 ጢሞ. 3:8-10, 12) የጉባኤ አገልጋዮች እንዲህ ያለውን ላቅ ያለ ብቃት ማሟላታቸው ኃላፊነት የተሰጣቸውን ወንዶች በተመለከተ በጉባኤው ላይ ነቀፋ እንዳይሰነዘር ያስችላል።

4 የጉባኤ አገልጋዮች ወጣትም ሆኑ በዕድሜ ጠና ያሉ በየወሩ በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። የኢየሱስን አርዓያ በመከተል አገልግሎታቸውን በቅንዓት ያከናውናሉ። ይህ ደግሞ ይሖዋ የሰው ልጆችን ለማዳን ያለውን ፍላጎት እንደሚጋሩ ያሳያል።—ኢሳ. 9:7

5 በተጨማሪም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው የሚያገለግሉ ወንዶች በአለባበሳቸው፣ በፀጉር አያያዛቸው፣ በአነጋገራቸው፣ በዝንባሌያቸውና በባሕርያቸው ለሌሎች ጥሩ አርዓያ ናቸው። እነዚህ ወንዶች ጤናማ አስተሳሰብ አላቸው፤ ይህ ደግሞ የሌሎችን አክብሮት እንዲያተርፉ ያስችላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድናም ሆነ በጉባኤው ውስጥ ያላቸውን የአገልግሎት መብት አክብደው ይመለከታሉ።—ቲቶ 2:2, 6-8

6 እነዚህ ወንዶች ‘ብቁ መሆናቸው ተፈትኖ’ ታይቷል። ከመሾማቸው በፊትም እንኳ ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ የወሰኑ መሆናቸውን አስመሥክረዋል። በሕይወታቸው ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ እንደሚሰጡ በተግባር አሳይተዋል፤ ደግሞም ሊያገኟቸው የሚችሉ የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ ይጣጣራሉ። በእርግጥም በጉባኤው ውስጥ ላሉ ሌሎች አስፋፊዎች ጥሩ ምሳሌ ናቸው።—1 ጢሞ. 3:10

ምን ዓይነት አገልግሎቶች ያከናውናሉ?

7 የጉባኤ አገልጋዮች ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው የተለያዩ ጠቃሚ አገልግሎቶች ይሰጣሉ፤ ይህም የበላይ ተመልካቾች የማስተማርና የእረኝነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላል። የሽማግሌዎች አካል ለጉባኤ አገልጋዮች ሥራ ሲሰጥ አገልጋዮቹ በግለሰብ ደረጃ ያላቸውን ችሎታና ጉባኤው የሚያስፈልገውን እገዛ ግምት ውስጥ ያስገባል።

የጉባኤ አገልጋዮች የተለያዩ ጠቃሚ አገልግሎቶች ይሰጣሉ፤ ይህም የበላይ ተመልካቾች የማስተማርና የእረኝነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተጨማሪ ጊዜ እንዲያገኙ ያስችላል

8 እስቲ እነዚህ ወንድሞች ከሚያከናውኗቸው አገልግሎቶች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት፦ አንድ የጉባኤ አገልጋይ ከጉባኤው ጽሑፎች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እንዲያከናውን ሊመደብ ይችላል፤ ይህም ለራሳችንም ሆነ ለመስክ አገልግሎት የምንጠቀምባቸውን ጽሑፎች እንድናገኝ ያስችለናል። ሌሎች አገልጋዮች ደግሞ የጉባኤውን ሒሳብ ወይም የአገልግሎት ክልል ፋይል ይይዛሉ። አንዳንዶች ደግሞ ማይክሮፎን እንዲያዞሩ፣ የድምፅ መሣሪያዎችን እንዲቆጣጠሩ፣ አስተናጋጅ ሆነው እንዲያገለግሉ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ሽማግሌዎችን እንዲረዱ ይመደባሉ። የስብሰባ አዳራሹን ለመጠገንና በንጽሕና ለመያዝ ሲባል የሚከናወኑ ብዙ ሥራዎች ስላሉ የጉባኤ አገልጋዮች አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ላሉት ሥራዎች ድጋፍ እንዲሰጡ ይጠየቃሉ።

