ምዕራፍ 9
ምሥራቹን የምንሰብክባቸው መንገዶች
ኢየሱስ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ በመሆን ለተከታዮቹ ጥሩ ምሳሌ ትቶላቸዋል። ቅድሚያውን ወስዶ ሰዎች ወደሚገኙበት ቦታ በመሄድ በየቤቱ እንዲሁም በአደባባይ ይሰብክና ያስተምር ነበር። (ማቴ. 9:35፤ 13:36፤ ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ሰዎችን በግል ቀርቦ አነጋግሯል፣ ደቀ መዛሙርቱን ለብቻቸው አስተምሯል እንዲሁም አንድ ላይ ተሰብስቦ ለነበረ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ትምህርት ሰጥቷል። (ማር. 4:10-13፤ 6:35-44፤ ዮሐ. 3:2-21) ባገኘው ምቹ አጋጣሚ ሁሉ፣ ሰዎችን የሚያበረታታና ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መልእክት ከመናገር ወደኋላ አላለም። (ሉቃስ 4:16-19) ማረፍ እንዲሁም መብላትና መጠጣት ባስፈለገው ጊዜም እንኳ መመሥከር የሚችልባቸውን አጋጣሚዎች አላለፈም። (ማር. 6:30-34፤ ዮሐ. 4:4-34) ኢየሱስ ስላከናወነው አገልግሎት የሚናገሩትን በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ዘገባዎች ስናነብ የእሱን አርዓያ ለመከተል አንነሳሳም? ሐዋርያት እንዳደረጉት ሁሉ እኛም እንዲህ ለማድረግ እንደምንነሳሳ ምንም ጥርጥር የለውም።—ማቴ. 4:19, 20፤ ሉቃስ 5:27, 28፤ ዮሐ. 1:43-45
2 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት በጀመረው ሥራ መካፈል የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች እስቲ ተመልከት።
ከቤት ወደ ቤት መስበክ
3 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የመንግሥቱን ምሥራች በተደራጀ መንገድ መስበክ ያለውን ጥቅም እንገነዘባለን። በዚህ ዘዴ በስፋት ከመጠቀማችን የተነሳ መለያ ምልክታችን ሆኗል። የተገኙት አስደሳች ውጤቶች ይህ የስብከት ዘዴ ምሥራቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ለማዳረስ የሚያስችል ውጤታማ አሠራር መሆኑን ያረጋግጣሉ። (ማቴ. 11:19፤ 24:14) በእርግጥም ከቤት ወደ ቤት የምናደርገው አገልግሎት ለይሖዋና ለሰዎች ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልበት ግሩም መንገድ ነው።—ማቴ. 22:34-40
4 ከቤት ወደ ቤት መስበክ የይሖዋ ምሥክሮች የጀመሩት አዲስ የስብከት ዘዴ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሰዎች ቤት እየሄደ ያስተምር እንደነበር ጽፏል። ያከናወነውን አገልግሎት አስመልክቶ ለኤፌሶን ጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በእስያ አውራጃ እግሬ ከረገጠበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ . . . የሚጠቅማችሁን ማንኛውንም ነገር ከመንገርም ሆነ . . . ከቤት ወደ ቤት ከማስተማር ወደኋላ ብዬ አላውቅም።” ጳውሎስ በዚህና በሌሎች መንገዶች “አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ንስሐ እንዲገቡና ወደ አምላክ እንዲመለሱ እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ በተሟላ ሁኔታ [መሥክሯል]።” (ሥራ 20:18, 20, 21) በዚያ ዘመን የሮማ ነገሥታት ጣዖት አምልኮን ያስፋፉ የነበረ ሲሆን ብዙዎች ‘አማልክትን ይፈሩ’ ነበር። በመሆኑም ሰዎች “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ [የፈጠረውን]” እንዲሁም “በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ እያሳሰበ” የነበረውን አምላክ መፈለጋቸው በጣም አጣዳፊ ነበር።—ሥራ 17:22-31
5 በዛሬው ጊዜ ምሥራቹ ለሰዎች ሁሉ እንዲዳረስ የማድረጉ ጉዳይ ከምንጊዜውም ይበልጥ አጣዳፊ ነው። የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በፍጥነት እየቀረበ ነው። ይህን መገንዘባችን የምናደርገውን ጥረት እንድናጠናክር ያነሳሳናል። እውነትን የተራቡ ሰዎችን ለማግኘት ለዘመናት ተፈትኖ ውጤታማነቱ ከተረጋገጠው ከዚህ ዘዴ ይኸውም ከቤት ወደ ቤት ከማገልገል የተሻለ መንገድ እንደሌለ እናውቃለን። ይህ ዘዴ በኢየሱስና በሐዋርያት ዘመን ውጤታማ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ውጤታማ ነው።—ማር. 13:10
6 ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እያደረግክ ነው? ከሆነ ይሖዋ በአንተ እንደሚደሰት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ሕዝ. 9:11፤ ሥራ 20:35) እርግጥ ነው፣ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ከባድ እንዲሆንብህ የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆናል። ከእነዚህ መካከል የአቅም ገደብ፣ በምትሰብክበት ክልል ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች ምሥራቹን መስማት አለመፈለግ፣ አልፎ ተርፎም መንግሥት የጣለው እገዳ እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ። አሊያም ደግሞ በባሕርይህ ዓይን አፋር ስለሆንክ፣ ከማታውቃቸው ሰዎች ጋር ውይይት መጀመር በጣም ሊከብድህ ይችላል። በመሆኑም ከቤት ወደ ቤት ባገለገልክ ቁጥር በተወሰነ መጠን ጭንቀት ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ተስፋ መቁረጥ አይኖርብህም። (ዘፀ. 4:10-12) እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም፤ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ወንድሞችህም ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸዋል።
