ምዕራፍ 10
አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልባቸው መንገዶች
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ስለ መንግሥቱ እንዲሰብኩ በላካቸው ጊዜ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው” ብሏቸው ነበር። መሠራት ያለበት ብዙ ሥራ ስለነበር ኢየሱስ “የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ማቴ. 9:37, 38) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎታቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ነግሯቸዋል። በተጨማሪም “የሰው ልጅ እስከሚመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞችና መንደሮች ፈጽሞ አታዳርሱም” በማለት ሥራው አጣዳፊ መሆኑን የሚጠቁም ሐሳብ ተናግሯል።—ማቴ. 10:23
2 በዛሬው ጊዜም ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። ይህ የመንግሥት ምሥራች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት መሰበክ አለበት፤ ጊዜው ደግሞ እየተሟጠጠ ነው! (ማር. 13:10) የምንሰብክበት መስክ ይህ ዓለም እንደመሆኑ መጠን ሁኔታችን ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ከነበሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል፤ እንዲያውም እኛ ይበልጥ ስፋት ያለው ሥራ ማከናወን ይጠበቅብናል። በዓለም ላይ ካለው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ጋር ሲነጻጸር ቁጥራችን በጣም ትንሽ ቢሆንም ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኞች ነን። የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ መጨረሻው ይመጣል። ታዲያ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ ማከናወን እንድንችል በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ እንሰጣለን? በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ ምን ቲኦክራሲያዊ ግቦች ማውጣት እንችላለን?
3 ይሖዋ ራሳቸውን ከወሰኑ አገልጋዮቹ የሚጠብቀውን ነገር በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።” (ማር. 12:30) ስለዚህ ለአምላክ የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ማቅረብ ይጠበቅብናል። በይሖዋ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ምን ያህል ለእሱ ያደርን እንደሆንን እንዲሁም ራሳችንን የወሰንነው ከልብ ተገፋፍተን እንደሆነ እናሳያለን። (2 ጢሞ. 2:15) እያንዳንዳችን እንደ ሁኔታችንና እንደ አቅማችን ልንካፈልባቸው የምንችላቸው የአገልግሎት መስኮች አሉ። ከእነዚህ የአገልግሎት መስኮች መካከል አንዳንዶቹን ተመልከት፤ ከዚያም አገልግሎትህን ለማከናወን የትኞቹን ቲኦክራሲያዊ ግቦች ልታወጣ እንደምትችል አስብ።
የጉባኤ አስፋፊ ሆኖ ማገልገል
4 እውነትን የተቀበሉ ሁሉ ምሥራቹን የማስፋፋት ውድ መብት አላቸው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ዋነኛ ሥራ ይህ ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ ሰው፣ አብዛኛውን ጊዜ ምሥራቹን ከሰማበት ጊዜ አንስቶ ስለተማረው ነገር ለሌሎች ይናገራል። እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ ቆርኔሌዎስና ሌሎች ደቀ መዛሙርትም ያደረጉት ይህንኑ ነበር። (ዮሐ. 1:40, 41, 43-45፤ ሥራ 10:1, 2, 24፤ 16:14, 15, 25-34) እንዲህ ሲባል ታዲያ አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊትም ምሥራቹን ለሌሎች መናገር ይችላል ማለት ነው? አዎ! አንድ ግለሰብ በጉባኤው ውስጥ ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆኖ ለማገልገል ብቁ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ የመመሥከር መብት ያገኛል። ከዚህም በተጨማሪ አቅሙና ሁኔታው በሚፈቅድለት መጠን በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች መካፈል ይችላል።
