1 “ሕይወታቸውን በእርግጥ ለአምላክ የወሰኑ፣ በመንግሥቱ አገልግሎት በቅንዓት በመሳተፍና ሌሎችን በእምነት ጠንካሮች እንዲሆኑ በመርዳት እምነታቸውን ያሳዩ ወንዶች ናቸው።” የጉባኤ አገልጋዮችን በተመለከተ የተሰጠው ይህ ሐሳብ አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 57 ላይ ይገኛል። በእርግጥም የጉባኤ አገልጋዮቻችን የሚያሳዩት መንፈሳዊ አርአያነት ልንኮርጀው የሚገባ ነው። ከእነርሱና ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ተባብረን መሥራታችን ‘በፍቅር ለመታነጽ አካሉ እንዲያድግ’ ያደርጋል።—ኤፌ. 4:16
2 የጉባኤ አገልጋዮች ጉባኤ ውስጥ ጠቃሚ ሥራ ያከናውናሉ። እስቲ የሚያከናውኗቸውን ጠቃሚ አገልግሎቶች ተመልከት! የጉባኤውን ሒሳብ፣ ጽሑፍ፣ መጽሔት፣ የመጽሔት ኮንትራትና የአገልግሎት ክልል ይሠራሉ፤ አስተናጋጅ ይሆናሉ፣ የድምፅ መሣሪያዎችን ይቆጣጠራሉ እንዲሁም ለመንግሥት አዳራሹ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ ያደርጋሉ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል ያቀርባሉ። ከዚህም በላይ አንዳንዶቹ የሕዝብ ንግግር ይሰጣሉ ወይም አንዳንድ የጉባኤ ስብሰባዎችን ይመራሉ። አንድ ሰብዓዊ አካል የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ብልቶች እንዳሉት ሁሉ የጉባኤ አገልጋዮችም ለእኛ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ያከናውናሉ።—1 ቆሮ. 12:12-26
3 የጉባኤ አገልጋዮች፣ የአንድ የአገልጋዮች አካል ክፍል በመሆን ከሽማግሌዎች ጋር ተከባብረውና ተግባብተው በስምምነት ሲሠሩ ማየቱ ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። (ቆላ. 2:19) በየሳምንቱ ኃላፊነቶቻቸውን በታማኝነት በመወጣትና ለሌሎች በግል ትኩረት በመስጠት ጉባኤው በመንፈሳዊ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
4 ትጉ ለሆኑት የጉባኤ አገልጋዮች ያለንን አድናቆት ለመግለጽ ምን ማድረግ እንችላለን? የተመደበላቸውን የሥራ ድርሻ ማወቅና እርዳታ እንድንሰጥ ስንጠየቅ ለመተባበር ዝግጁነታችንን ማሳየት አለብን። በቃልም ሆነ በተግባር ሥራቸውን እንደምናደንቅ ልንገልጽላቸው እንችላለን። (ምሳሌ 15:23) እኛን ለመጥቀም በትጋት የሚሠሩ ወንድሞቻችን ለሚያከናውኑት ሥራ ልባዊ አድናቆት ሊሰጣቸው ይገባል።—1 ተሰ. 5:12, 13
5 የአምላክ ቃል የጉባኤ አገልጋዮችን የሥራ ድርሻና ሊያሟሉት የሚገባውን ብቃት በዝርዝር ይዟል። (1 ጢሞ. 3:8-10, 12, 13) የሚያከናውኑት ጠቃሚ የሆነ ቅዱስ አገልግሎት ለጉባኤው እንቅስቃሴ የግድ አስፈላጊ ነው። እነዚህ ወንዶች ‘የጌታ ሥራ የበዛላቸው’ እንደመሆናቸው መጠን ዘወትር ማበረታቻ ልንሰጣቸው ይገባል።—1 ቆሮ. 15:58