7 ኢየሱስ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ሲል ለደቀ መዛሙርቱ ቃል ገብቷል። (ማቴ. 28:20) ኢየሱስ የሰጠው ይህ ዋስትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት እንድንሳተፍ ብርታት ይሰጠናል። እኛም “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” በማለት የተናገረው የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት አለን። (ፊልጵ. 4:13) ጉባኤው ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል ባደረጋቸው ዝግጅቶች በሚገባ ተጠቀም። ከሌሎች ጋር በማገልገል ማበረታቻና ድጋፍ ማግኘት ትችላለህ። ይሖዋ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም መሰናክል ማሸነፍ እንድትችል እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም ራስህን ሳትቆጥብ ምሥራቹን ስበክ።—1 ዮሐ. 5:14
8 ምሥራቹን ለሌሎች ስታካፍል ‘ስለ ተስፋህ ምክንያት የምታቀርብበት’ ብዙ አጋጣሚ ታገኛለህ። (1 ጴጥ. 3:15) በመንግሥቱ ተስፋ ላይ ጽኑ እምነት ባላቸውና ምንም ተስፋ በሌላቸው ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ይበልጥ እየተገነዘብክ ትሄዳለህ። (ኢሳ. 65:13, 14) ኢየሱስ “ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ እንዳደረግክ ስለምታውቅ እርካታ ታገኛለህ፤ አልፎ ተርፎም ሌሎች ሰዎች ይሖዋን እንዲሁም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውነት እንዲያውቁ የመርዳት መብት ልታገኝ ትችላለህ።—ማቴ. 5:16፤ ዮሐ. 17:3፤ 1 ጢሞ. 4:16
9 በሳምንቱ መሃልም ሆነ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል የሚቻልበት ዝግጅት ይደረጋል። ቀን ላይ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው አካባቢዎች ያሉ አንዳንድ ጉባኤዎች ምሽት ላይ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጅት ያደርጋሉ። ሰዎች ከጠዋት ይልቅ አመሻሹ ላይ ወደ ቤታቸው የሚመጣን ሰው መቀበል ሊቀላቸው ይችላል።
የሚገባቸውን ሰዎች መፈለግ
10 ኢየሱስ፣ የሚገባቸውን ሰዎች ‘እንዲፈልጉ’ ደቀ መዛሙርቱን አዝዟቸው ነበር። (ማቴ. 10:11) ኢየሱስ ጥሩ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ይፈልግ የነበረው ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ብቻ አልነበረም። ባገኘው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ፣ መደበኛ በሆነ መንገድም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ይመሠክር ነበር። (ሉቃስ 8:1፤ ዮሐ. 4:7-15) ሐዋርያትም በተለያዩ ቦታዎች ለሰዎች ይመሠክሩ ነበር።—ሥራ 17:17፤ 28:16, 23, 30, 31
ዓላማችን የመንግሥቱ መልእክት በተቻለ መጠን ለእያንዳንዱ ሰው እንዲደርስ ማድረግ ነው
11 በዛሬው ጊዜም ዓላማችን የመንግሥቱ መልእክት በተቻለ መጠን ለእያንዳንዱ ሰው እንዲደርስ ማድረግ ነው። ይህን ዓላማችንን ዳር ለማድረስ ደግሞ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ይጠቀሙበት የነበረውን ዘዴ መኮረጅ ይኖርብናል፤ በተጨማሪም በጊዜያችን የሚከሰቱትን ለውጦች ማስተዋልና በክልላችን የሚገኙ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በትኩረት መከታተል ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 7:31) ለምሳሌ አስፋፊዎች በንግድ አካባቢዎች በማገልገል ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። በመናፈሻዎች፣ በመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ወይም ሰዎች በሚገኙባቸው ሌሎች ሥፍራዎች እንደሚከናወነው የስብከት ሥራ ሁሉ የመንገድ ላይ ምሥክርነትም በብዙ አገሮች እጅግ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል። አንዳንድ ጉባኤዎች በክልላቸው ውስጥ ጠረጴዛዎችን ወይም የጽሑፍ ጋሪዎችን በመጠቀም ይሰብካሉ። ከዚህም በተጨማሪ ቅርንጫፍ ቢሮው በትላልቅ ከተሞች ውስጥ ከፍተኛ የእግረኛ ፍሰት ባለባቸው አካባቢዎች ልዩ የአደባባይ ምሥክርነት እንዲሰጥ ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል፤ ከተለያዩ ጉባኤዎች የተውጣጡ አስፋፊዎችም በዚህ ዝግጅት እንዲሳተፉ ይደረጋል። ይህ ዝግጅት፣ ቤታቸው ያልተገኙ ሰዎች በሌላ አካባቢ ምሥራቹ እንዲደርሳቸው አጋጣሚ ይከፍታል።