9 በአንዳንድ ጉባኤዎች ለእያንዳንዱ ሥራ የተለያዩ የጉባኤ አገልጋዮች ሊመደቡ ይችላሉ። በሌሎች ጉባኤዎች ግን አንድ የጉባኤ አገልጋይ በርከት ያሉ ኃላፊነቶችን ደርቦ ሊይዝ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሥራ ከአንድ በላይ የጉባኤ አገልጋዮች ሊመደቡ ይችላሉ። አንዳንዶቹን ኃላፊነቶች የሚይዙ በቂ የጉባኤ አገልጋዮች ከሌሉ የሽማግሌዎች አካል የተጠመቁና ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ ወንድሞች አስፈላጊ የሆኑትን እነዚህን ሥራዎች እንዲያከናውኑ ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ ወንድሞች በዚህ መንገድ የሚያገኙት ልምድ፣ ወደፊት የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ለማገልገል ብቃቱን ሲያሟሉ በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። በአንድ ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት የሚሸከሙ ወንድሞች ከሌሉ ግን ጥሩ ምሳሌ የሆኑ እህቶች በአንዳንድ ሥራዎች እገዛ እንዲያደርጉ ሊጠየቁ ይችላሉ፤ እርግጥ የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው አይሾሙም። አንድ ግለሰብ (ወንድም ወይም እህት) ምሳሌ ነው ሊባል የሚችለው በአኗኗሩም ሆነ ለይሖዋ በሚያቀርበው አምልኮ ረገድ ለሌሎች አርዓያ ከሆነ ነው። አዘውትሮ በስብሰባ ላይ በመገኘት፣ በአገልግሎት በሚያደርገው ተሳትፎ፣ በቤተሰብ ሕይወቱ፣ በመዝናኛ ምርጫው፣ በአለባበሱ፣ በአጋጌጡ፣ በፀጉር አያያዙና በመሳሰሉት ነገሮች ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ መሆን አለበት።

10 በጣም ጥቂት ሽማግሌዎች ባሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ጥሩ ችሎታ ያላቸው የጉባኤ አገልጋዮች በተጨማሪ መረጃው ላይ የሚገኘውን “ክፍል 1፦ የክርስትና ትምህርቶች” የሚለውን ክፍል ከጥምቀት ዕጩዎች ጋር እንዲከልሱ ሊጠየቁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ “ክፍል 2፦ የክርስትና ሕይወት” የሚል ርዕስ ያለው ክፍል ጥንቃቄ የሚሹ የግል ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ ለሽማግሌ መመደብ አለበት።

11 የሽማግሌዎች አካል አጥጋቢ ምክንያት ካለው በየተወሰነ ጊዜው የጉባኤ አገልጋዮችን ከአንዱ ሥራ ወደ ሌላው ማዛወሩን ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። ይሁን እንጂ ወንድሞች ለተወሰነ ጊዜ በአንድ ሥራ ላይ ተመድበው መቆየታቸው ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ ምክንያቱም ልምድ እያዳበሩና ቅልጥፍና እየጨመሩ እንዲሄዱ ያስችላቸዋል።