5 አንድ አስፋፊ ከተጠመቀ በኋላ፣ ለሌሎች ምሥራቹን ለመንገር የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በስብከቱ ሥራ የመሳተፍ መብት አላቸው። የአምላክን መንግሥት የሚደግፉ ጉዳዮችን በማከናወኑ ሥራ ጥቂትም ቢሆን ድርሻ ማበርከት መቻላችን ትልቅ በረከት ነው። በሌሎች የአገልግሎት መስኮችም በመሳተፍ አገልግሎቱን ለማስፋት ጥረት የሚያደርግ ማንኛውም ክርስቲያን ደስተኛ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ተዛውሮ ማገልገል
6 የጉባኤህ የአገልግሎት ክልል በተደጋጋሚ የሚሸፈንና በሚገባ የተሰበከበት ሊሆን ይችላል። ከሆነ በመስኩ ላይ ሠራተኞች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ በመዛወር አገልግሎትህን ማስፋት እንደምትችል ይሰማህ ይሆናል። (ሥራ 16:9) ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነህ በማገልገል ላይ የምትገኝ ከሆነ የአንተን ድጋፍ ቢያገኝ በጣም የሚጠቀም ሌላ ጉባኤ ይኖር ይሆናል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በወረዳው ውስጥ ያለን ሌላ ጉባኤ መርዳት ስለምትችልበት መንገድ ሐሳብ ሊሰጥህ ይችላል። ባለህበት አገር ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውረህ ማገልገል የምትፈልግ ከሆነ ደግሞ ቅርንጫፍ ቢሮው ጠቃሚ መረጃ ሊሰጥህ ይችላል።
7 ወደ ሌላ አገር ተዛውረህ የማገልገል ፍላጎት አለህ? ከሆነ ጉዳዩን በጥሞና ልታስብበት ይገባል። የጉባኤህን ሽማግሌዎች ስለ ጉዳዩ ለምን አታማክራቸውም? ወደ ሌላ ቦታ ተዛውሮ ማገልገል፣ በአንተም ሆነ አብረውህ በሚዛወሩት ቤተሰቦችህ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እርምጃ ነው። (ሉቃስ 14:28) ለረጅም ጊዜ የመቆየት ዕቅድ ከሌለህ ግን ባለህበት አገር ውስጥ ወደሚገኝ ሌላ አካባቢ ተዛውረህ ብታገለግል የተሻለ ሊሆን ይችላል።
8 በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆነው የሚያገለግሉት ወንድሞች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በእውነት ቤት ውስጥ ብዙም ያልቆዩ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ወንድሞች ትሑት ስለሆኑ፣ ወደ ጉባኤያቸው የመጡት ይበልጥ ልምድ ያላቸው ሽማግሌዎች ጉባኤውን የመምራቱን ኃላፊነት እንዲረከቡ ያደርጉ ይሆናል። እርዳታ ወደሚያስፈልግበት አገር ለመዛወር እያሰብክ ያለህ ሽማግሌ ከሆንክ ዓላማህ በአገሩ ያሉትን ወንድሞች ተክቶ ማገልገል ሳይሆን ከእነሱ ጋር አብሮ ማገልገል እንደሆነ አስታውስ። አስፈላጊውን ብቃት ለማሟላት እንዲጣጣሩና የጉባኤ ኃላፊነቶችን እንዲቀበሉ አበረታታቸው። (1 ጢሞ. 3:1) አንዳንድ ነገሮች የሚከናወኑበት መንገድ አንተ ከነበርክበት አገር የተለየ በሚሆንበት ጊዜ ትዕግሥተኛ ለመሆን ጥረት አድርግ። ሽማግሌ በመሆን ያካበትከውን ልምድ ወንድሞችን ለመርዳት ተጠቀምበት። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አንተ ወደ አገርህ እንድትመለስ የሚያስገድድህ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ እዚያው የሚቀሩት ሽማግሌዎች ጉባኤውን ለመምራት የተሻለ ብቃት ይኖራቸዋል።