12 ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች ስናገለግል ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ካገኘን ተስማሚ ጽሑፍ ልናበረክትላቸው እንችላለን። እንዲህ ያሉ ሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግ አድራሻችንን ለእነሱ መስጠትና ለተመላልሶ መጠየቅ ቀጠሮ መያዝ፣ jw.orgን እንዲጎበኙ መጋበዝ ወይም በአቅራቢያቸው የጉባኤ ስብሰባ የሚደረግበትን ቦታ አድራሻ መስጠት እንችላለን። አገልግሎትህን የማስፋት ፍላጎት ካለህ በአደባባይ ምሥክርነት መካፈልን አስደሳች የስብከት ዘዴ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ።
13 ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ለክርስቲያኖች የተሰጠው ሥራ ምሥራቹን ማወጅ ብቻ አይደለም። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ወደ ሕይወት የሚመራውን እውነት እንዲቀበሉ ለመርዳት በተደጋጋሚ ተመላልሰህ ማነጋገር ይኖርብሃል፤ ይህም እድገት እንዲያደርጉና የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።
ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ
14 ኢየሱስ ተከታዮቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሏቸዋል። (ሥራ 1:8) ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]።” (ማቴ. 28:19, 20) ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ በይሖዋ አገልግሎት ደስታ እንድታገኝ ያስችልሃል። ለመጀመሪያ ጊዜ ስትመሠክርላቸው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በድጋሚ ሄደህ ስታነጋግራቸው ደስ ሊላቸው ይችላል። ለእነዚህ ሰዎች ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማካፈል በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ልትረዳቸው ትችላለህ። (ማቴ. 5:3) ጥሩ ዝግጅት ካደረግክና እነሱን በሚያመቻቸው ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ከሞከርክ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ትችል ይሆናል። ደግሞም ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርግበት ዋነኛው ዓላማ ጥናት ማስጀመር ነው። በዚህ መንገድ በሰዎች ልብ ላይ እውነትን ከመትከል ባሻገር ውኃ ማጠጣትም እንችላለን።—1 ቆሮ. 3:6
15 አንዳንዶች ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ከባድ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ምናልባትም ምሥራቹን አጠር አድርግህ የማቅረብ ችሎታ ስላዳበርክ ለመጀመሪያ ጊዜ መመሥከር ብዙም ላይከብድህ ይችላል። ተመልሰህ በመሄድ ከግለሰቡ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተጨማሪ ውይይት ስለማድረግ ስታስብ ግን በጣም ከባድ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ጥሩ ዝግጅት ማድረግህ ድፍረት እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም በሳምንቱ መሃል በሚደረገው ስብሰባ ላይ የቀረቡ ጠቃሚ ሐሳቦችን ተግባራዊ ማድረግህ ይጠቅምሃል። ልምድ ያላቸው አስፋፊዎች አብረውህ እንዲያገለግሉ መጠየቅም ትችላለህ።
የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት
16 ወንጌላዊው ፊልጶስ፣ የአይሁድን እምነት የተቀበለ አንድ ሰው የአምላክን ቃል ሲያነብ ባገኘው ጊዜ “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” በማለት ጠይቆት ነበር። በዚህ ጊዜ ሰውየው “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” ሲል መለሰለት። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ፣ ፊልጶስ ሰውየው ያነበው ከነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንስቶ “ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ነገረው” ይላል። (ሥራ 8:26-36) ፊልጶስ ከሰውየው ጋር ምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ባናውቅም ምሥራቹን በግልጽ ስላብራራለት ይህ ሰው አማኝ ለመሆንና ለመጠመቅ በቅቷል። አዎ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኗል።
17 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የላቸውም፤ በመሆኑም እምነት እንዲያዳብሩና ለጥምቀት ብቁ እንዲሆኑ ብዙ ጊዜ ተመላልሰን ማነጋገር እንዲሁም ለበርካታ ሳምንታት፣ ወራት፣ ለአንድ ዓመት አልፎ ተርፎም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ማስጠናት ሊያስፈልገን ይችላል። ሆኖም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በትዕግሥትና በፍቅር መርዳት መልሶ የሚክስ ሥራ ነው፤ ኢየሱስም ቢሆን “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ተናግሯል።—ሥራ 20:35