12 በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ፣ እድገታቸው “በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ” ላደረጉ የጉባኤ አገልጋዮች ሊሰጡ የሚችሉ ሌሎች ኃላፊነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። (1 ጢሞ. 4:15) የሽማግሌዎች እጥረት ካለ አንድ የጉባኤ አገልጋይ የቡድን የበላይ ተመልካች ረዳት ሆኖ እንዲያገለግል ወይም ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች በቅርብ እየተከታተሉት የቡድን አገልጋይ ሆኖ እንዲያገለግል ሊመደብ ይቻላል። የጉባኤ አገልጋዮች በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ አንዳንድ ክፍሎችን እንዲያቀርቡ፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመሩ እንዲሁም የሕዝብ ንግግር እንዲያቀርቡ ሊመደቡ ይችላሉ። ጉባኤው አንድ የተለየ ኃላፊነት የሚይዝ ወንድም ቢያስፈልገውና ለዚያ ብቁ የሚሆኑ የጉባኤ አገልጋዮች ካሉ ተጨማሪ መብት ሊሰጣቸው ይችላል። (1 ጴጥ. 4:10) የጉባኤ አገልጋዮች ለሽማግሌዎች ድጋፍ ለመስጠት ራሳቸውን በፈቃደኝነት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

13 የጉባኤ አገልጋዮች የሚያከናውኑት ሥራ ከሽማግሌዎች ሥራ የተለየ ቢሆንም ለአምላክ የሚቀርብ ቅዱስ አገልግሎት ክፍል ከመሆኑም ባሻገር ጉባኤው ያለችግር እንዲንቀሳቀስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። የጉባኤ አገልጋዮች ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡ ሆነው ከተገኙ እንዲሁም እረኞችና አስተማሪዎች ሆነው ለማገልገል ብቃቱን ካሟሉ ከጊዜ በኋላ በሽምግልና እንዲያገለግሉ ሊታጩ ይችላሉ።

14 በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወይም በቅርቡ የተጠመቅክ ወንድም ከሆንክ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን እየተጣጣርክ ነው? (1 ጢሞ. 3:1) በየዓመቱ በጣም ብዙ ሰዎች ወደ እውነት እየመጡ ስለሆነ የጉባኤ ኃላፊነቶችን የሚወጡ ብቃት ያላቸው መንፈሳዊ ወንዶች ያስፈልጋሉ። በመሆኑም ብቃቱን ማሟላት እንድትችል ሌሎችን የመርዳት ፍላጎት ማዳበር ይኖርብሃል። እንዲህ ማድረግ የምትችልበት አንደኛው መንገድ ደግሞ ኢየሱስ በተወው ግሩም ምሳሌ ላይ ማሰላሰል ነው። (ማቴ. 20:28፤ ዮሐ. 4:6, 7፤ 13:4, 5) ለሌሎች መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እያጣጣምክ ስትሄድ ፍላጎትህም በዚያው መጠን እያደገ ይሄዳል። (ሥራ 20:35) እንግዲያው ሌሎችን ለመርዳት፣ የስብሰባ አዳራሹን በመጠገን ሥራ ለመሳተፍ ወይም በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ ሌሎችን ተክተህ ክፍል ለማቅረብ ራስህን በፈቃደኝነት አቅርብ። በተጨማሪም ብቃቱን ለማሟላት መጣጣር፣ ጥሩ የግል ጥናት ልማድ በመከተል መንፈሳዊ ባሕርያት ማዳበርን ያካትታል። (መዝ. 1:1, 2፤ ገላ. 5:22, 23) በሌላ በኩል፣ ብቃቱን ለማሟላት እየተጣጣረ ያለ ወንድም የጉባኤ ሥራ ሲሰጠው እምነት የሚጣልበትና ታማኝ መሆኑን ያሳያል።—1 ቆሮ. 4:2

15 የጉባኤ አገልጋዮች በመንፈስ ቅዱስ የሚሾሙት ለጉባኤው ጥቅም ሲባል ነው። የጉባኤ አገልጋዮች የተመደቡላቸውን ሥራዎች ለማከናወን ሲጥሩ ሌሎች የጉባኤው አስፋፊዎች ደግሞ ከእነሱ ጋር በመተባበር፣ በትጋት ለሚያከናውኑት ሥራ ያላቸውን አድናቆት ማሳየት ይችላሉ። በዚህ መንገድ፣ ጉባኤው ይሖዋ ቤቱ ሥርዓታማ እንዲሆን ላደረገው ዝግጅት አድናቆት እንዳለው ያሳያል።—ገላ. 6:10

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