9 ቅርንጫፍ ቢሮው እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ጉባኤዎች ዝርዝር ለአንተ ከመላኩ በፊት የጉባኤህ የአገልግሎት ኮሚቴ ለቅርንጫፍ ቢሮው የድጋፍ ደብዳቤ መላክ ይኖርበታል። ሽማግሌም ሆንክ የጉባኤ አገልጋይ አሊያም አቅኚ ወይም አስፋፊ የድጋፍ ደብዳቤ ሊጻፍልህ ይገባል። የአገልግሎት ኮሚቴው የድጋፍ ደብዳቤውን አንተ ካቀረብከው ማመልከቻ ጋር አያይዞ ማገልገል በምትፈልግበት አገር ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ይልከዋል።
በሌላ ቋንቋ መስበክ
10 አገልግሎትህን ለማስፋት ስትል ሌላ ቋንቋ፣ ለምሳሌ የምልክት ቋንቋ ለመማር ታስብ ይሆናል። ሌላ ቋንቋ ተምረህ በዚያ ቋንቋ የመስበክ ግብ ካለህ የጉባኤህን ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ለምን አታማክራቸውም? ጠቃሚ ሐሳቦችን ሊያካፍሉህና ማበረታቻ ሊሰጡህ ይችላሉ። አንዳንድ ወረዳዎች የቅርንጫፍ ቢሮውን አመራር በመከተል፣ ጥሩ ችሎታ ያላቸው አስፋፊዎችና አቅኚዎች በሌላ ቋንቋ መስበክ እንዲችሉ ቋንቋውን የሚማሩበት ዝግጅት ያደርጋሉ።
የአቅኚነት አገልግሎት
11 ሁሉም አስፋፊዎች በረዳት፣ በዘወትርና በልዩ አቅኚነት ለማገልገል እንዲሁም በሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ለመካፈል ስለሚያስፈልጉት ብቃቶች ጠቅለል ያለ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። አንድ አስፋፊ አቅኚ ለመሆን፣ ከአቅኚዎች የሚጠበቀውን የሰዓት ግብ ለማሟላት የግል ሁኔታው የሚፈቅድለትና ጥሩ አርዓያ ተደርጎ የሚታይ የተጠመቀ ክርስቲያን መሆን አለበት። ለረዳትና ለዘወትር አቅኚነት የሚቀርቡትን ማመልከቻዎች የሚያጸድቀው የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ሲሆን ልዩ አቅኚዎችን የሚሾመው ግን ቅርንጫፍ ቢሮው ነው።
12 ረዳት አቅኚዎች ቢያንስ ለአንድ ወር አሊያም በርከት ላሉ ተከታታይ ወራት ወይም ላልተወሰነ ጊዜ እንዲያገለግሉ ሊሾሙ ይችላሉ፤ ይህ በሁኔታቸው ላይ የተመካ ነው። ብዙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ለየት ባሉ ወቅቶች ለምሳሌ፣ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያቸውን በሚጎበኝበት ወር በረዳት አቅኚነት ያገለግላሉ። አንዳንዶች ደግሞ የዓመት ዕረፍታቸውን ተጠቅመው ረዳት አቅኚ ይሆናሉ። ተማሪ የሆኑ የተጠመቁ አስፋፊዎች ትምህርት ቤት ሲዘጋ ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ይችሉ ይሆናል። በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤውን በሚጎበኝበት ወር ከረዳት አቅኚዎች የሚጠበቀው የሰዓት ግብ ስለሚቀንስ አንዳንድ አስፋፊዎች በእነዚህ ወራት ረዳት አቅኚ ለመሆን ሊመርጡ ይችላሉ። የግል ሁኔታህ ምንም ይሁን ምን ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም ካለህ እንዲሁም የሚፈለግብህን ሰዓት ማሟላትና ለአንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ ረዳት አቅኚ ሆነህ ማገልገል የምትችል ከሆነ ሽማግሌዎቹ ለዚህ የአገልግሎት መብት የምታቀርበውን ማመልከቻ በደስታ ይቀበላሉ።
13 የዘወትር አቅኚ መሆን የምትችለው በዓመት ውስጥ ከዘወትር አቅኚዎች የሚጠበቀውን የሰዓት ግብ ለማሟላት በሚያስችል ሁኔታ ላይ የምትገኝ ከሆነ ነው። የዘወትር አቅኚ ስትሆን ከጉባኤህ ጋር በቅርብ ተባብረህ መሥራት ይኖርብሃል። ቀናተኛ አቅኚዎች ለጉባኤው ትልቅ በረከት ናቸው። በጉባኤው ውስጥ የአገልግሎት ቅንዓት እንዲቀጣጠል ሊያደርጉና ሌሎችም አቅኚነት እንዲጀምሩ ሊያበረታቱ ይችላሉ። ለዘወትር አቅኚነት ለማመልከት፣ ከተጠመቅህ ቢያንስ ስድስት ወር የሞላህና ጥሩ ምሳሌ የሆንክ አስፋፊ መሆን አለብህ።