18 መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ተብለው በተዘጋጁት ጽሑፎች አማካኝነት ጥናት መምራት እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ የሚሰጡትን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ካሉ ልምድ ያላቸው አስተማሪዎች ጋር አብረህ በማገልገል ውጤታማ በሆነ መንገድ ሰዎችን ማስጠናትና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ትችላለህ።
19 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ጥናቱን ለመምራት እርዳታ የሚያስፈልግህ ከሆነ በጉባኤህ ካሉ ሽማግሌዎች አንዱን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ ውጤታማ የሆነን ሌላ አስፋፊ ከማማከር ወደኋላ አትበል። በተጨማሪም በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ የሚወጡት ሐሳቦችና በስብሰባው ላይ የሚቀርቡት ሠርቶ ማሳያዎች ሊረዱህ ይችላሉ። ከዚህም ሌላ በይሖዋ መታመንህና ስለ ጉዳዩ አጥብቀህ መጸለይህ አስፈላጊ ነው። (1 ዮሐ. 3:22) በመሆኑም በተቻለህ መጠን፣ ከቤተሰብህ አባል በተጨማሪ ሌላ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲኖርህ ጥረት አድርግ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ከአገልግሎት የላቀ ደስታ ማግኘት ትችላለህ።
ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት መምራት
20 ሰዎች ይሖዋ አምላክን ሲያውቁና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሲሆኑ ከጉባኤው ጋር ይቀላቀላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋ የሚጠቀምበትን ድርጅት ካወቁና በዚህ ድርጅት ውስጥ ከታቀፉ መንፈሳዊ እድገት ሊያደርጉ ብሎም ወደ ጉልምስና ሊደርሱ ይችላሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ማስተማራችን በጣም አስፈላጊ ነው። በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የተባለው ብሮሹር በዚህ ረገድ ሊረዳን ይችላል፤ ለዚሁ ዓላማ ተብለው የተዘጋጁ ቪዲዮዎችም አሉ። በተጨማሪም በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ ያሉትን አንዳንድ ሐሳቦች ጠቃሚ ሆነው ልታገኛቸው ትችላለህ።
21 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ማድረግ ከጀመራችሁበት ጊዜ አንስቶ ተማሪው፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የስብከቱን ሥራ ዳር ለማድረስ የሚጠቀምበት አንድ ድርጅት እንዳለ እንዲገነዘብ እርዳው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የምንጠቀምባቸው ጽሑፎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ እንዲሁም እነዚህ ጽሑፎች የሚዘጋጁትና በዓለም ዙሪያ የሚሰራጩት እንዴት እንደሆነ አስረዳው፤ በተጨማሪም ይህ ሥራ የሚከናወነው ራሳቸውን ለአምላክ በወሰኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንደሆነ ግለጽለት። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪህ ወደ ስብሰባ አዳራሻችን መጥቶ ስብሰባዎቻችን ምን እንደሚመስሉ እንዲያይ ጋብዘው። ስብሰባዎቹ እንዴት እንደሚካሄዱ ግለጽለት፤ እንዲሁም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር አስተዋውቀው። በተጨማሪም በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ልታስተዋውቀው ትችላለህ። በእነዚህም ሆነ በሌሎች ወቅቶች የይሖዋ ሕዝቦች፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት የሆነውን ፍቅርን እንዴት እንደሚያንጸባርቁ ማየት የሚችልበት አጋጣሚ እንዲያገኝ አድርግ። (ዮሐ. 13:35) ፍላጎት ያሳየው ሰው ለይሖዋ ድርጅት ያለው አድናቆት እያደገ ሲሄድ ይበልጥ ወደ ይሖዋ ይቀርባል።
በጽሑፎቻችን መጠቀም
22 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል ቅጂዎች በትጋት ያዘጋጁ ነበር። በግል የሚጠቀሙባቸውንና በጉባኤ የሚያጠኗቸውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች በእጃቸው ይገለብጡ ነበር። ሌሎችም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት እንዲያነቡ ያበረታቱ ነበር። በእጅ የገለበጧቸው ቅጂዎች ጥቂት ከመሆናቸውም ሌላ ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣቸው ነበር። (ቆላ. 4:16፤ 2 ጢሞ. 2:15፤ 3:14-17፤ 4:13፤ 1 ጴጥ. 1:1) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ የማተሚያ ዘዴዎችን በመጠቀም በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችንና ማጥኛ ጽሑፎችን ያትማሉ። ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ትራክቶች፣ ብሮሹሮች፣ መጻሕፍትና መጽሔቶች ይገኙበታል።