14 አብዛኛውን ጊዜ ልዩ አቅኚ ሆነው የሚሾሙት በአገልግሎት ውጤታማ መሆናቸውን ያስመሠከሩ የዘወትር አቅኚዎች ናቸው። ቅርንጫፍ ቢሮው በሚመድባቸው ቦታ ለማገልገል የሚችሉ መሆን አለባቸው። ብዙውን ጊዜ ልዩ አቅኚዎች የሚላኩት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች አግኝተው አዳዲስ ጉባኤዎችን ማቋቋም ወደሚችሉባቸው ገለልተኛ ክልሎች ነው። አንዳንድ ጊዜ ልዩ አቅኚዎች፣ የአገልግሎት ክልላቸውን ለመሸፈን እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጉባኤዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ ይመደባሉ። ሽማግሌ ሆነው የሚያገለግሉ ልዩ አቅኚዎች፣ መስኩ ላይ ተጨማሪ ሠራተኛ ባያስፈልግም እንኳ ትናንሽ ጉባኤዎችን እንዲረዱ ሲባል የሚመደቡበት ጊዜ አለ። ልዩ አቅኚዎች ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የሚያስችል መጠነኛ አበል ይሰጣቸዋል። አንዳንዶቹ ልዩ አቅኚዎች የሚሾሙት በጊዜያዊነት እንዲያገለግሉ ነው።
መስክ ላይ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን
15 የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ በመስክ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያንን የሚሾም ሲሆን በተመደቡበት አገር ያለው የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ ደግሞ ብዙ ነዋሪዎች ባሉባቸው ክልሎች ውስጥ እንዲያገለግሉ ይመድባቸዋል። ሚስዮናውያን ከስብከቱ ሥራና ከጉባኤ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ ወንድሞችን በማበረታታትና በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። መስክ ላይ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን አብዛኛውን ጊዜ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ገብተው ሥልጠና ያገኙ ናቸው። የሚኖሩበት ቤት የሚዘጋጅላቸው ከመሆኑም ሌላ ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚያስችል መጠነኛ አበል ይሰጣቸዋል።
የወረዳ ሥራ
16 የበላይ አካሉ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚሾማቸው ወንድሞች በመጀመሪያ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች በመሆን ሥልጠናና ተሞክሮ እንዲያገኙ ይደረጋል። እነዚህ ወንዶች ለአገልግሎትም ሆነ ለወንድሞቻቸው ፍቅር አላቸው። ቀናተኛ አቅኚዎችና ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከመሆናቸውም ሌላ ጥሩ የንግግርና የማስተማር ችሎታ አላቸው። የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን በማንጸባረቅ ረገድ አርዓያ ተደርገው ይታያሉ፤ እንዲሁም ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊና አስተዋይ ናቸው። ወንድም ባለትዳር ከሆነ አቅኚ የሆነችው ሚስቱ በባሕርይዋም ሆነ ከሌሎች ጋር ባላት ግንኙነት ምሳሌ ተደርጋ የምትታይ ናት። ውጤታማ ሰባኪ ነች። በተጨማሪም ክርስቲያን ሚስት እንደመሆኗ መጠን ለባሏ መገዛት እንዳለባት ትገነዘባለች፤ ባሏን ወክላ ከመናገር ወይም እኔ ብቻ ላውራ ከማለት ትቆጠባለች። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው ፕሮግራማቸው አድካሚ ስለሆነ ለዚህ የአገልግሎት መብት ለመብቃት የሚጣጣሩ ሁሉ ጥሩ ጤንነት ሊኖራቸው ይገባል። አቅኚዎች በወረዳ ሥራ ለመካፈል ማመልከት አይችሉም። ከዚህ ይልቅ በወረዳ ሥራ የመካፈል ፍላጎት እንዳላቸው ለወረዳ የበላይ ተመልካቻቸው ያሳውቃሉ፤ እሱም አንዳንድ ሐሳቦችን ያካፍላቸዋል።
ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች
17 የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት፦ ምሥራቹ ብዙም ባልተሰበከባቸው ክልሎች የሚያገለግሉና ለጉባኤዎች መንፈሳዊ ድጋፍ የሚሰጡ ተጨማሪ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ያስፈልጋሉ። በመሆኑም ነጠላ ወንድሞች፣ ነጠላ እህቶች እንዲሁም ባለትዳሮች በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ገብተው በዚያ የሚሰጠውን ልዩ ሥልጠና ለማግኘት ማመልከት ይችላሉ። በትምህርት ቤቱ ከተካፈሉ በኋላ ተመራቂዎቹ በአገራቸው ውስጥ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች የዘወትር አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ይመደባሉ። ራሳቸውን በፈቃደኝነት ማቅረብ የቻሉ አንዳንድ ተመራቂዎች በአገራቸው ወይም በውጭ አገር ሌላ ምድብ ሊሰጣቸው ይችላል። የተወሰኑት ደግሞ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ሊመደቡ ይችላሉ። በዚህ ትምህርት ቤት የመካፈል ፍላጎት ያላቸው አቅኚዎች በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ስለሚያስፈልጉት ብቃቶች ለማወቅ በክልል ስብሰባ ላይ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ በሚደረገው ስብሰባ ላይ መገኘት ይችላሉ።
18 ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት፦ የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑና እንግሊዝኛ የሚችሉ ነጠላ ወንድሞች፣ ነጠላ እህቶች እንዲሁም ባለትዳሮች በዚህ ትምህርት ቤት እንዲካፈሉ ሊጋበዙ ይችላሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በመስኩ ወይም በቅርንጫፍ ቢሮው የሚከናወነው ሥራ እንዲጠናክር እርዳታ ያበረክታሉ። ወደ ትምህርት ቤቱ ከመጋበዛቸው በፊትም ቅዱስ ጽሑፋዊና ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችን እንዲያውቁና በጥብቅ እንዲከተሉ ሌሎችን በደግነት የመርዳት ችሎታ እንዳላቸው እንዲሁም ወንድሞቻቸውን ማገልገል እንደሚያስደስታቸው አስመሥክረዋል። ቅርንጫፍ ኮሚቴው በዚህ ትምህርት ቤት ለመማር ብቃቱን የሚያሟሉ ተማሪዎች ቅጽ ሞልተው እንዲያስገቡ ይጋብዛል። ከዚህ ትምህርት ቤት የሚመረቁ ተማሪዎች በአገራቸው አሊያም በውጭ አገር፣ መስክ ላይ ወይም ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ እንዲያገለግሉ ሊመደቡ ይችላሉ።
የቤቴል አገልግሎት
19 በቤቴል ማገልገል ልዩ መብት ነው። ቤቴል የሚለው ስም “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም አለው፤ በእርግጥም ይህ መጠሪያ የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ለሆኑት ለእነዚህ ቦታዎች ተስማሚ ነው። በቤቴል የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከማዘጋጀት፣ ከመተርጎምና ከመላክ ጋር የተያያዙ ወሳኝ ሥራዎችን ያከናውናሉ። በምድር ዙሪያ ለሚገኙት ጉባኤዎች ክትትል የሚያደርገውና አመራር የሚሰጠው የበላይ አካል ቤቴላውያን የሚያከናውኑትን ሥራ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። የትርጉም ሥራ የሚሠሩ በርካታ ቤቴላውያን፣ የሚኖሩትም ሆነ የሚሠሩት በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ባለ እነሱ የሚተረጉሙበት ቋንቋ በሚነገርበት አካባቢ ነው። ይህም ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ቋንቋውን ሲናገሩ የመስማት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም የተተረጎሙት ጽሑፎች ለአንባቢዎቹ ግልጽ መሆን አለመሆናቸውን በቀጥታ ለማየት ያስችላቸዋል።