23 ምሥራቹን ለሌሎች ስትሰብክ የይሖዋ ድርጅት ባዘጋጃቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በሚገባ ተጠቀም። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማንበብህና ማጥናትህ አንተን በግልህ ምን ያህል እንደጠቀመህ መገንዘብህ ጽሑፎቹን ለሌሎች ለማሰራጨት እንደሚያነሳሳህ ጥርጥር የለውም።—ዕብ. 13:15, 16
24 ኢንተርኔትን እንደ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ አድርገው የሚጠቀሙበት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በመሆኑም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን በተጨማሪ jw.org የተባለው ድረ ገጻችን ምሥራቹን ለማሰራጨት የሚያስችል ውጤታማ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ኮምፒውተር በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ማንበብ ወይም ማዳመጥ ይችላሉ። ከእኛ ጋር ለመነጋገር የሚያቅማሙ ወይም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝተው የመነጋገር አጋጣሚ የሌላቸው ሰዎች ቤታቸው ቁጭ ብለው jw.org የተባለውን ድረ ገጽ በመጠቀም ስለምናምንባቸው ነገሮች መመርመር ይችላሉ።
25 ስለዚህ ምቹ አጋጣሚ በምናገኝበት ጊዜ ሁሉ jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን እናስተዋውቃለን። የቤቱ ባለቤት ስለምናምንባቸው ነገሮች ቢጠይቀን በኮምፒውተር ወይም በያዝነው የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ተጠቅመን እዚያው መልሱን ልናሳየው እንችላለን። የምልክት ቋንቋን ጨምሮ ሌላ ቋንቋ የሚናገር ሰው ብናገኝ በድረ ገጻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በቋንቋው ማግኘት እንደሚችል ልንነግረው እንችላለን። ብዙ አስፋፊዎች በድረ ገጻችን ላይ የሚገኙትን ቪዲዮዎች ተጠቅመው ከሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት መጀመር ችለዋል።
መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት
26 ኢየሱስ፣ የሚያስተምረውን ትምህርት በትኩረት ይከታተሉ ለነበሩት ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። . . . ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።” (ማቴ. 5:14-16) እነዚያ ደቀ መዛሙርት “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” በማለት ስለ ራሱ የተናገረውን የኢየሱስን አርዓያ በመከተል የአምላክን መንገዶችና ባሕርያት በሕይወታቸው አንጸባርቀዋል። ኢየሱስ መልእክቱን ለሚሰሙ ሰዎች ጥቅም ሲል “የሕይወት ብርሃን” በማብራት ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቷል።—ዮሐ. 8:12
27 ሐዋርያው ጳውሎስም ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል። (1 ቆሮ. 4:16፤ 11:1) አቴንስ ውስጥ በነበረበት ወቅት በገበያ ለሚያገኛቸው ሰዎች በየቀኑ ይመሠክር ነበር። (ሥራ 17:17) በፊልጵስዩስ የነበሩ ክርስቲያኖች የእሱን ምሳሌ ተከትለዋል። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች አስመልክቶ “በጠማማና በወልጋዳ ትውልድ መካከል” ሆነው “እንደ ብርሃን አብሪዎች [እንደሚያበሩ]” ሊጽፍ ችሏል። (ፊልጵ. 2:15) እኛም ምሥራቹን ለሌሎች የመናገር አጋጣሚ በምናገኝበት ጊዜ ሁሉ በቃልም ሆነ በተግባር የመንግሥቱ እውነት እንዲያበራ ማድረግ እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ሐቀኛና ቅን በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆናችን በራሱ ሰዎች ከዓለም የተለየን መሆናችንን እንዲያስተውሉ ሊያደርግ ይችላል። ይሁን እንጂ ሰዎች ከሌሎች የተለየን የሆንበትን ምክንያት ማወቅ የሚችሉት ምሥራቹን ከነገርናቸው ነው።
28 አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በሕዝብ መጓጓዣ ወይም በሌላ ቦታ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ሲያከናውኑ በዚያ ለሚያገኟቸው ሰዎች ምሥራቹን ይናገራሉ። በጉዞ ላይ ስንሆን አብረውን የሚጓዙትን ሰዎች ማነጋገር የምንችልበት አጋጣሚ እናገኝ ይሆናል። ከሰዎች ጋር ስንጨዋወት ውይይቱን ወደ ምሥክርነት ማዞር የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች በንቃት መከታተል ይኖርብናል። አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ ለሌሎች ለመመሥከር ዝግጁ እንሁን።
29 ምሥራቹን ማወጃችን ፈጣሪያችንን ለማወደስና ለስሙ ክብር ለማምጣት እንደሚያስችለን መገንዘባችን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለሰዎች እንድንሰብክ ይገፋፋናል። በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ የመርዳት አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን፤ በውጤቱም እነሱም ይሖዋን ማገልገል ሊጀምሩና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሊጨብጡ ይችላሉ። ይሖዋ እንዲህ ባለው ጥረት የሚደሰት ከመሆኑም ሌላ እንደ ቅዱስ አገልግሎት ይቆጥረዋል።—ዕብ. 12:28፤ ራእይ 7:9, 10
የአገልግሎት ክልል
30 ይሖዋ የመንግሥቱ መልእክት በዓለም ዙሪያ በከተማም ሆነ በገጠር እንዲሰበክ ይፈልጋል። ይህን ለማሳካት ሲባል ቅርንጫፍ ቢሮው ለጉባኤዎችና ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች ለሚያገለግሉ ግለሰቦች የአገልግሎት ክልል ይሰጣል። (1 ቆሮ. 14:40) ይህም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በአምላክ አመራር ከተደረገው ዝግጅት ጋር የሚስማማ ነው። (2 ቆሮ. 10:13፤ ገላ. 2:9) የመንግሥቱን ምሥራች የማወጁ ሥራ በፍጥነት እየተስፋፋ ባለባቸው በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የጉባኤውን የአገልግሎት ክልል ለመሸፈን የተደረገው ዝግጅት በሚገባ የተደራጀ ከሆነ ብዙ ሥራ ማከናወን ይቻላል።
31 ይህን ዝግጅት በበላይነት የሚከታተለው የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ነው። የአገልግሎት ክልል የመመደቡን ሥራ አንድ የጉባኤ አገልጋይ ሊያከናውን ይችላል። የአገልግሎት ክልል፣ ለቡድን አሊያም ለአንድ አስፋፊ ሊሰጥ ይችላል። ጉባኤው ያለው የአገልግሎት ክልል ብዛት ትንሽ ከሆነ በአገልግሎት ቡድኑ ውስጥ የታቀፉ አስፋፊዎች የሚያገለግሉባቸው ክልሎች ለቡድን የበላይ ተመልካቾች ይሰጣሉ። በአንጻሩ ደግሞ የጉባኤው ክልል ብዙ ከሆነ አስፋፊዎች የግል ክልል መውሰድ ይችላሉ።
32 አንድ አስፋፊ የግል ክልል ካለው የመስክ አገልግሎት ስብሰባ በማይኖርበት ጊዜ ወይም ስምሪት መገኘት ሳይችል ሲቀር በዚያ ማገልገል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ አስፋፊዎች በሥራ ቦታቸው አካባቢ ያለ ክልል በመውሰድ በምሳ እረፍታቸው ላይ ወይም ከሥራ ሰዓት በኋላ በዚያ ይሰብካሉ። አንዳንድ ቤተሰቦች፣ በሚኖሩበት ሰፈር አቅራቢያ የግል ክልል ወስደው አልፎ አልፎ ምሽት ላይ ይሰብካሉ። አንድ አስፋፊ ለእሱ በሚያመቸው አካባቢ የግል ክልል መውሰዱ ለአገልግሎት የመደበውን ጊዜ በሚገባ እንዲጠቀምበት ያስችለዋል። እርግጥ ነው፣ በግል የአገልግሎት ክልልም ውስጥ በቡድን ማገልገል ይቻላል። የግል ክልል እንዲኖርህ ከፈለግክ የክልል አገልጋዩን መጠየቅ ትችላለህ።
33 አንድ አስፋፊ የግል ክልሉንም ሆነ የቡድን የበላይ ተመልካቹ ለቡድኑ የወሰደውን ክልል ሲሠራ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ቢያንስ አንድ ሰው አግኝቶ ለመመሥከር የቻለውን ያህል ጥረት ያደርጋል። የአገልግሎት ክልሎችን ለመሸፈን የሚደረገው ዝግጅት ለአካባቢው ከሚሠሩ የመረጃ ጥበቃ ሕጎች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። አንድ የቡድን የበላይ ተመልካች ወይም አስፋፊ የወሰደውን ክልል በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ለመሸፈን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ክልሉ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ለክልል አገልጋዩ ማሳወቅ ያስፈልጋል። የቡድን የበላይ ተመልካቹ ወይም አስፋፊው እንደ ሁኔታው ክልሉን ሳይመልስ በድጋሚ ሊሠራው አሊያም ለክልል አገልጋዩ መልሶ ሊሰጠው ይችላል።
34 የጉባኤው አስፋፊዎች በተቀናጀ መንገድ ከሠሩ የአገልግሎት ክልሉ በተጣራ ሁኔታ ሊሸፈን ይችላል። በተጨማሪም ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አስፋፊዎች አንድን ክልል በተመሳሳይ ጊዜ በመሥራት ነዋሪዎቹን እንዳያስቆጡ ይረዳል። እንዲህ ማድረጋችን ለወንድሞቻችንም ሆነ በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ያለንን አሳቢነት ያሳያል።
በተቀናጀ መንገድ ለሁሉም ቋንቋ ተናጋሪዎች መስበክ
35 ሁሉም ሰው ስለ ይሖዋ አምላክ፣ ስለ ልጁና ስለ መንግሥቱ መስማት አለበት። (ራእይ 14:6, 7) የሁሉም ቋንቋ ተናጋሪዎች የይሖዋን ስም ጠርተው እንዲድኑና ክርስቲያናዊ ስብዕና እንዲላበሱ መርዳት እንፈልጋለን። (ሮም 10:12, 13፤ ቆላ. 3:10, 11) የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገርባቸው አካባቢዎች ምሥራቹን ስንሰብክ ምን ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች በደንብ በሚረዱት ቋንቋ የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?—ሮም 10:14
36 የአገልግሎት ክልል ለየጉባኤው የሚከፋፈለው ቋንቋን መሠረት በማድረግ ነው። ስለዚህ ብዙ ቋንቋዎች በሚነገሩባቸው አካባቢዎች፣ ከተለያዩ ጉባኤዎች የመጡ አስፋፊዎች በተመሳሳይ አካባቢ ሊያገለግሉ ይችላሉ። እንዲህ ባለ ሁኔታ ሥር፣ የእያንዳንዱ ጉባኤ አስፋፊ ጉባኤው የሚያገለግልበትን ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ለመስበክ ጥረት ማድረጉ የተሻለ ነው። የመጋበዣ ወረቀቶችን በምናሰራጭባቸው ዓመታዊ ዘመቻዎች ወቅትም ይህንኑ አሠራር እንከተላለን። አስፋፊዎች በአደባባይና መደበኛ ባልሆነ መንገድ በሚመሠክሩበት ጊዜ ግን የፈለጉትን ሰው ማናገር እንዲሁም በፈለጉት ቋንቋ ጽሑፍ ማበርከት ይችላሉ።