20 በቤቴል የሚከናወነው አብዛኛው ሥራ አካላዊ ጥንካሬ ይጠይቃል። በዚህም ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቤቴል የሚጠሩት ወጣት የሆኑ፣ ጥሩ ጤንነትና አካላዊ ጥንካሬ ያላቸው እንዲሁም ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው የተጠመቁ ወንድሞች ናቸው። በምትኖርበት አገር የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት በሚከታተለው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ቤቴላውያን የሚያስፈልጉ ከሆነና በቤቴል የማገልገል ፍላጎት ካለህ፣ የትኞቹን ብቃቶች ማሟላት እንደሚያስፈልግህ ለማወቅ የጉባኤ ሽማግሌዎችህን መጠየቅ ትችላለህ።
የግንባታ አገልግሎት
21 የሰለሞንን ቤተ መቅደስ መገንባት ቅዱስ አገልግሎት እንደነበረው ሁሉ ቲኦክራሲያዊ ሥራዎች የሚካሄዱባቸውን ሕንፃዎች መገንባትም ቅዱስ አገልግሎት ነው። (1 ነገ. 8:13-18) ብዙ ወንድሞችና እህቶች ለዚህ ሥራ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲሉ ጊዜያቸውንም ሆነ ንብረታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት ከፍተኛ ቅንዓት አሳይተዋል።
22 አንተስ ለዚህ ሥራ የበኩልህን አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለህ? የተጠመቅክ አስፋፊ ከሆንክና በዚህ ሥራ የመካፈል ፍላጎት ካለህ በአካባቢህ ያለውን የግንባታ ሥራ በበላይነት የሚከታተሉት ወንድሞች የምትሰጠውን ድጋፍ በአድናቆት ይቀበላሉ፤ በተጨማሪም ከሥራው ጋር በተያያዘ ያን ያህል ሙያ ባይኖርህም አንተን ለማሠልጠን ፈቃደኞች ናቸው። ታዲያ በዚህ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኛ እንደሆንክ ለጉባኤህ ሽማግሌዎች ለምን አትነግራቸውም? በግንባታ ሥራ ለመካፈል ብቃቱን ያሟሉ አንዳንድ የተጠመቁ አስፋፊዎች በሌላ አገር በሚከናወኑ የቲኦክራሲያዊ ሕንፃ ግንባታ ሥራዎችም የመሳተፍ አጋጣሚ አግኝተዋል።
23 በግንባታ ሥራ መሳተፍ የሚቻልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። መጠነኛ የግንባታ ሙያ ያላቸውና በሚኖሩበት አካባቢ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ድጋፍ መስጠት የሚችሉ አርዓያ ተደርገው የሚታዩ የተጠመቁ አስፋፊዎች የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው ማገልገል ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች በመሄድ በዚያ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ለተወሰነ ጊዜ ያህል ድጋፍ መስጠት ይችሉ ይሆናል፤ ቅርንጫፍ ቢሮው እነዚህን አስፋፊዎች ከሁለት ሳምንት እስከ ሦስት ወር ለሚያክል ጊዜ ፈቃደኛ የግንባታ ሠራተኞች ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾማቸዋል። ረዘም ላለ ጊዜ እንዲያገለግሉ የሚሾሙ ደግሞ የግንባታ አገልጋዮች ተብለው ይጠራሉ። ውጭ አገር ሄዶ እንዲያገለግል የሚመደብ የግንባታ አገልጋይ በውጭ አገር የሚያገለግል የግንባታ አገልጋይ ተብሎ ይጠራል። አንድ የግንባታ ቡድን የግንባታ አገልጋዮችንና የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፈ ሲሆን ቡድኑ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት ላይ የግንባታ ሥራውን በግንባር ቀደምትነት ያከናውናል። የአካባቢ ንድፍና ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዲሁም ከተለያዩ ጉባኤዎች የሚመጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለግንባታ ቡድኑ ድጋፍ ይሰጣሉ። የግንባታ ቡድኖች በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ የሚገኝን አንድ ፕሮጀክት ሲጨርሱ ወደ ቀጣዩ ፕሮጀክት በመሄድ ሥራቸውን ያከናውናሉ።
ምን መንፈሳዊ ግቦች አሉህ?