37 አንዳንድ ጊዜ ግን በሌላ ቋንቋ የሚካሄዱ ጉባኤዎች፣ ርቀው የሚገኙ ክልሎቻቸውን በቋሚነት መሸፈን ሊያቅታቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ በአንድ አካባቢ የሚሠሩ ጉባኤዎች የአገልግሎት የበላይ ተመልካቾች፣ የጉባኤዎቻቸውን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብተው እርስ በርስ በመነጋገር ክልሉን የሚሸፍኑበትን መንገድ መቀየስ ይኖርባቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ሁሉም ሰው የመንግሥቱን ምሥራች የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኝና አንድ ቤት ሳያስፈልግ ተደጋግሞ እንዳይንኳኳ ያስችላል።—ምሳሌ 15:22
38 በሩን የከፈተው ሰው ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገር ቢሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? እሱ የሚናገረውን ቋንቋ የሚችሉ አስፋፊዎች መጥተው ያነጋግሩታል ብለን ማሰብ አይኖርብንም። አንዳንድ አስፋፊዎች በክልላቸው ውስጥ በተደጋጋሚ የሚያጋጥሟቸው የትኛውን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች እንደሆኑ ግምት ውስጥ በማስገባት በዚያ ቋንቋ ቀለል ያሉ መግቢያዎችን ይዘጋጃሉ። ለግለሰቡ በቋንቋው ጽሑፍ ልናመጣለት እንደምንችል ልንነግረው አሊያም jw.org ከተባለው ድረ ገጻችን ላይ ጽሑፎችን ማንበብ ወይም ማውረድ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ልናሳየው እንችላለን።
39 ግለሰቡ ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ከተረዳን እሱ በሚናገረው ቋንቋ ሊያወያየው የሚችል ጥሩ ችሎታ ያለው አስፋፊ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ እሱ በሚናገረው ቋንቋ ስብሰባ የሚደረግበትን ቦታ ልንጠቁመው እንችላለን። በቋንቋው የሚያናግረው ሰው ማግኘት ከፈለገ አድራሻውን jw.org ላይ መሙላት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ልናሳየው እንችላለን። ቅርንጫፍ ቢሮው፣ አድራሻው ሲደርሰው ለግለሰቡ ተጨማሪ እርዳታ ሊሰጠው የሚችል በአቅራቢያው ያለ አስፋፊ፣ ቡድን ወይም ጉባኤ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል።
40 ፍላጎት ያሳየው ግለሰብ ቋንቋውን የሚችል ሰው መጥቶ እንዳናገረው እስኪያሳውቀን ድረስ እሱን ማናገራችንን መቀጠል ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ ግን ግለሰቡ የሚናገረውን ቋንቋ የሚችል አስፋፊ ማግኘት አይቻል ይሆናል። በዚህ ጊዜ እኛ ራሳችን የግለሰቡን ፍላጎት ለማሳደግ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። የሚቻል ከሆነ እሱ በሚናገረው ቋንቋ በተዘጋጀ ጽሑፍ እየታገዝን መጽሐፍ ቅዱስን ልናስጠናው እንችላለን። በጽሑፉ ላይ ያሉትን ሥዕሎች ጥሩ አድርገን ከተጠቀምንባቸው እንዲሁም የተጠቀሱትን ጥቅሶች ግለሰቡ ራሱ እንዲያነብ ካደረግን በተወሰነ መጠን መሠረታዊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲያገኝ ልንረዳው እንችላለን። ፍላጎት ያሳየው ሰው፣ እሱም ሆነ እኛ የምንናገረውን ቋንቋ የሚችል የቤተሰብ አባል ካለው ይህ ግለሰብ ውይይቱን እንዲያስተረጉምልን ማድረግ እንችል ይሆናል።
41 ፍላጎት ያሳየው ሰው ፕሮግራሙን ሙሉ በሙሉ መረዳት ባይችልም እንኳ ወደ ጉባኤያችን እንዲመጣ መጋበዛችን ከአምላክ ድርጅት ጋር እንዲተዋወቅ ያስችለዋል። በራሱ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ከተቻለ ጥቅስ በሚነበብበት ጊዜ አውጥቶ እንዲከታተል ልንረዳው እንችላለን። ከጉባኤው አስፋፊዎች ጋር መቀራረቡ በራሱ ሊያንጸውና ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ሊረዳው ይችላል።
42 ቅድመ ቡድኖች፦ ጉባኤው ከሚመራበት ቋንቋ በተለየ ቋንቋ የሚሰብኩ የተወሰኑ አስፋፊዎች እስካሉ ድረስ በቋንቋው ሳምንታዊ ስብሰባዎችን መምራት የሚችል ብቃት ያለው ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ባይኖርም እንኳ ቅድመ ቡድን ሊቋቋም ይችላል። ቅርንጫፍ ቢሮው አንድን ጉባኤ የቅድመ ቡድን አስተናጋጅ ጉባኤ አድርጎ እውቅና የሚሰጠው የሚከተሉት መሥፈርቶች ከተሟሉ ነው፦
(1) በአካባቢው ከጉባኤው ቋንቋ ውጭ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ በርካታ ሰዎች ካሉ።
(2) ቢያንስ ጥቂት አስፋፊዎች ይህን ቋንቋ መናገር የሚችሉ ወይም ቋንቋውን ለመማር ራሳቸውን የሚያቀርቡ ከሆነ።
(3) የሽማግሌዎች አካል በዚህ ቋንቋ የስብከቱን ሥራ ለማደራጀት ተነሳሽነትና ፈቃደኝነት ካለው።
የሽማግሌዎች አካል አንድን ቅድመ ቡድን የማስተናገድ ፍላጎት ካለው የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ማማከር ይኖርበታል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በዚያ ቋንቋ ለመስበክ ጥረት እያደረገ ያለ ሌላ ጉባኤ እንዳለና ቅድመ ቡድኑን ለማስተናገድ የትኛው ጉባኤ እንደሚሻል ለመወሰን የሚያስችል ጠቃሚ መረጃ ሊኖረው ይችላል። ጉባኤው ከተመረጠ በኋላ በሌላ ቋንቋ የሚመራ ቅድመ ቡድን አስተናጋጅ ሆኖ እውቅና እንዲሰጠው የጉባኤው ሽማግሌዎች ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ መጻፍ ይችላሉ።
43 ቡድኖች፦ የሚከተሉት መሥፈርቶች ከተሟሉ ቅርንጫፍ ቢሮው አንድን ጉባኤ በሌላ ቋንቋ የሚመራ ቡድን አስተናጋጅ አድርጎ እውቅና ይሰጠዋል፦
(1) ቡድኑ በሚቋቋምበት ቋንቋ በቂ ቁጥር ያላቸው ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ካሉና መስኩ ሊያድግ እንደሚችል የሚጠቁም ነገር ካለ።