24 ራስህን ለይሖዋ የወሰንክ ክርስቲያን ከሆንክ ዋነኛው ግብህ ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁንና ዋነኛው ግብህ ላይ ለመድረስ በምታደርገው ጉዞ ምን ሌሎች መንፈሳዊ ግቦች ልታወጣ ትችላለህ? መንፈሳዊ ግቦች ማውጣትህ ጉልበትህንም ሆነ ያለህን ማንኛውንም ነገር በጥበብ እንድትጠቀም ያስችልሃል። (1 ቆሮ. 9:26) እንዲህ ያሉ ግቦች ማውጣትህ መንፈሳዊ እድገት እንድታደርግ ይረዳሃል፤ እንዲሁም ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ መጣጣርህ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንድታተኩር ያስችልሃል።—ፊልጵ. 1:10፤ 1 ጢሞ. 4:15, 16
25 ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ከምናቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ልንከተለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ፣ ይሖዋ ብዙ አጋጣሚዎችን እንደከፈተለት የተገነዘበ ከመሆኑም ሌላ ለይሖዋ አገልግሎት ራሱን ሳይቆጥብ ሰጥቷል። በቆሮንቶስ ለነበሩት ወንድሞች “ትልቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል” በማለት ጽፎላቸዋል። የእኛስ ሁኔታ ተመሳሳይ አይደለም? በእርግጥም ከጉባኤው ጋር ሆነን ይሖዋን ማገልገል የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፤ በተለይም የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ረገድ “ትልቅ የሥራ በር” ተከፍቶልናል። ሆኖም እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በዚህ ‘ትልቅ በር’ ለመግባት ‘ከብዙ ተቃዋሚዎች’ ጋር መፋለም ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 16:9) ጳውሎስ ራሱን ለመገሠጽ ፈቃደኛ ነበር። “ሰውነቴን እየጎሰምኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:24-27) እኛስ እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች ነን?
መንፈሳዊ ግቦች ማውጣትህ ጉልበትህንም ሆነ ያለህን ማንኛውንም ነገር በጥበብ እንድትጠቀም ያስችልሃል
26 ሁላችንም የግል ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን ቲኦክራሲያዊ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣጣር እንችላለን። ብዙዎች በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መስክ መሳተፍ የቻሉት በልጅነታቸው ቲኦክራሲያዊ ግቦችን ስላወጡ ነው። ገና ልጆች በነበሩበት ጊዜም፣ ወላጆቻቸውና ሌሎች ክርስቲያኖች ግብ እንዲያወጡ አበረታተዋቸው ነበር። በመሆኑም በይሖዋ አገልግሎት እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ማከናወን ችለዋል፤ እንዲህ በማድረጋቸውም ፈጽሞ አይቆጩም። (ምሳሌ 10:22) ልናወጣቸው ከምንችላቸው ሌሎች ጠቃሚ ግቦች መካከል በየሳምንቱ በመስክ አገልግሎት መሳተፍ፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና መምራት ወይም ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት ተጨማሪ ጊዜ መመደብ ይገኙበታል። ዋናው ነገር በአቋማችን መጽናታችንና አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸማችን ነው። እንዲህ ካደረግን ይሖዋን ማስከበርና የመጨረሻው ግባችን ላይ መድረስ ይኸውም ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል እንችላለን።—ሉቃስ 13:24፤ 1 ጢሞ. 4:7ለ, 8