(2) ቋንቋውን የሚናገሩ ወይም በመማር ላይ ያሉ ቢያንስ የተወሰኑ አስፋፊዎች ካሉ።
(3) ቡድኑን የሚያስተባብርና በዚያ ቋንቋ ቢያንስ አንዱን ሳምንታዊ ስብሰባ ወይም ከአንዱ ሳምንታዊ ስብሰባ ውስጥ አንዱን ክፍል (ለምሳሌ የሕዝብ ንግግር ወይም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት) መምራት የሚችል ብቃት ያለው ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ካለ።
እነዚህ መመዘኛዎች በተወሰነ ደረጃ ከተሟሉ የሽማግሌዎች አካል ቡድኑን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠቅሶ ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ በመጻፍ የውጭ አገር ቋንቋ ቡድን አስተናጋጅ ጉባኤ ተደርጎ እውቅና እንዲሰጠው ይጠይቃል። ግንባር ቀደም ሆኖ ቡድኑን የሚያስተባብረው ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ “የቡድን የበላይ ተመልካች” ወይም “የቡድን አገልጋይ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከቡድኑ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመከታተል ኃላፊነት ይኖረዋል።
44 ቡድኑ ከተቋቋመ በኋላ የአስተናጋጅ ጉባኤው የሽማግሌዎች አካል ከጉባኤ ስብሰባዎች መካከል ሌሎች ተጨማሪ ክፍሎች መቅረብ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲሁም እነዚህ ስብሰባዎች በወሩ ውስጥ ስንት ጊዜ መደረግ እንዳለባቸው ይወስናል። በተጨማሪም ቡድኑ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ማድረግ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይቻላል። በቡድኑ ውስጥ ያሉ ሁሉ ቡድኑ በታቀፈበት ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል አመራር ሥር ሆነው ይሠራሉ። ሽማግሌዎቹ ሚዛናዊ አመራር የሚሰጡ ከመሆኑም ሌላ ቡድኑ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት በንቃት ይከታተላሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ቡድኑ የታቀፈበትን ጉባኤ ሲጎበኝ ከቡድኑ ጋር አብሮ የሚሠራ ሲሆን ቡድኑ ስላደረገው እድገትና ስለሚያስፈልጉት ነገሮች የሚገልጽ አጠር ያለ ሪፖርት ለቅርንጫፍ ቢሮው ይጽፋል። በጊዜ ሂደት ቡድኑ አድጎ ጉባኤ ሊሆን ይችላል። የሚመለከታቸው ሁሉ ቲኦክራሲያዊ የሆኑ መመሪያዎችን ሥራ ላይ የሚያውሉ ከሆነ ይሖዋ በዚህ ይደሰታል።—1 ቆሮ. 1:10፤ 3:5, 6
የቡድን ምሥክርነት
45 ራሱን ለአምላክ የወሰነ እያንዳንዱ ክርስቲያን ምሥራቹን ለሌሎች የማካፈል ኃላፊነት አለበት። ይህን ማድረግ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች ቢኖሩም አብዛኞቻችን ከሌሎች ጋር አብረን ማገልገል ያስደስተናል። (ሉቃስ 10:1) ስለሆነም ጉባኤዎች በሳምንቱ መሃልም ሆነ በሳምንቱ መጨረሻ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ያደርጋሉ። በበዓል ቀናትም ብዙ ወንድሞች ከሥራ ነፃ ስለሚሆኑ በቡድን ለመመሥከር ጥሩ አጋጣሚ ይኖራል። የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ቀንም ሆነ አመሻሹ ላይ አመቺ በሆነ ሰዓትና ቦታ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ዝግጅት ያደርጋል።
46 የቡድን ምሥክርነት፣ አስፋፊዎች አብረው እንዲሠሩ የሚያስችል ከመሆኑም ሌላ ‘እርስ በርስ የሚበረታቱበት’ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሮም 1:12) አዳዲስ አስፋፊዎች፣ ጥሩ ችሎታና ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር አብረው በማገልገል ሥልጠና ማግኘት ይችላሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች ከደህንነት አንጻር ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አስፋፊዎች አብረው ማገልገላቸው ይመከራል። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ብቻህን የማገልገል እቅድ ቢኖርህም እንኳ የመስክ ስምሪት ስብሰባ ላይ መገኘትህ ሁሉንም ያበረታታል። ሌሎችም በአገልግሎት ተሰማርተው በዚያው አካባቢ እየሰበኩ መሆኑን ማወቅህ በራሱ ድፍረት ሊጨምርልህ ይችላል። ይሁንና አቅኚዎችም ሆኑ ሌሎች አስፋፊዎች በተለይ ጉባኤያቸው በየቀኑ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የሚያደርግ ከሆነ በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ በመገኘት ስምሪቱን የመደገፍ ግዴታ እንዳለባቸው ሊሰማቸው አይገባም። ሆኖም በየሳምንቱ በተወሰኑ የስምሪት ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ድጋፍ መስጠት ይችሉ ይሆናል።
47 ሁላችንም ኢየሱስና ሐዋርያቱ የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ጥረት እናድርግ! ወሳኝ በሆነው የስብከቱ ሥራ በተሟላ ሁኔታ ለመሳተፍ የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርከው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሉቃስ 9:57-62